መሰረታዊ መረጃዎች

አጭር መግለጫ

ዓለም አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ማለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በዓለም አቀፍ ሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የሚመሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ሰ/ት/ቤት ያለውን አገልግሎት ወጥ ለማድረግ የሚሠራ መዋቅር ነው፡፡

ራእይ

በሀገርና ከሀገር ውጭ ባለ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ተቋማት አባል በመኾንና ለመኾን የተዘጋጁ አዳጊ ሕፃናትና ወጣቶች በቤተ ክርስቲያኒቷ የሃይማኖት ዶግማና ሥርዓት የተኮተኮቱ፣ ሃይማኖቱ የሚያዘውን አኗኗር የሚጠብቁ፣ የሚያስጠብቁና በየዘመናቸው ለክርስትና መከፈል የሚገባውን መንፈሳዊ የተጋድሎ ዋጋ በመክፈል ከትውልድ ወደ ትውልድ ክርስትናን ከነሙሉ መገለጫዎቹ ጋር የሚያሸጋግሩ፣ የነገ ቤተ ክርስቲያንን የሚረከቡ፣  ሀገርን በቅንነት የሚያስተዳድሩ ታማኝነት ያላቸውን በሕዝብ ዘንድ እንደ ምሳሌ የሚታዩ፣ የተወደዱና የተከበሩ በሁለት ወገን የተሣለ ሰይፍ የኾኑ ክርስቲያኖችን ማፍራት

ተልእኮ

  • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር በየደረጃው በተዋቀሩ የመምሪያው ተቋማት ለሚታቀፉ ሕፃናት፣ አዳጊ ሕፃናት፣ ወጣቶችና ጎልማሶች በቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓት፣ በኢትዮጵያና በዓለም የክርስትና ታሪክ፣ በቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርቶች፣ በተቀደሰ ትውፊት ላይ ወጥነትና ተከታታይነት ያለው ዕውቀትን ማስተላለፍ፤
  • ለሕፃናትና ለወጣቶች የሚሰጠው ትምህርት በአሰጣጡ፣ በአደረጃጀቱና በዘዴው ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ እየተሻሻለ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮና የማደራጃ መምሪያውን ራእይ የሚያሳካ በሚኾንበት መልኩ የተቃኘ ማድረግና መቆጣጠር፡፡
  • ወጣቶችን ከቤተ ክርስቲያኒቷ ትምህርት ሥርዓትና የክርስቲያናዊ ማንነት መገለጫ ከሆኑት ማኅበራዊ መስተጋብርና አኗኗር፣ ጠባይና ሥነ ምግባር የሚያስወጡ የየዘመናቱን ኢክርስቲያናዊ ለውጦች በመከታተል በክርስቲያናዊ ትምህርት መታገልና ወጣቶችን ከመወሰድ መጠበቅ፣ እንዲሁም ይህንን ተጋድሎ ማስጠበቅ የሚችልና ለመጭው ትውልድ ጽኑዕ ተቋማዊ መሠረት መጣሉን ማረጋገጥ ነው፡፡
  • ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት፣ ከክርስቲያናዊ ወላጆች ትውፊት፣ ከማኅበረሰቡ ኢትዮያዊ ክርስቲያናዊ አኗኗርና ፍልስፍና ይልቅ በዘመናዊ መገናኛ ብዙኀንና በዘመናዊ ትምህርት ስርጭት የበለጠ የተጋለጡትን የዘመናችንን ሕፃናት፣ ወጣቶች እና ጎልማሶች የሚመጥንና ክርስቲያናዊ ማንነትን የሚያስጠብቁ አዳዲስ ስልቶችንና ዘዴዎችን በመዘርጋት ክርስቲያናዊ ማንነትን ከጥፋት መታደግ፡፡

እሤቶች

  • ቅዱስና ምሳሌ የሆነ አስተዳደራዊ አገልግሎት፡- ተቋማዊ አገልግሎት በይዘት፣ በአኗኗርና በድርጊት ቅድስናን የሚመሰክር ሕፃናትና ወጣቶች <<እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ኹኑ>> በማለት የአምላካችንን ትዕዛዝ የሚተረጉም መኹኑን የሚያረጋግጥ
  • ጽናትና ምስክርነት፡- በጊዜውም አለጊዜውም በክርስቲያናዊ ማንነት መጽናትን በተግባር የሚተረጉምና የተጋድሎ ምሳሌ የኾነ ውሳኔ፣ አገልግሎትና ተግባራዊ ምስክርነት
  • በፍቅር የኾነ አገልግሎት፡- በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ለማጽናት የሌሉትን በትምህርትና በኑሮ ምሳሌነት ለማምጣት ፣ እየተጉ ለኹሉም ፍቅርን መስጠት
  • ዘመኑን መቅደም፡- ክርስቲያን ወጣቶች ኢክርስቲያናዊ እሤቶች ላይ የቆመ ነገር ግን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመረዳት እየተፋፋመ በሚገኘው ሉላዊነት አንጻር “….. ዓለሙን ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው” የሚለውን የክርስቲያናዊ ሉላዊነት አምላካዊ ትዕዛዝ በሚፈጽሙት ላይ የተደቀነውን የክርስቲያኖችን ፈተናዎች የመቋቋሚያ አቅም እንዲያዳብሩ ማስቻል
  • ክርስቲያናዊ ኀላፊነት፡- የእውነትን መንገድ የሚያቆሽሽ የወጣቶችን ውል ፍጹም በኾነ ትጋት መከላከልና ቁጥጥር በማድረግ የመልካም ሥነ ምግባር፣ የታታሪነት፣ የሀገርና የሰው ልጆች ፍቅር ምሳሌ መኾን