የ2019 ዓ/ም የሥርዓተ ትምህርት ማስተግበሪያ የጊዜ ሰሌዳ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ከቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ተልዕኮ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሚገኙ ሕፃናት፣ ወጣቶች እና ጎልማሶችን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት የጸኑ፣ ሥነ ምግባራቸው ያማረ፣ ቀደምት አባቶቻቸውን በመምሰል ቤተ ክርስቲያንን የሚረከቡ እና ሀገርን የሚጠብቁ ትውልድን የማፍራት ሥራውን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ይህንንም ከተዥጎረጎረ እና ወጥነት ከጎደለው፣ ለአንድ ዓላማና ግብ የተናጠል ሩጫ ከበዛበት አሠራር ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ተላቀው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በአንድ ሐሳብና በአንድ ቃል እንዲጓዙ የሚያስችል ሥራን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ከነዚህም አንዱና ዋነኛው የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ነው፡፡ ይህም ሥርዓተ ትምህርት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ባሉ አህጉረ ስብከት በትግበራ ላይ ይገኛል። ሰንበት ትምህርት ቤቶችም ለአተገባበር ያመቻቸው ዘንድ ዓመታዊ የትምህርት መርሐ ግብር የሚያስፈልግ በመሆኑ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ይህን ማስተገበሪያ ሰነድ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል። ይህም ዓመታዊ የትምህርት ማስተግበርያ ሰነድ ለ2019 ዓ/ም የትምህርት ዘመን እንዲሆን ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡

በዚህ ማስተግበርያ ሰነድ ውስጥ የዓመቱን የትምህርት መርሐ ግብር መጀመርያ እና መጨረሻ ጊዜ፣ የፈተና መርሐ ግብራት፣ የሴሚስተር የሪፖርት ጊዜያትን፣ የመርጃ መሣርያ ዝግጅትን ወዘተ በዝርዝር የያዘ ነው፡፡ ለዚህም የትምህርት መርሐ ግብር የየአህጉረ ስብከት ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት እንዲሁም አጥቢያ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሓላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ሰፊውን ድርሻ መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ የትግበራ ሰነድ ወይም የትምህርት መርሐ ግብር በተቀመጠለት ጊዜና ሰዓት ተፈጻሚ መደረግ ይኖርበታል።
ሰነዱን በዚህ ማስፈንጠሪያ ማግኘት ይችላሉ።

የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት
ሐምሌ 2018 ዓ/ም

መጋቤ ሐዲስ ኀይለ እግዚእ አሰፋ በ2018 ዓ/ም የአህጉረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች የአሠልጣኞች ሥልጠና መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ያስተላለፉት መልእክት

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ፣

ክቡር መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ሐላፊ

ዲ/ን ስንታየሁ ምስጋና  የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት  ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ

ክቡራን የሰንበት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አገልጋዮችና የሀገር አቀፍ የሰንበት ትምህርት አንድነት አመራርና  አገልጋዮች

ክቡራን ከየአህጉረ ስብከቱ የመጣችሁ ወድሞቻችንና እኅቶቻችን፣

ከሁሉ አስቀድሞ ልዑል እግዚአብሔር በሰላምና በጤና ጠብቆ፣ በአባታዊ ፍቅሩ ጠርቶ፣ በበረከቱ  ጎብኝቶ፣ በሰላም አምጥቶ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በሀገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ከሐምሌ 6  እስከ ሐምሌ 21 ቀን 2018 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ዩንቨርሲቲ አዳራሽ የሚሰጠውን የመምህራን አሠልጣኞች ሥልጠና በብፁዓን አባቶቻችን ቡራኬ እንደዲከፈት ስለ ፈቀደልን  ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰው እያልኩ  ብፁዓን አባቶቻችን ልጆቻችሁንን ለመባረክና አባታዊ መልእክት ለማስተላለፍ ፣ ወንድሞቻችንም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሰጠው የሥርዐተ ትምህርት ትግበራ ላይ  ሥልጠናውን ለመከታተል የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችሁን ድምፅ ሰምታችሁ መዋቅራችሁን አክብራችሁ በመምጣታችሁ የተሰማኝን ደስታ በመመሪያችን ስም እየገለጽኩ  ሁላችሁም እንኳን ደኅና መጣችሁ  እያልኩ ትንሽ መልእክት እንዳስተላልፍ ይፈቀድልኝ ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

“ዘጸምአ ይምጻእ ኀቤየ ወይስተይ ወዘሂ የአምን ብየ አፍላገ ማየ ሕይወት ይውሕዝ እምከርሡ” “የተጠማ ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፣ በእኔም የሚያምን መጽሐፍ እንደተናገረ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል” (ዮሐ7፡37) ይኸን ቃል የተናገው መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ነው፡፡   ቃሉም የተነገራቸው በሥልጠና ላይ ለነበሩ ደቀ መዛሙርት ነው፡፡ ቃሉን ጠጥተው ጽምዐ ነፍሳቸውን እንዲያርቁ፣ ከዓለማዊ ግብር እንዲላቀቁ፣ በሃይማኖትና በምግባር እንዲልቁ  ፣ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን አንዲለብሱ፣ ከብሌት እንዲታደሱ፣ በአእምሮ እንዲጎለብሱ ስለጠራቸው “የተጠማ ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ” በማለት የሰውን ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ጠርቷቸዋል፡፡  በመተርጒማን ዘይቤ ደረቅ ሐዲስ በሚል  የትንቢት መጽሐፉ የሚታወቀው ነገረ ክርስቶስን በተመለከተ በምልአትና በስፋት የጻፈው ልዑለ ቃል ኢሳይስም  “እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ  ወደ ውኃ ሂዱ”  ሲል ትንቢታዊ ምክሩን ለግሶአል፡፡ ( ትን .ኢሳ 55፡1)

ለሐዋርያነት በመረጠው በክርስቶስ አንደበት “ንዋይ ኅሩይ” “ምርጥ ዕቃ” የተሰኘው ቅዱስ ጳውሎስም “ምድርኒ ለእመ ሰትየት ዝናመ ዘይመጽእ ላዕሌሃ ትወልድ ሣዕረ ሠናየ ሶቤሃ ዘበእንቲኣሁ ሐረስዋ ወትነሥእ በረከተ እምኀበ እግዚአብሔር” “ምድርም በእርስዋ የሚወርደውን  ዝናም ከጠጣች ያን ጊዜ ስለ እርሱ ያረሱላትን መልካም ቡቃያ ታበቅላለች ከእግዚአብሔርም ዘንድ በረከትን ታገኛለች” ብሏል፡፡

የሰው ልጅ ከተፈጠረባቸው አራቱ ባሕርያት መካከል አንዱ ውኃ ነው፡፡  በሥነ ተፈጥሮ ከሰው እስከ እንስሳት፣ ከአራዊት እስከ ዕፀዋት ውኃን ይፈልጋሉ፡፡ ሁሉም የውኃ ጥገኞች ናቸው፡ በተለይ የሰው ልጅ ልብሱን የሚያጥብበት፣ ንጽሕናውን የሚጠብቅበት፣ ምግቡን የሚያዘግጅበት፣  ቢጠማው ጥሙን የሚያርቅበት፣ እንደ ዛሬው መስተዋት በሌለበት ዘመን መልክአ ገጹን የሚመለከትበት አእምሮውን የሚያዝናናበት ውኃ ነው፡፡ ተፈጥሮው ከውኃ ጋር የተሳሰረ ነውና፡፡ የውኃ ጥቅምና አገልግሎት እጅግ  ብዙ ነው፡፡

በልዑለ ቃል ኢሳይያስ አገላለጽ ውኃ፡- የትምህርት፣ የልጅነት፣ የሀብተ ክህነት ምሳሌ ነው፡፡

ልዑለ ቃል ኢሳይያስ  እናንተ የተጠማችሁ ወደ ውኃ ሂዱ ማለቱ እስራኤል ዘሥጋ በፋርስ በባቢሎን ሰባ ዘመን በስደት ከኖሩ በኋላ “ማርና ወተት ወደ ምታፈስሰው ምድረ ከነዓን ተመልሰው የተራቡት በልተው እንደ ሚጠግቡ የተጠሙት ጠጥተው እንደሚረኩ ሲያመለክት  የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ሂዱ ብሏል፡፡

አስራኤል ዘሥጋ የተራቡና የተጠሙት ከምግበ ሥጋ ብቻ አልነበረም  ምግበ ነፍስ ከሆነው ከቃሉም  ተርበውና ተጠምተው ስለ ነበር በመዓር የተመሰለው  ብሉይ ኪዳን በወተት የተመሰለው ሐዲስ ኪዳን በመጀመሪያ በትንቢት በመቀጠልም በገቢር ወደ ሚተረጐምባት የተስፋ ምድር ተመልሰው ጽምዐ ነፍስ ተወግዶላቸው ክብራቸው ተመልሶላቸው  “ንሥኣ ወብልዓ ለእንታክቲ መጽሐፍ”  “እንካ ይህችን መጽሐፍ ብላት”  “ሲሲተ ልብ ቃላቲሁ ለእግዚአብሔር  የእግዚአብሔር ቃል የአእምሮ (የነፍስ) ምግብ ነው” እንዲል ቃሉን ተመግበው እንደ ውኃም ጠጥተው ረክተው የሚኖሩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡  “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ለዘለዓለም አይጠማም ያ እኔ  የምሰጠው ውኃ በውስጡ ለዘለዓለም ሕይወት  የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆንለታል”  እንዳለ ጌታ (ዮሐ 4፡14)፡፡

በክርስቶስ  ትምህርት ውኃ፡- የቅዱስ ወንጌል፣ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ መሆኑን ያመለክታል፡፡

የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክትን አንድምታ ትርጓሜ ያዘጋጁ መተርጒማን ደግሞ ምድር የሚማር ደቀ መዝሙር (ሠልጣኝ)  ዝናም ቃለ እግዚአብሔር፣ ገበሬው መምህር፣ መሆኑን በአብርሆት ትርጓሜያቸው ያስረዳሉ፡፡  የገበሬው ተግባር ማረስ፣ መዝራት፣ ማረም መንከባከብ ነው፡፡ ገበሬው ይዘራል እንጂ አንዱን ቅንጣት ሰላሳ፣ ሥልሳ፣ መቶ ማድረግ አይችልም አሠልጣኝ መምህርም ተግቶና ነቅቶ ያስተምራል እንጂ በሠልጣኞቹ አእምሮ ቃሉን ጽፎ ሠላሳ ሥልሳ መቶ ማድረግ አይችልም ይህን ማድረግ  የእግዚአብሔር ድርሻ ነውና፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡፡

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሥራ ሐላፊዎች

ክቡራን ከየአህጉረ ስብከቱ የመጣችሁ አሠልጣኝ መምህራን፡፡

መምህረ ዓለም ቅዱስ ቄርሎስ “ይእዜኒ ደቂቅየ ጽሑቃን ወፃእክሙ ዝየ ወመላእክሙ ቤተ ክርስቲያን እንዘ ጽሙኣን አንትሙ ትትረወዩ ማየ ዘቤተክርስቲያን ወይፍረይ ልብክሙ ፍሬ ሠናየ በከመ ሀብተ ማይ ያበቊል ፍሬሃ ለምድር ዘወትረ ይሠቅይዋ ከማሁ ቃሎሙ ወትምህርቶሙ ለአበው ቅዱሳን  እለ ተምህሩ በኲሉ ጥበብ ወአእምሮ ይበውእ ውስተ አልባበ ሰብእ ለመድኀኒት ይእዜኒ ንዑ ጽሙኣን ወናረውየክሙ ጽምዐክሙ  ነሢአነ እምጳውሎስ ጠቢብ ማየ እስመ ነቅዐ ሕይወት ውእቱ”

ዛሬም ለትምህርት የምትተጉ ልጆቼ ትምህርትን ወዳችሁ ወደ ጉባኤ መጥታችኋል፤ የቤተ ክርስቲያንን ውኃ ትጠጡ  ዘንድ ማለት  የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ትማሩ፣ ልቡናችሁም በጎ ፍሬን ያፈራ ዘንድ፤ ቤተ ክርስቲያንንም መልታችኋል፡ የውኃ ለምድር መሰጠት ጥዋት ማታ የሚያጠጧት የምድር ፍሬን እንዲያስገኝ  ፍጹም ጥበብን የተማሩ የሊቃውንት ምክራቸውና ትምህርታቸው ሕይወት ለመሆን በሰው ልቡና ያድራል፤ አሁንም ትምህርትን የምትወድዱ ወደ ጉባኤው ኑ  ከጥበበኛው ጳውሎስ ትምህርት አግኝተን አጠጥተን እናረካችኋለን፤ የጳውሎስ ትምህርት የሕይወት ምንጪ የድኅነት መገኛ ነውና (ተረፈ ቄርሎስ ምዕ 23፡5)፡፡

በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት የትምህርት ተቋማት አንዱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ነው፡፡ ይህ መመሪያ ከመንበረ ፓትርያረክ እስከ አጥቢያ ድረስ መዋቅሩ የተጠናከረ ከሀገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጋር እየተናበበ የሚሠራ ሥራዎቹንም ከንግግር ባለፈ በተግባር ገልጦ ያሳየ  ታላቅ መምሪያ ነው፡፡ በተለይ ከአንደኛ እስከ ዐሥራ ሁለተኛ ክፍል በተለያዩ ቋንቋዎች በሀገር አቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት የታተሙትና  እየታተሙ ያሉት  መጻሕፍት መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት  በፈቀደው በጀት፣ በመምሪያው የበላይ ሐላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ አባታዊ መመሪያና ክትትል፣ በመምሪያው የሥራ ሐላፊዎች ትጋት፣ በሀገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች  አንድነት ከፍተኛ ጥረት  የተከናወነ  በመሆኑ መምሪያችን ለሁሉም ምስጋናውን  ያቀርባል፡፡ ጉባኤውንም እንዲያመሰግንልን ይጠይቃል፡፡

በመጨረሻም ከአህጉረ ስብከት የመጣችሁ ሁላችሁም የነገዋ ቅድስት  ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን እናታችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምግበ ነፍሱንና ምግበ ሥጋውን ለእናንተ አዘጋጅታ “ንዑ ብልዑ ኅብስትየ ወስትዩ  ወይንየ ዘቀዳሕኩ ለክሙ ወኅድግዋ ለእበድ ወኅሡ አእምሮ ከመ ትሕየዉ” “ኑ እንጀራዬን ብሉ፤የጠመቅሁላችሁን  የወይን ጠጅም ጠጡ፤ ስንፍናን ትትችሁ በሕይወት ኑሩ” ትላችኋለች (ምሳሌ 9፥5)፡፡  እናንተም የእናታችሁን ምክር ሰምታችሁ በምክሯ ስትኖሩ ደግሞ “ እምዛቲ ትፍሥሕት እንተ ተዐቢ አልብየ ከመ እስማዕ እንዘ በጽድቅ የሐውሩ ደቂቅየ” ልጆቼ በእውነት ሲሄዱ ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም በማለት የእናትነት ደስታዋን በአደባባይ  ትገልጥላችኋለች፡፡

ስለሆነም በቆይታችም እንደ ንብ በምጥቀስሙት የቃል አበባ  የተግባር ማር ወለላን ሠርታችሁ ስትመለሱ ወድሞቻችሁንና እኅቶቻችሁን እንድተመግቡቸው ረክታችሁ እንድታረኩአቸው የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን፡፡

መጋቤ ሐዲስ ኀይለ እግዚእ አሰፋ

በትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሐላፊ

“ስፉሐ ይኩን ትምህርትክሙ ከመ መንጦላዕት”

ከዚህ ይቆየን፡፡

ሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ፡፡

 

 

 

 

 

ሦስተኛ ዙር የ፲፪ ክፍል ምርቃት መርሐ ግብር ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በተገኙበት ተከናወነ።

 

በሰንበት ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ከሙከራ ትግበራ ጀምሮ ትምህርታቸውን ለተከታተሉ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችና የዕውቅና መርሐ ግብር ተከናወነ።

የዕውቅና መርሐ ግብሩ የተከናወነው በ2015 ዓ.ም የዐሥረኛ ክፍል ምዘናን በሀገረ ስብከት ደረጃ ወስደው ለዘንድሮ የዐሥራ ኹለተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ምዘና ለወሰዱ በአዲስ አበባና በሸገር ሀገረ ስብከት የሚገኙ አጥቢያ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነው።

ይህ የዕውቅና መርሐ ግብር በትላንትናው ዕለት በጠቅላይ ቤተክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ሲከናወን ለሦስተኛ ጊዜ ነው።በመርሐ ግብሩ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ የሆኑት መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ የእንኳን ደስ አላቹ  መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን በጉባኤው የተገኙት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የማዕከላዊ ጎንደር ሊቀ ጳጳስ “ይህ የትምህርት መጨረሻ እንዳልሆነ እና የተማረ ትውልድ ለቅድስት ቤተክርስቲያን እንደሚያስፈልጋት” ተናግረው አባታዊ መልዕክት እና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም ተመራቂ ተማሪዎች የምሥክር ወረቀት እንዲሁም ለደረጃ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት በመስጠት የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል። የሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ሰ/ት/ቤት ከሌሎች ተፈታኝ ሰ/ት/ቦእቶች የላቀ ውጤት በማስመዝገቡ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል።

ሦስተኛ ዙር የ፲፪ኛ ክፍል የምርቃት መርሐ ግብር

 

በሙከራ ትግበራ ቀድመው ከጀመሩ እና በልዩ ምዘና ከመካከለኛ ክፍል ከጀመሩ አጥቢያዎች መካከል በ2017 ዓ.ም በሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የ፲፪ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ምዘና የተመዘኑ ተማሪዎች ምረቃ

ዕለተ እሑድ መስከረም ፲፩ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም

በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ

ከቀኑ ፯ ጀምሮ

እንኳን ለደብረ ታቦር በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!

ደብር ማለት ተራራ ሲሆን ታቦር ደግሞ የተራራው ስም ነው፡፡ ደብረ ታቦር ከገሊላ ባሕር በስተምዕራብ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን ገልጦበታል፡፡ ይህም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነሐሴ 13 ቀን ዘጠኙን ሐዋርያት ከእግረ ደብር/ከተራራው ግርጌ/ ትቶ ሦስቱን ሐዋርያት (ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን) አስከትሎ ወደ ተራራው ወጣ። በዚያም ለሦስቱ አርዓያው ተለውጦ፣ ፊቱ እንደ ፀሐይ አብርቶ፣ ልብሱ እንደ በረዶ ነጽቶ፣ ሙሴና ኤልያስ በቀኝና በግራው ቁመው ታዩአቸው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስ ‹‹እመሰ ትፈቅድ ንንበር ዝየ ወንግበር ሠልስተ ማኅደረ አሐደ ለከ፣ አሐደ ለሙሴ፣ ወአሐደ ለኤልያስ›› ትርጓሜውም ‹‹በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ፣ አንዱን ለሙሴ፣ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ›› እያለ ሲናገር ወዲያው ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸውና ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድዬ ዘአፈቅር ወሎቱ ስምዕዎ›› ትርጓሜውም ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚል ቃል ሰሙ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም መቆም ተሳናቸው፤ ሙሴ ‹‹ትኄይሰኒ መቃብርየ›› መቃብሬ ትሻለኛለች ብሏል፤ ኤልያስም በሠረገላው ወደየመጡበት ተመልሰዋል፡፡ ሦስቱ ሐዋርያትም ደንግጠው ወድቀው ነበርና ጌታ ዳስሶ በአስነሳቸው ጊዜ ከእርሱ በቀር ሌላ ሰውን አላዩም፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዝዟቸው ከተራራው ወርደዋል፤ (ማቴ 17፥1-9)።
ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ሲሆን ነብያት እና ሐዋርያት በተራራው ላይ መገኘታቸው ቤተ ክርስቲያን የነብያትንም የሐዋርያትንም ትምህርት ይዛ የመገኘቷ፡፡ ሙሴ ከሞት ተነስቶ በተራራው ላይ ተገኘ ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን መጣ፡፡ ይህም በሰማይ ያሉትም ይሁኑ በምድር ያሉት በአንድነት የሚያመሰግኑባት ቦታ እንደሆነች ሲያስተምረን ነው፡፡

ምሥጢረ መንግሥቱን ለምን በታቦር ተራራ ገለጸው?
መድኃኔዓለም ሌሎች ተራሮች እያሉ ክብሩን ለመግለጥ ስለምን ደብረ ታቦርን መረጠ ቢሉ ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡

1/ ትንቢቱን ለመፈጸም
“ታቦርና አርሞንኤም በስምህ አምነው በተደረገላቸው ነገር ደስ ይላቸዋል፣ ስምህን ያመሰግናሉ፣ ለስምህም ምስጋና ያቀርባሉ” እንዲል /መዝ. 88፡12/፡፡

2./ ምሳሌውን ለመፈጸም
ይህ ተራራ ባርቅ ሲሳራን ድል አድርጎበታል /መሳ.4፡6/፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፡፡ “የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደገና ክፉ ሥራ ሠሩ፡፡ እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቡስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ በአሕዛብ አሪሶት የተመረጠው ሲሣራ ነበር፡፡… ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና የእስራኤልንም ልጆች ሃያ ዓመት ያስጨንቃቸው ነበር” /መሳ 4.1-3/፡፡ ሁሌም ቢሆን የሰውን በደል ዐይቶ እንደወጣችሁ ግቡት፣ እንደገባችኋት ውጧት የማይልና “ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” የተባለለት እግዚአብሔር ከዚህ ቀንበር የሚላቀቁበትን መላ ራሱ አመለከታቸው /1ቆሮ. 10-13/፡፡ እስራኤላውያን ወደ ፈጣሪያቸው በጮኹ ጊዜ የለፊዶት ሚስት የሆነችውንና እስራኤልን በነቢይነትና ዳኝነት ታገለግል የነበረችው ነቢይቱን ዲቦራን ተጠቅሞ የማሸነፊያ መላውን አመለከታቸው፡፡ ነቢይቱ ዲቦራ ትንቢት ከመናገር አልፋ የእስራኤልን ንጉሥ ባርቅ ከእኔ ጋር ወደ ጦርነቱ ውጪ ብሎ ባስጨነቃት ጊዜ በጦር አዝማችነትም ተሳተፈች፡፡ እግዚአብሔር በነቢይቱ በዲቦራ በኩል ለእስራኤል ንጉሥ “ሔደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጡ” ብሎ አዞት ነበርና ንጉሡ ዐሥር ሺሕ ብረት ለበስ ያልሆነ እግረኛ ሠራዊት ይዞ ደብረ ታቦርን ተማምኖ በተራራው ላይ መሸገ፤ ጦርነቱም ሳይጀመር አለቀ፡፡ ምክንያቱም “እግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፡፡ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ” /መሳ. 4.15/፡፡ እስራኤል በእግዚአብሔር አጋዥነት በታቦር ተራራ ላይ የሃያ ዓመት የግፍና የሰቀቀን አገዛዝ ቀንበራቸውን ከትከሻቸው አሽቀንጥረው በምትኩ የድል ካባን ደረቡ፡፡ “በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩ” ተብሎም ጀግንነታቸው ተጻፈላቸው፡፡ የታቦር ተራራ ያኔ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ባለውለታቸው ነበር /ዕብ. 11.32-34/፡፡

ጌታም በልበ ሐዋርያት ያለ ሰይጣንን ድል ያደርጎበታልና ማለትም በልባቸው ጥርጥርን እና ፍቅረ ሢመትን (የሥልጣን ፍቅር) ያሳደረ ዲያብሎስን ድል ነስቶላቸዋል ፡፡ ከዚህም በመነሣት ነው “በዓለ ደብረታቦር የደቀመዛሙርት ተማሪዎች በዓል ነው” የሚባለው ፡፡

ኤልያስና ሙሴን ለምን አመጣቸው?
1/. በአንድ ወቅት ሙሴ እግዚአብሔርን ፡- “በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴ እውነት ከሆነስ ፊት ለፊት ተገልጸህልኝ ልይህና በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴን ልወቀው” ሲል ጠይቆት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም “ጀርባዬን ታያለህ ፊቴን ግን አታይም” ብሎት ነበር /ዘጸ. 33.13፣23/፡፡ የዚህ ኃይለ ቃል ትርጓሜና ሐተታ በደብረ ታቦር ተፈጽሟል፡፡ እንዲህ ማለቱ “አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ሰው ሆኜ ሥጋ ለብሼ ኋላ በደብረ ታቦር እስክገለጽልህ ድረስ አንተ በመቃብር ተወስነህ ትኖራለህ” ማለቱ ነበርና፡፡ ይህን ማለቱ እንደሆነ የታወቀው ግን በደብረ ታቦር ሙሴን ከብሔረ ሙታን አምጥቶ ባቆመው ጊዜ ነበር፡፡

2/ ልዑል እግዚአብሔር ነቢዩ ኤልያስን፡- “አንተ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትሆነኛለህ” ብሎት ነበር፡፡ ይኸውም ኃይለ ቃል ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ “የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ነው ይልሃል? እግዚአ ኤልያስ፤ አምላከ ኤልያስ ይበሉህ እንጂ” ሲል በደብረ ታቦር ተፈጸመ፡፡ ታያለህ የተባለው ሙሴም አየ፣ ትመሰክራለህ የተባለው ኤልያስም መሰከረ፡፡

3/ በፊልጶስ ቂሳርያ ጌታ ሐዋርያትን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?” ብሎ በጠየቃቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ሙሴ ነው ይሉሃል ፤ እንዲሁም የኃይል ሥራህን ተመልክተው ኤልያስ ነው ይሉሃል” ብለው ነበርና ሙሴን ከመቃብር ፤ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ እግዚአ ሙሴ ፤ አምላከ ሙሴ ፤ እግዚአ ኤልያስ ፤ አምላከ ኤልያስ መሆኑን ለማስመስከር፡፡

4/ አይሁድ ፈሪሳውያን ጌታን እንደ ሕግ ተላላፊና የእግዚአብሔርን ክብር ለራሱ የሚወስድ አድርገው ያስቡት ስለነበረ /ዮሐ.9፡16፣ 10፡33/ ሕግን የሰጣቸው ሙሴንና ለሕገ እግዚአብሔር ቀናተኛ የነበረው ኤልያስን አምጥቶ ሕግ አፍራሽ አለመሆኑን የእግዚአብሔር ተቃዋሚም አለመሆኑን ለማስረገጥ፡፡

5/ ጌታችን በሙታንና በሕያዋን ላይ ሥልጣን ያለው እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ ሞተው ከተቀበሩት ሙሴን ከብሔረ ሕያዋንም ደግሞ አልያስን አምጥቶ ሲነጋገር ታየ፡፡

6/ የሐዋርያቱን የወደፊት አገልግሎት ሲነግራቸው፡፡ ይኸውም ሙሴ እና ኤልያስ ለሕዝበ እስራኤል በጣም ታማኝ እንደነበሩ ሁሉ እነርሱም ለሚያገለግሉት ሕዝብ ታማኝ እረኞች እንዲሆኑ፡፡ ሆኖም ግን አገልግሎታቸው ከሙሴና ከኤልያስ ይልቅ ጠንከር እንደሚልም አሳይቶአቸዋል፡፡ ምክንያቱም ውጊያቸው እንደ ሙሴ ከፎርዖን እንደ ኤልያስም ከአክዓብ ጋር ሳይሆን ከክፋት መናፍስት ጋር ነውና፡፡

# የበዓሉ መጠሪያ ስሞች (ደብረ ታቦር / ቡሄ/ ቡሔ መባሉ ስለምንድ ነው ?
• ደብረ ታቦር የተባለው ጌታ ክብሩን የገለጠበት ስፍራ ደብረ ታቦር ስለሆነ በዚሁ በዓሉ ስያሜውን አግኝቷል፡፡

• ቡሔ ይባላል ፡- ቡሄ ብርሃን ማለት ነው በደብረታቦር ቧ ብሎ የተገለጠውን የጌታችንን የፊቱን ብርሃን ጸዳል፤ የልብሱንም እንደ ነጭ በረዶ ጸዓዳ መሆን ያስረዳል፡፡
አንድም፡- ቡሔ ማለት መላጣ (ገላጣ) ማለት ነው፡፡ ይኸውም በበዓሉ ዋዜማ ልጆች ‹‹ ቡሔ በሉ፤ ቡሔ መጣ ፣ ያ መላጣ፣ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ›› ይላሉ እዚህ ላይ ቡሄ ያለው ዳቦውን ነው፡፡
• አንድም፡- ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለምሌሊት›› እንደሚባል ወቅቱ በሃገራችን የጸዓተ ክረምት ዋዜማ ስለሆነ የክረምቱ አፈናው ተወግዶ /ተጋምሶ/ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት ፤ በዶፉና በጎርፉ ተሸፍና የነበረች መሬት የምትገለጥበት በመሆኑ ነው፡፡

• አንድም፡- ቡሔ (ቡሔእየ) ተብሎ ይተረጎማል ይኸውም የደብረታቦር እለት እርሾ ሳይገባበት ተቦክቶ የሚጋገረውን ኅብስት ያሳያል፡፡

# “ችቦ የመብራቱ ፣ የሙልሙል ዳቦ የመጋገሩና የጅራፍ ማጮኽ ምክንያት፡-
ችቦ የሚበራው 12 ለ13 ዋዜማ ሌሊት በ3 ሰዓት ነው ።
• የጌታችን ክብሩ በተገለጠበት ጊዜ ብርሃኑ የሌሊቱን ጨለማ ገፍቶት እስከ አርሞንዔም ደርሶ ነበርና በዚያ አካባቢ የነበሩ እረኞች በሁኔታው ተገርመው ቀንም መስሎኣቸው ሌሊቱም ተዘንግቷቸው በዚያው ቆይተው ነበርና ቤተሰዎቻቸው ምን አግኝቷቸው ይሆን በማለት መብራት አብርተው (ችቦ ይዘው)፣ የሚመገቡትን ይዘው ወገኖቻቸውን ፍለጋ ወጥተዋል እረኞችም ያሉበትን ቦታ ለቤተሰዎቻቸው ጅራፍን በማጮኸ አመልክተዋቸዋልና ይህን ለማሰብ ነው፡፡
• ዋናው ምሥጢሩ ግን፡- የችቦው ብርሃን የጌታ ክብር መገለጡን፣ የጅራፋ ጩኸት ሓዋርያትን ያስደነገጣቸው የአብ የምስክርነቱ ቃል ምሳሌ ሲሆን፣ ኅብስቱ ጌታችን በመስቀል ላይ መሥዋዕት የመሆኑ (የሥጋወደሙ) ምሳሌ ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አዝልፍኬ አንብቦ መጻሕፍት እስመ እማንቱ ይመርሃሁ ለልብከ ኀበ አንክሮተ እግዚአብሔር- መጻሕፍትን አዘውትረህ አንብብ፤ መጻሕፍት እግዚአብሔርን ወደማድነቅ ልብህን ይመሩታልና፡፡ (ማር ይስሐቅ)

ማር ይስሐቅ መጻሕፍትን ማንበብ በውስጣቸው ያለውን እውቀት ከማግኘት ባለፈ ወደ ተመስጦ፣ እግአብሔርንም ወደማድነቅ እንደሚያደርስ ይነግረናል፡፡ ለማወቅም ሆነ ያወቁት ለማስተማር ከጉባኤ ከዋሉ ምስጢር ካደላደሉ ሊቃውንት እግር ስር ቁጭ ብሎ ለሚማሩት ትምህርት በቂ ጊዜ ሰጥቶ መማር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ጉባኤ ቤት ገብቶ በቂ ጊዜም ሰጥቶ መማር ለሁሉ የሚቻል አይደለምና በማደራጃ መምሪያችን በየዓመቱ በክረምት ወቅት የሚሰጥ እንደዚህ ዓይቱ የአጭር ጊዜ ሥልጠና መነቃቃትን የሚፈጥር ለተጨማሪም ትምህርትና ንባብ የሚያነሳሳ ስለሆነ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “መከሩ ብዙ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡” ብሎ እንዳስተማረ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በሁሉም ሰንበት ት/ቤቶች ተግባራዊ እንዲሆን የተጋጀው ወጥ ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም አህጉረ ስብከት በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ መምህራን ያስፈልጉናል፡፡ ይህንን የመምህራን ፍላጎት በአንድ ጊዜ ማሟላት የሚቻል ስላልሆነ እንደዚህ ያሉ ሥርዓተ ትምህርቱን መሠረት ያደረጉ አጫጭር ስልጠናዎች በጣም አስፈላጊዎች ናቸው፡፡

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጋር በመሆንና አህጉረ ስብከትን በማስተባበር ሥርዓተ ትምህርቱ በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ በክረምት ወቅት ከየአህጉረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤት መምህራንን ወደማዕከል በማስመጣት በዚህ መልኩ ሥልጠና ሲሰጥ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ሲሆን በቀጣይም ከአህጉረ ስብከት ጋር በመነጋገርና የሥልጠና ማዕከላቱን በማብዛት የተሻለ ሥራ ለመሥራት ታስቧል፡፡ በዘንድሮው ለሁለት ሳምንታትና ለ200 ሰዓታት በታወቁ የቤተ ክርስቲያናችን መምህራን የተሰጠው ሥልጠና እጅግ የተሳካ ሠልጣኞችም ጥሩ እውቀትና ልምድ የቀሰሙበት እንደነበር እናምናለን፡፡

ስለሆነም ውድ ተመራቂዎች የተማራችሁት ትምህርት መጻሕፍትን በማንበብና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊቃውንትን በመጠየቅ አዳብራችሁ ሥራ ልትሠሩበት ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በትምህርት የወለደው የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስን “ወተዐቀብ እስከ እመጽእ በአንብቦ ወበምሂር ወበገሥጾ ወበጸልዮ – እስክመጣ ድረስ በማንበብና በመምከር በማስተማርም ተጠንቀቅ።” 1ጢሞ. 4፡13 ብሎ እንዳስተማረው እግዚአብሔር ቢፈቅድ ወደፊት ወደጉባኤ ቤትና ወደ መንፈሳዊ ኮሌጆች ገብታችሁ ከዚህ የበለጠ ትምህርት እስክታገኙ ድረስ ከጸሎት ጋር በማንበብና በመምከር በማስተማርም አብዝታችሁ ልትተጉ ይገባል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ  አፈ ወርቅ  “ቅዱሳት መጻሕፍትን አለማወቅ የስህተት ሁሉ ምንጭ ነው፡፡” ብሎ እንዳሰተማረ መጻሕፍትን ባለማወቅ የሚመጣን ስሕተት ቅዱሳት መጻሕፍት አብዝቶ በማንበብና በመመርመር መከላከል ይቻላልና ለማንበብ እንድትተጉ ማደራጃ መምሪያችን አጥብቆ ያሳስባል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቈላስይስ መልእክቱ “ወይኩን ነገርክሙ በጸጋ ወቅሱመ በጼው – ነገራችሁ በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ይሁን በማለት መናፍቃን አብዝተው ቢጠቅሱ እናንተም አብዝታችሁ ጠቅሳችሁ በለጋስነት መልሱላቸው፡፡ ንግግራችሁም በፍቅርና በትሕትና የጣፈጠ ይሁን ብሎ እንዳስተማረ አሁን ያለንበት ዘመን ሐሳውያን የበዙበት መጽሐፍ ቅዱስን እየጠቀሱ የዋሃን ምእመናንን የሚያደናግሩ ሰዎች እንደ አሸን የፈሉበት ዘመን ስለሆነ በየምትሄዱበት አካባቢ ወጣቶችና ሕጻናትን ከመናፍቃን ቅሰጣ ጠብቆ በቃለ እግዚአብሔር ማሳደግ ይቻል ዘንድ የተማራችሁትን ትምህርት በሥራ ላይ በማዋል ዛሬ የተቀበላችሁትን አደራ በአግባቡ ልትወጡ ይገባል፡፡

በእነዚህ ሁለት ሳምንታት በነበራችሁ ቆይታ በተማራችሁት ትምህርት ሳትወሰኑ ሁል ጊዜ ለማንበብና ለመጠየቅ የተዘጋጃችሁ በመሆን ክህደትንና ኑፋቄን የምትቃወሙ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲን ዶግማዋን ቀኖናዋንና ሥርዓቷን ጠብቃችሁ የምታስጠብቁ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃዎች ልትሆኑ ይገባችኋል፡፡

ሰዎችን ለመለወጥ በብዙ የትምህርት ተቋማት አልፎ ብዙ ዕውቀት መሰብሰብ ብቻው በቂ አይደለምና ከማስተማር ጋር አርአያ የሚሆን ሕይወት ሊኖረን ይገባል፡፡ እንዲህ ሲሆን በአገልግሎታችን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ብዙ ኢማንያንን ወደ እምነት እንዲመጡ እናደርጋለን በእምነት ያሉ ወጣቶችና ሕጻናትም በዕውቀት እናሳድጋለን፡፡

በመጨረሻም ውድ ተመራቂዎች ለዚች ቀን እንኳን አደረሳችሁ እያልኩ ያለንበት ወቅት ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እጅግ የፈተና ወቅት እንደሆነ ተድተን ወጣቶችና ሕጻናት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ አገልግሎታችንም ለዘመኑ እንደሚገባ በጥበብና በእውቀት ልናደርግ ይገባል በማለትና አገልግሎታችሁ የተሳካ እንዲሆን በመመኘት መልእክቴን በዚሁ አጠቃልላለሁ፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወ/ትንሣኤ

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ

ሦስተኛው የአህጉረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና የምርቃት መርሐ ግብር ተከናወነ።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 21 / 11 / 2017 ዓ.ም

ሦስተኛው የአህጉረ ስብከቶች የሰ/ት/ቤቶች መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና የምርቃት መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ተከናውኗል። በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የሸገር ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የምስካየ ኅዙናን ገዳም የበላይ ጠባቂ እና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ፣ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋኒዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ በርናባስ የዋግህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ ፣ ዲ.ን ስንታየሁ ምስጋናው የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ተ/ም/ሰብሳቢ ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች ፣ መምህራነ ወንጌል ፣ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የሥራ አመራር አባላት ተገኝተዋል።

ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ባስተላለፉት መልእክት “ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ለ3 ዓመት ከ3 ወር ሐዋርያትን ከተለያየ ግብርና ክፍል መርጦ ካስተማራቸው በኋላ ሂዱና አስተምሩ በሀገር ሁሉ ቋንቋ አስተምሩ ብሎ እንዳዘዛቸውና አልጫ የሆነውን ዓለም በማስተማር እንዳጣፈጡ ሁሉ እናንተም በተማራችሁት ትምህርት ሄዳችሁ እንድታስተምሩ ፣ እንድታሰለጥኑ ፣ ፍሬ እንድታፈሩ” በማለት አባታዊ ምክርና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል።

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም እንዲሁ “ከእግዚአብሔር የተላከ ከእግዚአብሔር የተመረጠ የአምላኩ የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል” በሚል ኃይለ ቃል ተነስተው እርሱን ለማገልገል የሚጠራ ማንኛውም አገልጋይ የእግዚአብሔርን ዓላማ ፣ ሐሳብ የእርሱን ዕቅድና እርሱ ለሰው ያለውን አምላካዊ ጥበብ ፣ መግቦት በፍጥረቱም ላይ እንዴት እንደሚሠራና ጥልቅ የሆነውን ፍቅሩን ሁሉ ይናገራል። ብለው ወደ መጣችሁበት ስንቃችሁን ያዛችሁ በመሄድ በሚገባ አገልግሎታችሁን እንድትፈጽሙ ይሁን በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈው ቋጭተዋል።

በዕለቱ ሌላኛውን አባታዊ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ በርናባስ የዋግህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም እንዲሁ “በአባቶች ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ” የሚለውን የልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ቃል መነሻ አድርገው እናንተም በአባቶቻችሁ ፈንታ የተተካችሁ እንደመሆናችሁ አባቶቻችሁን መስላችሁ ቤተ ክርስቲያንን ልታገለግሉ ይገባል በማለት ለተመራቂ መምህራን የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ “መጻሕፍት እግዚአብሔርን ወደ ማድነቅ ልብህን ይመሩታልና” በሚል ኃይለ ቃል በመነሣት የማደራጃ መምሪያውን መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ተ/ም/ሰብሳቢ ዲያቆን ስንታየሁ ምስጋናው በሥልጠናው ጊዜ አጠቃላይ የተከወኑ ተግባራትና በቀጣይ እንዲሠሩ የሚፈለጉ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል። ሠልጣኝ መምህራኑም የነበራቸውን የ15 ቀን ቆይታ የተመለከተ ዘገባ እና አቋማቸውንም እንዲሁ በተወካያቸው በኩል አቅርበው ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እጅ የዕውቅና የምስክር ወረቀታቸውን ተቀብለው የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።

ሥልጠናው ከሐምሌ 7 እስከ ሐምሌ 20 ቀን ድረስ በተከታታይ ለ15 ቀናት የተሰጠ ሲሆን በሥልጠናውም ላይ ከ30 አህጉረ ስብከት የተወጣጡ 209 መምህራን ተከታትለው አጠናቅቀዋል። ከነዚህም መካከል 106 ቀሳውስትና ዲያቆናት እንዲሁም 8 ሴቶች ይገኙበታል።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት)

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የክረምት የመምህራን አሰልጣኞች ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ መምህራንን ጎበኙ።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 18/11/2017ዓ.ም

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አዘጋጅነት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ እየተሰጠ የሚገኘው የክረምት የመምህራን የአሰልጣኞች ሥልጠና ላይ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በመገኘት አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ የተናገረውን “ለወንድሞችህ ይህንን አስተምራቸው” የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ አድርገው አባታዊ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ልጄ ሆይ ጆሮህን ለመምህራን ስጥ እንደተባለ ከመምህራን እግር ስር ቁጭ ብለው የሚማሩት ቃለ እግዚአብሔር ለሕይወታች ስንቅ ነውና ቅዱስ ጢሞቴዎስን አብነት አድርጎ በሕይወት መተርጎም ይገባል የተማርነውንም ለወንድሞች ማስረዳት መንገር ይገባል ብለዋል።

በመጨረሻም ሰልጣኞች በተከታታይ በቀንም በማታም እየተሰጣቸው ያለውን ሥልጠና በሚገባ ተከታትለው በየሀገረ ስብከታቸው ሲመለሱ በትኩረት ሊሰሩ ለሌሎችም ሊያጋሩ እንደሚገባ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክረምት የመምህራን አሰልጣኞች ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ መምህራንን ጎበኙ።

የሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 14/11/2017ዓ.ም

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አዘጋጅነት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ እየተሰጠ 7ኛ ቀኑን በያዘው የክረምት የመምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በመገኘት አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው ለእናንተ የመንግስተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል” ማቴ 13፥11 በሚል ርዕስ ቃለ እግዚአብሔርና አባታዊ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የመንግስተ ሰማያት ምሥጢር ለማወቅ ጾታና ማዕረግ ሳይለይ ለሁሉም የሰው ዘር የተሰጠ ጸጋ መሆኑንና ይህን ምስጢር አውቆ ማሳወቅ ከመምህራን የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።

አያይዘውም ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት አሳስበው እንደ ሀገረ ስብከታቸው ሰሜን ወሎ ለሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰልጣኞችን በመላክና በመማርያ መጻሕፍት ግዥ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመጨረሻም ሰልጣኞች እየተሰጣቸው ያለውን ሥልጠና በሚገባ ተከታትለው በየሀገረ ስብከታቸው ሲመለሱ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)