በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ ፣
በጾምና በጸሎት ወደ እርሱ የሚቀርቡትን በዓይነ ምሕረት የሚቀበል እግዚአብሔር አምላካችን፣ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ዓራት ዓመተ ምሕረት የፆመ ኢየሱስ ሱባዔ በሰላም አደረሳችሁ!!
“ትግሁ ወጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት፤ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ”፤
(ማቴ ፳፮.፵፩) ።
ምድራውያን ሰዎች የምንኖርባት ይህች ዓለመ መሬት ከሰው ውድቀት በኋላ በልዩ ልዩ ፈተና የምትናጥ እንደ ሆነች ሁላችንም የምናውቀው ነው፤ እሷን ከፈተና ነፃ ማድረግም ሆነ መከላከል የሚችል ከፍጡራን ወገን አልተገኘም፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ወበዓለምሰ ሀለወክሙ ትርከቡ ሕማመ፤ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ “ማለቱ ይህንን የሚያመለክት ነው፤ ከዚህ አኳያ ሲታይ ዓለም ምን ጊዜም ከፈተና ውጭ አይደለችም ማለት ነው፤ ይህ እውነት እንደ ሆነ እኛም በዓይናችን የምናየው፣ በአእምሮአችን የምንገነዘበው ሓቅ ነው፤
ግብረ ኃጢአትና ክፉ ሕሊና እስካሉ ድረስ ፈተና ባይቀርም፣ መለኮታዊ መከላከያ የሌለው ግን አይደለም፤ መከላከያውም ኃይለ እግዚአብሔር ነው፤ የእግዚአብሔር ኃይልና ረድኤት ለማግኘት ደግሞ፣ ሰው ቆም ብሎ ማሰብና በንሥሐ ወደ እግዚአብሔር፤ መመለስ ያስፈልገዋል፤ ከዚህ አንጻር የንሥሐ፣ የጾምና የጸሎት አስፈላጊነት ፈተናን ለመከላከል እንደሆነ እንገነዘባለን፤ ይህም በመሆኑ ጌታችን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ በማለት አስተማረን።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
በጌታችን አስተምህሮ መሠረት ፈተናው ከማየሉ በፊት ተግተን ካልጸለይን ፈተና ሁሌም ይጸናብናል፤ ይሁን እንጂ ጌታችን በሌላ በኩል “ለምኑ ይሰጣችኋል” ብሎ ቃል የገባልን በመሆኑ በፈተና ውስጥ ሆነንም በንሥሐ፣ በጾምና በጸሎት እሱን በመለመን ፈተናን መከላከል እንችላለን ፤ ጌታችን እኛን ለማስተማር ዓርባ ቀንና ዓርባ ሌሊት በጾመ ጊዜ በፈተና አምጪው ፍጡር ላይ የተቀዳጀው ድል የምናውቀው ነው፤ አሁን የምንጀምረው የጾመ ኢየሱስ ሱባዔም ፈተናን እንዲያስቀርልን፣ በምትኩም ምሕረቱን እንዲያወርድልን ለመለመን እንደሆነ ሕዝበ ክርስቲያኑ በውል ተገንዝቦ በተመሥጦ ወደፈጣሪው መማፀን ይኖርበታል።
እንግዲህ መዋዕለ ጾም የንሥሐ ጊዜ ነው ሲባል፣ ንሥሐ የምንገባው እንዴት ነው የሚለውንም ማስተዋሉ ተገቢ ነው፤ ልባችን እንደ ሚመሰክርብን ያለንበት ጊዜ፣ጥል ያየለበት፣ ጭካኔ ሥር የሰደደበት እንደሆነ አይካድም፤ በዚህም ምክንያት የብዙ ልጆቻችንና ወገኖቻችን ሕይወት ተቀጥፎአል ፣ኑሮም ተመሰቃቅሎአል፤ ጥላቻ ቦታ ካገኘ ውጤቱ ከዚህ ሌላ ሊሆን አይችልምና ይህንን ሁሉ አስከትሎብናል፤ በመሆኑም በዚህ ወርኃ ጾም ንሥሐ መግባት አለብን ስንል የከረምንበቱን የጥላቻ ሕሊና ከሥር መሠረቱ ነቅለን በመጣል፤ ፍቅርንና ሰላምን በመሻት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አለብን ማለታችን ነው ፤
ጾምን በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ መሥዋዕት የሚያደርገው፣ ኃይል ሰጪ ከሆኑት መባልዕት መከልከል ብቻ ሳይሆን ከጠብና ጥላቻ መራቅና መከልከል እንደ ሆነ በሚገባ ማስተዋል ይኖርብናል፤ በመዋዕለ ጾም ወቅት ኃይል ሰጪ ከሆኑ መባልዕት መከልከል ያስፈለገውም ጠብና ጥላቻን ለመቀነስ፣ብሎም ለማስወገድ ምቹ መደላድልን ለመፍጠር እንጂ ምግቦቹ በራሳቸው ኃጢአት ሆነው አይደለም፤ በመሆኑም ከፈተና ለማምለጥ የእግዚአብሔር ኃይል ያስፈልገናል የእግዚአብሔርን ኃይል ለማግኘት ደግሞ በኃይለ ሥጋ ሳይሆን በኃይለ መንፈስ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ያስፈልጋል፤
ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ደግሞ ከባልንጀራ ጋር በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ፍጹም ፍቅር መመሥረት ያስፈልጋል፣ ፍቅር ስለተባለውም ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ “በአጠገብህ ያለውን ወንድምህን ሳትወድ እግዚአብሔርን እወዳለሁ ማለት ውሸት ነው” ብሎ እንዳስተማረን ወንድማችንን ሳንወድ ወደ እግዚአብሔር ብንቀርብ ተቀባይነት እንደ ማይኖረን ማወቅ አለብን፤ በመሆኑም ለእግዚአብሔር ክብርና ለዘላቂ ሰላም ሲባል ወደ እውነተኛው ፍቅር መሸጋገር አለብን፤ ያን ጊዜ እግዚአብሔር ፍቅራችንን ድልድይ አድርጎ ፈተናውን ያርቅልናል፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት !
ባጋጠመን ሀገራዊ ፈተና መነሻነት ሕዝባችን ሲፈተን ቤተ ክርስቲያናችንም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከመሆን እንዳላመለጠች ሁላችንም የምንገነዘበው ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ለሕዝብ የተፈጠረችና በሕዝብ መካከል ያለች በመሆኗ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው ሁሉ በእርስዋ ላይም በቀጥታ ይደርሳል፤ ከዚህ አኳያ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምም በዚህ መዋዕለ ጾም ፍቅርን በተላበሰ ንሥሐ እግዚአብሔርን እንድንጠይቅ በዚህ አጋጣሚ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤
በመጨረሻም፦
በመዋዕለ ጾሙ ስለ ሀገርና ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ፣ስለ ሕዝባችን ዘላቂ ፍቅርና ስምምነት አጥብቀን እንድንጸልይ፣እንደዚሁም በግጭቱና በድርቁ ለተጐዱ ወገኖቻችን ካለን በማካፈል የችግሮቻቸው ተካፋይ እንድንሆን፣ ከዚህም ጋር ለሀገራዊ ሰላምና ፍቅር መሳካት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ መዋዕለ ጾሙን እንድናሳልፍ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን ።
እግዚአብሔር ወርኃ ሙን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በደህና ያድርሰን ፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን !
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
የካቲት ፳፩ ቀን ፳፻፲፬ ዓመተ ምሕረት ፤
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ፤