የጥናትና ምርምር ቋሚ ኮሚቴ
“ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከሳራውን የማይቈጥር ማን ነው?” – ሉቃ ፲፬ ፥ ፳፰
እጅግ ፈጣን በሆነ ለውጥ ውስጥ በምትጓዝ ዓለም እንደመኖራችን መጠን የዓለምን አቅጣጫ አስቀድሞ እየቃኘ ሰ/ት/ቤቶች በየዘመኑ የሚኖረውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ እና ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት እንዲሰጡ በክርስቲያናዊ ዕሴቶች የተቃኙ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ድጋፎችን ያካተቱ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከዚህ አንጻር የጥናት እና ምርምር ቋሚ ኮሚቴ በመላው ዓለም ከመንበረ ፓትርያርክ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እስከ አጥቢያ ሰ/ት/ቤት ድረስ በተዘረጋው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች መዋቅራዊ አደረጃጀት ውስጥ የሰ/ት/ቤቶችን አደረጃጀት የሚያጠናክሩ እና የቤተ ክርስቲያንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የጥናት ሥራዎችን ማካሄድ፣ አዳዲስ የአገልግሎት መርሐ ግብሮችንም እያጠና ዘመኑን የቀደመ ዝግጅት ማድረግ ዋነኛ ተግባሩ ነው።
ይህ አገልግሎት በጎ ፈቃደኛ በሆኑ የሰ/ት/ቤት አባላት እና ባለሙያዎች እንዲተገበር አባላትን ይመለምላል፣ ያስተባብራል፣ አስፈላጊ ሲሆንም በሙያው ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች አማካኝነት ያስፈጽማል።