በረሃብ ከመሞት በጦርነት መሞት ይሻላል

በረሃብ ከመሞት በጦርነት መሞት ይሻላል

በረሃብ ከመሞት በጦርነት መሞት ይሻላል

ዓለም ለዘመናት የተለያዩ መከራዎችንና ፈተናዎችን አስተናግዳለች። የብዙዎቹ ችግሮች ምንጮች ደግሞ ሰው ሠራሽ ናቸው። ሰው በእግዚአብሔር አርአያ መፈጠሩ፣ ዐዋቂና አስተዋይ ፍጡር መሆኑ ለችግሮቹ መፍቻ ቁልፍ ለማግኘት እንዲችል አድርጎታል። በዚያው ልክ ራሱ ለፈጠራቸው ችግሮች መፍትሔ አጥቶ ሲባዝን ይታያል። በዚህም ምክንያት ሰው የስኬቱ ተጎጂ (the victim of his own success) ሆኗል። እሳትና ውኃ ቀርቦልሃል ወደ ወደድኸው እጅህን ጨምር ሲባል ሁለቱንም እጁን ወደ ሁለቱም የሚልክ ባክኝ ፍጡር እየሆነ ነው። የሰው ልጅን ሁሉ ሊያጠፋ የሚችል አቶሚክ ቦንብ ሠራ። በሽታንም የበሽታ መድኀኒትንም፣ ኮምፒዩተርን የኮምፒዩተር ቫይረስንም መፍጠሩ እሳትንም፣ ውኃንም ለመምረጡ ማሳያዎች ናቸው። ሞትንም፣ ሕይወትንም በአንድ ጊዜ ምርጫው አድርጎ ለመኖር የሚሻ ፍጡር ሰው ብቻ ሳይሆን አይቀርም። የሰው ልጅ ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ሰልፍ ነው እንደ ተባለ፣ በእያንዳንዱ ርምጃው ምርጫ አለው። ይህ ምርጫው ከመልካምና ከመጥፎ ብቻ ሳይሆን ከሁለት መጥፎዎች ውስጥ አንዱን እስከ መምረጥ ድረስ ይዘልቃል።

ለዚህም ነው ሞት ለሁሉም የተሰጠ መክሊት መሆኑን የተረዱት አበው “በረሀብ ከመሞት በጦርነት መሞት ይሻላል” የሚል የአሟሟት ምርጫ ውስጥ የገቡት። ይህ ምርጫ የችግር ምርጫ ነው። ቢሆንልን የሁላችንም ምኞት በሕይወት መኖር ነው። ዳሩ ግን ሞት ከመጣ የአሟሟታችን ነገር ስቃይ ያልበዛበት እንዲሆን እንመኛለን። ምርጫው የሚያወዳድረው ጦርነትንና ረሀብን ሳይሆን ከሁለቱ በየትኛው መሞት እንደሚሻል ነው። ረሀብም ጦርነትም ሁለቱም መልካም ነገሮች አይደሉም። እንዲያውም አንዱ የአንዱ መንስኤ፣ አንዱ የሌላኛው ውጤት ሆነው የሚታዩበት ጊዜ ብዙ ነው። ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ዘርቶ ማጨድ፣ ሠርቶ ማደር፣ ነግዶ ማትረፍ የሚታሰብ አይደለም። እነዚህ ተግባራት ደግሞ ሰው ራሱን ለማኖር የሚሰማራባቸው ናቸው። በሰላም እጦት ሥራቸውን መከወን ያልቻሉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ነዋሪዎች ከኖሩበት ቀየ ተፈናቅለው ለስደት ይዳረጋሉ። ከባለሀብትነት ከፍታ ወደ ድህነት አዘቅት ይወርዳሉ። በጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ብቻ ሳይሆኑ ከጦርነቱ በአፍአ ያሉ ንጹሐንም የችግሩ ተቋዳሽ ይሆናሉ። በጦርነት ከሚያልቀው ባልተናነሰ ጦርነቱ በሚፈጥራቸው የጎንዮች ችግሮች የሚጎዱት ቁጥር የሚበዛበት ጊዜ ቀላል አይሆንም። በአብዛኛው ረሃብ ጦርነት ወለድ ሆኖ ይታያል።
ይህም ሆኖ በረሀብ ከመሞት ይልቅ በጦርነት መሞት ይሻላል። በጦርነት ሰዎች የሚሞቱት አንዴ ነው። ረሀብ ግን ሰዎችን የሚገድለው በሒደት ነው። በረሀብ ውስጥ ያሉ ወገኖች በእያንዳንዱ ቀን ለመኖር ካላቸው ተስፋ የተነሣ በብዙ መከራ ውስጥ ለማለፍ ይገደዳሉ። ወላጆች የልጆቻቸውን ፊት መገርጣት፣ የሥጋቸውን መሟሸሽ፣ የዐይናቸውን ወደ ውስጥ መግባት በማየት በየቀኑ ይሞታሉ። ጦርነት የምንወዳቸውን ሰዎች ያሳጣናል፤ ረሀብ የምንወዳቸው ሰዎች በፊታችን በብዙ መከራ ሲሰቃዩ ያሳየናል። ሞት የማይቀር ዕዳ ነውና አልቅሰን እንቀብራለን፤ በየቀኑ እየሞተ የሚሔድ ወዳጃችንን ግን ምን ልናደርገው እንችላለን።
አሁን አገራችን ያለችበትን ሁኔታ በእጅጉ አሳዛኝ የሚያደርገው የኢትዮጵያውያን መከራ ጦርነት ከረሀብ ያስተባበረ መሆኑ ነው። ኢትዮጵያውያንን ለማጥፋት ቁንጣንም፣ ጠኔም ተባብረዋል። በአንድ በኩል ዜጎችን ከመኖሪያ ቀያቸው የሚያፈናቅል፣ የሚያግት፣ ሀብት ንብረታቸውን የሚያወድምና ሰላም የሚነሣ አካል አለ። በሌላ በኩል በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት በተፈጠረ ረሀብ ምክንያት በስቃይ ውስጥ የሚገኝ ሕዝብ አለ። በረሀብ የሚሰቃየውን ሕዝብ ለመርዳት መንገድ የለም። መንገዶች ሁሉ በጦርነት ተዘግተዋል። ከረሀብ ጋር የሚታገልን ሕዝብ በጦርነት ለማድቀቅ የሚፈልጉ ደግሞ አሉ። ጦርነትም ሕግ አለው፤ ሰብአዊ ርዳታ በየትኛውም መልኩ ሊከለከል አይገባም። ስለሆነም በረሀብ የሚሰቃዩ ወገኖች ለከፋ ጉዳት ከመዳረጋቸው በፊት ሰብአዊ ርዳታ ሊደርስላቸው ይገባል። ሁሉም ወገን የንጹሐንን ጉዳት የሚቀንስ መንገድን መፈለግ አለባቸው። በተለይም መንግሥት የዜጎቹን ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት አካል መሆኑን ለአንዴም መዘንጋት የለበትም። ከአላስፈላጊ እልህ መውጣት፣ ርዳታ የሚስፈልጋቸውን ማገዝና በብዙ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ለረሃብ የተጋለጡ ወገኖችን መታደግ ይገባል።