በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የተዘጋጁት የ1ኛ ክፍል መጻሕፍት ተሰራጩ
በቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝ በሊቃውንት ጉባኤ ተገምግሞ በጸደቀው የሰ/ት/ቤቶች ወጥ ሥርዓተ ትምህርት ማዘጋጃ መምሪያ መሠረት ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የተማሪዎች መጻሕፍት ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከሰ/ት/ቤቶች መምህራን እና ከዘርፉ ባለሙያዎች በማወቀር ዝግጅት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ በዋናነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ያሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በትምህርት አሰጣጥ ረገድ አንድ የሚያደርገው የሰንበት ትምህርት ቤቶች መማርያ እና ማስተማሪያ ሥርዓተ ትምህርት መጽሐፍ ለአንደኛ ክፍል ተጠናቅቆ ተሰራጨ።
ይህ የሥርዓተ ትምህርት መጽሕፍ በአምስት የትምህርት ዓይነት እና ከአንድ የማስተግበሪያ ሰነድ ጋር የተዘጋጀ ነው። ትምህርቶቹም መሠረተ ሃይማኖት ፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ጥናት ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እና የግእዝ ትምህርት ናቸው። የመጽሐፍት ዝግጅቱም አድካሚ እና እልህ አስጨራሽ እንደ ነበር የአንድነቱ የትምህርት ክፍል ተጠሪ መምህር ምትኬነህ ገልጿል።
መጻሕፍቱ በሁሉም ሀገረ ስብከቶች ተሰራጭተው በ2014 የትምህርት ዘመን በቀረበው የማስተግበሪያ ረቂቅ መሠረት በሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል። መጽሐፍቱ በሌሎችም ሀገርኛ እና የውጭ ቋንቋ የሚተረጎሙ ሲሆን በዚህ ዓመት እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ለማዘጋጀት እንደታቀድ የመጽሐፍት አዘጋጅ ቡድኑ ገልጿል።