አዝልፍኬ አንብቦ መጻሕፍት እስመ እማንቱ ይመርሃሁ ለልብከ ኀበ አንክሮተ እግዚአብሔር- መጻሕፍትን አዘውትረህ አንብብ፤ መጻሕፍት እግዚአብሔርን ወደማድነቅ ልብህን ይመሩታልና፡፡ (ማር ይስሐቅ)

ማር ይስሐቅ መጻሕፍትን ማንበብ በውስጣቸው ያለውን እውቀት ከማግኘት ባለፈ ወደ ተመስጦ፣ እግአብሔርንም ወደማድነቅ እንደሚያደርስ ይነግረናል፡፡ ለማወቅም ሆነ ያወቁት ለማስተማር ከጉባኤ ከዋሉ ምስጢር ካደላደሉ ሊቃውንት እግር ስር ቁጭ ብሎ ለሚማሩት ትምህርት በቂ ጊዜ ሰጥቶ መማር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ጉባኤ ቤት ገብቶ በቂ ጊዜም ሰጥቶ መማር ለሁሉ የሚቻል አይደለምና በማደራጃ መምሪያችን በየዓመቱ በክረምት ወቅት የሚሰጥ እንደዚህ ዓይቱ የአጭር ጊዜ ሥልጠና መነቃቃትን የሚፈጥር ለተጨማሪም ትምህርትና ንባብ የሚያነሳሳ ስለሆነ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “መከሩ ብዙ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡” ብሎ እንዳስተማረ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በሁሉም ሰንበት ት/ቤቶች ተግባራዊ እንዲሆን የተጋጀው ወጥ ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም አህጉረ ስብከት በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ መምህራን ያስፈልጉናል፡፡ ይህንን የመምህራን ፍላጎት በአንድ ጊዜ ማሟላት የሚቻል ስላልሆነ እንደዚህ ያሉ ሥርዓተ ትምህርቱን መሠረት ያደረጉ አጫጭር ስልጠናዎች በጣም አስፈላጊዎች ናቸው፡፡

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጋር በመሆንና አህጉረ ስብከትን በማስተባበር ሥርዓተ ትምህርቱ በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ በክረምት ወቅት ከየአህጉረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤት መምህራንን ወደማዕከል በማስመጣት በዚህ መልኩ ሥልጠና ሲሰጥ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ሲሆን በቀጣይም ከአህጉረ ስብከት ጋር በመነጋገርና የሥልጠና ማዕከላቱን በማብዛት የተሻለ ሥራ ለመሥራት ታስቧል፡፡ በዘንድሮው ለሁለት ሳምንታትና ለ200 ሰዓታት በታወቁ የቤተ ክርስቲያናችን መምህራን የተሰጠው ሥልጠና እጅግ የተሳካ ሠልጣኞችም ጥሩ እውቀትና ልምድ የቀሰሙበት እንደነበር እናምናለን፡፡

ስለሆነም ውድ ተመራቂዎች የተማራችሁት ትምህርት መጻሕፍትን በማንበብና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊቃውንትን በመጠየቅ አዳብራችሁ ሥራ ልትሠሩበት ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በትምህርት የወለደው የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስን “ወተዐቀብ እስከ እመጽእ በአንብቦ ወበምሂር ወበገሥጾ ወበጸልዮ – እስክመጣ ድረስ በማንበብና በመምከር በማስተማርም ተጠንቀቅ።” 1ጢሞ. 4፡13 ብሎ እንዳስተማረው እግዚአብሔር ቢፈቅድ ወደፊት ወደጉባኤ ቤትና ወደ መንፈሳዊ ኮሌጆች ገብታችሁ ከዚህ የበለጠ ትምህርት እስክታገኙ ድረስ ከጸሎት ጋር በማንበብና በመምከር በማስተማርም አብዝታችሁ ልትተጉ ይገባል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ  አፈ ወርቅ  “ቅዱሳት መጻሕፍትን አለማወቅ የስህተት ሁሉ ምንጭ ነው፡፡” ብሎ እንዳሰተማረ መጻሕፍትን ባለማወቅ የሚመጣን ስሕተት ቅዱሳት መጻሕፍት አብዝቶ በማንበብና በመመርመር መከላከል ይቻላልና ለማንበብ እንድትተጉ ማደራጃ መምሪያችን አጥብቆ ያሳስባል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቈላስይስ መልእክቱ “ወይኩን ነገርክሙ በጸጋ ወቅሱመ በጼው – ነገራችሁ በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ይሁን በማለት መናፍቃን አብዝተው ቢጠቅሱ እናንተም አብዝታችሁ ጠቅሳችሁ በለጋስነት መልሱላቸው፡፡ ንግግራችሁም በፍቅርና በትሕትና የጣፈጠ ይሁን ብሎ እንዳስተማረ አሁን ያለንበት ዘመን ሐሳውያን የበዙበት መጽሐፍ ቅዱስን እየጠቀሱ የዋሃን ምእመናንን የሚያደናግሩ ሰዎች እንደ አሸን የፈሉበት ዘመን ስለሆነ በየምትሄዱበት አካባቢ ወጣቶችና ሕጻናትን ከመናፍቃን ቅሰጣ ጠብቆ በቃለ እግዚአብሔር ማሳደግ ይቻል ዘንድ የተማራችሁትን ትምህርት በሥራ ላይ በማዋል ዛሬ የተቀበላችሁትን አደራ በአግባቡ ልትወጡ ይገባል፡፡

በእነዚህ ሁለት ሳምንታት በነበራችሁ ቆይታ በተማራችሁት ትምህርት ሳትወሰኑ ሁል ጊዜ ለማንበብና ለመጠየቅ የተዘጋጃችሁ በመሆን ክህደትንና ኑፋቄን የምትቃወሙ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲን ዶግማዋን ቀኖናዋንና ሥርዓቷን ጠብቃችሁ የምታስጠብቁ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃዎች ልትሆኑ ይገባችኋል፡፡

ሰዎችን ለመለወጥ በብዙ የትምህርት ተቋማት አልፎ ብዙ ዕውቀት መሰብሰብ ብቻው በቂ አይደለምና ከማስተማር ጋር አርአያ የሚሆን ሕይወት ሊኖረን ይገባል፡፡ እንዲህ ሲሆን በአገልግሎታችን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ብዙ ኢማንያንን ወደ እምነት እንዲመጡ እናደርጋለን በእምነት ያሉ ወጣቶችና ሕጻናትም በዕውቀት እናሳድጋለን፡፡

በመጨረሻም ውድ ተመራቂዎች ለዚች ቀን እንኳን አደረሳችሁ እያልኩ ያለንበት ወቅት ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እጅግ የፈተና ወቅት እንደሆነ ተድተን ወጣቶችና ሕጻናት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ አገልግሎታችንም ለዘመኑ እንደሚገባ በጥበብና በእውቀት ልናደርግ ይገባል በማለትና አገልግሎታችሁ የተሳካ እንዲሆን በመመኘት መልእክቴን በዚሁ አጠቃልላለሁ፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወ/ትንሣኤ

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ

ሦስተኛው የአህጉረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና የምርቃት መርሐ ግብር ተከናወነ።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 21 / 11 / 2017 ዓ.ም

ሦስተኛው የአህጉረ ስብከቶች የሰ/ት/ቤቶች መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና የምርቃት መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ተከናውኗል። በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የሸገር ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የምስካየ ኅዙናን ገዳም የበላይ ጠባቂ እና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ፣ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋኒዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ በርናባስ የዋግህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ ፣ ዲ.ን ስንታየሁ ምስጋናው የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ተ/ም/ሰብሳቢ ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች ፣ መምህራነ ወንጌል ፣ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የሥራ አመራር አባላት ተገኝተዋል።

ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ባስተላለፉት መልእክት “ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ለ3 ዓመት ከ3 ወር ሐዋርያትን ከተለያየ ግብርና ክፍል መርጦ ካስተማራቸው በኋላ ሂዱና አስተምሩ በሀገር ሁሉ ቋንቋ አስተምሩ ብሎ እንዳዘዛቸውና አልጫ የሆነውን ዓለም በማስተማር እንዳጣፈጡ ሁሉ እናንተም በተማራችሁት ትምህርት ሄዳችሁ እንድታስተምሩ ፣ እንድታሰለጥኑ ፣ ፍሬ እንድታፈሩ” በማለት አባታዊ ምክርና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል።

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም እንዲሁ “ከእግዚአብሔር የተላከ ከእግዚአብሔር የተመረጠ የአምላኩ የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል” በሚል ኃይለ ቃል ተነስተው እርሱን ለማገልገል የሚጠራ ማንኛውም አገልጋይ የእግዚአብሔርን ዓላማ ፣ ሐሳብ የእርሱን ዕቅድና እርሱ ለሰው ያለውን አምላካዊ ጥበብ ፣ መግቦት በፍጥረቱም ላይ እንዴት እንደሚሠራና ጥልቅ የሆነውን ፍቅሩን ሁሉ ይናገራል። ብለው ወደ መጣችሁበት ስንቃችሁን ያዛችሁ በመሄድ በሚገባ አገልግሎታችሁን እንድትፈጽሙ ይሁን በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈው ቋጭተዋል።

በዕለቱ ሌላኛውን አባታዊ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ በርናባስ የዋግህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም እንዲሁ “በአባቶች ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ” የሚለውን የልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ቃል መነሻ አድርገው እናንተም በአባቶቻችሁ ፈንታ የተተካችሁ እንደመሆናችሁ አባቶቻችሁን መስላችሁ ቤተ ክርስቲያንን ልታገለግሉ ይገባል በማለት ለተመራቂ መምህራን የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ “መጻሕፍት እግዚአብሔርን ወደ ማድነቅ ልብህን ይመሩታልና” በሚል ኃይለ ቃል በመነሣት የማደራጃ መምሪያውን መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ተ/ም/ሰብሳቢ ዲያቆን ስንታየሁ ምስጋናው በሥልጠናው ጊዜ አጠቃላይ የተከወኑ ተግባራትና በቀጣይ እንዲሠሩ የሚፈለጉ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል። ሠልጣኝ መምህራኑም የነበራቸውን የ15 ቀን ቆይታ የተመለከተ ዘገባ እና አቋማቸውንም እንዲሁ በተወካያቸው በኩል አቅርበው ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እጅ የዕውቅና የምስክር ወረቀታቸውን ተቀብለው የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።

ሥልጠናው ከሐምሌ 7 እስከ ሐምሌ 20 ቀን ድረስ በተከታታይ ለ15 ቀናት የተሰጠ ሲሆን በሥልጠናውም ላይ ከ30 አህጉረ ስብከት የተወጣጡ 209 መምህራን ተከታትለው አጠናቅቀዋል። ከነዚህም መካከል 106 ቀሳውስትና ዲያቆናት እንዲሁም 8 ሴቶች ይገኙበታል።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት)

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የክረምት የመምህራን አሰልጣኞች ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ መምህራንን ጎበኙ።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 18/11/2017ዓ.ም

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አዘጋጅነት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ እየተሰጠ የሚገኘው የክረምት የመምህራን የአሰልጣኞች ሥልጠና ላይ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በመገኘት አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ የተናገረውን “ለወንድሞችህ ይህንን አስተምራቸው” የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ አድርገው አባታዊ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ልጄ ሆይ ጆሮህን ለመምህራን ስጥ እንደተባለ ከመምህራን እግር ስር ቁጭ ብለው የሚማሩት ቃለ እግዚአብሔር ለሕይወታች ስንቅ ነውና ቅዱስ ጢሞቴዎስን አብነት አድርጎ በሕይወት መተርጎም ይገባል የተማርነውንም ለወንድሞች ማስረዳት መንገር ይገባል ብለዋል።

በመጨረሻም ሰልጣኞች በተከታታይ በቀንም በማታም እየተሰጣቸው ያለውን ሥልጠና በሚገባ ተከታትለው በየሀገረ ስብከታቸው ሲመለሱ በትኩረት ሊሰሩ ለሌሎችም ሊያጋሩ እንደሚገባ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክረምት የመምህራን አሰልጣኞች ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ መምህራንን ጎበኙ።

የሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 14/11/2017ዓ.ም

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አዘጋጅነት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ እየተሰጠ 7ኛ ቀኑን በያዘው የክረምት የመምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በመገኘት አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው ለእናንተ የመንግስተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል” ማቴ 13፥11 በሚል ርዕስ ቃለ እግዚአብሔርና አባታዊ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የመንግስተ ሰማያት ምሥጢር ለማወቅ ጾታና ማዕረግ ሳይለይ ለሁሉም የሰው ዘር የተሰጠ ጸጋ መሆኑንና ይህን ምስጢር አውቆ ማሳወቅ ከመምህራን የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።

አያይዘውም ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት አሳስበው እንደ ሀገረ ስብከታቸው ሰሜን ወሎ ለሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰልጣኞችን በመላክና በመማርያ መጻሕፍት ግዥ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመጨረሻም ሰልጣኞች እየተሰጣቸው ያለውን ሥልጠና በሚገባ ተከታትለው በየሀገረ ስብከታቸው ሲመለሱ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)

የ2017 ዓ.ም የክረምት የአሰልጣኞች መምህራን ሥልጠና ተጀመረ

ሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 07 2017 ዓ.ም

የ2017 ዓ.ም የክረምት የአሰልጣኝ መምህራን ሥልጠና በዛሬው ዕለት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ተጀመረ። በዛሬው የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይም አረጋዊው አባት ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ የተገኙ ሲሆን ብፁዕነታቸው “እነሆ ጊዜው ደረሰ” በሚል መነሻ ቃለ ወንጌል ፣ አባታዊ ምክርና ቃለ ምዕዳን ለሰልጣኝ መምህራኑ አስተላልፈዋል። “እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤” የሚለውን የልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትን ቃል መነሻ በማድረግ የማደራጃ መምሪያው ሐላፊ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። በዛሬው የመክፈቻው መርሐ ግብር ላይ ሰልጣኞች በሚኖራቸው ቆይታ ሊያውቋቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በሚመለከት ገለጻ ተሰጥቶ የመክፈቻ መርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል። ሥልጠናው በዛሬው ዕለት በምሽት የሰንበት ት/ቤቶች መዋቅራዊ አደረጃጀትን በሚመለከት የሚቀጥል ሲሆን እስከ ሐምሌ 20 ድረስ በተከታታይ ለ15 ቀናት የሚቆይ ሲሆን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነትን ፣ የተለያዩ ክህሎትን የሚያዳብሩ እንዲሁም በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ትኩረት ያደረጉ ከ15 በላይ ሥልጠናዎችን የሚያገኙ ይሆናል። ሥልጠናውን ከ30 ሀገረ ስብከት የተወጣጡ 213 መምህራን የሚወስዱ ይሆናል።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት)

ከየሀገረ ስብከቱ ለተውጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራን የክረምት የአሠልጣኞች ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አስታወቀ።

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት በዓመቱ መጨረሻ ከየሀገረ ስብከቱ ለተውጣጡ መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና በማዘጋጀት አሠልጥኖ ወደየ ሀገረ ስብከታቸው ለአገልግሎት የማሰማራት ሥራ በየዓመቱ ሲያከናውን ቆይቷል። በዘንድሮም ዓመት ከ23 ሀገረ ስብከት በላይ ለተውጣጡና መመዘኛውን ለሚያሟሉ ከ200 በላይ ሠልጣኞች ሥልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አንድነቱ አስታውቋል።

ሥልጠናው የሚሰጠው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ ሲሆን ሠልጣኞች በቆይታቸው በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ዕውቀትን የሚያጎለብቱ፣ የግንዛቤ ለውጥ የሚያመጡ፣ ክህሎታቸውንም የሚያዳብሩ ሥልጠናዎች እንደሚሰጣቸውና ወደ ሀገረ ስብከታቸው ሲመለሱ በሥርዓተ ትምህርት ትግበራው ሰፊ ሥራ እንደሚሠሩ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አስታውቋል።