ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ምልዓተ ጉባኤ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ደሙ ወረዳ ሀሮ በዓለወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጸመውን ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ የሃይማኖት፣ የቀኖናና የአስተዳደር ጥሰት አስመልክቶ በሰፊው ተወያይቶ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት ልዩ ልዩ ሕግጋት ውጭ ጳጳስ ሾመናል ባሉ አካላት እና ተሹመናል በሚሉት አካላት ላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግጋት በሚፈቅድለት መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻር አውግዞ የለያቸው ሲሆን፣ በዕለቱ ይኸው ውግዘት በመላው ዓለም ለሚገኙ የዕምነቱ ተከታዮች ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምዕመናን ውግዘቱን እንዲያውቁት መንግሥትም በዚህ ጉዳይ የሚፈጠር ችግር እንዳይኖር ሰላም እንዲያስከብር ዓለም በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ መረጃ ኖሮት ቤተ ክርስቲያን ለወሰነችውም ውሳኔ ግንዛቤ እንዲወስድ በመግለጫ ማሳወቃችን ይታወሳል፡፡

Read more

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ እንዲሁም በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር 3 አስቸኳይና ድንገተኛ ጉዳይ ሲያጋጥም ምልዓተ ጉባኤ እንደሚያደርግ በተደነገገው መሠረት ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ በተፈጠረው ወቅታዊ የሃይማኖት፣ የቀኖና እና የአስተዳደራዊ ጥሰቶችን አስመልክቶ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

Read more

ኢ-ቀኖናዊ የሆነውን “ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት” አስመልክቶ ከሀገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት የተሰጠ መግለጫ

ቀኖናዊ ሥርዓቷን ጠብቃና አስጠብቃ አያሌ ዘመናትን የተሻገረቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየደረሰባት ካለው ፈተና፣ መሰናክል፣  መከራ እና ውጣ ውረድ  በእግዚአብሔር ቸርነት ተጠብቃ አሁን ካለንበት ዘመን ደርሳለች ::  ዛሬ ግን ከፈተናዎች ሁሉ የከፋው ፈተና የበጐች እረኛ አድርጋ ሾማ እስከ ማዕረገ ጵጵስና ባከበረቻቸው ልጆቿ  ተፈጽሞባታል።  መንጋውን እንዲጠብቁ የመረጠቻቸው ልጆቿ ሊያፈርሷትና ሊከፍሏት  መነሳታቸው  በእጅጉ አሳዝኖናል ::ይኸንን ኢ -ቀኖናዊ  ተግባርም በጽኑ እንቃወማለን። በመሆኑም ፦ Read more

በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤቶች የማጠቃለያ ፈተና  ተሰጠ

በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አስተባባሪነት አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ባደረጉ ሰ/ት/ቤቶች ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ማጠቃለያ ፈተና በዛሬው ዕለት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

በሀገረ ስብከት ደረጃ 2014 ዓ.ም የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ማጠቃለያ በደመቀ ሁኔታ በደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ጊዜያዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መሰጠቱንም ነው የተገለጸው።

በፈተና ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ንቡረ ዕድ ቆሞስ አባ መዘምር አሰግደው ፣የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤት ማደራጃ ክፍል ሓላፊ መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ አብርሃም ሙሉጌታ እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ ትምህርት ክፍል ሓላፊ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ ዮርዳኖስ አቢ በተገኙበት በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን ከሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ይፋዊ ፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በዓለ ጰራቅሊጦስ

ጰራቅሊጦስ የሚለው ቃል ከሦስቱ አካላት አንዱ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መጠሪያ ሲኾን ፣ ትርጕሙም በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ናዛዚ (የሚናዝዝ)፣ መጽንዒ (የሚያጸና)፣ መስተፍሥሒ (የሚያስደስት) ማለት ነው፡፡ በዓለ ጰራቅሊጦስ በሌላ ቃል በዓለ ጰንጠቆስጤ በመባልም ይታወቃል፡፡ ይኸውም በግሪክ ቋንቋ በዓለ ኀምሳ፣ የፋሲካ ኀምሳኛ ዕለት፣ በዓለ ሠዊት (የእሸት፣ የመከር በዓል) ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፱፻፮ እና ፱፻፯/፡፡ Read more

የብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል አስመልክተው ለመላው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ። Read more

የቅዱስ ፓትርያርኩ የዐቢይ ፆም መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ ፣
በጾምና በጸሎት ወደ እርሱ የሚቀርቡትን በዓይነ ምሕረት የሚቀበል እግዚአብሔር አምላካችን፣ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ዓራት ዓመተ ምሕረት የፆመ ኢየሱስ ሱባዔ በሰላም አደረሳችሁ!!
“ትግሁ ወጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት፤ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ”
(ማቴ ፳፮.፵፩) ።
ምድራውያን ሰዎች የምንኖርባት ይህች ዓለመ መሬት ከሰው ውድቀት በኋላ በልዩ ልዩ ፈተና የምትናጥ እንደ ሆነች ሁላችንም የምናውቀው ነው፤ እሷን ከፈተና ነፃ ማድረግም ሆነ መከላከል የሚችል ከፍጡራን ወገን አልተገኘም፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ወበዓለምሰ ሀለወክሙ ትርከቡ ሕማመ፤ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ “ማለቱ ይህንን የሚያመለክት ነው፤ ከዚህ አኳያ ሲታይ ዓለም ምን ጊዜም ከፈተና ውጭ አይደለችም ማለት ነው፤ ይህ እውነት እንደ ሆነ እኛም በዓይናችን የምናየው፣ በአእምሮአችን የምንገነዘበው ሓቅ ነው፤
ግብረ ኃጢአትና ክፉ ሕሊና እስካሉ ድረስ ፈተና ባይቀርም፣ መለኮታዊ መከላከያ የሌለው ግን አይደለም፤ መከላከያውም ኃይለ እግዚአብሔር ነው፤ የእግዚአብሔር ኃይልና ረድኤት ለማግኘት ደግሞ፣ ሰው ቆም ብሎ ማሰብና በንሥሐ ወደ እግዚአብሔር፤ መመለስ ያስፈልገዋል፤ ከዚህ አንጻር የንሥሐ፣ የጾምና የጸሎት አስፈላጊነት ፈተናን ለመከላከል እንደሆነ እንገነዘባለን፤ ይህም በመሆኑ ጌታችን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ በማለት አስተማረን።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

በጌታችን አስተምህሮ መሠረት ፈተናው ከማየሉ በፊት ተግተን ካልጸለይን ፈተና ሁሌም ይጸናብናል፤ ይሁን እንጂ ጌታችን በሌላ በኩል “ለምኑ ይሰጣችኋል” ብሎ ቃል የገባልን በመሆኑ በፈተና ውስጥ ሆነንም በንሥሐ፣ በጾምና በጸሎት እሱን በመለመን ፈተናን መከላከል እንችላለን ፤ ጌታችን እኛን ለማስተማር ዓርባ ቀንና ዓርባ ሌሊት በጾመ ጊዜ በፈተና አምጪው ፍጡር ላይ የተቀዳጀው ድል የምናውቀው ነው፤ አሁን የምንጀምረው የጾመ ኢየሱስ ሱባዔም ፈተናን እንዲያስቀርልን፣ በምትኩም ምሕረቱን እንዲያወርድልን ለመለመን እንደሆነ ሕዝበ ክርስቲያኑ በውል ተገንዝቦ በተመሥጦ ወደፈጣሪው መማፀን ይኖርበታል።
እንግዲህ መዋዕለ ጾም የንሥሐ ጊዜ ነው ሲባል፣ ንሥሐ የምንገባው እንዴት ነው የሚለውንም ማስተዋሉ ተገቢ ነው፤ ልባችን እንደ ሚመሰክርብን ያለንበት ጊዜ፣ጥል ያየለበት፣ ጭካኔ ሥር የሰደደበት እንደሆነ አይካድም፤ በዚህም ምክንያት የብዙ ልጆቻችንና ወገኖቻችን ሕይወት ተቀጥፎአል ፣ኑሮም ተመሰቃቅሎአል፤ ጥላቻ ቦታ ካገኘ ውጤቱ ከዚህ ሌላ ሊሆን አይችልምና ይህንን ሁሉ አስከትሎብናል፤ በመሆኑም በዚህ ወርኃ ጾም ንሥሐ መግባት አለብን ስንል የከረምንበቱን የጥላቻ ሕሊና ከሥር መሠረቱ ነቅለን በመጣል፤ ፍቅርንና ሰላምን በመሻት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አለብን ማለታችን ነው ፤

ጾምን በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ መሥዋዕት የሚያደርገው፣ ኃይል ሰጪ ከሆኑት መባልዕት መከልከል ብቻ ሳይሆን ከጠብና ጥላቻ መራቅና መከልከል እንደ ሆነ በሚገባ ማስተዋል ይኖርብናል፤ በመዋዕለ ጾም ወቅት ኃይል ሰጪ ከሆኑ መባልዕት መከልከል ያስፈለገውም ጠብና ጥላቻን ለመቀነስ፣ብሎም ለማስወገድ ምቹ መደላድልን ለመፍጠር እንጂ ምግቦቹ በራሳቸው ኃጢአት ሆነው አይደለም፤ በመሆኑም ከፈተና ለማምለጥ የእግዚአብሔር ኃይል ያስፈልገናል የእግዚአብሔርን ኃይል ለማግኘት ደግሞ በኃይለ ሥጋ ሳይሆን በኃይለ መንፈስ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ያስፈልጋል፤

ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ደግሞ ከባልንጀራ ጋር በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ፍጹም ፍቅር መመሥረት ያስፈልጋል፣ ፍቅር ስለተባለውም ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ “በአጠገብህ ያለውን ወንድምህን ሳትወድ እግዚአብሔርን እወዳለሁ ማለት ውሸት ነው” ብሎ እንዳስተማረን ወንድማችንን ሳንወድ ወደ እግዚአብሔር ብንቀርብ ተቀባይነት እንደ ማይኖረን ማወቅ አለብን፤ በመሆኑም ለእግዚአብሔር ክብርና ለዘላቂ ሰላም ሲባል ወደ እውነተኛው ፍቅር መሸጋገር አለብን፤ ያን ጊዜ እግዚአብሔር ፍቅራችንን ድልድይ አድርጎ ፈተናውን ያርቅልናል፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት !
ባጋጠመን ሀገራዊ ፈተና መነሻነት ሕዝባችን ሲፈተን ቤተ ክርስቲያናችንም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከመሆን እንዳላመለጠች ሁላችንም የምንገነዘበው ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ለሕዝብ የተፈጠረችና በሕዝብ መካከል ያለች በመሆኗ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው ሁሉ በእርስዋ ላይም በቀጥታ ይደርሳል፤ ከዚህ አኳያ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምም በዚህ መዋዕለ ጾም ፍቅርን በተላበሰ ንሥሐ እግዚአብሔርን እንድንጠይቅ በዚህ አጋጣሚ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤
በመጨረሻም፦
በመዋዕለ ጾሙ ስለ ሀገርና ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ፣ስለ ሕዝባችን ዘላቂ ፍቅርና ስምምነት አጥብቀን እንድንጸልይ፣እንደዚሁም በግጭቱና በድርቁ ለተጐዱ ወገኖቻችን ካለን በማካፈል የችግሮቻቸው ተካፋይ እንድንሆን፣ ከዚህም ጋር ለሀገራዊ ሰላምና ፍቅር መሳካት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ መዋዕለ ጾሙን እንድናሳልፍ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን ።

እግዚአብሔር ወርኃ ሙን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በደህና ያድርሰን ፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን !

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
የካቲት ፳፩ ቀን ፳፻፲፬ ዓመተ ምሕረት ፤
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ፤

በላዔ ሰብ እና እሥራኤል ዘሥጋ

በታሪክ እንደሚታወቀው እሥራኤል ዘሥጋ በግብጽ ባርነት ለ430 ዓመት ተገዝተው ነበር፡፡ እግዚአብሔርም የሲዖል ምሳሌ ከምትሆን ግብጽ በዘጠኝ ታላላቅ ተዓምራት በአሥረኛ ሞተ በኵር በአሥራ አንደኛ ስጥመተ ባሕር ግብጽን በመቅሰፍ ነጻ አውጥቷቸዋል፡፡

እስራኤል ዘሥጋ ግን ይህንን ታላቅ ውለታ በማሰብ ፈንታ አምላካቸው እግዚብሔርን አሳዘኑ ቀልጦ ለተሠራ ጣዖት ሰገዱ ሰዉለትም፡፡ ‹‹እስራኤል ሆይ ስማ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አሉ፡፡›› ዘጸ 32፡1-14 መዝ 105፡23 የእግዚአብሔርም ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፡፡ ያጠፋቸውም ዘንድ ከተመረጠው መስፍን ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጋር መከረ፡፡ ‹‹ይህንን ህዝብ አየሁት እነሆ አንገተ ደንዳና ነው፡፡ አሁንም ቁጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፡፡ አንተ ግን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለው፡፡›› አለው፡፡ ዘጸ 32፡9-10

ሙሴም ሕዝቡን እንዳያጠፋቸውና ከቁጣው ይመለስ ዘንድ ስለ ሕዝቡ ያማልድ ጀመር፡፡ በተለይም እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ከአብርሃም ከይስሐቅ እና ከያዕቆብ ጋር የገባውን ቃልኪዳን ያስብ ዘንድ ለመነ፡፡ ‹‹ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለው፡፡ ይህችንም የተናገርኳትን ምድር ለዘራችሁ ሁሉ እሰጣለው፡፡ ለዘላለምም ይወርሷታል ብለህ በራስህ የማልክላቸውን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ፡፡›› አለው፡፡ ዘጸ 32፡13

እግዚአብሔርም የቅዱሳኑ ስም ተጠርቶ ሲሰማ የገባላቸውን ቃል ኪዳን አሰበ፡፡ በሕዝቡ ላይ ሊያደርገው ስለነበረው መቅሰፍት ፈጽሞ ራራላቸው፡፡ ይቅርም አላቸው፡፡ ‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃልኪዳኔን አደረግሁ፡፡›› ያለ አምላክ ከተመረጡት ቅዱሳን ከአብርሃም ከይስሐቅ ከያዕቆብና ከሌሎችም ቅዱሳን ጋር ቃልኪዳኑን እንዳደረገ እንዲሁ ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከእናታችን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያምም ጋር እንዲሁ ቃልኪዳኑን በዛሬው ዕለት የካቲት 16 ቀን አድርጓል፡፡ እመቤታችንም ‹‹መታሰቢያዬን የሚያደርገውን፣ በስሜ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጸውን ፣ የተራቆተ የሚያለብሰውን፣ በሽተኛ የሚጎበኘውን፣ የተራበ የሚያበላውን፣ የተጠማ የሚያጠጣውን፣ ያዘነን የሚያረጋጋውን የተበሳጨ የሚያስደስተውን፣ መመስገኛየን የጻፈና ያጻፈ ፣ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በስሜ የሰየመውን፣ በምመሰገንበት ቀን ዝማሬ ያቀረበውን ዓይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን የሰው ኅሊና ተመራምሮ ያልደረሰበትን መልካም ዋጋ ትሰጥልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡›› ብትለው፡ ጌታም ‹‹መሃልኩ ለኪ በርዕስየ በከመ ኢይሔሱ ኪዳንየ›› ያልሽውን ሁሉ ላደርግልሽ ቃል ኪዳኔንም ልጠብቅልሽ በራሴ ማልሁልሽ በማለት የምህረት ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡

የአብርሃም የይስሐቅ እና የያዕቆብ ቃልኪዳን የእግዚአብሔርን ሕልውና ለካዱ ቀልጦ ለተሠራ ጣዖት ለሠገዱ ለእስራኤል ዘሥጋ መትረፉን መጽሐፍ ቅዱስ ከነገረን በተዓምረ ማርያም ላይ ደግሞ ስምዖን በግብር ስሙ በላዔ ሰብ 70 ሰዎችን በልቶ በቃል ኪዳኗ ተጠቅሞ መዳኑን ይነግረናል፡፡ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ቃልኪዳን የማይሆነውን እንዲሆን የሚሆነን ደግሞ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ ያጠረውን ያስረዝማል፡፡ የረዘመውን ያሳጥራል፡፡ ኃጥኡን ያጸድቃል፡፡

ዛሬም እስራኤል ዘነፍስ የምንሆን እኛ ክርስቲያኖች በእመቤታችን ቃልኪዳን በመታመን ሀገራችን ላይ እና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተቃጣውንና እየደረሰ ያለውን መከራ እርሱ በቸርነቱ ያርቅልን ዘንድ ስለ እናትህ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብለህ ማረን ይቅር በለን እያልን ተግተን ልንለምነው ይገባል፡፡
የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ ስም ሲነሳ በእስራኤል ዘሥጋ ላይ ያልጨከነ ለድካማቸውም የራራ አምላካችን የእናቱን ስም ጠርተን በቃልኪዳኗ ብናምለው እንደምን አይራራልንም?

50 ሺህ መጻሕፍት ለ50 ሰንበት ት/ቤቶች

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ ክፍል በጦርነት ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው በ10 ወረዳ ውስጥ ለሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች 50 ሺህ መጻሕፍት ለማበርከት ድጋፍ ማሰባሰብ መጀመሩን አስታውቋል።

ድጋፉ የሚደረገው በወቅታዊ ጦርነት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው በ10 ወረዳ ቤተ ክህነቶች ሥር ለሚገኙ ሃምሳ ሰንበት ትምህርት ቤቶች 50 ቤተመጻሕፍት ለመክፈት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 50 ሺህ መጻሕፍት ድጋፍ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ተመላክቷል።

ሁሉንም ምዕመናንን ተሳታፊ ያደረገ የልገሳ መርሐ-ግብር ከየካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለ1 ወር የሚቆይ መጻሕፍት የማሰባሰብ ተግባር መጀመሩን የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ ክፍል ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር ዲያቆን ስንታዬሁ ማሩ አስታውቀዋል።

የመጻሕፍት ልገሳ ማሰባሰብ መርሐ-ግብሩ በተመረጡ አድባራትና የሚካሄድ ሲሆን የመጻሕፍት ልገሳ ተግብሩ ከአንድ ወር በኋላ ሲጠናቀቅ ከየሰንበት ትምህርት ቤቱ በተውጣጡ ተወካዮች አማካኝነት በተመሳሳይ ቀን በ10ሩም ወረዳዎች ርዕሰ ከተሞች ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የመጻሕፍት ስጦታው የእርስ በእርስ የመደጋገፍ ግንኙነታችንን ለማጠንከርና በጦርነቱ ውስጥ የነበሩ ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችንን በተሻለ መልኩ ለማጠናከር የስርጭት ተግባራት ይከናወናል ሲሉ ዲያቆን ስንታየሁ ተናግረዋል።

እንኳን ለጾመ ነነዌ በሰላም አደረሳችሁ!

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን በመዋዕለ ስብከቱ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ከጠየቁት ጥያቄ በመነሳት ስለ ሰብዓ ነነዌ እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር። “በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና፦ መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን አሉ። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።” ማቴ 12፡38-41

ቀድሞ አምላካቸውን ያሳዘኑት ሰብዓ ነነዌ (የነነዌ ሰዎች) ስለ ኃጢአታቸውና ስለ በደላቸው ምሕረትን ጠይቀው ንስሐ ገብተው ሦስት ቀን ጾመው ጸልየው በአምላካቸው እስኪመሰከርላቸውና በትውልዱም ላይ ለመፍረድ ሥልጣኑን እስኪሰጣቸው ድረስ ይቅርታውን ምሕረቱን ቸርነቱን እንደገለጠላቸው እኛም ጾሙን ጾመን ንስሐ ገብተን አምላካችን ይቅር ይለን ዘንድ ተግተን እንለምነው።