መንፈሳዊ በዓል ለማክበር በወጡ ኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚደርስ ጥቃትን አጥብቀን እንቃወማለን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል አንዱ የሆነውን የጥምቀት በዓል እና የቃና ዘገሊላ በዓልን በመላ ሃገሪቱ በሚባል ደረጃ በሠላም ለማክበር የተቻለ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ቤተክርስቲያኒቱ እና አማኞቿ በጋራ ላሳዩት ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ስርዓትና ለጸጥታ ኃይሉ ባሳዩት መልካም ትብብር ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።
ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም በየሺ ደበሌ አካባቢ በምትገኘው የወይብላ ማርያም ታቦትን አክብረው በሚጓዙ ካህናት ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና አዛውንት፣ ጎልማሳና ወጣት ምዕመናን ላይ ለጸጥታ ማስከበር ስራ በተሰማራ የጸጥታ አካል ኃይል የተሞላበት ጥቃት ምክንያት የደረሰው ችግር በተደጋጋሚ አንድ አካባቢ ሆነ ተብሎ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የሚፈጽሙ ክርስቲያኖችን ከማወክ አልፎ ለሞት መዳረጉ በቤተክርስቲያናችን ላይ የሚደርሰውን በደል የሚያሳይ ኢ፟-ሰብአዊ እና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት በመሆኑ የሰንበት ት/ ቤቶች አንድነት በጽኑ ይቃወማል።
ተመሳሳይ ድርጊት ባለፈው ዓመትም የተከናወነ በመሆኑ ካለፈው ተመክሮ በመነሳት ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን እና የጸጥታ አካላት ጋር በዓሉ በሰላም ለማክበር ሰፊ ውይይት በማድረግ ሁሉም ድርሻውን ለመወጣት ኃላፊነት ተወስዶ  በዚያ መልኩ እንዲፈጸም ተደርጓል። ነገር ግን ችግሩ በቦታው ዘንድሮም በድጋሚ መፈጠሩ በአጋጣሚ የተፈጠረ ክስተት ሳይሆን የመንግስትን ስልጣን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያጠቁ አካላት ለመኖራቸው ትልቅ ማሳያ በመሆኑ መንግስት አስቸኳይ ማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ፣ እንዲሁም በድርጊቱ በቀጥታ የተሳተፉና ትዕዛዝ በመስጠት ያስፈጸሙ አካላትን በሕግ አግባብ እንዲጠየቁና ውጤቱን ለህዝቡ ይፋ እንዲያደርግ እያሳሰብን፣በዚህ ሂደት ለተፈጠረው ችግር የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን በቀጣይ ሙሉ ሂደቱን እና ቀጣይ ሥራዎችን የምናሳውቅ መሆኑን እንገልጻለን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!
የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት
ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም

የአንደኛ ክፍል ፈተና ተሰጠ

በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተሰጠው የአንደኛ ክፍል የአጋማሽ ዓመት ፈተና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አስታወቀ። ፈተናው እሑድ ፣ ታኅሣሥ 10 ቀን፣ 2014 ዓ/ም የተሰጠ ሲሆን፤ በሀገረ ስብከቱ በሚገኙ እና የአዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ባስጀመሩ ሃያ ሰባት ሰንበት ት/ቤቶች የሚገኙ  አንድ ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት (1,247) ህጻናት ፈተናውን ወስደዋል።

ከነዚህም ሰንበት ት/ቤቶች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ በማስፈተን ቅድሚያውን የወሰዱ ሰንበት ት/ቤቶች የሚከተሉት ናቸው፦

  1. ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤት አንድ መቶ ሃያ አራት (124)  ህጻናት በማስፈተን፣
  2. መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰ/ት/ቤት አንድ መቶ አምስት (105) ህጻናት በማስፈተን፣
  3. የጽርሐ አርያም ደብረ ሲና በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤት ስድሳ ዘጠኝ (69) ህጻናትን በማስፈተን፣

ከዚሁ ጋር በማከልም በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት የትምህርት ክፍለ ጊዜ የሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶች መሠረተ ሃይማኖት ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና የልሳነ ግእዝ  መሆናቸውን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አስታውቋል።