ፍኖተ-ጎርጎርዮስ
ሕዝበ ክርስቲያኑ የቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙን ትምህርቱን ሰምተው ግብሩን ዐይተው ሲወዱት ኖረዋል፡፡ ወላጆቹን በተለይ በእርግና ዘመን ላይ የነበረ አባቱን ጠይቆ ለመመለስ ወደ ወላጆቹ በሔደበት አጋጣሚ በሕዝቡ ግፊት ሥልጣነ ክህነት እንዲቀበል ተደረገ፡፡ እርሱ ግን ገዳማዊ ሕይወትን እጅግ ወድዶ ነበርና በብሕትውና ወደሚኖርበት ገዳም ሔዶ ተደበቀ፡፡ የቃልም የሕይወትም መምህር ነበር፤ በአንዲት በዓት ረጅም ጊዜ በጾም በጸሎት በመወሰን የሚታወቅ ገዳማዊ አባት፡፡ በትምህርትም ዓለማዊውን ትምህርት ከቂሣሪያ እስከ አቴና በመጓዝ በግሪክ ፍልስፍና የተራቀቀ፣ በመንፈሳዊው ትምህርትም ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በኋላ ነባቤ መለኮት (ታኦሎጎስ) እስከ መባል የደረሰ የነገረ መለኮት ሊቅ ነበር፡፡