የመዝሙርና ተጓዳኝ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

“ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ቅዱሳን እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር መልአ ሰማያተ ወምድረ ቅዱሳተ ስብሐቲከ – ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ የክብርህ ምስጋና ሰማያትንና ምድርን የመላ ነው እያሉ በሰማይ ከሚኖሩ ቅዱሳን መላእክት የሰማሁት ዜማ ምንኛ ድንቅ ነው?” – (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ ከምትፈጽምባቸው ሰማያዊ ሀብቶች አንዱና ዋነኛው እ.ኢአ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት ከቅዱሳን መላእክት የወረሰችው የማሕሌት ዜማ ሥርዓት ነው። የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትም አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምባቸውን የጸሎት እና የምስጋና ሥርዓቶች በቅዱስ ያሬድ የዜማ ምልክቶች በተቀመሩ እና መንፈስን በሚመስጡ የዜማ ስልቶች ይከውናሉ።

የመዝሙር እና ተጓዳኝ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በሚሰጠው የአገልግሎት አቅጣጫ አማካኝነት የነገዋን ቤተ ክርስቲያናችንን ተተኪ ትውልድ የሚያፈሩ ሰንበት ት/ቤቶችም ይህንኑ ትውፊት ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እየተማሩ ዘመኑን በዋጀ ኪነ ጥበባዊ ትእይንት አስውበው ለጸሎት ለምስጋና እንዲሁም ለምዕመናን የወንጌልን ቃል ለማድረስ እንዲያገለግሉ ያስተባብራል። የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በቃለ ዓዋዲ እና በቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በመላው ዓለም ከመንበረ ፓትርያርክ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እስከ አጥቢያ ሰ/ት/ቤት ድረስ በተዘረጋው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች መዋቅራዊ አደረጃጀት ውስጥ  ለአገልግሎት የሚያቀርቡ መዝሙሮች ይዘት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ ቀኖና ትውፊት እና ሥርዓት የጠበቁ እንዲሆኑ በሊቃውንት ጉባኤ እያስገመገመ ወጥነት ያለው የመዝሙር እና ተጓዳኝ አገልግሎቶችን በኮሚቴው አማካኝነት ያስተገብራል።

በፌስቡክ ያግኙን