የነገረ ሰብእ ትምህርት ጉድለት የወለደው አገራዊ ቀውስ

የነገረ ሰብእ ትምህርት ጉድለት የወለደው አገራዊ ቀውስ
በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነገረ ሰብእ (አንትሮፖሎጂ) አንደኛው የጥናት ዘርፍ ነው። ይህ የጥናት ዘርፍ ስለ ሰው አፈጣጠርና ክብር የሚናገር ነው። ስለ ፍጥረት አመጣጥ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት ሰው በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር መሆኑን ይነግረናል። ሊቀ ነቢያት ሙሴ ስለ አፈጣጠሩ ሲተርክልንም “እግዚአብሔርም አለ፤ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፣ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ፡ እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ. ፩፡፳፮-፳፯) ይለናል። የሚወዱትን እንግዳ ሁሉን አዘጋጅቶ እንደሚጠሩት እግዚአብሔርም ለሰው የሚያስፈልገውን ሁሉ አስቀድሞ ካዘጋጀ በኋላ ሰውን የፍጥረት መደምደሚያና መካተቻ አድርጎ ፈጥሮታል። እግዚአብሔር ሌሎች ፍጥረታትን በኀልዮ (በማሰብ) እና በነቢብ (በመናገር) ሲፈጥራቸው ሰውን ግን በእጁ ሠርቶታል። “እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በፊቱም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” (ዘፍ. ፪፡፯) የተባለው ለዚህ ነው። ስለሆነም ሰው ክብሩና ልእልናው ከፍ ያለ ነው። Read more