የወርኃ ጾም መዝሙሮች

የወርኃ ጾም መዝሙሮች ከዘወረደ እስከ ኒቆዲሞስ፣ ከመዝሙረ ማኅሌት መጽሐፍ ከገጽ 150 – 156 የተወሰደ።

የቅዱስ ፓትርያርኩ የዐቢይ ፆም መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ ፣
በጾምና በጸሎት ወደ እርሱ የሚቀርቡትን በዓይነ ምሕረት የሚቀበል እግዚአብሔር አምላካችን፣ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ዓራት ዓመተ ምሕረት የፆመ ኢየሱስ ሱባዔ በሰላም አደረሳችሁ!!
“ትግሁ ወጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት፤ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ”
(ማቴ ፳፮.፵፩) ።
ምድራውያን ሰዎች የምንኖርባት ይህች ዓለመ መሬት ከሰው ውድቀት በኋላ በልዩ ልዩ ፈተና የምትናጥ እንደ ሆነች ሁላችንም የምናውቀው ነው፤ እሷን ከፈተና ነፃ ማድረግም ሆነ መከላከል የሚችል ከፍጡራን ወገን አልተገኘም፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ወበዓለምሰ ሀለወክሙ ትርከቡ ሕማመ፤ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ “ማለቱ ይህንን የሚያመለክት ነው፤ ከዚህ አኳያ ሲታይ ዓለም ምን ጊዜም ከፈተና ውጭ አይደለችም ማለት ነው፤ ይህ እውነት እንደ ሆነ እኛም በዓይናችን የምናየው፣ በአእምሮአችን የምንገነዘበው ሓቅ ነው፤
ግብረ ኃጢአትና ክፉ ሕሊና እስካሉ ድረስ ፈተና ባይቀርም፣ መለኮታዊ መከላከያ የሌለው ግን አይደለም፤ መከላከያውም ኃይለ እግዚአብሔር ነው፤ የእግዚአብሔር ኃይልና ረድኤት ለማግኘት ደግሞ፣ ሰው ቆም ብሎ ማሰብና በንሥሐ ወደ እግዚአብሔር፤ መመለስ ያስፈልገዋል፤ ከዚህ አንጻር የንሥሐ፣ የጾምና የጸሎት አስፈላጊነት ፈተናን ለመከላከል እንደሆነ እንገነዘባለን፤ ይህም በመሆኑ ጌታችን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ በማለት አስተማረን።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

በጌታችን አስተምህሮ መሠረት ፈተናው ከማየሉ በፊት ተግተን ካልጸለይን ፈተና ሁሌም ይጸናብናል፤ ይሁን እንጂ ጌታችን በሌላ በኩል “ለምኑ ይሰጣችኋል” ብሎ ቃል የገባልን በመሆኑ በፈተና ውስጥ ሆነንም በንሥሐ፣ በጾምና በጸሎት እሱን በመለመን ፈተናን መከላከል እንችላለን ፤ ጌታችን እኛን ለማስተማር ዓርባ ቀንና ዓርባ ሌሊት በጾመ ጊዜ በፈተና አምጪው ፍጡር ላይ የተቀዳጀው ድል የምናውቀው ነው፤ አሁን የምንጀምረው የጾመ ኢየሱስ ሱባዔም ፈተናን እንዲያስቀርልን፣ በምትኩም ምሕረቱን እንዲያወርድልን ለመለመን እንደሆነ ሕዝበ ክርስቲያኑ በውል ተገንዝቦ በተመሥጦ ወደፈጣሪው መማፀን ይኖርበታል።
እንግዲህ መዋዕለ ጾም የንሥሐ ጊዜ ነው ሲባል፣ ንሥሐ የምንገባው እንዴት ነው የሚለውንም ማስተዋሉ ተገቢ ነው፤ ልባችን እንደ ሚመሰክርብን ያለንበት ጊዜ፣ጥል ያየለበት፣ ጭካኔ ሥር የሰደደበት እንደሆነ አይካድም፤ በዚህም ምክንያት የብዙ ልጆቻችንና ወገኖቻችን ሕይወት ተቀጥፎአል ፣ኑሮም ተመሰቃቅሎአል፤ ጥላቻ ቦታ ካገኘ ውጤቱ ከዚህ ሌላ ሊሆን አይችልምና ይህንን ሁሉ አስከትሎብናል፤ በመሆኑም በዚህ ወርኃ ጾም ንሥሐ መግባት አለብን ስንል የከረምንበቱን የጥላቻ ሕሊና ከሥር መሠረቱ ነቅለን በመጣል፤ ፍቅርንና ሰላምን በመሻት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አለብን ማለታችን ነው ፤

ጾምን በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ መሥዋዕት የሚያደርገው፣ ኃይል ሰጪ ከሆኑት መባልዕት መከልከል ብቻ ሳይሆን ከጠብና ጥላቻ መራቅና መከልከል እንደ ሆነ በሚገባ ማስተዋል ይኖርብናል፤ በመዋዕለ ጾም ወቅት ኃይል ሰጪ ከሆኑ መባልዕት መከልከል ያስፈለገውም ጠብና ጥላቻን ለመቀነስ፣ብሎም ለማስወገድ ምቹ መደላድልን ለመፍጠር እንጂ ምግቦቹ በራሳቸው ኃጢአት ሆነው አይደለም፤ በመሆኑም ከፈተና ለማምለጥ የእግዚአብሔር ኃይል ያስፈልገናል የእግዚአብሔርን ኃይል ለማግኘት ደግሞ በኃይለ ሥጋ ሳይሆን በኃይለ መንፈስ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ያስፈልጋል፤

ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ደግሞ ከባልንጀራ ጋር በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ፍጹም ፍቅር መመሥረት ያስፈልጋል፣ ፍቅር ስለተባለውም ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ “በአጠገብህ ያለውን ወንድምህን ሳትወድ እግዚአብሔርን እወዳለሁ ማለት ውሸት ነው” ብሎ እንዳስተማረን ወንድማችንን ሳንወድ ወደ እግዚአብሔር ብንቀርብ ተቀባይነት እንደ ማይኖረን ማወቅ አለብን፤ በመሆኑም ለእግዚአብሔር ክብርና ለዘላቂ ሰላም ሲባል ወደ እውነተኛው ፍቅር መሸጋገር አለብን፤ ያን ጊዜ እግዚአብሔር ፍቅራችንን ድልድይ አድርጎ ፈተናውን ያርቅልናል፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት !
ባጋጠመን ሀገራዊ ፈተና መነሻነት ሕዝባችን ሲፈተን ቤተ ክርስቲያናችንም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከመሆን እንዳላመለጠች ሁላችንም የምንገነዘበው ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ለሕዝብ የተፈጠረችና በሕዝብ መካከል ያለች በመሆኗ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው ሁሉ በእርስዋ ላይም በቀጥታ ይደርሳል፤ ከዚህ አኳያ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምም በዚህ መዋዕለ ጾም ፍቅርን በተላበሰ ንሥሐ እግዚአብሔርን እንድንጠይቅ በዚህ አጋጣሚ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤
በመጨረሻም፦
በመዋዕለ ጾሙ ስለ ሀገርና ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ፣ስለ ሕዝባችን ዘላቂ ፍቅርና ስምምነት አጥብቀን እንድንጸልይ፣እንደዚሁም በግጭቱና በድርቁ ለተጐዱ ወገኖቻችን ካለን በማካፈል የችግሮቻቸው ተካፋይ እንድንሆን፣ ከዚህም ጋር ለሀገራዊ ሰላምና ፍቅር መሳካት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ መዋዕለ ጾሙን እንድናሳልፍ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን ።

እግዚአብሔር ወርኃ ሙን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በደህና ያድርሰን ፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን !

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
የካቲት ፳፩ ቀን ፳፻፲፬ ዓመተ ምሕረት ፤
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ፤

በላዔ ሰብ እና እሥራኤል ዘሥጋ

በታሪክ እንደሚታወቀው እሥራኤል ዘሥጋ በግብጽ ባርነት ለ430 ዓመት ተገዝተው ነበር፡፡ እግዚአብሔርም የሲዖል ምሳሌ ከምትሆን ግብጽ በዘጠኝ ታላላቅ ተዓምራት በአሥረኛ ሞተ በኵር በአሥራ አንደኛ ስጥመተ ባሕር ግብጽን በመቅሰፍ ነጻ አውጥቷቸዋል፡፡

እስራኤል ዘሥጋ ግን ይህንን ታላቅ ውለታ በማሰብ ፈንታ አምላካቸው እግዚብሔርን አሳዘኑ ቀልጦ ለተሠራ ጣዖት ሰገዱ ሰዉለትም፡፡ ‹‹እስራኤል ሆይ ስማ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አሉ፡፡›› ዘጸ 32፡1-14 መዝ 105፡23 የእግዚአብሔርም ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፡፡ ያጠፋቸውም ዘንድ ከተመረጠው መስፍን ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጋር መከረ፡፡ ‹‹ይህንን ህዝብ አየሁት እነሆ አንገተ ደንዳና ነው፡፡ አሁንም ቁጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፡፡ አንተ ግን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለው፡፡›› አለው፡፡ ዘጸ 32፡9-10

ሙሴም ሕዝቡን እንዳያጠፋቸውና ከቁጣው ይመለስ ዘንድ ስለ ሕዝቡ ያማልድ ጀመር፡፡ በተለይም እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ከአብርሃም ከይስሐቅ እና ከያዕቆብ ጋር የገባውን ቃልኪዳን ያስብ ዘንድ ለመነ፡፡ ‹‹ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለው፡፡ ይህችንም የተናገርኳትን ምድር ለዘራችሁ ሁሉ እሰጣለው፡፡ ለዘላለምም ይወርሷታል ብለህ በራስህ የማልክላቸውን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ፡፡›› አለው፡፡ ዘጸ 32፡13

እግዚአብሔርም የቅዱሳኑ ስም ተጠርቶ ሲሰማ የገባላቸውን ቃል ኪዳን አሰበ፡፡ በሕዝቡ ላይ ሊያደርገው ስለነበረው መቅሰፍት ፈጽሞ ራራላቸው፡፡ ይቅርም አላቸው፡፡ ‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃልኪዳኔን አደረግሁ፡፡›› ያለ አምላክ ከተመረጡት ቅዱሳን ከአብርሃም ከይስሐቅ ከያዕቆብና ከሌሎችም ቅዱሳን ጋር ቃልኪዳኑን እንዳደረገ እንዲሁ ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከእናታችን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያምም ጋር እንዲሁ ቃልኪዳኑን በዛሬው ዕለት የካቲት 16 ቀን አድርጓል፡፡ እመቤታችንም ‹‹መታሰቢያዬን የሚያደርገውን፣ በስሜ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጸውን ፣ የተራቆተ የሚያለብሰውን፣ በሽተኛ የሚጎበኘውን፣ የተራበ የሚያበላውን፣ የተጠማ የሚያጠጣውን፣ ያዘነን የሚያረጋጋውን የተበሳጨ የሚያስደስተውን፣ መመስገኛየን የጻፈና ያጻፈ ፣ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በስሜ የሰየመውን፣ በምመሰገንበት ቀን ዝማሬ ያቀረበውን ዓይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን የሰው ኅሊና ተመራምሮ ያልደረሰበትን መልካም ዋጋ ትሰጥልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡›› ብትለው፡ ጌታም ‹‹መሃልኩ ለኪ በርዕስየ በከመ ኢይሔሱ ኪዳንየ›› ያልሽውን ሁሉ ላደርግልሽ ቃል ኪዳኔንም ልጠብቅልሽ በራሴ ማልሁልሽ በማለት የምህረት ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡

የአብርሃም የይስሐቅ እና የያዕቆብ ቃልኪዳን የእግዚአብሔርን ሕልውና ለካዱ ቀልጦ ለተሠራ ጣዖት ለሠገዱ ለእስራኤል ዘሥጋ መትረፉን መጽሐፍ ቅዱስ ከነገረን በተዓምረ ማርያም ላይ ደግሞ ስምዖን በግብር ስሙ በላዔ ሰብ 70 ሰዎችን በልቶ በቃል ኪዳኗ ተጠቅሞ መዳኑን ይነግረናል፡፡ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ቃልኪዳን የማይሆነውን እንዲሆን የሚሆነን ደግሞ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ ያጠረውን ያስረዝማል፡፡ የረዘመውን ያሳጥራል፡፡ ኃጥኡን ያጸድቃል፡፡

ዛሬም እስራኤል ዘነፍስ የምንሆን እኛ ክርስቲያኖች በእመቤታችን ቃልኪዳን በመታመን ሀገራችን ላይ እና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተቃጣውንና እየደረሰ ያለውን መከራ እርሱ በቸርነቱ ያርቅልን ዘንድ ስለ እናትህ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብለህ ማረን ይቅር በለን እያልን ተግተን ልንለምነው ይገባል፡፡
የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ ስም ሲነሳ በእስራኤል ዘሥጋ ላይ ያልጨከነ ለድካማቸውም የራራ አምላካችን የእናቱን ስም ጠርተን በቃልኪዳኗ ብናምለው እንደምን አይራራልንም?

50 ሺህ መጻሕፍት ለ50 ሰንበት ት/ቤቶች

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ ክፍል በጦርነት ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው በ10 ወረዳ ውስጥ ለሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች 50 ሺህ መጻሕፍት ለማበርከት ድጋፍ ማሰባሰብ መጀመሩን አስታውቋል።

ድጋፉ የሚደረገው በወቅታዊ ጦርነት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው በ10 ወረዳ ቤተ ክህነቶች ሥር ለሚገኙ ሃምሳ ሰንበት ትምህርት ቤቶች 50 ቤተመጻሕፍት ለመክፈት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 50 ሺህ መጻሕፍት ድጋፍ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ተመላክቷል።

ሁሉንም ምዕመናንን ተሳታፊ ያደረገ የልገሳ መርሐ-ግብር ከየካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለ1 ወር የሚቆይ መጻሕፍት የማሰባሰብ ተግባር መጀመሩን የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ ክፍል ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር ዲያቆን ስንታዬሁ ማሩ አስታውቀዋል።

የመጻሕፍት ልገሳ ማሰባሰብ መርሐ-ግብሩ በተመረጡ አድባራትና የሚካሄድ ሲሆን የመጻሕፍት ልገሳ ተግብሩ ከአንድ ወር በኋላ ሲጠናቀቅ ከየሰንበት ትምህርት ቤቱ በተውጣጡ ተወካዮች አማካኝነት በተመሳሳይ ቀን በ10ሩም ወረዳዎች ርዕሰ ከተሞች ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የመጻሕፍት ስጦታው የእርስ በእርስ የመደጋገፍ ግንኙነታችንን ለማጠንከርና በጦርነቱ ውስጥ የነበሩ ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችንን በተሻለ መልኩ ለማጠናከር የስርጭት ተግባራት ይከናወናል ሲሉ ዲያቆን ስንታየሁ ተናግረዋል።

እንኳን ለጾመ ነነዌ በሰላም አደረሳችሁ!

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን በመዋዕለ ስብከቱ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ከጠየቁት ጥያቄ በመነሳት ስለ ሰብዓ ነነዌ እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር። “በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና፦ መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን አሉ። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።” ማቴ 12፡38-41

ቀድሞ አምላካቸውን ያሳዘኑት ሰብዓ ነነዌ (የነነዌ ሰዎች) ስለ ኃጢአታቸውና ስለ በደላቸው ምሕረትን ጠይቀው ንስሐ ገብተው ሦስት ቀን ጾመው ጸልየው በአምላካቸው እስኪመሰከርላቸውና በትውልዱም ላይ ለመፍረድ ሥልጣኑን እስኪሰጣቸው ድረስ ይቅርታውን ምሕረቱን ቸርነቱን እንደገለጠላቸው እኛም ጾሙን ጾመን ንስሐ ገብተን አምላካችን ይቅር ይለን ዘንድ ተግተን እንለምነው።

የቋሚ ኮሚቴዎች እና ንዑሳን ኮሚቴዎች የውስጥ አሠራር መመሪያዎች ትግበራ ሂደት ላይ ገለጻ ተሰጠ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ መንበረ ፓትርያርክ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት በመላው ዓለም ለሚገኙ ሰ/ት/ቤቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ዘመኑን በዋጀ ተደራሽነት ወጥነት እና ዘላቂነት ባለው አሠራር ለመምራት እንዲያስችለው የሚያግዝ የቋሚ ኮሚቴዎች፣ የዋና ክፍሎች እና የንዑሳን ኮሚቴዎች የውስጥ አሰራር መመሪያ ረቂቅ ሰነድ መዘጋጀቱን ተከትሎ ትላንት እሁድ የሰነዶቹን የትግበራ ሂደት የሚዳስስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ለሥራ አመራር አባላት መሰጠቱን የአንድነቱ ም/ሰብሳቢ ዲ/ን ስንታየሁ ምስጋናው ገለጹ።

አንድነቱ የመጀመሪያውን ዙር የመሪ ዕቅድ ትግበራ አጠናቆ በአሁኑ ወቅት በሁለተኛው ዙር የመሪ ዕቅድ ትግበራ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ም/ሰብሳቢው በዕቅድ ከተያዙት ተግባራት መካከል የሰ/ት/ቤ/ትን ተቋማዊ ጥንካሬ እና የአፈጻጸም ብቃት ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ በሚጠይቀው ደረጃ ማሳደግ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ ምክትል ሰብሳቢው ገለጻ የቋሚ ኮሚቴዎችን፣ የዋና ክፍሎችን እና የንዑሳን ኮሚቴዎችን የዕለት ተዕለት አፈጻጸም በወጥነት እና በዘላቂነት ለመምራት በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የተዘጋጁት የውስጥ አሠራር መመሪያዎች የሙከራ ትግበራ ሂደት የሰ/ት/ቤት ተቋም ግንባታ ሂደት አካል ሲሆን ዝግጅቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ትግበራ ሲጀመር አንድነቱ ለሰ/ት/ቤቶች ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ተቋማዊ ብቃት ለማጠናከር አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስኬደው መሆኑ ይታመናል። የተዘጋጁት መመሪያዎችም የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ውስጣዊ አሠራር የተቋማዊ አሠራር መገለጫዎች የሆኑትን ወጥነትን፣ ዘላቂነትን እና የማያቋርጥ መሻሻልን ታሳቢ ያደረጉ እንደሆኑ እና በዓለም አቀፍ መልካም ተሞክሮዎች ላይ የተመሠረቱ ዘመናዊ የሥራ አመራር ጥበቦችን ያገናዘቡ እንደሆኑ ምክትል ሰብሳቢው ገልጸዋል።

የመመሪያዎቹ የትግበራ ሂደት የአንድነቱን የመዋቅር አካላት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ ያስገባ እና የተቀናጀ ትግበራ ስልት አሳላጭ መንገዶችን ያካተተ ሲሆን ይህንኑ ሂደት በዋናነት የሚመራ አጋዥ ኃይለ ግብር ግብረኀይል በማካተት በሙያው የካበተ ልምድ ባላቸው የሥራ አመራሩ አባላት እንዲመራ በቋሚ ኮሚቴ ደረጃ የተዋቀረ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። የቋሚ ኮሚቴው ኃላፊ እንደገለጹት ኮሚቴው የመጀመሪያውን የስድስት ወር መሰናዶ ዕቅድ በመንደፍ ሥራውን የጀመረ ሲሆን በቀጣይ ሂደቶችም ከመነሻ የትግበራ ሂደቱ የሚገኙትን ተሞክሮዎች መሠረት በማድረግ እና የአህጉረ ስብከት ሰ/ት/ቤቶች አንድነት መዋቅር አካላትን በማሳተፍ በአህጉረ ስብከት ደረጃ ሥራ ላይ የሚውል ተመሳሳይ የውስጥ አሠራር መመሪያዎችን የማዘጋጀት እቅድ መኖሩ ገልጸዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አያይዘውም በመላው ዓለም የሚገኙ የአህጉረ ስብከት ሰ/ት/ቤቶች አንድነት መዋቅር አካላት ብሎም አጥቢያ ሰ/ት/ቤቶች በዚሁ ዙሪያ በመጪዎቹ ወራት በሚኖረው የትግበራ ሂደት እንዲሳተፉ እና የሚጠበቅባቸውን ግብዓት እንዲሰጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በአንድነቱ የውስጥ አሠራር ማሻሻያዎች ዙሪያ ከተጠናቀቁት ተግባራት መካከል በያዝነው የትምህርት ዘመን መጀመሪያ የተለቀቀው የአንድነቱ ድረ ገጽ መሆኑን የገለጹት ምክትል ሰብሳቢው በቀጣይ ሂደቶችም በርካታ የተቋም ግንባታ ሥራዎች መታቀዳቸውን እና የሰ/ት/ቤቶች ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሚበረታታ መሆኑን አስታውሰዋል።

በትግበራ ሂደቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ ከተነሱት ነጥቦች መካከል ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ወቅት እያጋጠማት ያለውን ውጫዊ ፈተና ሰ/ት/ቤቶች በተሻለ ተቋማዊ አንድነት ላይ ቆመው ለመመከት የተቀናጀ፣ ዘላቂነት እና ወጥነት ያላቸው የውስጥ አሠራርን የሚያቀላጥፉ የተቋም ግንባታ መርሖዎችን መከተል እንደሚገባቸው ተገልጿል።

የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መዋቅር ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መመሪያ በኩል የምትሠራውን ሥራ የበለጠ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ መመሪያ ወጥቶለት ሥራ የገባ መዋቅር ነው፡፡ መዋቅሩም በዋናነት ሁሉም ሰንበት ት/ቤቶች ዘንድ ወጥ የሆነ የአገልግሎት ሥርዓት ከመዘርጋት በተጨማሪ ተተኪው ትውልድ ወጣቱ ከተናጠል አገልግሎት ተናባቢና ተልዕኮ መር አገልግሎት ውስጥ በሁሉም ዓለም ተደራሽ ለማድረግ ታሳቢ በማድረግ የተቋቋመ አደረጃጀት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ኃላፊነት መሠረት ይህ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጀው የውስጥ መመሪያ፣ በአኅጉረ ስብከት፣ በወረዳ ቤተ ክህነትና በአጥቢያ ደረጃ በተመሳሳይ እየተዘጋጀ እንደሚወረድ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡  በግንኙነት ክፍል ቋሚ ኮሚቴ የውጭ ግንኙነት ዋና ክፍል የዜና እና ወቅታዊ መረጃዎች ዝግጅት ንዑስ ክፍል