ይቅርታና ክረምት
በወርሐ ክረምት ከሚታሰቡ እና ከሚናፈቁ ነገሮች አንዱ አዲሱን ዓመት መቀበል፣ ስለ አዲሱ ዓመት ማሰብ ፣አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ምኞትና በአዲሱ ዓመት ስለ ሚሠሩ ሥራዎች፣ ስለምናሳካቸው ተግባራት እቅድ ማቀድ ነው።
አብዛኞቻችን ከማናስበው ነገር አንዱ አሮጌውንስ ዓመት እንዴት እንሸኘው የሚለውን ነው:: ሁሌም ይሄ ሲታሰብ ወደ አእምሮ ከሚመጡ ነገሮች ዉስጥ ጾመ ፍልሠታ አንዱ ነው። በተለይም ደግሞ ከአዲስ ዓመት በፊት መምጣቱ አሮጌውን ዓመት ለመሸኘት ጥሩ አጋጣሚ ነው። በፍልሰታ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ምዕመን በመሚባል ደረጃ ከሕፃን እስከ አዋቂ የሚጾምበት የሚያስቀድስበት ወቅት ነው። ግን ምን ያህሎቻችን ነን ቅዳሴ ስንሄድ የካህኑን “በልቦናው ቂምን ያዘለ ክፋትን ያሰበ ቢኖር እዚህ አይቁም” የሚለውን ቃል ልብ የምንል የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።
ጾም ጸሎታችን ቅዳሴያችን ምጽዎታችን ሳይቀር ያለ ይቅርታ በረከት ማናገኝበት እንደሆነ የምናስበው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና) በማቴ 5÷23-24 ባለው ኃይለ ቃል፤ “እንግዲህ መባህን በመሰዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች አንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሰዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፤ አስቀድመክም ከወንድምክ ጋር ታረቅ፤ በኋላም መጥተክ መባክን አቅርብ።” ያለውን አምላካዊ ቃል አስበን አሮጌው ዓመታችንን በይቅርታ ለመሸኘት የተዘጋጀን መሆን ይገባናል። በዘዉትር ጸሎት ላይ፤ “በደላችንን ይቅር በለን፣ እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል” እንላለን። ታድያ፤ ይቅርታ ምንድነው? ለምንስ ነው ይቅርታ ማደርገው? ደሞስ ለማ? የሉትን ጥያቄዎች በመመለስ አሮጌውን ዓመታችንን በይቅርታ ለመሸኘት እንዘጋጅ።