ከደቂቀ እስጢፋኖስ እስከ መንበረ ሰላማ
የተከበራችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ የሆነውን እና አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ተሐድሶ መናፍቃን እና ተስፈንጣሪ ፖለቲከኞች የሚያነሷቸውን የፈጠራ ድርሰቶች መነሻ ምክንያት የሚያስነብበውን ጽሑፍ ለንባብ ማብቃታችን የሚታወቅ ነው። ቀጣዩን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ፡-
ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ
በመካከለኛው ዘመን ለቤተ ክርስቲያን መልካም ካደረጉ ነገሥታት አንዱ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ነው። ንጉሡ አገሪቱን ለሁለት ሊከፍል ጫፍ ደርሶ የነበረውን የቤተ ተክለ ሃይማኖት እና የቤተ ኤዎስጣቴዎስ ጉዳይ መፍትሔ በመስጠት ሰላም እንዲወርድ አድርጓል። ጉዳዩ እንዲህ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን በሐዋርያዊ አገልግሎታቸው የሚታወቁት የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም መነኰሳት እና የአባ ኤዎስጣቴዎስ ተከታዮች ልዩነት ፈጥረው ነበር። የልዩነቱ ምክንያት ቤተ ተክለ ሃይማኖቶች መከበር የሚገባት ሰንበተ ክርስቲያን እንጂ ሰንበተ አይሁድ መከበር የለባትም ሲሉ ኤዎስጣቴዎሳውያን ደግሞ ቅዳሜም፣ እሑድም መከበር አለባቸው የሚል አቋም ያዙ። በዘመኑ የነበሩ ነገሥታት አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ያከበርን መስሏቸው የእርሳቸውን ገዳም መነኰሳት አሳብ ደግፈው ቤተ ኤዎስጣቴዎሳውያንን መግፋት በመጀመራቸው ልዩነቱ እየሰፋ ሄደ። Read more