“ኢሀሎ ዝየ ዳእሙ ተንሥአ በከመ ይቤ – ከዚህ የለም እንደ ተናገረው ተነሥቷል፡፡” ማቴ.28፡6
በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር በራስጌና በግርጌ የነበሩ ቅዱሳን መላእክት ማልደው ወደ ጌታ መቃብር ለሄዱ ሴቶች ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ ከዚህ የለም እንደ ተናገረው ተነሥቷል በማለት መልሰውላቸዋል፡፡ ሴቶቹ ወደ መቃብሩ መሄድ የጌታችንን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ጠበቁት ሦስት ቀን የሞላው ጠረኑ የተቀየረ ሥጋ ሳይሆን ባዶ መቃብር ነበር ያገኙት፡፡ ማስተዋል አቅቷቸው እንጂ ጌታችን ከሞቱ አስቀድሞ “ይህንን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አነሣዋለሁ” ብሎ በሥልጣኑ በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ነግሯቸው ነበር፡፡ (ዮሐ.2፡18) በሌላም የወንጌል ክፍል “ያለ እኔ ፈቃድ ነፍሴን ከሥጋዬ የሚለያት የለም፤ እኔ ወድጄ እለያታለሁ እንጂ በመቃብር ላኖራት አዋሕጄም ላስነሣት ሥልጣን አለኝ፡፡” በማለት ስለሞቱና ስለ ትንሣኤው ተናግሮ ነበር፡፡ (ዮሐ.10፡18)
የጌታችን ሥጋ በመቃብር መፍረስ መበስበስን ሊያጠፋል ወደ መቃብር ወረደ እንጂ እስከ ክርስቶስ ድረስ በነበሩ ሙታን ሲሆን እንደነበረው መፍረስ መበስበስ ያለበት በሦስተኛውም ቀን ሽቱ መቀባት የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ አይሁድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ካንተ ምልክት ማየት እንሻለን ባሉት ጊዜ “አመጸኛና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ትሻለች ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጣትም፡፡ ዮናስ በአሳአንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት እንደቆየ የሰው ልጅም በምድር ሆድ ውስጥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ይቆያል፡፡” በማለት መቃብር እንደማያስቀረው ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፡፡ (ማቴ.12፡39)
ወደ መቃብሩ የሄዱ ሴቶች በተደጋጋሚ በሰሙት የአይሁድ የውሸት ወሬ ምክንያት አስቀድሞ የሰሙትን የጌታ የትንሣኤውን ነገር በሙሉ እምነት መቀበል አልቻሉም ነበርና ሽቱ ለመቀባት ሄዱ፡፡ በለሊት ከወንዶቹ ቀድመውና ጨክነው ወደ መቃብሩ የሄዱበት ጥንካሬ ግን የሚደንቅ ነው፡፡ ቀድመው በመሄዳቸው ቀድመው የትንሣኤውን ብስራት ሰሙ፤ በዓይናቸውም አይተው አረጋገጡ፡፡ ጌታችን ከሙታን መካከል እንደሌለ፣ መሞቱ ሞታችንን ሊያጠፋ፣ ወደ መቃብር መውረዱም በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን ሊያስወግድ እንደሆነ ተረዱ፡፡
የጌታችን የሞተው ሞታችንን ለመግደል የተነሣውም እኛን ለማሥነሳት ነውና የጌታችን ትንሣኤን ስናከብር የምናከብረው ትንሣኤያችንን እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ዘተሰቅለ በእንተ ኃጢአትነ ከመ ያጽድቀነ ወትንሥአ ከመ ያንሥአነ – ሊያጸድቀን ስለኃጢአታችን ተሰቀለ፤ ሊያነሣንም ተነሣ” ይላል፡፡ (ሮሜ.4፡25) ስለዚህ የትንሣኤን በዓል ስናከብር የተነሣንበት በዓል እያከበርን ነውና በዓሉ ሙት በሆነ ሕይወት እንዳናከብር በትንሣኤ ልቡና ተነሥተን ስለእኛ ሕይወት የተቆረሰውን የክርስቶስ ሥጋን በመብላት ደሙንም በመጠጣት ሊሆን ይገባል፡፡ በዓለ ትንሣኤ የመነሣት በዓል ነውና ለፍቅር ለአንድነት ለሰላም ከመነሣት ጋር በዓሉን ማክበር ይገባል፡፡
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ “ወአድኃነነ በርደቱ እመስቀሉ ውስተ ሲኦል ወፈትሐ እለሀለዉ ሕየ ጻድቃነ ሙቁሐነ በኃጢአተ አዳም አቡሆሙ – ከመስቀሉ ወደ ሲኦል በመውረዱ አዳነን በዚያም በአባታቸው አዳም ኃጢአት ምክንያት የታሰሩ ጻድቃንን ፈታ፡፡ ብሎ እንዳስተማረ የምናከብረው በዓል የመፈታት በዓል ስለሆነ ከኃጢአት፣ ከክፋት ከዘረኝነትና መሰል እስራቶች ተፈትተን ልናከብረው ይገባል፡፡
በመጨረሻም በመላው ዓለም የምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን፣ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ያላችሁ በሰንበት ትምህርት ቤት የምታገለግሉ ወጣቶችና ሕጻናት በዓሉ ለንስኃ፣ ለአገልግሎትና ለመልካም ነገር የመነሣትና ከተለያዩ የዓለም እስራቶች የመፈታት በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡
እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ! መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንላችሁ!
መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወ/ትንሣኤ
በመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ
የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!
(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)
Youtube
https://www.youtube.com/@eotc-gssu
https://www.facebook.com/gssu.eotc
Telegram
https://t.me/eotcgssu21
Tiktok
@eotc_gssu