ጸሎታቸው የሚጠቅም ውግዘታቸው የሚጎዳ
ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ከመንፈሳዊ ብቃት ደረጃ ላይ የደረሰ አባት መሆኑን መጻሕፍት ይመሰክሩለታል። መንፈሳዊ ሕይወቱን ሢመት ያላደበዘዘበት፣ በዘመኑ ከተነሣ ኑፋቄ ጋር ሲጋደል የኖረ አባት ነው። በጣም መንፈሳዊ በመሆኑም አምላኩን በጸሎት ጠይቆ ሊሞት ለነበረ አንድ ካህን ዕድሜ እንዲጨምርለት አድርጓል። እንደ ኢያሱ ፀሐይ ከመግባት እንድትዘገይ አድርጓል (ድርሳነ ቄርሎስ ገጽ፣ ፫-፭)። ቅዱስ ቄርሎስ መናፍቃንን ቀጥቅጦ የሚያደቅ መዶሻ መሆኑን የምትመሰክረው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳትሆን ፈላስፎች ጭምር መሆናችን በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የዶግማ መምህር የነበሩት ቀሲስ ዶክተር ዮሴፍ ያዕቆብ ክፍል ውስጥ ደጋግመው ይናገሩ ነበር።
በፎክሎርና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል “ዘመን አይሽሬ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ” የተሰኘውን ትምህርት ለማስተርስ ተማሪዎች ያስተምሩ የነበሩት ዶክተር ዮናስ አድማሱ የቅዱሱን ድርሰት ለማስተማሪያ እንዲሆን አባዝተው ለተማሪዎቻቸው ይሰጧቸው ነበር። ቅዱስ ቄርሎስን ያሳደገው የእናቱ ወንድም አጎቱ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ዘእስክንድርያ ነው። መንፈሳዊ ትምህርትን ከተግባራዊ ክርስትና ጋር እየተማረ ያደገው በእስክንድርያ መንበረ ፕትርክና ውስጥ ነው። አጎቱ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ከዚህ ዓለም ድካም ሲያርፍ በየሀገረ ስብከቱ የነበሩ ጳጳሳትና የእስክንድርያ ክርስቲያኖች ፓትርያርክ እንዲሆን መርጠው አሾሙት።
ቅዱሱ አባት መንፈሳዊ ዕውቀት፣ ከጽኑ መንፈሳዊ ተጋድሎ ጋር የሠመረለት፣ ሃይማኖት ከምግባር ጋር የተዋሐደለት ነበር። እርሱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ በሆነበት ዘመን ንስጥሮስም በቍስጥንጥንያ መንበር ላይ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ። መናፍቃን ሹመት ሲያገኙ ደብቀውት የኖሩትን ኑፋቄ ማውጣት መገለጫቸው በመሆኑ ንስጥሮስም ሲሾም በድርያድርስ ተጽፎ ዕቃ ቤት የነበረን ጽሑፍ አግኝቶ በማንበብ “ደግ ሃይማኖት ነው” ብሎ በውስጡ ደብቆት የኖረውን ኑፋቄ በገሀድ ማስተማር ጀመረ። መናፍቃን ሹመት ሲያገኙ ደብቀውት የኖሩትን ኑፋቄ የሚያወጡት አንድም ሥልጣን ስለያዝን ማን ይነካናል በማለት ሲሆን ሁለትም እነርሱን ያህል አባቶች ጥቅም ባያገኙበት ኖሮ ሃይማኖታቸውን በቀላሉ አይቀይሩም ነበር በማለት የዋሃን እንዲከተሏቸው በማሰብ ነው።
የንስጥሮስን ድርጊት የሰማው ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ድርጊቱን የፈጸመው ራሱ ንስጥሮስ መሆኑን ዕያወቀ ሌላ ሰው የፈጸመው አስመስሎ እንዲህ ያለ ክሕደት የሚያስተምር ሰው በሀገረ ስብከትህ አለና መርምር ብሎ ይልክበታል። ንስጥሮስም በሀገረ ስብከቴ አንተ ያልከውን አይነት ኑፋቄ የሚያስተምር ሰው የለም ብሎ መልሶ ይልክበታል። ትንሽ ቆይቶ እንደ ገና እንዲህ ያለ ኑፋቄ የሚያስተምር ሰው በሀገረ ስብከትህ አለና አጣራ ብሎ ይልክበታል። እርሱ ግን የለም ብሎ መልስ ሰጥቶ ኑፋቄውን በዐደባባይ ማስተማሩን ይቀጥላል።
ሦስተኛም ሲልክበት ከእርሱ ኑፋቄ ይከፋል ብሎ ያሰባቸውን መናፍቃን ስም ጠርቶ እኔ እንደ እነርሱ አላስተማርኩም። አንተ የጠቀስከውን አይነት ትምህርት ባስተምር ምንድን ነው ጥፋቴ አይነት መልስ ይሰጠዋል። ቅዱሱ አባት እንደ ገና በዘመኑ የምሥራቅ ሮማ ግዛት ንጉሥ ወደ ነበረው ወደ ታናሹ ወይም ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ እንዲህ ያለ ኑፋቄ የሚያስተምር ሰው በግዛትህ አለና አጣራ ብሎ ይልክበታል። መልእክቱንም ለንጉሡ ብቻ ሳይሆን በንጉሡ ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ለንጉሡ እኅትና ለልጁ ይልክላቸዋል።
ጉዳዩን አጣርቶ የደረሰበት ዳግማዊ ቴዎዶስዮስም ቅዱስ ቄርሎስን አባቴ ያልከው ትክክል ነው። ንስጥሮስ የጠቀስኸውን ኑፋቄ በማስተማር ላይ ነው ብሎ ነገረው። በመቀጠልም አባቴ ጉባኤ ልጥራልህና ተከራከሩ አለው። ቅዱሱ አባትም በንጉሡ አሳብ ተስማማ። በዚህ ምክንያት በ፬፴፩ በቍስጥንጥን ጉባኤ ተደረገ። ቅዱስ ቄርሎስ ጉባኤ ወደ ተጠራበት ቍስጥንጥንያ ሲሄድ ጳጳሳትን ብቻ ሳይሆን የገዳም አባቶችን ጭምር ይዞ ነበር የሄደው። ቅዱሱ እንዲህ ያደረገበት ምክንያት በበረሃ በተጋድሎ የሚኖሩ አባቶች በጸሎት እንዲያግረዙት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከመካከላቸው ለፓትርያርክነትም ሆነ ለጵጵስና የሚያበቃቸው አባቶች ቢኖሩ በጉባኤ መልስ መስጠት እንዲማሩ በማሰብ ነበር።
ቅዱስ ቄርሎስ ይዟቸው ከሄዳቸው ገዳማውያን አባቶች አንዱ ከመንፈሳዊ ብቃቱ የተነሣ ደመና ጠቅሶ ይጓዝ እንደ ነበር ከመጋቢት እስከ ጷግሜን የሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር ያስነብበናል። የቅዱሱ አባት መንፈሳዊ ብቃትም ከጉባኤ ቍስጥንጥንያ በኋላ ተፈጽሞ ታይቷል። ይኸውም ጉባኤው ተጠናቆ ሁሉም ወደየመጣበት ሲመለስ ቅዱሱ አባት ለብሶት የነበረው በጣም የተበጣተሰ ልብስ መሆኑን የተመለከቱ መርከበኞች ቆሻሻ ልብስ ለብሰህ ከታላላቅ አባቶች ጋር መሄድ አትችልም ብለው በመርከብ ከመሳፈር አስቀሩት። መርከበኞቹ የፈጸሙትን ድርጊት ቅዱስ ቄርሎስ አላወቀም ነበር። ፓትርያርኩ የተሳፈረባት መርከብ ከባሕሩ መሐል ስትደርስ በመርከብ እንዳይሳፈር የተከለከለው አባት በደመና ተጭኖ በመርከቧ አናት ላይ ሲያልፍ የተመለከተው ቅዱስ ቄርሎስ አባቴ በጸሎት አስበኝ በማለት ተማጸነው። በሌላ በኩል ማለፍ ሲችል እግዚአብሔር ይህን ያደረገው መርከበኞቹ እንዲያምኑ ነበር። ያም አባት ዕለቱን ከገዳሙ ገብቶ ከመነኰሳት ጋር በጸሎት ተሳትፏል።
በንጉሡ አሳብ አቅራቢነት ለተጠራው ጉባኤ ሊቀ መንበሩ ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ነበር። ቅዱሱ አባት ንስጥሮስን መልስ አሳጥቶ ከረታው በኋላ ወደ አማናዊቷ ሃይማኖት እንዲመለስ አባቶች ቢለምኑትም ንስጥሮስ ግን ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። በዚህ ምክንያትም ንስጥሮስ ወደ ላዕላይ ግብፅ ተጋዘ (ድርሳነ ቄርሎስ በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ፣ ገጽ ፫-፭)። መናፍቁ ንስጥሮስ በላዕላይ ግብፅ ከተጋዘ በኋላም ቢሆን ቅዱስ ቄርሎስ ደጋግሞ “እመቤታችንን ወላዲተ አምላክ፣ ጌታችንን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ደግሞ አምላክ ወሰብእ” ብሎ እንዲያምን ከልመና ጋር መልእክት ይልክበት ነበር። ንስጥሮስ ግን “የያዝኩት ተስማምቶኛል አልመለስም” ብሎ በክሕደቱ ቀጠለ።
ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ብዙ ጊዜ ለምኖት ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ “እመቤታችንን ወላዲተ አምላክ፣ ጌታችንን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ደግሞ አምላክ ወሰብእ” ብላ ለማመን ፈቃደኛ ያልሆነች ምላስህ አትታዘዝልህ በማለት ረገመው። ወዲያውም የንስጥሮስ ምላስ ተጎልጉሎ ደምና መግል ይወጣው ጀመር። በዚህ ሁኔታ ሲሠቃይ ኖሮ ንስጥሮስ ይህን ዓለም ተሰናበተ። በደዌ በመሠቃየቱ ይህን ዓለም፣ ከአምላኩ በመለየቱት የወዲያኛውን ዓለም አጣ። የመንፈሳውያን አባቶች ጸሎታቸው እንደሚጠቅም ሁሉ ውግዘታቸው ቆርጦ የሚጥል ሰይፍ መሆኑን ከቅዱስ ቄርሎስና ከንስጥሮስ ታሪክ እንረዳለን።
በዘመናችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚመሩ አባቶችም እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ቢሆኑ አገር ትጠቀማለች። በዚህ ዘመን ፈልጋ መሾም የሚገባትም እንደ እርሱ ያሉትን አባቶች ነው። ቅዱስ ቄርሎስን የመሰሉ አባቶችን ማግኘት የሚቻለው ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ክርስቲያኖች ሁሉ ጸሎት በመያዝ አምላካቸውን እንዲማጸኑ በማድረግ ነው። እኛ ከለመንነው “ለምኑ ይሰጣችኋል” ብሎ ቃል የገባልን አምላክ የፈቀድነውን ሊሰጠን የታመነ ነው።