የሰላም ዋጋው ስንት ነው?

የሰላም ዋጋው ስንት ነው?

የሰላም ዋጋው ስንት ነው?

ሰላም የሚለው ቃል ሲጠራ ቀላል ቢመስልም ዋጋው ግን በገንዘብ ከመተመን በላይ ነው፡፡ ሰላም እንኳን ለሰው ልጅ ለእንስሳት፣ ለአራዊት እና በጠቅላላው ለሥነ ፍጥረት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ማንም ወጥቶ መግባት፣ ነግዶ ማትረፍ፣ አርሶ መብላት፣ ደግሶ መዳር አይችልም፡፡ ሠርቶ የመለወጥን ተስፋም ያመነምናል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ቅዳሴዋ “እግዚአብሔር በይቅርታው አንድ ያደርገን ዘንድ ስለ ሰላም እንማልዳለን፤ በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ሰላምን እግዚአብሔር ይሰጣት ዘንድ እግዚአብሔርን ስለምትወድ ስለ አገራችን ኢትዮጵያ እንማልዳለን” በማለት ዕለት ዕለት ፈጣሪዋን የምታሳስበው ያለ ምክንያት አይደለም – ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ስለሆነ እንጂ፡፡ እንኳን ሰማያዊ ለሆነው ሃይማኖት ለምድራዊ ኑሮም ቢሆን ዓለም የምትሸልመው ሳይታክቱ ለሰላም የደከሙትን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥቅምት 19 ቀን በሰጠው መግለጫ “በሀገራችን እና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየተከሠተ ያለው ችግር እና ፈተና የሚወገደው ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት እና በኅብረት ለችግሮቹ መፈታት ድርሻ እንዳለን ዐውቀን እንደየእምነታችን አስተምህሮ በጸሎት እና በምሕላ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር በንስሓ በመመለስ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያምናል፡፡ በመሆኑም ስለ ሀገራችን ሰላም እና ስለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት በመላው ዓለም በሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ከኅዳር 15 ቀን 2016 እስከ ታኅሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ጸሎት እና ምሕላ እንዲፈጸም እና መላው ሕዝበ ክርስቲያንም በአንድነትና በኅብረት ከላይ በተጠቀሱት ዕለታት በቤተ ክርስቲያን በመገኘት የበረከቱና የሥርዓተ ጸሎቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖ ጥሪውን ያስተላልፋል” በማለት የገለጠው ያለ ምክንያት አለመሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
እንዲህ ያለው ለአገር ሰላምና ደኅንነት የሚደረግ ጸሎት ሀገረ ነነዌን ከጥፋት የታደጋትን ምሕላ የሚያስታውስ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ግን በአንድ ወገን በጸሎት እየጠየቅን በሌላ በኩል ደግሞ ጥፋት የምንፈጽም ከሆነ ጸሎታችን ተቀባይነት የማያገኝ፣ ፈጣሪያችንን በዕንባ ብንማጸነው እንኳ ልመናችን ጉዳይ እንደማይፈጽም መረዳት የሚገባን መሆኑን ነው፡፡ ሌላው መታወቅ የሚገባው ጉዳይ ጾም ጸሎታችን በአምላካችን ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኘው ከልብ በሆነ መሻት በፍቅር፣ በመከባበርና በመመካከር ሲፈጸም ነው፡፡
የሃይማኖት አባቶች ችግሩን በጾምና በጸሎት ለመፍታት ጥረት ሲያደርጉ መንግሥትና ፖለቲከኞች ደግሞ በመቻቻል አገራቸውን የሚያስቀጥል፣ ትውልዱን ከመከራ የሚታደግ፣ ኋላ ቀርነትን የሚያስወግድ ተግባር ለመፈጸም መተባበር ይኖርባቸዋል፡፡ እየታየና እየተሰማ ያለው ግን የኦርቶዶክሳውያን አሻራ ያለበትን ሁሉ ከምድረ ገጽ አጥፍቶ በሌላ የመተካት ሙከራ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሚዛናዊነት የጎደለው ድርጊት ደግሞ ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ ይቅርና ጊዜያዊ ፋታ እንኳ መስጠት አይችልም፡፡
መንግሥት ሁለንተናዊ አገራዊ ሰላም ለማስፈን በሚል አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙ ተገቢ ቢሆንም አገራችንንም፣ ሕዝባችንንም የሚጠቅመው የታሰበውን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ጉዳዩ ያሳሰበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ “ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ላይ ስለሚኖራት ተሳትፎና ሚና በተመለከተ ጉባኤው በስፋት የተወያየ ሲሆን ሀገራዊ ምክክሩ ሀገራዊ ችግራችንን እንደሚፈታና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚነገሩት የሐሰት ትርክቶች ሁሉ የሚታረሙበት እንደሚሆን ጉባኤው በጽኑ ያምናል፡፡ በመሆኑም በምክክር ሂደቱ ላይ ስለሚኖረን ተሳትፎና ሚና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል እየተጠና አስፈላጊው ሁሉ እንዲፈጸም ሆኖ የምክክር ኮሚሽኑም ይህን የቤተ ክርስቲያናችን ዕቅድ በመርሐ ግብሩ በማካተት ቤተ ክርስቲያናችን የድርሻዋን እንድትወጣ እድሉን እንዲያመቻችልን ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል” በማለት የገለጠው አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ መሄድ መፍትሔ ስለማያመጣ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ይዘነው የኖርነውን መልካም ነገር ወደ ጎን በመተው አዲስ ትርክት እናመጣለን እየተባለ በየመገናኛ ብዙኀኑ ሃያ አራት ሰዓት የሚለፈፈው ጉዳይ ትኩረት ሊሰጥበትና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያማክል፣ አንዱን በይ ሌላውን ተመልካች የማያደርግ መሆኑን በሚገባ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ይህን ምንለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን ሲሠራና ሲፈጸም የምንመለከተው ጉዳይ ኦርቶዶክሳውያንን ያገለለ በመሆኑ ሰላም ማምጣት አልቻለም፡፡ ወደ ፊት ለመተግበር የታሰበውም አካታች የሆነ ትርክት እናመጣለን በሚል ምክንያት የነበረውን አጥፍቶ የራስን ፍላጎት ለማሳካት ይጠቅመናል ያሉትን ይዞ ለመምጣት ከሆነ የደፈረሰው ሰላም ይበልጥ እንዲበጠበጥ ያደርጋል እንጂ መፍትሔ አያመጣም፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ተግባር እና ኃላፊነቱን ሲወጣ ዐሳብ በማቅረቡና መፍትሔ በመጠቆሙ ድርሻ ያላት መሆኑን ያሳሰበችው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
በአገራዊ ምክክር ብቻ ሳይሆን ምሁራን ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች ጦርነት ይብቃ፣ ትውልድ አይለቅ በማለት ተማጽኖ ሲያቀርቡ ሰምቶ እንዳልሰሙ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ቆይቶ ሲጨንቅ ብቻ አስታርቁን ብሎ አማላጅ መላክ ወደ አማናዊው ሰላም እንደማያደርስ መረዳት ይገባል፡፡ መንግሥትም ሆነ ሌሎች አካላት ሰላም የሰፈነ፣ ይህም ባይሆን በኃይላቸው የሚያሸንፉ ሲመስላቸው ይዋጣልን ማለት፣ አቅም ያነሣቸው ሲመስላቸው ደግሞ ሽማግሌ ፍለጋ መውጣት፣ መውረድ ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣ መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ የሚጠቅመው ሰዎች እምነት የሚያሳድሩበትን ተግባር በመፈጸም በልጦ መገኘትና ሁል ጊዜም ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የችግሮችን መንስኤ ለመረዳት ልምድ ያላቸውን ምሁራን በመጥራት ጥናት ካደረገች በኋላ ከሚመለከታቸው ጋር በመተባበር መፍትሔ መስጠት ይገባታል፡፡ ምክረ ሐሳብ ማመንጨት የሚችሉ ወገኖችን በመጋበዝ ዐሳባቸውን መቀበል፣ ላበረከቱት ነገር ዕውቅና መስጠት እና ሌሎችን መልካም ተግባራት ማከናወን ይኖርባታል፡፡ የሚያስተሳስሩንን ከሚያባሉን ለይቶ መጥፎውን በማስወገድ መልካም የሆነውን ማስቀጠል ይገባል፡፡
ጥልቅ ምርመራ የሚጠይቁ ጉዳዮችን በመለየት እንዴት፣ በማን፣ በምን ያህል የሰው ኃይል እንደሚፈታ፣ የሚወሰደው መፍትሔ ሊያስከትለው የሚችለውን ተያያዥ ጉዳይ በመለየት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ጥረት ማድረግ ከቤተ ክርስቲያን፣ ከማኅበራት፣ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት የሚጠበቅ ክርስቲያናዊ ተግባርና ኃላፊነት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የነባራትን ተሰሚነትና የማሸማገል ተግባር መመለስና በሁሉም ዘንድ ሊታመን እና ተስፋ ሊደረግበት የሚገባ የአስታራቂነት ሚናን መወጣት ይገባል። በአጠቃላይ ከዝግጅት እስከ ትግበራ በሚኖረው ሂደት በየምዕራፉ ተሳትፎ እንዲኖራት መሥራት ካልተቻለ በቤተ ክርስቲያን ብሎም በአገር ላይ እየደረሰ ያለው መከራ ከዚህም የከፋ ሊሆን እና የሰላም ጭላንጭልም ጨርሶ ሊጠፋ ስለሚችል ሊታሰብበት ይገባል።