የቋሚ ኮሚቴዎች እና ንዑሳን ኮሚቴዎች የውስጥ አሠራር መመሪያዎች ትግበራ ሂደት ላይ ገለጻ ተሰጠ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ መንበረ ፓትርያርክ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት በመላው ዓለም ለሚገኙ ሰ/ት/ቤቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ዘመኑን በዋጀ ተደራሽነት ወጥነት እና ዘላቂነት ባለው አሠራር ለመምራት እንዲያስችለው የሚያግዝ የቋሚ ኮሚቴዎች፣ የዋና ክፍሎች እና የንዑሳን ኮሚቴዎች የውስጥ አሰራር መመሪያ ረቂቅ ሰነድ መዘጋጀቱን ተከትሎ ትላንት እሁድ የሰነዶቹን የትግበራ ሂደት የሚዳስስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ለሥራ አመራር አባላት መሰጠቱን የአንድነቱ ም/ሰብሳቢ ዲ/ን ስንታየሁ ምስጋናው ገለጹ።

አንድነቱ የመጀመሪያውን ዙር የመሪ ዕቅድ ትግበራ አጠናቆ በአሁኑ ወቅት በሁለተኛው ዙር የመሪ ዕቅድ ትግበራ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ም/ሰብሳቢው በዕቅድ ከተያዙት ተግባራት መካከል የሰ/ት/ቤ/ትን ተቋማዊ ጥንካሬ እና የአፈጻጸም ብቃት ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ በሚጠይቀው ደረጃ ማሳደግ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ ምክትል ሰብሳቢው ገለጻ የቋሚ ኮሚቴዎችን፣ የዋና ክፍሎችን እና የንዑሳን ኮሚቴዎችን የዕለት ተዕለት አፈጻጸም በወጥነት እና በዘላቂነት ለመምራት በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የተዘጋጁት የውስጥ አሠራር መመሪያዎች የሙከራ ትግበራ ሂደት የሰ/ት/ቤት ተቋም ግንባታ ሂደት አካል ሲሆን ዝግጅቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ትግበራ ሲጀመር አንድነቱ ለሰ/ት/ቤቶች ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ተቋማዊ ብቃት ለማጠናከር አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስኬደው መሆኑ ይታመናል። የተዘጋጁት መመሪያዎችም የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ውስጣዊ አሠራር የተቋማዊ አሠራር መገለጫዎች የሆኑትን ወጥነትን፣ ዘላቂነትን እና የማያቋርጥ መሻሻልን ታሳቢ ያደረጉ እንደሆኑ እና በዓለም አቀፍ መልካም ተሞክሮዎች ላይ የተመሠረቱ ዘመናዊ የሥራ አመራር ጥበቦችን ያገናዘቡ እንደሆኑ ምክትል ሰብሳቢው ገልጸዋል።

የመመሪያዎቹ የትግበራ ሂደት የአንድነቱን የመዋቅር አካላት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ ያስገባ እና የተቀናጀ ትግበራ ስልት አሳላጭ መንገዶችን ያካተተ ሲሆን ይህንኑ ሂደት በዋናነት የሚመራ አጋዥ ኃይለ ግብር ግብረኀይል በማካተት በሙያው የካበተ ልምድ ባላቸው የሥራ አመራሩ አባላት እንዲመራ በቋሚ ኮሚቴ ደረጃ የተዋቀረ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። የቋሚ ኮሚቴው ኃላፊ እንደገለጹት ኮሚቴው የመጀመሪያውን የስድስት ወር መሰናዶ ዕቅድ በመንደፍ ሥራውን የጀመረ ሲሆን በቀጣይ ሂደቶችም ከመነሻ የትግበራ ሂደቱ የሚገኙትን ተሞክሮዎች መሠረት በማድረግ እና የአህጉረ ስብከት ሰ/ት/ቤቶች አንድነት መዋቅር አካላትን በማሳተፍ በአህጉረ ስብከት ደረጃ ሥራ ላይ የሚውል ተመሳሳይ የውስጥ አሠራር መመሪያዎችን የማዘጋጀት እቅድ መኖሩ ገልጸዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አያይዘውም በመላው ዓለም የሚገኙ የአህጉረ ስብከት ሰ/ት/ቤቶች አንድነት መዋቅር አካላት ብሎም አጥቢያ ሰ/ት/ቤቶች በዚሁ ዙሪያ በመጪዎቹ ወራት በሚኖረው የትግበራ ሂደት እንዲሳተፉ እና የሚጠበቅባቸውን ግብዓት እንዲሰጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በአንድነቱ የውስጥ አሠራር ማሻሻያዎች ዙሪያ ከተጠናቀቁት ተግባራት መካከል በያዝነው የትምህርት ዘመን መጀመሪያ የተለቀቀው የአንድነቱ ድረ ገጽ መሆኑን የገለጹት ምክትል ሰብሳቢው በቀጣይ ሂደቶችም በርካታ የተቋም ግንባታ ሥራዎች መታቀዳቸውን እና የሰ/ት/ቤቶች ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሚበረታታ መሆኑን አስታውሰዋል።

በትግበራ ሂደቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ ከተነሱት ነጥቦች መካከል ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ወቅት እያጋጠማት ያለውን ውጫዊ ፈተና ሰ/ት/ቤቶች በተሻለ ተቋማዊ አንድነት ላይ ቆመው ለመመከት የተቀናጀ፣ ዘላቂነት እና ወጥነት ያላቸው የውስጥ አሠራርን የሚያቀላጥፉ የተቋም ግንባታ መርሖዎችን መከተል እንደሚገባቸው ተገልጿል።

የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መዋቅር ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መመሪያ በኩል የምትሠራውን ሥራ የበለጠ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ መመሪያ ወጥቶለት ሥራ የገባ መዋቅር ነው፡፡ መዋቅሩም በዋናነት ሁሉም ሰንበት ት/ቤቶች ዘንድ ወጥ የሆነ የአገልግሎት ሥርዓት ከመዘርጋት በተጨማሪ ተተኪው ትውልድ ወጣቱ ከተናጠል አገልግሎት ተናባቢና ተልዕኮ መር አገልግሎት ውስጥ በሁሉም ዓለም ተደራሽ ለማድረግ ታሳቢ በማድረግ የተቋቋመ አደረጃጀት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ኃላፊነት መሠረት ይህ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጀው የውስጥ መመሪያ፣ በአኅጉረ ስብከት፣ በወረዳ ቤተ ክህነትና በአጥቢያ ደረጃ በተመሳሳይ እየተዘጋጀ እንደሚወረድ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡  በግንኙነት ክፍል ቋሚ ኮሚቴ የውጭ ግንኙነት ዋና ክፍል የዜና እና ወቅታዊ መረጃዎች ዝግጅት ንዑስ ክፍል

መንፈሳዊ በዓል ለማክበር በወጡ ኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚደርስ ጥቃትን አጥብቀን እንቃወማለን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል አንዱ የሆነውን የጥምቀት በዓል እና የቃና ዘገሊላ በዓልን በመላ ሃገሪቱ በሚባል ደረጃ በሠላም ለማክበር የተቻለ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ቤተክርስቲያኒቱ እና አማኞቿ በጋራ ላሳዩት ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ስርዓትና ለጸጥታ ኃይሉ ባሳዩት መልካም ትብብር ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።
ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም በየሺ ደበሌ አካባቢ በምትገኘው የወይብላ ማርያም ታቦትን አክብረው በሚጓዙ ካህናት ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና አዛውንት፣ ጎልማሳና ወጣት ምዕመናን ላይ ለጸጥታ ማስከበር ስራ በተሰማራ የጸጥታ አካል ኃይል የተሞላበት ጥቃት ምክንያት የደረሰው ችግር በተደጋጋሚ አንድ አካባቢ ሆነ ተብሎ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የሚፈጽሙ ክርስቲያኖችን ከማወክ አልፎ ለሞት መዳረጉ በቤተክርስቲያናችን ላይ የሚደርሰውን በደል የሚያሳይ ኢ፟-ሰብአዊ እና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት በመሆኑ የሰንበት ት/ ቤቶች አንድነት በጽኑ ይቃወማል።
ተመሳሳይ ድርጊት ባለፈው ዓመትም የተከናወነ በመሆኑ ካለፈው ተመክሮ በመነሳት ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን እና የጸጥታ አካላት ጋር በዓሉ በሰላም ለማክበር ሰፊ ውይይት በማድረግ ሁሉም ድርሻውን ለመወጣት ኃላፊነት ተወስዶ  በዚያ መልኩ እንዲፈጸም ተደርጓል። ነገር ግን ችግሩ በቦታው ዘንድሮም በድጋሚ መፈጠሩ በአጋጣሚ የተፈጠረ ክስተት ሳይሆን የመንግስትን ስልጣን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያጠቁ አካላት ለመኖራቸው ትልቅ ማሳያ በመሆኑ መንግስት አስቸኳይ ማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ፣ እንዲሁም በድርጊቱ በቀጥታ የተሳተፉና ትዕዛዝ በመስጠት ያስፈጸሙ አካላትን በሕግ አግባብ እንዲጠየቁና ውጤቱን ለህዝቡ ይፋ እንዲያደርግ እያሳሰብን፣በዚህ ሂደት ለተፈጠረው ችግር የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን በቀጣይ ሙሉ ሂደቱን እና ቀጣይ ሥራዎችን የምናሳውቅ መሆኑን እንገልጻለን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!
የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት
ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም

የአንደኛ ክፍል ፈተና ተሰጠ

በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተሰጠው የአንደኛ ክፍል የአጋማሽ ዓመት ፈተና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አስታወቀ። ፈተናው እሑድ ፣ ታኅሣሥ 10 ቀን፣ 2014 ዓ/ም የተሰጠ ሲሆን፤ በሀገረ ስብከቱ በሚገኙ እና የአዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ባስጀመሩ ሃያ ሰባት ሰንበት ት/ቤቶች የሚገኙ  አንድ ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት (1,247) ህጻናት ፈተናውን ወስደዋል።

ከነዚህም ሰንበት ት/ቤቶች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ በማስፈተን ቅድሚያውን የወሰዱ ሰንበት ት/ቤቶች የሚከተሉት ናቸው፦

  1. ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤት አንድ መቶ ሃያ አራት (124)  ህጻናት በማስፈተን፣
  2. መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰ/ት/ቤት አንድ መቶ አምስት (105) ህጻናት በማስፈተን፣
  3. የጽርሐ አርያም ደብረ ሲና በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤት ስድሳ ዘጠኝ (69) ህጻናትን በማስፈተን፣

ከዚሁ ጋር በማከልም በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት የትምህርት ክፍለ ጊዜ የሚሰጡት የትምህርት ዓይነቶች መሠረተ ሃይማኖት ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና የልሳነ ግእዝ  መሆናቸውን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አስታውቋል።

 

ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2014ዓ.ም. ጀምሮ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማህበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡ በዚህም መሠረት፡-

  1. የ2014 ዓ.ም. የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ መልእክት አሁን በአገራችን እየታየ ባለው ጦርነት እና የርስበርስ ግጭት ላይ ያተኮረ ሲሆን፡-
  • ጦርነቱ በወንድማማቾች መካከል እየተደረገ ያለና ሀዘኑን የከፋ ያደረገው መሆኑ፣
  • በዚሁ ጦርነትና ግጭት በርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ለሞት ለስደትና ለረሀብ መዳረጋቸው፣
  • በዚህም ምክንያት በአገሪቱ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት አገራዊ ልማት ላይ እያደረሰ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ይህ ጦርነትና ግጭት ተወግዶ በአገሪቱ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ከሁሉም በላይ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ይቅርታ ምሕረት መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን የሚያስገነዝብ በመሆኑ ጉባኤው ይህንኑ መልእክት ተቀብሎ በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል፡፡
  1. በአገራችን በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሰላም እጦትና ጦርነት ወደፊትም ሊያስከትል የሚችለው ችግር ከፍተኛ መሆኑ ስለታመነበት በተቻለ አቅም ዜጐች ሁሉ ለአገራዊው አንድነትና ሰላም መገኘት ዘብ እንዲቆሙ የየበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
  2. በዚሁ አገራዊ የሰላም እጦት እየተደረገ ያለውን ጦርነት ምክንያት አድርገው ከአገር ውጭ የሚገኙ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትና ካህናት አገራዊ ሰላም ላይ ጥላ በሚያጠላ አገራዊና ሕዝባዊ አንድነትን በሚያፈርስ መልኩ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ከቤተ ክርስቲያንና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ነን ከሚሉ በፍጹም የማይጠበቅ ሆኖ አግኝቶታል፡፡
    በመሆኑም በአውስትራልያ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ሁነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እየፈጸሙ ካለው አገራዊና ሕዝባዊ አንድነት ከሚያደፈርስ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ እያሳሰበ አሁንም ወደ ሰላሙና አንድነቱ እንዲመለሱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ይህንንም የሰላም ተልዕኮ የሚያስፈጽም በውጭው ዓለም የሚገኙ ብፁዓን አባቶች የሚመሩት የጋራ የሰላም ልዑክ እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
  3. በአገራችን በኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉና በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግር ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ዕርዳታ እንዲሆን ብር 50,000,000.00 (ሃምሳ ሚሊየን ብር) በቤተ ክርስቲያናችን ስም ችግሩ ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
  4. የአገራችንን ቀጣይ የዕድገት ደረጃ በእጅጉ ከፍ ያደርጋል የሕዝቦችን አኗኗር በመቀየር ከድኀነት ያወጣል በሚል ታስቦበት ከዓመታት በፊት ግንባታው የተጀመረው የሕዳሴ ግድብ እየተጠናቀቀ ያለበት ምዕራፍ ላይ መድረሱና 2ኛ ሙሌት መከናወኑ ለአገራችን ለኢትዮጵያ ትልቅ የድል ምዕራፍ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ አድንቋል፡፡ በቀጣይም ለመጨረሻው የድል ምዕራፍ ለመድረስ መላው ኢትዮጵያውያን በጉልበት በገንዘባቸውም በሐሳብም ጭምር ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል፡፡
  5. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ መንፈሳውያን ኮሌጆችን አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ ጋር ለማመጣጠንና ተጨማሪ ኮሌጆች በማስፈለጉ በደቡብ ክልል የሚገኙ ሁለት ካህናት ማሠልናዎች ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲያድጉ አስፈላጊውም በጀት እንዲመደብላቸው ጉባኤው ወስኗል፡፡
  6. ለመንበረ ፓትርያርክና ለየአህጉረ ስብከት የሚያገለግል የ2014ዓ.ም. ዓመታዊ በጀት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተደልድሎ በቀረበው መሠረት ዝርዝሩን ተመልክቶ በጀቱ እንዲፀድቅ በማድረግ በሥራ ላይ እንዲውል ጉባኤው ወስኗል፡፡
  7. የ4ዐኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫ ላይ የተነጋገረው ጉባኤ በመግለጫው ላይ በመወያየት አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማድረግ እና በማጽደቅ የ2014ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ መመሪያ እንዲሆን ጉባኤው ወስኗል፡፡
  8. በአገራችን በኢትዮጵያ የተደረገው 6ኛ አገራዊ ምርጫ ነጻና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መከናወኑና በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመመረጣቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተሰማውን ደስታ እየገለጸ፤ ቀጣዩ አገራዊ ሥራቸውም ለአገርና ለወገን የሚጠቅም የተሳካ የአመራር ዘመን እንዲሆንላቸው በሥራቸውም እግዚአብሔር አብሮአቸው እንዲሆን ቤተ ክርስቲያን ትፀልያለች፡፡
    በአጠቃላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በጉባኤ በሰነበተባቸው ቀናት ስለ አብነት ት/ቤቶች እና ስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ስለ ሰንበት ት/ቤቶች መጠናከር ስለ አገራዊ ሰላምና አንድነት ሰፊ ምክክርና ውይይት ያደረገ ከመሆኑም በላይ በአገራችን በተከሰተው የሰላም እጦት የደረሰው ጦርነት ረሀብና የጤና ማጣት አብቅቶ ሰላም እንዲሰፍን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰባት ቀናት ጸሎት ያደረገ ሲሆን በቀጣይም መላው ካህናትና ምዕመናን ስለ አገራችን ሰላምና አንድነት እንዲጸልዩ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ አሳስቧል፡፡
    በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ ለ8 ቀናት ሲያከናውን የቆየውን የጥቅምቱ 2014 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ዛሬ ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በጸሎት ዘግቷል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለአገራችን ሰላሙን ለመላው ሕዝባችን አንድነቱን ይስጥልን፡፡
ጥቅምት 18 ቀን 2014ዓ.ም.
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

 

የሰ/ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም አጥቢያዎች እንዲተገበር መመሪያ ተላለፈ

በዓለም አቀፍ ሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ በተወሰነው ውሳኔ መሠረት ሁሉም አኅጉረ ስብከት ተዘጋጅቶ የቀረበውን የአንደኛ ክፍል መጻሕፍት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለሁሉም አኅጉረ ስብከቶች ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ደብዳቤ ወጣ።

በዚህም መሠረት ሁሉም አኅጉረ ስብከት እስከ አጥቢያ በማሳወቅና ያልደረሳቸው እንዲደርሳቸው በማድረግ በትኩረት እንዲሠራ መመሪያ ተላልፏል፡፡

መጻሕፍቱን ለማግኘት ይህን ሊንክ ይጠቀሙ : ሥርዓተ ትምህርት

ስለ አተገባበር መልእክት ለመላክ የአንድነቱን የቴሌግራም ቻናል ይጠቀሙ

በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የተዘጋጁት የ1ኛ ክፍል መጻሕፍት ተሰራጩ

ሥርዓተ ትምህርቱ በዋናነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ያሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በትምህርት አሰጣጥ ረገድ አንድ የሚያደርገው የሰንበት ትምህርት ቤቶች መማርያ እና ማስተማሪያ ሥርዓተ ትምህርት መጽሐፍ ለአንደኛ ክፍል ተጠናቅቆ ተሰራጨ

የ2014 ዓ.ም መስቀል በዓል የሰ/ት/ቤቶች ዝግጅት ላይ መሆናቸው ተገለጸ

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በደማቁ ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል ዝግጅት ትርኢትና ወረብ ለማቅረብ ከአዲስ አበባ ከሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ቁጥራቸው ከ5500 ባላይ የሆነ ወጣቶች ለተከታታይ 25 ቀናት ዝግጅት አደረጉ . . .

በሀገረ ስብከት ደረጃ የሰ/ት/ቤት ተማሪዎቸ ተመረቁ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት በሙከራ ትግበራ ላይ የሚገኙ ሰ/ት/ቤቶች አባላት መካከል በከተማ ደረጃ ወጥ ፈተና እንዲወስዱ በማድረግ በሀገረ ስብከት ደረጃ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ከ1200 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችንበቀን በ09/01/2014 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ አስመረቀ።