ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2014ዓ.ም. ጀምሮ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማህበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡ በዚህም መሠረት፡-

 1. የ2014 ዓ.ም. የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ መልእክት አሁን በአገራችን እየታየ ባለው ጦርነት እና የርስበርስ ግጭት ላይ ያተኮረ ሲሆን፡-
 • ጦርነቱ በወንድማማቾች መካከል እየተደረገ ያለና ሀዘኑን የከፋ ያደረገው መሆኑ፣
 • በዚሁ ጦርነትና ግጭት በርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ለሞት ለስደትና ለረሀብ መዳረጋቸው፣
 • በዚህም ምክንያት በአገሪቱ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት አገራዊ ልማት ላይ እያደረሰ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ይህ ጦርነትና ግጭት ተወግዶ በአገሪቱ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ከሁሉም በላይ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ይቅርታ ምሕረት መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን የሚያስገነዝብ በመሆኑ ጉባኤው ይህንኑ መልእክት ተቀብሎ በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል፡፡
 1. በአገራችን በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሰላም እጦትና ጦርነት ወደፊትም ሊያስከትል የሚችለው ችግር ከፍተኛ መሆኑ ስለታመነበት በተቻለ አቅም ዜጐች ሁሉ ለአገራዊው አንድነትና ሰላም መገኘት ዘብ እንዲቆሙ የየበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
 2. በዚሁ አገራዊ የሰላም እጦት እየተደረገ ያለውን ጦርነት ምክንያት አድርገው ከአገር ውጭ የሚገኙ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትና ካህናት አገራዊ ሰላም ላይ ጥላ በሚያጠላ አገራዊና ሕዝባዊ አንድነትን በሚያፈርስ መልኩ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ከቤተ ክርስቲያንና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ነን ከሚሉ በፍጹም የማይጠበቅ ሆኖ አግኝቶታል፡፡
  በመሆኑም በአውስትራልያ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ሁነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እየፈጸሙ ካለው አገራዊና ሕዝባዊ አንድነት ከሚያደፈርስ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ እያሳሰበ አሁንም ወደ ሰላሙና አንድነቱ እንዲመለሱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ይህንንም የሰላም ተልዕኮ የሚያስፈጽም በውጭው ዓለም የሚገኙ ብፁዓን አባቶች የሚመሩት የጋራ የሰላም ልዑክ እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
 3. በአገራችን በኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉና በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግር ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ዕርዳታ እንዲሆን ብር 50,000,000.00 (ሃምሳ ሚሊየን ብር) በቤተ ክርስቲያናችን ስም ችግሩ ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
 4. የአገራችንን ቀጣይ የዕድገት ደረጃ በእጅጉ ከፍ ያደርጋል የሕዝቦችን አኗኗር በመቀየር ከድኀነት ያወጣል በሚል ታስቦበት ከዓመታት በፊት ግንባታው የተጀመረው የሕዳሴ ግድብ እየተጠናቀቀ ያለበት ምዕራፍ ላይ መድረሱና 2ኛ ሙሌት መከናወኑ ለአገራችን ለኢትዮጵያ ትልቅ የድል ምዕራፍ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ አድንቋል፡፡ በቀጣይም ለመጨረሻው የድል ምዕራፍ ለመድረስ መላው ኢትዮጵያውያን በጉልበት በገንዘባቸውም በሐሳብም ጭምር ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል፡፡
 5. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ መንፈሳውያን ኮሌጆችን አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ ጋር ለማመጣጠንና ተጨማሪ ኮሌጆች በማስፈለጉ በደቡብ ክልል የሚገኙ ሁለት ካህናት ማሠልናዎች ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲያድጉ አስፈላጊውም በጀት እንዲመደብላቸው ጉባኤው ወስኗል፡፡
 6. ለመንበረ ፓትርያርክና ለየአህጉረ ስብከት የሚያገለግል የ2014ዓ.ም. ዓመታዊ በጀት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተደልድሎ በቀረበው መሠረት ዝርዝሩን ተመልክቶ በጀቱ እንዲፀድቅ በማድረግ በሥራ ላይ እንዲውል ጉባኤው ወስኗል፡፡
 7. የ4ዐኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫ ላይ የተነጋገረው ጉባኤ በመግለጫው ላይ በመወያየት አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማድረግ እና በማጽደቅ የ2014ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ መመሪያ እንዲሆን ጉባኤው ወስኗል፡፡
 8. በአገራችን በኢትዮጵያ የተደረገው 6ኛ አገራዊ ምርጫ ነጻና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መከናወኑና በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመመረጣቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተሰማውን ደስታ እየገለጸ፤ ቀጣዩ አገራዊ ሥራቸውም ለአገርና ለወገን የሚጠቅም የተሳካ የአመራር ዘመን እንዲሆንላቸው በሥራቸውም እግዚአብሔር አብሮአቸው እንዲሆን ቤተ ክርስቲያን ትፀልያለች፡፡
  በአጠቃላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በጉባኤ በሰነበተባቸው ቀናት ስለ አብነት ት/ቤቶች እና ስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ስለ ሰንበት ት/ቤቶች መጠናከር ስለ አገራዊ ሰላምና አንድነት ሰፊ ምክክርና ውይይት ያደረገ ከመሆኑም በላይ በአገራችን በተከሰተው የሰላም እጦት የደረሰው ጦርነት ረሀብና የጤና ማጣት አብቅቶ ሰላም እንዲሰፍን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰባት ቀናት ጸሎት ያደረገ ሲሆን በቀጣይም መላው ካህናትና ምዕመናን ስለ አገራችን ሰላምና አንድነት እንዲጸልዩ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ አሳስቧል፡፡
  በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ ለ8 ቀናት ሲያከናውን የቆየውን የጥቅምቱ 2014 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ዛሬ ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በጸሎት ዘግቷል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለአገራችን ሰላሙን ለመላው ሕዝባችን አንድነቱን ይስጥልን፡፡
ጥቅምት 18 ቀን 2014ዓ.ም.
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ