የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት - በኢ/ኦ/ተ/ቤ የመንበረ ፓትርያርክ ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ስለ አንድነቱ
    • መሠረታዊ መረጃዎች
      • ተቋማዊ ራእይ፣ ተልእኮ
      • መዋቅራዊ አደረጃጀት
      • የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ተቋማዊ አደረጃጀት
      • የሰንበት ት/ቤቶች የሥራ አመራር ምርጫ ማስፈጸሚያ
    • ስልታዊ እቅድ 2018 – 2021 ዓ/ም
  • ሥርዓተ ትምህርት
    • መሠረታዊ መረጃዎች
    • የሰንበት ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት አደረጃጀት መመሪያ
    • የሥርዓተ ትምህርቱ መመማሪያ መጻሕፍት ይዘት
      • የአንደኛ ክፍል መማሪያ መጻሕፍት ይዘት
      • የኹለተኛ ክፍል መማሪያ መጻሕፍት ይዘት
      • የሦስተኛ ክፍል መማሪያ መጻሕፍት ይዘት
    • የሥርዓተ ትምህርቱ ዓመታዊ የጊዜ ሰሌዳ /ካሌንደር
    • የመምህራን ሥልጠና እና መልእክቶች
    • መጻሕፍቱን ለማግኘት እና ተጨማሪ መረጃ
    • ልዩ ልዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች
  • ፕሮጀክቶች
  • መዝሙረ ማኅሌት
    • የመስከረም ወር መዝሙሮች
      • የዮሐንስ መዝሙር
      • የመስቀል መዝሙሮች
      • የብዙኃን ማርያም መዝሙር (መስከረም ፳፩ )
      • የዘመነ ጽጌ መዝሙር
    • የጥቅምት ወር መዝሙሮች
      • የአብርሃ ወአጽብሐ መዝሙር (ጥቅምት 4 ቀን)
    • የኅዳር ወር መዝሙሮች
      • የቅዱስ ሚካኤል መዝሙር (ኅዳር 12 ቀን)
    • የጥር ወር መዝሙሮች
      • የዘመነ ጥምቀት መዝሙር
      • የቃና ዘገሊላ መዝሙር (ጥር 12 ቀን)
    • የመጋቢት ወር መዝሙሮች
      • የወርኃ ጾም መዝሙሮች
      • የሆሣዕና መዝሙራት
      • የሰሙነ ሕማማት መዝሙሮች
  • ዜና
    • አጫጭር ዜናዎች
    • ዝርዝር ዜናዎች
    • ወቅታዊ መረጃዎች
    • ማስታወቂያ
      • የሰንበት ትምህርት ቤቶች መጻሕፍት እንግሊዝኛ ትርጉም ሥራ ተሳትፎ ጥሪ
  • ያግኙን
  • ቋንቋ
    • ትግርኛ
    • Afaanoromo
  • Menu Menu

ከወርቃማው ሕግ አትንሸራተቱ (የነገረ ሰብእ ትምህርት ጉድለት የወለደው አገራዊ ቀውስ ክፍል ሁለት)

የነገረ ሰብእ ትምህርት ጉድለት የወለደው አገራዊ ቀውስ

የነገረ ሰብእ ትምህርት ጉድለት የወለደው አገራዊ ቀውስ

የተከበራችሁ የማኅበራዊ ሚዲያችን ተከታታዮች አስቀድምን ባስነበብነው የዚህ ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ሰው በእግዚአብሔር አርአያ እና ምሳሌ የተፈጠረ የፍጥረታት ንጉሥ፣ ከሌሎች ፍጥረታት ተለይቶ ዐዋቂ እና ሕያውነት ያለው፣ በፍጥረታት ላይ የሠለጠነ ባለጸጋ ፍጡር መሆኑን አቅርበን ነበር። በዚህም ምክንያት ሰው ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ ሲጠፋ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ “እስመ በፈቃዱ፣ ወበሥምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጽዐ አድኀነነ” እንደ ተባለው ሰው ሆኖ ሰውን ከውድቀት አነሣው። ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ትቶ አንዱን ነገድ ሰውን ለመፈለግ ሰው የሆነው ለሰው ካለው ጽኑ ፍቅር የተነሣ ነው።

ሰውን ያዳነውም ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ በሚበልጥ ጥበብ ነው። በከብቶች ግርግም የተወለደው፣ ረኃቡን እና ጥሙን ታግሦ ወደ ግብፅ የተሰደደው፣ ሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት ዞሮ ያስተማረው፣ በአይሁድ መከራ የተቀበለው፣ የተገረፈው፣ የተጎተተው፣ በመስቀል የተሰቀለው፣ በሚስማር የተቸነከረው፣ ነፍሱን በገዛ ፈቃዱ የሰጠው እና ወደ መቃብር የወረደው ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ለመግለጥ ነው። ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ቢሆንም ክርስቶስ ሞትን የተቀበለው በራሱ ፈቃድ ለሰው ልጆች ካለው ፍቅር ነው። በመስቀል ላይ እንዲሰቀል ያደረገው፣ ያስገረፈው ጲላጦስ ቢሆንም ግርፋቱን የተቀበለው በፈቃዱ ለሰው ልጅ ካለው ፍቅር የተነሣ ነው። በመስቀል ላይ የተቸነከረው በሚስማር አይደለም በፍቅር ነው። እርሱ ሁሉን ቻይ አምላክ ሲሆን በፈቃዱ ለድኅነተ ዐለም መከራውን ታግሷል።

ለሰው ልጅ ይህ ሁሉ የተደረገለት፣ ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለለት ክቡር ፍጥረት ነው። ሰው አምላክ ለመሆን ፈልጎ በእግዚአብሔር ላይ ዐምጾ ከእባብ ጋር የማይገባ ምክር ተመካክሮ ነበር። እግዚአብሔር ግን ሰው ሆኖ የሰውን የአምላክነት ተምኔት ፈጸመለት። አዳም በበደለው ተበዳዩ ራሱ ቤዛ ሆኖ ከፈለለት። ቅዱስ ጳውሎስ “ጠላቶቹ ሳለን በልጁ ሞት ታረቀን” በማለት እንደ ገለጠው ሕግ አፍራሾች ብሆንም ቸል ብሎ ይተውን ዘንድ አልፈቀደም። በራሳችን መሻት ተቅበዝብዘን ከክብር ብንጎድል፣ በሞቱ ከሞት እስራት ፈትቶ ወደ ቀደመ ክብራችን መለሰን። ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ “አምላክ ሰው የሆነው ሰውን አምላክ ለማድረግ ነው” በማለት ያስተማረው ለዚህ ነው። አምላክ ሰው ሲሆን ከእመቤታችን የነሣውን ሥጋ የባሕርይ አምላክ፣ እኛን ደግሞ የጸጋ አማልክት አደረገን። በዚህም ቅዱሳን “የጸጋ አማልክት ለመሆን የተጠራን ድንቅ ፍጡራን ነን” ብለው ለመናገር በቁ። በቅድመ ፍጥረት ለሰው ልጅ ምድራዊ ምግብን ሁሉ ያዘጋጀ አምላክ በዳግም ፍጥረት ሰማያዊ ምግብና መጠጥ አዘጋጀለት። አትብላ የሚል ትእዛዝ ሰጥቶት መጠበቅ ቢከብደው ሥጋውን ቆርሶ፣ ደሙን አፍስሶ ብላ ጠጣ ብሎ የሕይወት እንጀራ እና የሕይወት ውኃን ሰጠው። ከዚህ የምንረዳው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያልሰጠው ክብር አለመኖሩን ነው።

ከዚህ በተቃራኒው ዐለም ሰውን ግብ ያደረገ ፍልስፍና፣ ሳይንስ፣ ርእዮተ ዓለም እና ሥርዓት ስትከተል አትታይም። እንዲያውም በተቃራኒው ሰው ቁሳቁስ ለማምረት እንደ አንድ ግብዓት ነው የሚቆጠረው። የሳይንስ ግቡ የሰውን ሕይወት ማቅለል ነው ቢባልም ቅሉ አጠቃላይ ሥሪቱ ግን ሰውን በቁሳቁስ ሊተካ የሚችል “ተራ ፍጡር” እንጂ ክብር እና ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ፍጥረት መሆኑን መረዳት አይችልም። የሰው ሞት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ነጻነት መገፈፍና ሌሎች ሰው ሠራሽ ችግሮች ሁሉ በዚህ ምድር ላይ ለሰው የተሰጠው ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑን የሚያስገነዝቡ ናቸው።

ሰዎች በተለያዩ በሽታዎች ሲጠቁና ሲሞቱ “በሽታው አምራቹን የሰው ኃይል እያሳጣን ነው” የሚል ዜና ሲሠራ የምንሰማው የሰውን ክብር ከመግለጥ ይልቅ ከሟቹ ይገኝ የነበረውን ጥቅም ብቻ አስልቶ ኀዘንን መግለጥ የሰውን ታላቅነት አለመረዳት ነው። የጉዳዩ ትኩረት አምራችነቱ ላይ እንጂ ሰውነቱ ላይ ሲያርፍ አለመታየቱም ክብሩን ካለመረዳት የመነጨ ነው። ሰውን የሚገፋ እና የበይ ተመልካች ያደረገ ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለም፣ ለሰው ሳይሆን ሰው ለሚያስገኘው ነገር ቅድሚያ የሚሰጥ የትምህርት ሥርዓት፣ ለብዙኀን ሳይሆን ለኅዳጣን ቅድሚያ የሚሰጥ የአስተዳደር ፍልስፍና በዐለም ላይ የተንሰራፋው ሰው የራሱን ክብር ባለመረዳቱ ምክንያት ነው።

ሰው በሰው ላይ በደል ሲፈጽም፣ ሰውን ሲያሳድድ፣ ንብረቱን ሲቀማ እና ሲያወድም አልፎ ተርፎም ሰውን ሲገድል የማይሳቀቀው ሰው እንስሳ ነው ተብሎ የተነገረውን አምኖ ተቀብሎ በዚያው ስለሚመራ እንጂ ሰውን ሲበድል የራሱንም ክብር እያዋረደ መሆኑን ስለማይረዳው ነው። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “ሰው ጅምር ፍጡር ነው፤ የሚሞርዱት እና አስተካክለው የሚቀርፁት መጻሕፍትና መምህራን ናቸው” የሚሉት ያለ ምክንያት አይደለም። በዚህም ምክንያት ሰው የአካባቢው ፍጡር ነው ይባላል። ሰውን ዐውሬም፣ ሰውም አድርጎ በማሳደጉ ረገድ ሁሉም የራሱ ድርሻ አለው። የሰው ጠባይ እና ማንነት በቤተሰቦቹ፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ፣ በአጠቃላይ በአገር ዕሴት ላይ ተመሠረተ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ለሰው ክብር በመስጠት እና የሰውነትን ዋጋ በመረዳት አንጻር ጥያቄ የሚነሣበት ማንነት አልነበረም። ካለፉት አርባ ዐመታት ጀምሮ እየተከተልነው ያለነው የዘውግ ፖለቲካ ግን ሰውን በሰውነቱ ሳይሆን በንኡስ ማንነቱ የሚለካ ሆነ። በዚህም ምክንያት ዘውግ ተኮር የፖለቲካ አራማጆች እና ጭፍሮቻቸው ከእነርሱ ጎሣና ቋንቋ ውጭ ያለውን በሙሉ እንደ ሰው የማይቆጥሩ፤ ጉዳታቸውና ሞታቸውም የማይገዳቸው ሆኑ። እንዲህ ያለው አመለካከት ሰብእናን የሚያዋርድ ከመሆኑ በተጨማሪ አገርን የሚያጠፋና አደገኛ ከመሆኑም በላይ ማቆሚያ ለሌለው ቂምና እልቂት የሚዳርግ ነው። አንድ ሰው ቋንቋ ከመቻሉ በፊት፣ የእገሌ ዘውግ ነኝ ከማለቱ በፊት ሰው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

በዚህ ምድር ላይ ያሉት ፍልስፍናዎች ሁሉ በኦርቶዶክሳዊው የነገረ ሰብእ ዕሳቤ ሊቃኙ እና ሊጠመቁ ይገባል የምንለውም ፍልስፍናው ጎደሎ በመሆኑ ነው። ኦርቶዶክሳውያንም ለዚህም አስተምህሮ ቅርብና ተገዢ መሆን አለብን። ከኦርቶዶክሳዊው የነገረ ሰብእ አስተምህሮ መራቅ እና መውጣት በአገራችን ብሎም በዐለም ላይ እያመጣ ያለውን ቀውስ እየተመለከትነው ነው። ሰውን መግደል፣ የሰው ነፍስ ማጥፋት ዶሮ የማረድ ያህል ቀላል ተደርጎ መታየት የጀመረው የሰው አመለካከት በመብዛቱ ነው። የግፍ አገዳደል በየዕለቱ የምንሰማው መደበኛ ዜና ከሆነ ሰነባበተ። የሰው ክቡርነታ እና የተፈላላጊ ጾታዎች በጋብቻ መዋሐድ ግንዛቤ በመንሸዋረሩም ግብረ ሰዶማዊነት ሕጋዊ እየሆነ መጥቷል። ጾታን መቀየር የዘመናዊነትና የሥልጣኔ መገለጫ ተደርጎ ተቆጥሯል። ሰዎች በመረጡት መንገድ በመሔድ ሰላም ለማግኘት ይጥራሉ። ይህን ሁሉ እያደረጉም ግን ሰላም ማግኘት አልቻሉም። ምክንያቱ ደግሞ ሰላም የሚገኘው ለሕሊና የሚስማማ ተግባር በመፈጸም እንጂ ከሥነ ፍጥረት ሕግ ውጪ በመሆን አይደለም። ሰው የሚያደርገው ነገር ትክክል ስለመሆን አለመሆኑ ለማወቅ መምህር አያስፈልገውም፤ የራሱ ሕሊና ያውቀዋል።

የአሕዛብ መምህር የተባለው ቅዱስ ጳውሎስ ሕግ ያላቸው በሕግ፣ ሕግ የሌላቸው ደግሞ በልቡናቸው ሕግ እንደሚፈረድባቸው እንዲህ ተናግሯል። “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፣ ሕግ ባይኖራቸው አንኳን ለራሻቸ ኽግ ናቸው። እነርሱ ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፣ አሳባቸውም እርስ በእርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ” (ሮሜ ፪፡፲፬-፲፭)። ክፉን በሚያደርግ ሰው መከራና ጭንቀት ሆንበታል እንደሚል ሰዎች የሚያደርጉት ከንቱ ተግባር ዕረፍት ይነሣቸዋል። ለዚህም ነው በተለይም በምዕራቡ ዐለም ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ የሚያሻቅበው። ከሰዎች መሸሸግና መራቅ ይቻል ይሆናል። ከሕሊና ግን ወዴትም መሸሽ አይቻልም። የሕሊና ወቀሳን የሰሙት ወደ ልቡናቸው ይመለሳሉ። ለመስማት ያልፈለጉ ደግሞ ራሳቸውን እስከወዲያኛው በማጥፋት ከወቀሳ መዳን እንደሚቻል በማሰብ ራሳቸውን ያጠፋሉ። ራሳቸውን ለማጥፋት ካነሣሣቸው ድርጊት ጀምሮ ራሳቸውን እስከ ማጥፋት ድረስ የፈጸሟቸው ተግባራት ሰውነትን በአግባቡ ካለመረዳት፣ የተፈጠሩበትን ዓላማ ካለመገንዘብ የመጡ ናቸው።

ወንድም በወንድሙ ላይ የሚነሣው ከሰው ይልቅ ገንዘብን በማስቀደም፣ ከሕይወት ይልቅ ቁስን በማስበለጥ ነው። እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ኃይሉና በፍጹም አሳቡ እንዲወድ የታዘዘው ሰው፣ ሰውን እንደራሱ እንዲወድም ይህ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው። ወንድም ማለትም በሰውነት የሚመስለንን ሁሉ ማለት ነው። ሰው ሌላውን እንደ ራሱ ሲወድ ሊገድለው፣ ሊሰርቀው፣ በሐሰት ሊመሰክርበት፣ ገንዘቡንና ንብረቱን ሊመኝና ሊቀማ፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ክብር ሊነፍገው አይችልም። ስለሆነም ሰው የተፈጠረበትን ዐላማ ሊገነዘብ፣ የተሰጠውን ክብርና ልዕልና ሊረዳ፣ በራሱም ላይ ሆነ በሌላው ላይ ሥልጣን የሌለው መሆኑን ሊያውቅ፣ ከዚህ እውነት በተቃራኒ የሚነገሩ ፍልስፍናዎች፣ ርእዮተ ዐለማት፣ “ትምህርቶች” እና “አመክንዮዎች” ሁሉ ከንቱ ልፍለፋዎች መሆናቸውን ሊያስተውል ይገባል።

በተግባር ባይመራበትም ዐለሙም ወርቃማ ሕግ በማለት የሚጠራው “በአንተ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን በሌላው ላይ አታድርግ” የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ነው። “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና” (ማቴ. ፯፡፲፪)። ይህን ሕግ ማክበር ቢቻል እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን ከብር መረዳት፣ የእግዚአብሔርን ሕግ ሁሉ መፈጸም ማለት ነበር። በእርግጥ ክርስትና ከዚህም በላይ ነው። “በሰማይ ላላ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ፣ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አደርጉ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ። እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፤ በጻድቃንና በኀጢአተኞች ላይ ዝናቡን ያዘንባልና” (ማቴ. ፭፡፵፬-፵፭) ተብለናል። ፍጹም እንዲሆን የታዘዘ ሰው ቢያንስ ሰው መሆን ሊከብደው አይገባም። ሰው ሕይወቱን ሊመራበት የሚገባው ብቸኛው መንገድም ይህ ነው። ከማስተዋል ጎዳና በመውጣት እንደ ውኃ ሌሎች በመሩት መንገድ መንጎድ ግን መዳረሻው ሞት ነው። ይህ ደግሞ በየዕለቱ ሕይወታችን የምናየው ሐቅ ነው። በዐዲሱ ዐመት ከዚህ የጥፋት፣ የስሕተትና የሞት መንገድ ወጥተን፣ ሕይወት በሚገኝበት የእግዚአብሔር ቃል አሳባችንን እና ልቡናችንን ሁሉ እንድንቃኝ እግዚአብሔር ይርዳን።

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on LinkedIn
  • Share on Telegram
  • Share by Mail
https://eotc-gssu.org/a/wp-content/uploads/anthropology-2.jpg 1080 1920 Abenezer Mamushet https://eotc-gssu.org/a/wp-content/uploads/logo-2-1-300x74-1.png Abenezer Mamushet2023-10-23 20:43:302023-10-23 20:43:30ከወርቃማው ሕግ አትንሸራተቱ (የነገረ ሰብእ ትምህርት ጉድለት የወለደው አገራዊ ቀውስ ክፍል ሁለት)
Search Search

Recent Posts

  • የሦስተኛ ክፍል መማሪያ መጻሕፍት ይዘት
  • የኹለተኛ ክፍል መማሪያ መጻሕፍት ይዘት
  • የአንደኛ ክፍል መማሪያ መጻሕፍት ይዘት
  • የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ
  • ሦስተኛ ዙር የ፲፪ ክፍል ምርቃት መርሐ ግብር ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በተገኙበት ተከናወነ።

Archives

  • April 2026
  • September 2025
  • August 2025
  • July 2025
  • June 2025
  • May 2025
  • April 2025
  • October 2024
  • December 2023
  • November 2023
  • October 2023
  • September 2023
  • August 2023
  • July 2023
  • June 2023
  • May 2023
  • February 2023
  • January 2023
  • December 2022
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • July 2022
  • June 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
© Ethiopian Orthodox Church Global Sunday School Union | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
  • Link to Youtube
  • Link to Telegram
  • Link to TikTok
Link to: ብሔር ተኮር ሃይማኖታዊ ስብከት Link to: ብሔር ተኮር ሃይማኖታዊ ስብከት ብሔር ተኮር ሃይማኖታዊ ስብከት Link to: በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ አባቶች Link to: በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ አባቶች በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ አባቶች
Scroll to top Scroll to top Scroll to top