እንኳን ለደብረ ታቦር በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!

ደብር ማለት ተራራ ሲሆን ታቦር ደግሞ የተራራው ስም ነው፡፡ ደብረ ታቦር ከገሊላ ባሕር በስተምዕራብ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን ገልጦበታል፡፡ ይህም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነሐሴ 13 ቀን ዘጠኙን ሐዋርያት ከእግረ ደብር/ከተራራው ግርጌ/ ትቶ ሦስቱን ሐዋርያት (ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን) አስከትሎ ወደ ተራራው ወጣ። በዚያም ለሦስቱ አርዓያው ተለውጦ፣ ፊቱ እንደ ፀሐይ አብርቶ፣ ልብሱ እንደ በረዶ ነጽቶ፣ ሙሴና ኤልያስ በቀኝና በግራው ቁመው ታዩአቸው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስ ‹‹እመሰ ትፈቅድ ንንበር ዝየ ወንግበር ሠልስተ ማኅደረ አሐደ ለከ፣ አሐደ ለሙሴ፣ ወአሐደ ለኤልያስ›› ትርጓሜውም ‹‹በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ፣ አንዱን ለሙሴ፣ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ›› እያለ ሲናገር ወዲያው ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸውና ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድዬ ዘአፈቅር ወሎቱ ስምዕዎ›› ትርጓሜውም ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚል ቃል ሰሙ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም መቆም ተሳናቸው፤ ሙሴ ‹‹ትኄይሰኒ መቃብርየ›› መቃብሬ ትሻለኛለች ብሏል፤ ኤልያስም በሠረገላው ወደየመጡበት ተመልሰዋል፡፡ ሦስቱ ሐዋርያትም ደንግጠው ወድቀው ነበርና ጌታ ዳስሶ በአስነሳቸው ጊዜ ከእርሱ በቀር ሌላ ሰውን አላዩም፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዝዟቸው ከተራራው ወርደዋል፤ (ማቴ 17፥1-9)።
ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ሲሆን ነብያት እና ሐዋርያት በተራራው ላይ መገኘታቸው ቤተ ክርስቲያን የነብያትንም የሐዋርያትንም ትምህርት ይዛ የመገኘቷ፡፡ ሙሴ ከሞት ተነስቶ በተራራው ላይ ተገኘ ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን መጣ፡፡ ይህም በሰማይ ያሉትም ይሁኑ በምድር ያሉት በአንድነት የሚያመሰግኑባት ቦታ እንደሆነች ሲያስተምረን ነው፡፡

ምሥጢረ መንግሥቱን ለምን በታቦር ተራራ ገለጸው?
መድኃኔዓለም ሌሎች ተራሮች እያሉ ክብሩን ለመግለጥ ስለምን ደብረ ታቦርን መረጠ ቢሉ ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡

1/ ትንቢቱን ለመፈጸም
“ታቦርና አርሞንኤም በስምህ አምነው በተደረገላቸው ነገር ደስ ይላቸዋል፣ ስምህን ያመሰግናሉ፣ ለስምህም ምስጋና ያቀርባሉ” እንዲል /መዝ. 88፡12/፡፡

2./ ምሳሌውን ለመፈጸም
ይህ ተራራ ባርቅ ሲሳራን ድል አድርጎበታል /መሳ.4፡6/፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፡፡ “የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደገና ክፉ ሥራ ሠሩ፡፡ እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቡስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ በአሕዛብ አሪሶት የተመረጠው ሲሣራ ነበር፡፡… ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና የእስራኤልንም ልጆች ሃያ ዓመት ያስጨንቃቸው ነበር” /መሳ 4.1-3/፡፡ ሁሌም ቢሆን የሰውን በደል ዐይቶ እንደወጣችሁ ግቡት፣ እንደገባችኋት ውጧት የማይልና “ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” የተባለለት እግዚአብሔር ከዚህ ቀንበር የሚላቀቁበትን መላ ራሱ አመለከታቸው /1ቆሮ. 10-13/፡፡ እስራኤላውያን ወደ ፈጣሪያቸው በጮኹ ጊዜ የለፊዶት ሚስት የሆነችውንና እስራኤልን በነቢይነትና ዳኝነት ታገለግል የነበረችው ነቢይቱን ዲቦራን ተጠቅሞ የማሸነፊያ መላውን አመለከታቸው፡፡ ነቢይቱ ዲቦራ ትንቢት ከመናገር አልፋ የእስራኤልን ንጉሥ ባርቅ ከእኔ ጋር ወደ ጦርነቱ ውጪ ብሎ ባስጨነቃት ጊዜ በጦር አዝማችነትም ተሳተፈች፡፡ እግዚአብሔር በነቢይቱ በዲቦራ በኩል ለእስራኤል ንጉሥ “ሔደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጡ” ብሎ አዞት ነበርና ንጉሡ ዐሥር ሺሕ ብረት ለበስ ያልሆነ እግረኛ ሠራዊት ይዞ ደብረ ታቦርን ተማምኖ በተራራው ላይ መሸገ፤ ጦርነቱም ሳይጀመር አለቀ፡፡ ምክንያቱም “እግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፡፡ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ” /መሳ. 4.15/፡፡ እስራኤል በእግዚአብሔር አጋዥነት በታቦር ተራራ ላይ የሃያ ዓመት የግፍና የሰቀቀን አገዛዝ ቀንበራቸውን ከትከሻቸው አሽቀንጥረው በምትኩ የድል ካባን ደረቡ፡፡ “በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩ” ተብሎም ጀግንነታቸው ተጻፈላቸው፡፡ የታቦር ተራራ ያኔ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ባለውለታቸው ነበር /ዕብ. 11.32-34/፡፡

ጌታም በልበ ሐዋርያት ያለ ሰይጣንን ድል ያደርጎበታልና ማለትም በልባቸው ጥርጥርን እና ፍቅረ ሢመትን (የሥልጣን ፍቅር) ያሳደረ ዲያብሎስን ድል ነስቶላቸዋል ፡፡ ከዚህም በመነሣት ነው “በዓለ ደብረታቦር የደቀመዛሙርት ተማሪዎች በዓል ነው” የሚባለው ፡፡

ኤልያስና ሙሴን ለምን አመጣቸው?
1/. በአንድ ወቅት ሙሴ እግዚአብሔርን ፡- “በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴ እውነት ከሆነስ ፊት ለፊት ተገልጸህልኝ ልይህና በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴን ልወቀው” ሲል ጠይቆት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም “ጀርባዬን ታያለህ ፊቴን ግን አታይም” ብሎት ነበር /ዘጸ. 33.13፣23/፡፡ የዚህ ኃይለ ቃል ትርጓሜና ሐተታ በደብረ ታቦር ተፈጽሟል፡፡ እንዲህ ማለቱ “አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ሰው ሆኜ ሥጋ ለብሼ ኋላ በደብረ ታቦር እስክገለጽልህ ድረስ አንተ በመቃብር ተወስነህ ትኖራለህ” ማለቱ ነበርና፡፡ ይህን ማለቱ እንደሆነ የታወቀው ግን በደብረ ታቦር ሙሴን ከብሔረ ሙታን አምጥቶ ባቆመው ጊዜ ነበር፡፡

2/ ልዑል እግዚአብሔር ነቢዩ ኤልያስን፡- “አንተ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትሆነኛለህ” ብሎት ነበር፡፡ ይኸውም ኃይለ ቃል ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ “የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ነው ይልሃል? እግዚአ ኤልያስ፤ አምላከ ኤልያስ ይበሉህ እንጂ” ሲል በደብረ ታቦር ተፈጸመ፡፡ ታያለህ የተባለው ሙሴም አየ፣ ትመሰክራለህ የተባለው ኤልያስም መሰከረ፡፡

3/ በፊልጶስ ቂሳርያ ጌታ ሐዋርያትን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?” ብሎ በጠየቃቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ሙሴ ነው ይሉሃል ፤ እንዲሁም የኃይል ሥራህን ተመልክተው ኤልያስ ነው ይሉሃል” ብለው ነበርና ሙሴን ከመቃብር ፤ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ እግዚአ ሙሴ ፤ አምላከ ሙሴ ፤ እግዚአ ኤልያስ ፤ አምላከ ኤልያስ መሆኑን ለማስመስከር፡፡

4/ አይሁድ ፈሪሳውያን ጌታን እንደ ሕግ ተላላፊና የእግዚአብሔርን ክብር ለራሱ የሚወስድ አድርገው ያስቡት ስለነበረ /ዮሐ.9፡16፣ 10፡33/ ሕግን የሰጣቸው ሙሴንና ለሕገ እግዚአብሔር ቀናተኛ የነበረው ኤልያስን አምጥቶ ሕግ አፍራሽ አለመሆኑን የእግዚአብሔር ተቃዋሚም አለመሆኑን ለማስረገጥ፡፡

5/ ጌታችን በሙታንና በሕያዋን ላይ ሥልጣን ያለው እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ ሞተው ከተቀበሩት ሙሴን ከብሔረ ሕያዋንም ደግሞ አልያስን አምጥቶ ሲነጋገር ታየ፡፡

6/ የሐዋርያቱን የወደፊት አገልግሎት ሲነግራቸው፡፡ ይኸውም ሙሴ እና ኤልያስ ለሕዝበ እስራኤል በጣም ታማኝ እንደነበሩ ሁሉ እነርሱም ለሚያገለግሉት ሕዝብ ታማኝ እረኞች እንዲሆኑ፡፡ ሆኖም ግን አገልግሎታቸው ከሙሴና ከኤልያስ ይልቅ ጠንከር እንደሚልም አሳይቶአቸዋል፡፡ ምክንያቱም ውጊያቸው እንደ ሙሴ ከፎርዖን እንደ ኤልያስም ከአክዓብ ጋር ሳይሆን ከክፋት መናፍስት ጋር ነውና፡፡

# የበዓሉ መጠሪያ ስሞች (ደብረ ታቦር / ቡሄ/ ቡሔ መባሉ ስለምንድ ነው ?
• ደብረ ታቦር የተባለው ጌታ ክብሩን የገለጠበት ስፍራ ደብረ ታቦር ስለሆነ በዚሁ በዓሉ ስያሜውን አግኝቷል፡፡

• ቡሔ ይባላል ፡- ቡሄ ብርሃን ማለት ነው በደብረታቦር ቧ ብሎ የተገለጠውን የጌታችንን የፊቱን ብርሃን ጸዳል፤ የልብሱንም እንደ ነጭ በረዶ ጸዓዳ መሆን ያስረዳል፡፡
አንድም፡- ቡሔ ማለት መላጣ (ገላጣ) ማለት ነው፡፡ ይኸውም በበዓሉ ዋዜማ ልጆች ‹‹ ቡሔ በሉ፤ ቡሔ መጣ ፣ ያ መላጣ፣ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ›› ይላሉ እዚህ ላይ ቡሄ ያለው ዳቦውን ነው፡፡
• አንድም፡- ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለምሌሊት›› እንደሚባል ወቅቱ በሃገራችን የጸዓተ ክረምት ዋዜማ ስለሆነ የክረምቱ አፈናው ተወግዶ /ተጋምሶ/ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት ፤ በዶፉና በጎርፉ ተሸፍና የነበረች መሬት የምትገለጥበት በመሆኑ ነው፡፡

• አንድም፡- ቡሔ (ቡሔእየ) ተብሎ ይተረጎማል ይኸውም የደብረታቦር እለት እርሾ ሳይገባበት ተቦክቶ የሚጋገረውን ኅብስት ያሳያል፡፡

# “ችቦ የመብራቱ ፣ የሙልሙል ዳቦ የመጋገሩና የጅራፍ ማጮኽ ምክንያት፡-
ችቦ የሚበራው 12 ለ13 ዋዜማ ሌሊት በ3 ሰዓት ነው ።
• የጌታችን ክብሩ በተገለጠበት ጊዜ ብርሃኑ የሌሊቱን ጨለማ ገፍቶት እስከ አርሞንዔም ደርሶ ነበርና በዚያ አካባቢ የነበሩ እረኞች በሁኔታው ተገርመው ቀንም መስሎኣቸው ሌሊቱም ተዘንግቷቸው በዚያው ቆይተው ነበርና ቤተሰዎቻቸው ምን አግኝቷቸው ይሆን በማለት መብራት አብርተው (ችቦ ይዘው)፣ የሚመገቡትን ይዘው ወገኖቻቸውን ፍለጋ ወጥተዋል እረኞችም ያሉበትን ቦታ ለቤተሰዎቻቸው ጅራፍን በማጮኸ አመልክተዋቸዋልና ይህን ለማሰብ ነው፡፡
• ዋናው ምሥጢሩ ግን፡- የችቦው ብርሃን የጌታ ክብር መገለጡን፣ የጅራፋ ጩኸት ሓዋርያትን ያስደነገጣቸው የአብ የምስክርነቱ ቃል ምሳሌ ሲሆን፣ ኅብስቱ ጌታችን በመስቀል ላይ መሥዋዕት የመሆኑ (የሥጋወደሙ) ምሳሌ ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አዝልፍኬ አንብቦ መጻሕፍት እስመ እማንቱ ይመርሃሁ ለልብከ ኀበ አንክሮተ እግዚአብሔር- መጻሕፍትን አዘውትረህ አንብብ፤ መጻሕፍት እግዚአብሔርን ወደማድነቅ ልብህን ይመሩታልና፡፡ (ማር ይስሐቅ)

ማር ይስሐቅ መጻሕፍትን ማንበብ በውስጣቸው ያለውን እውቀት ከማግኘት ባለፈ ወደ ተመስጦ፣ እግአብሔርንም ወደማድነቅ እንደሚያደርስ ይነግረናል፡፡ ለማወቅም ሆነ ያወቁት ለማስተማር ከጉባኤ ከዋሉ ምስጢር ካደላደሉ ሊቃውንት እግር ስር ቁጭ ብሎ ለሚማሩት ትምህርት በቂ ጊዜ ሰጥቶ መማር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ጉባኤ ቤት ገብቶ በቂ ጊዜም ሰጥቶ መማር ለሁሉ የሚቻል አይደለምና በማደራጃ መምሪያችን በየዓመቱ በክረምት ወቅት የሚሰጥ እንደዚህ ዓይቱ የአጭር ጊዜ ሥልጠና መነቃቃትን የሚፈጥር ለተጨማሪም ትምህርትና ንባብ የሚያነሳሳ ስለሆነ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “መከሩ ብዙ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡” ብሎ እንዳስተማረ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በሁሉም ሰንበት ት/ቤቶች ተግባራዊ እንዲሆን የተጋጀው ወጥ ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም አህጉረ ስብከት በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ መምህራን ያስፈልጉናል፡፡ ይህንን የመምህራን ፍላጎት በአንድ ጊዜ ማሟላት የሚቻል ስላልሆነ እንደዚህ ያሉ ሥርዓተ ትምህርቱን መሠረት ያደረጉ አጫጭር ስልጠናዎች በጣም አስፈላጊዎች ናቸው፡፡

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጋር በመሆንና አህጉረ ስብከትን በማስተባበር ሥርዓተ ትምህርቱ በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ በክረምት ወቅት ከየአህጉረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤት መምህራንን ወደማዕከል በማስመጣት በዚህ መልኩ ሥልጠና ሲሰጥ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ሲሆን በቀጣይም ከአህጉረ ስብከት ጋር በመነጋገርና የሥልጠና ማዕከላቱን በማብዛት የተሻለ ሥራ ለመሥራት ታስቧል፡፡ በዘንድሮው ለሁለት ሳምንታትና ለ200 ሰዓታት በታወቁ የቤተ ክርስቲያናችን መምህራን የተሰጠው ሥልጠና እጅግ የተሳካ ሠልጣኞችም ጥሩ እውቀትና ልምድ የቀሰሙበት እንደነበር እናምናለን፡፡

ስለሆነም ውድ ተመራቂዎች የተማራችሁት ትምህርት መጻሕፍትን በማንበብና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊቃውንትን በመጠየቅ አዳብራችሁ ሥራ ልትሠሩበት ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በትምህርት የወለደው የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስን “ወተዐቀብ እስከ እመጽእ በአንብቦ ወበምሂር ወበገሥጾ ወበጸልዮ – እስክመጣ ድረስ በማንበብና በመምከር በማስተማርም ተጠንቀቅ።” 1ጢሞ. 4፡13 ብሎ እንዳስተማረው እግዚአብሔር ቢፈቅድ ወደፊት ወደጉባኤ ቤትና ወደ መንፈሳዊ ኮሌጆች ገብታችሁ ከዚህ የበለጠ ትምህርት እስክታገኙ ድረስ ከጸሎት ጋር በማንበብና በመምከር በማስተማርም አብዝታችሁ ልትተጉ ይገባል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ  አፈ ወርቅ  “ቅዱሳት መጻሕፍትን አለማወቅ የስህተት ሁሉ ምንጭ ነው፡፡” ብሎ እንዳሰተማረ መጻሕፍትን ባለማወቅ የሚመጣን ስሕተት ቅዱሳት መጻሕፍት አብዝቶ በማንበብና በመመርመር መከላከል ይቻላልና ለማንበብ እንድትተጉ ማደራጃ መምሪያችን አጥብቆ ያሳስባል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቈላስይስ መልእክቱ “ወይኩን ነገርክሙ በጸጋ ወቅሱመ በጼው – ነገራችሁ በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ይሁን በማለት መናፍቃን አብዝተው ቢጠቅሱ እናንተም አብዝታችሁ ጠቅሳችሁ በለጋስነት መልሱላቸው፡፡ ንግግራችሁም በፍቅርና በትሕትና የጣፈጠ ይሁን ብሎ እንዳስተማረ አሁን ያለንበት ዘመን ሐሳውያን የበዙበት መጽሐፍ ቅዱስን እየጠቀሱ የዋሃን ምእመናንን የሚያደናግሩ ሰዎች እንደ አሸን የፈሉበት ዘመን ስለሆነ በየምትሄዱበት አካባቢ ወጣቶችና ሕጻናትን ከመናፍቃን ቅሰጣ ጠብቆ በቃለ እግዚአብሔር ማሳደግ ይቻል ዘንድ የተማራችሁትን ትምህርት በሥራ ላይ በማዋል ዛሬ የተቀበላችሁትን አደራ በአግባቡ ልትወጡ ይገባል፡፡

በእነዚህ ሁለት ሳምንታት በነበራችሁ ቆይታ በተማራችሁት ትምህርት ሳትወሰኑ ሁል ጊዜ ለማንበብና ለመጠየቅ የተዘጋጃችሁ በመሆን ክህደትንና ኑፋቄን የምትቃወሙ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲን ዶግማዋን ቀኖናዋንና ሥርዓቷን ጠብቃችሁ የምታስጠብቁ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃዎች ልትሆኑ ይገባችኋል፡፡

ሰዎችን ለመለወጥ በብዙ የትምህርት ተቋማት አልፎ ብዙ ዕውቀት መሰብሰብ ብቻው በቂ አይደለምና ከማስተማር ጋር አርአያ የሚሆን ሕይወት ሊኖረን ይገባል፡፡ እንዲህ ሲሆን በአገልግሎታችን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ብዙ ኢማንያንን ወደ እምነት እንዲመጡ እናደርጋለን በእምነት ያሉ ወጣቶችና ሕጻናትም በዕውቀት እናሳድጋለን፡፡

በመጨረሻም ውድ ተመራቂዎች ለዚች ቀን እንኳን አደረሳችሁ እያልኩ ያለንበት ወቅት ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እጅግ የፈተና ወቅት እንደሆነ ተድተን ወጣቶችና ሕጻናት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ አገልግሎታችንም ለዘመኑ እንደሚገባ በጥበብና በእውቀት ልናደርግ ይገባል በማለትና አገልግሎታችሁ የተሳካ እንዲሆን በመመኘት መልእክቴን በዚሁ አጠቃልላለሁ፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወ/ትንሣኤ

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ

ሦስተኛው የአህጉረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና የምርቃት መርሐ ግብር ተከናወነ።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 21 / 11 / 2017 ዓ.ም

ሦስተኛው የአህጉረ ስብከቶች የሰ/ት/ቤቶች መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና የምርቃት መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ተከናውኗል። በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የሸገር ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የምስካየ ኅዙናን ገዳም የበላይ ጠባቂ እና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ፣ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋኒዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ በርናባስ የዋግህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ ፣ ዲ.ን ስንታየሁ ምስጋናው የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ተ/ም/ሰብሳቢ ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች ፣ መምህራነ ወንጌል ፣ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የሥራ አመራር አባላት ተገኝተዋል።

ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ባስተላለፉት መልእክት “ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ለ3 ዓመት ከ3 ወር ሐዋርያትን ከተለያየ ግብርና ክፍል መርጦ ካስተማራቸው በኋላ ሂዱና አስተምሩ በሀገር ሁሉ ቋንቋ አስተምሩ ብሎ እንዳዘዛቸውና አልጫ የሆነውን ዓለም በማስተማር እንዳጣፈጡ ሁሉ እናንተም በተማራችሁት ትምህርት ሄዳችሁ እንድታስተምሩ ፣ እንድታሰለጥኑ ፣ ፍሬ እንድታፈሩ” በማለት አባታዊ ምክርና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል።

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም እንዲሁ “ከእግዚአብሔር የተላከ ከእግዚአብሔር የተመረጠ የአምላኩ የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል” በሚል ኃይለ ቃል ተነስተው እርሱን ለማገልገል የሚጠራ ማንኛውም አገልጋይ የእግዚአብሔርን ዓላማ ፣ ሐሳብ የእርሱን ዕቅድና እርሱ ለሰው ያለውን አምላካዊ ጥበብ ፣ መግቦት በፍጥረቱም ላይ እንዴት እንደሚሠራና ጥልቅ የሆነውን ፍቅሩን ሁሉ ይናገራል። ብለው ወደ መጣችሁበት ስንቃችሁን ያዛችሁ በመሄድ በሚገባ አገልግሎታችሁን እንድትፈጽሙ ይሁን በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈው ቋጭተዋል።

በዕለቱ ሌላኛውን አባታዊ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ በርናባስ የዋግህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም እንዲሁ “በአባቶች ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ” የሚለውን የልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ቃል መነሻ አድርገው እናንተም በአባቶቻችሁ ፈንታ የተተካችሁ እንደመሆናችሁ አባቶቻችሁን መስላችሁ ቤተ ክርስቲያንን ልታገለግሉ ይገባል በማለት ለተመራቂ መምህራን የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ “መጻሕፍት እግዚአብሔርን ወደ ማድነቅ ልብህን ይመሩታልና” በሚል ኃይለ ቃል በመነሣት የማደራጃ መምሪያውን መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ተ/ም/ሰብሳቢ ዲያቆን ስንታየሁ ምስጋናው በሥልጠናው ጊዜ አጠቃላይ የተከወኑ ተግባራትና በቀጣይ እንዲሠሩ የሚፈለጉ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል። ሠልጣኝ መምህራኑም የነበራቸውን የ15 ቀን ቆይታ የተመለከተ ዘገባ እና አቋማቸውንም እንዲሁ በተወካያቸው በኩል አቅርበው ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እጅ የዕውቅና የምስክር ወረቀታቸውን ተቀብለው የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።

ሥልጠናው ከሐምሌ 7 እስከ ሐምሌ 20 ቀን ድረስ በተከታታይ ለ15 ቀናት የተሰጠ ሲሆን በሥልጠናውም ላይ ከ30 አህጉረ ስብከት የተወጣጡ 209 መምህራን ተከታትለው አጠናቅቀዋል። ከነዚህም መካከል 106 ቀሳውስትና ዲያቆናት እንዲሁም 8 ሴቶች ይገኙበታል።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት)

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የክረምት የመምህራን አሰልጣኞች ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ መምህራንን ጎበኙ።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 18/11/2017ዓ.ም

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አዘጋጅነት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ እየተሰጠ የሚገኘው የክረምት የመምህራን የአሰልጣኞች ሥልጠና ላይ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በመገኘት አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ የተናገረውን “ለወንድሞችህ ይህንን አስተምራቸው” የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ አድርገው አባታዊ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ልጄ ሆይ ጆሮህን ለመምህራን ስጥ እንደተባለ ከመምህራን እግር ስር ቁጭ ብለው የሚማሩት ቃለ እግዚአብሔር ለሕይወታች ስንቅ ነውና ቅዱስ ጢሞቴዎስን አብነት አድርጎ በሕይወት መተርጎም ይገባል የተማርነውንም ለወንድሞች ማስረዳት መንገር ይገባል ብለዋል።

በመጨረሻም ሰልጣኞች በተከታታይ በቀንም በማታም እየተሰጣቸው ያለውን ሥልጠና በሚገባ ተከታትለው በየሀገረ ስብከታቸው ሲመለሱ በትኩረት ሊሰሩ ለሌሎችም ሊያጋሩ እንደሚገባ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክረምት የመምህራን አሰልጣኞች ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ መምህራንን ጎበኙ።

የሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 14/11/2017ዓ.ም

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አዘጋጅነት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ እየተሰጠ 7ኛ ቀኑን በያዘው የክረምት የመምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በመገኘት አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው ለእናንተ የመንግስተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል” ማቴ 13፥11 በሚል ርዕስ ቃለ እግዚአብሔርና አባታዊ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የመንግስተ ሰማያት ምሥጢር ለማወቅ ጾታና ማዕረግ ሳይለይ ለሁሉም የሰው ዘር የተሰጠ ጸጋ መሆኑንና ይህን ምስጢር አውቆ ማሳወቅ ከመምህራን የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።

አያይዘውም ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት አሳስበው እንደ ሀገረ ስብከታቸው ሰሜን ወሎ ለሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰልጣኞችን በመላክና በመማርያ መጻሕፍት ግዥ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመጨረሻም ሰልጣኞች እየተሰጣቸው ያለውን ሥልጠና በሚገባ ተከታትለው በየሀገረ ስብከታቸው ሲመለሱ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)

የ2017 ዓ.ም የክረምት የአሰልጣኞች መምህራን ሥልጠና ተጀመረ

ሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 07 2017 ዓ.ም

የ2017 ዓ.ም የክረምት የአሰልጣኝ መምህራን ሥልጠና በዛሬው ዕለት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ተጀመረ። በዛሬው የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይም አረጋዊው አባት ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ የተገኙ ሲሆን ብፁዕነታቸው “እነሆ ጊዜው ደረሰ” በሚል መነሻ ቃለ ወንጌል ፣ አባታዊ ምክርና ቃለ ምዕዳን ለሰልጣኝ መምህራኑ አስተላልፈዋል። “እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤” የሚለውን የልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትን ቃል መነሻ በማድረግ የማደራጃ መምሪያው ሐላፊ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። በዛሬው የመክፈቻው መርሐ ግብር ላይ ሰልጣኞች በሚኖራቸው ቆይታ ሊያውቋቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በሚመለከት ገለጻ ተሰጥቶ የመክፈቻ መርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል። ሥልጠናው በዛሬው ዕለት በምሽት የሰንበት ት/ቤቶች መዋቅራዊ አደረጃጀትን በሚመለከት የሚቀጥል ሲሆን እስከ ሐምሌ 20 ድረስ በተከታታይ ለ15 ቀናት የሚቆይ ሲሆን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነትን ፣ የተለያዩ ክህሎትን የሚያዳብሩ እንዲሁም በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ትኩረት ያደረጉ ከ15 በላይ ሥልጠናዎችን የሚያገኙ ይሆናል። ሥልጠናውን ከ30 ሀገረ ስብከት የተወጣጡ 213 መምህራን የሚወስዱ ይሆናል።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት)

ከየሀገረ ስብከቱ ለተውጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራን የክረምት የአሠልጣኞች ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አስታወቀ።

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት በዓመቱ መጨረሻ ከየሀገረ ስብከቱ ለተውጣጡ መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና በማዘጋጀት አሠልጥኖ ወደየ ሀገረ ስብከታቸው ለአገልግሎት የማሰማራት ሥራ በየዓመቱ ሲያከናውን ቆይቷል። በዘንድሮም ዓመት ከ23 ሀገረ ስብከት በላይ ለተውጣጡና መመዘኛውን ለሚያሟሉ ከ200 በላይ ሠልጣኞች ሥልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አንድነቱ አስታውቋል።

ሥልጠናው የሚሰጠው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ ሲሆን ሠልጣኞች በቆይታቸው በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ዕውቀትን የሚያጎለብቱ፣ የግንዛቤ ለውጥ የሚያመጡ፣ ክህሎታቸውንም የሚያዳብሩ ሥልጠናዎች እንደሚሰጣቸውና ወደ ሀገረ ስብከታቸው ሲመለሱ በሥርዓተ ትምህርት ትግበራው ሰፊ ሥራ እንደሚሠሩ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አስታውቋል።

“ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ።” ዳን 10፡13

እንኳን ለተራዳኢው መልአክ ለቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ መታሰቢያ በሰላም አደረሳችሁ!
#ሚካኤል ማለት መኑ ከመ አምላክ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው የሚል ትርጉም አለው። ይህም እንደ እግዚአብሔር ያለ በባሕርይው ቅዱስ የሆነ ፣ እንደ እግዚአብሔር ያለ ንጹሐ ባሕርይ ፣ እንደ እግዚአብሔር ያለ ፍጹም ማነው የሚል ነው። ቅድስና ፣ ንጽሕና እና ፍጹምነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ከእግዚአብሔር በቀር የለምና። ዘዳ 33፡26
ሰኔ 12 በዚህች ቀን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በዓለ ሲመቱ ይታሰባል። እንዲሁም የባህራንን የሞቱን ደብዳቤ ወደ ሕይወት የቀየረበት እንዲሁም ቅድስት አፎምያን ከሰይጣን ያዳነበት መታሰቢያ ነው። “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ።” ዘጸ 23፡20 ይህ መልአክ በብሉይ እስራኤል ዘሥጋን ከግብጽ ባርነት መርቶ ነጻ እንዳወጣቸውና ምድረ ርስት ከንዐንን እንዲወርሱ በመንገዳቸው ሁሉ እንደረዳቸው፤ እንደጠበቃቸው ሁሉ ባሕራንም ይሄድ ከነበረበት የሞት መንገድ ሕይወትን ሰጥቶ ፤ አፎምያን ደግሞ ከጥንተ ጠላታችን ከዲያብሎስ እጅ በተራዳኢነቱ አድኖ ለክብር አብቅቷቸዋል።
በባሕራን እና በቅድስት አፎሚያ ታሪክ ውስጥ የምናገኘው የመልአኩ ተራዳኢነት ዛሬ ላይ ላለነው ለክርስቲያኖች በሕይወታችን ውስጥ የመልአኩን ተራዳኢነት አምነን እንድንጠቀም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ቅዱስ ሚካኤል ወይም ቅዱሳን መላእክት በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ መዳን መንግሥተ ሰማይን ለመውረስ በሚደረጉ ሒደቶች ሁሉ የሚራዱና የሚያግዙ ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ላይ “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስ አይደሉምን?” ብሏል። ዕብ 1፡14 ዛሬም እኛ ከቅዱሳን መናፍስት ወገን አንዱና አለቃቸው የሆነ ቅዱስ ሚካኤል መዳን መንግሥተ ሰማይን እንወርስ ዘንድ የሚላክ የሚያገለግል አይደለምን እንላለን። ማመን መጠመቅ በጎ ሥራ መሥራት ሕጉን ትዕዛዙን መጠበቅ ንስሐ መግባት እነዚህ በሙሉ ወደ መዳን / መንግሥተ ሰማያት / የሚያደርሱን መንገዶች ናቸው ፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል
ለሰዎች የሚራራ ፣ በተጨነቁም ጊዜ የሚያረጋጋ ፣ በደከሙ ጊዜ የሚያበረታ ፣ ባዘኑ ጊዜ የሚያጽናና ነው። ሉቃ 22፡43 ፣ ዳን 10፡20
የሰው ልጆችን ከመከራ ሥጋ እና ከመከራ ነፍስ የሚያድን የሚታደግ ነው። መዝ 33፡7 ፣ ዘፍ 48፡16 ፣ ዕብ 1፡14
ሰውን ከሚገጥመው ክፉ ነገር ሁሉ ይራዳል። ዳን 10፡13 ፣ ዳን 12፡1
ስለ ሰዎች ይማልዳል ከአምላካቸው ያስታርቃል። ዘካ 1፡12-13
ለሰው ሁሉ በጎን የሚያደርግ መልአክ ነው። ሔኖክ 6፡1-2
የከበረ መልአክ ነው። ከክብሩ የተነሳም ምድር ሁሉ ትበራለች። ራእ 10፡1 ፣ ራእ 18፡1
ትሕትናን የሚያስተምር ትሑት መምህረ ትሕትና ነው። ይሁ 1፡9
በሰዎች ድኅነት ሀሴት ደስታን የሚያደርግ ነው። ሉቃ 15፡7
የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነቱ አማላጅነቱ በዚህም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም ይጠብቀን።
ይቆየን!
መልካም በዓል!

የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና የሞዴልና ማጠቃለያ ፈተና ለመፈተን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የሀገር አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አሳወቀ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በትግበራ ላይ በሚገኘው ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ተምረው ለምዘናው የተዘጋጁ ሰንበት ተማሪዎችን የመመዘኛ ፈተና ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ።

ለምዘናው የሚቀርቡ አጥቢያ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በ2015ዓ.ም በሀገረ ስብከት ደረጃ የተዘጋጀውን የ10ኛ ክፍል መመዘኛ ፈተና ወስደው 12ኛ ክፍል የደረሱ ሰንበት ተማሪዎችን ሲሆን ለዚህም አስፈላጊውን መረጃ የመሰብሰብ አጥቢያዎችን የመለየት ሥራ መሥራቱን አንድነቱ አስታውቋል።

አንድነቱ በዘገባው የሞዴል ፈተናው የፊታችን ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን ዋናውና ማጠቃለያ ፈተናው ደግሞ በአምስት የፈተና ማዕከላት ሐምሌ 27 የሚሰጥ መሆኑን ተናግሯል።

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ በ14ኛው ዓለም አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ላይ ያስተላለፉት መልእክት

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ በ14ኛው ዓለም አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ላይ ያስተላለፉት መልእክት

“ወይረድአነ ለነ ድካመነ በመንፈስ ቅዱስ – ድካማችንን በመንፈስ ቅዱስ ያግዛል፡፡ ሮሜ 8፡26

ከሁሉ በማስቀደም አምላካች ቅዱስ እግዚአብሔር እንደ ሐዋርያት በተስፋ ለምንጠብቀውና ኃይል መንፈሳዊም አግኝተን ለበለጠ ሥራ ለምንነሳበት ለበዓለ ጰራቅሊጦስ፣ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን እና ለ14ኛው ዓለም ዐቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ፡፡ እንኳን ደህና መጣችሁ።

መንፈስ ቅዱስ የደከሙትን የሚያበረታ ያዘኑትን የሚያጽናና የታወኩትን የሚያረጋጋ ኃጢአተኞችን የሚያነጻ መንፈስ ነውና በደከምን ጊዜ ብርታትን፣ በመከራ ጊዜ ጽናትን፣ በፍርሐት ጊዜ ጥብአትን፣ በሁከት ጊዜ መረጋጋትን ይሰጠናል፡፡
በዘመነ ሐዋርያት የነበረው አገልግሎት በሰይፍና በስለት ውስጥ አልፎ የጠፉትን መፈለግ፣ በሞት ተወራርዶ በጎችን፣ ጠቦቶችንና ግልገሎችን መጠበቅን የሚጠይቅ ነበርና የሚያደክሙና የሚያፍገመግሙ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች በርካቶች ቢሆኑም ሲፍገመገሙ ያጸናቸው በድካማቸውም ሁሉ ያገዛቸው የብርታታቸውና የጽናታቸው ምክንያት መንፈስ ቅዱስ ነውና “ወይረድአነ ለነ ድካመነ በመንፈስ ቅዱስ-ድካማችንን በመንፈስ ቅዱስ ያግዛል” በማለት ሐዋርያው ተናገረ፡፡
ይህ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን የሆነው በዓለ ጰራቅሊጦስ በ፭ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን ተብሎ ከተሰየመ እነሆ ዛሬ ፲፬ኛ ዓመት ላይ እንገኛለን፡፡ ባለፉት 14 ዓመታት መንፈስ ቅዱስ ድካማችንን እያገዘ ብዙ መልካም ሥራዎችን ለማከናወን በመቻላችን የጅማሬም የፍጻሜም ባለቤት የሆነውን ልዑል እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡
ዕለተ ጰራቅሊጦስ ሐዋርያት በአንድ ሐሳብ በአንዲትም ልብ ሆነው በተሰበሰቡባት ጽርሐ ጽዮን መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሁሉም የራሱን ቋንቋ በሚሰማበት ልሳን እንዲያስተምሩ የተለያዩ ልሳኖች ለሐዋርያት የተገለጡባት፣ ፍርሐት ጠፍቶላቸው ጥብአትን ገንዘብ ያደረጉባት ዕለት ናት።

ይህችን ዕለት መነሻ በማድረግ በየዓመቱ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን የሚያከብረው የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያም እንደ ሐዋርያት አንድ ልብ በመሆን ከመምሪያው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጋር የሊቃውንት ጉባኤ አባላትን፣ የመንፈሳዊ ዩንቨርስቲና የኮሌጆች መምህራንን እንዲሁም የሥርዓተ ትምህርት ባለሙያዎችን በማሳተፍ በተዘጋጀው ወጥ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ሁሉም እንደ እድሜው ደረጃ ሊረዳው በሚችለው ልክና አቅም በተለያዩ ልሳናት መጻሕፍትን በማዘጋጀት ስያሜውን በተግባር በማሳየት ላይ ይገኛል።
ይህም ውጤት ከዚህ ቀደምም በተግባር የታየና ዛሬም በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ታትመው ለምረቃ በተዘጋጁት መጻሕፍት የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ ወደ ፊትም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቋንቋዎች መጻሕፍቱን ለማሳተም በዝግጅት ላይ ነን፡፡

ይህ ሁሉ ዘመን ተሸጋሪ የሆነና በዘላቂነት ትውልድን የሚታደግ ሥራ የተሠራውና እየተሠራም ያለው “ወሀሎ ምስሌሆሙ ኅቡረ መንፈስ ቅዱስ” መንፈስ ቅዱስ በጉባኤያቸው ሁሉ አብሯቸው ነበር እንዲል መጽሐፈ ምስጢር በሥራችን ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ስላልተለየን በድካማችንም ስላገዘን ነው።
ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ በሁሉም ቋንቋ ባስተማሩት ትምህርት ብዙ ነፍሳትን ማርከው “ምንተ ንግበር አኃዊነ” እንዳሰኙ ሁሉ በእነዚህ ፲፬ ዓመታት በተለይም ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በትኩረት በተሠራው ሥራ እና በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰንበት ት/ቤት አገልግሎት በሰጠው ትኩረትና በፈቀደው በጀት በ2016 ዓ.ም ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል በአማርኛ፣ በዚህ ዓመት በ2017 ዓ.ም ከ5ኛ እስከ 7ኛ ክፍል በአማርኛ እና ከ1ኛ እስከ 4ኛ በአፋን ኦሮሞ የሰንበት ት/ቤት መማሪያ መጻሕፍት በመታተማቸው ያለቋንቋ ገደብ ወጣቶችንና ሕጻናትን በማስተማር ግልገሎችንና ጠቦቶችን የመጠበቅ የመምሪያውን ተልእኮ ለማስፈጸም ትልቅ በር ተከፍቷል፡፡ በሥርዓተ ትምህርቱም ቤተ ክርስቲያናቸውን በሚገባ ያወቁና የተረዱ፣ በሥነ ምግባርም አርዓያ፣ “ምንተ ንግበር” በማለትም የቤተ ክርስቲያን ተስፋ የሚሆኑ ወጣቶችን ለማፍራት የተሻለ ዕድል ተገኝቷል፡፡

ወደፊትም በቤተ ክርስቲያናችን በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድና በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ በጸደቀው የ5ዓመት ሥልታዊ ዕቅድ እየተመራን የበለጠ ለመሥራት የምንጥር መሆናችንን እየገለጽኩ እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ልዩ ክትትልና የቅዱስነትዎ አባታዊ መመሪያ፣ ጸሎትና ቡራኬ እንዳይለየን በታላቅ ትሕትና እየጠየቅሁ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት የማደራጃ መምሪያው ሠራተኞችና የመምሪያውን ተልዕኮ ለማስፈጸም በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ከተዋቀረው የመምሪያው የሀገር አቀፍ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልጋዮች ጋር በመሆን፣ በመምሪያው ሊቀ ጳጳስ መመሪያ ሰጪነት ታግዘን ከምንጊዜው በተሻለ ውጤታማ ሥራ በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡

በአጠቃላይ በዘንድሮው የጉባኤያችን መሪ ቃል “የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡” ብሎ ሐዋርያው እንደተናገረው የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ሕጻናት መንፈሳዊ ሰይፍ የሆነውን ቃለ እግዚአብሔርን በአግባቡ ታጥቀው ክህደት ጥርጥርና ኑፋቄን ቆርጠው ይጥሉበት ዘንድ በ2017 ዓ.ም ዕቅዳችን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተነው የነበረው የሰንበት ት/ቤት መማሪያ መጻሕፍትን ቀጣይ ኅትመት የማከናወን ተግባር ተሳክቶ በዕቅዳችን መሠረት ከ5ኛ እስከ 7ኛ ክፍል በአማርኛ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል በአፋን ኦሮሞ ማሳተም በመቻላችን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡

በሚቀጥለው በ2018 በጀት ዓመት እግዚአብሔር ቢፈቅድ ቀሪዎቹ ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ መጻሕፍት የአርትዖት ሥራን በልዩ ትኩረት በማጠናቀቅ ለማሳተምና በተመሳሳይ በአፋን ኦሮሞም ቀጣይ የትርጉም፣ አርትዖትና የኅትመት ሥራን ለመሥራት ከወዲሁ ዝግጅት ጀምረናል፡፡

በመጨረሻም በ10 ዓመቱ የቤተ ክርስቲያናችን መሪ ዕቅድ መሠረት የተዘጋጀውን የ5 ዓመቱ ስልታዊ ዕቅድ አግባቡ በለመተግበር እንችል ዘንድ በእነዚህ ሁለት ቀናት በሚኖረን የምክክር መድረክ በዓለ ጰራቅሊጦስንና ዓመታዊ የሰንበት ት/ቤቶችን ቀን እያከበርን በቀጣይ ሥራዎቻችን ዙሪያ በትኩረት ተመካክረን የሚጠብቀንን ሰፊ አገልግሎት ባገናዘበ መልኩ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሚጠቅም፣ የወጣቱንም ሕይወት የሚታደግ ምክክር እንድናደርግ በትሕትና አሳስባለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወ/ትንሣኤ
የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ

ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት)

 

የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!

Youtube
https://www.youtube.com/@eotc-gssu

Facebook
https://www.facebook.com/gssu.eotc

Telegram
https://t.me/eotcgssu21

Tiktok

@eotc_gssu