የትምህርትና ሥልጠና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ ፳፰፥ ፲፱-፳)

 

የመንበረ ፓትርያርክ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የትምህርትና ሥልጠና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሕፃናት፣ አዳጊዎች እና ወጣቶች

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን ዶግማ ቀኖና ትውፊት እና ይትበሃል ጠንቅቀው እንዲማሩ፣
  • የቤተ ክርስቲያንን ሕግ እና ሥርዓት እንዲያውቁና እንዲያከብሩ፣
  • በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው ሕይወታቸውን በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እንዲመሩ እና ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለመውረስ እንዲዘጋጁ፣
  • በምድር ሳሉም ብርሃናቸው ለዓለም ሁሉ የሚያበራ እንዲሆን እና
  • የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ከትውልድ ወደ ትውልድ በጠንካራ መሠረት ላይ ለማስተላለፍ የነገይቱን ቤተ ክርስቲያን በብቃት እንዲረከቡ ለማመቻቸት ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል።

ለዚህም አገልግሎት የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በቃለ ዓዋዲ እና በቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በማዕከል የሚያዘጋጀውን የሰ/ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት መመሪያ በመላው ዓለም ከመንበረ ፓትርያርክ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እስከ አጥቢያ ሰ/ት/ቤት ድረስ በተዘረጋው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች መዋቅራዊ አደረጃጀት ውስጥ ወጥነት ባለው መልኩ እና የየአህጉረ ስብከቱን ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም የሰንበት ት/ቤት አባላትን የአኗኗር ዘይቤ ባገናዘበ መልኩ እንዲተገበር ያስተባብራል። የሰንበት ት/ቤት አባላት ከሃይማኖት ትምህርታቸው ጎን ለጎን በዓለማዊ የትምህርት መስክም እንደየተሰጣቸው ጸጋ በሚሳተፉባችው መስኮች ሁሉ ውጤታማ እንዲሆኑ፣ ለሌሎች አርአያ መሆን እንዲችሉ እና በቀሰሙት ሙያ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን፣ ሀገርን እና ወገንን በቅንነት እና በፈሪሃ እግዚአብሔር ማገልገል እንዲችሉ ድጋፍ የሚሰጡ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን ያዘጋጃል፣ ያስተባብራል።

በፌስቡክ ያግኙን