ከቅዱስ ሲኖዶስ ለ ፫ ቀናት የታወጀውን የነነዌ ፆም እና ምሕላ መጠናቀቅን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
በስመ አብ፤ ወወልድ፤ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
በትንቢተ ዮናስ በሰፊው እንደተጠቀሰው የነነዌ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ላይ ስለአመጹ እና ግብራቸውም በእግዚአብሔር ፊት አጸያፊ በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ዮናስን “ተነስተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ ክፋታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቷልና በእርስዋ ላይ ስበክ” በማለት አዘዘው፡፡ ትንቢተ ዮናስ ምዕ ፩ ቁጥር ፪ ዮናስም ድምፁን ከፍ አድርጎ ለነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰብክ “የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፡፡ ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነስቶ መጎናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ፡፡ አዋጅም አስነገረ፤ በነነዌ ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፤ እንዲህም አለ ሰዎችና እንስሶች፤ ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፣ አይሰማሩ፣ ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፣ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ጩኸት ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ፡፡ እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደሆነ ማን ያውቃል፡፡ እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውንም አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም” ትንቢተ ዮናስ ፫፡ ፭-፲