እንኳን ለደብረ ታቦር በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!
ደብር ማለት ተራራ ሲሆን ታቦር ደግሞ የተራራው ስም ነው፡፡ ደብረ ታቦር ከገሊላ ባሕር በስተምዕራብ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን ገልጦበታል፡፡ ይህም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነሐሴ 13 ቀን ዘጠኙን ሐዋርያት ከእግረ ደብር/ከተራራው ግርጌ/ ትቶ ሦስቱን ሐዋርያት (ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን) አስከትሎ ወደ ተራራው ወጣ። በዚያም ለሦስቱ አርዓያው ተለውጦ፣ ፊቱ እንደ ፀሐይ አብርቶ፣ ልብሱ እንደ በረዶ ነጽቶ፣ ሙሴና ኤልያስ በቀኝና በግራው ቁመው ታዩአቸው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስ ‹‹እመሰ ትፈቅድ ንንበር ዝየ ወንግበር ሠልስተ ማኅደረ አሐደ ለከ፣ አሐደ ለሙሴ፣ ወአሐደ ለኤልያስ›› ትርጓሜውም ‹‹በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ፣ አንዱን ለሙሴ፣ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ›› እያለ ሲናገር ወዲያው ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸውና ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድዬ ዘአፈቅር ወሎቱ ስምዕዎ›› ትርጓሜውም ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚል ቃል ሰሙ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም መቆም ተሳናቸው፤ ሙሴ ‹‹ትኄይሰኒ መቃብርየ›› መቃብሬ ትሻለኛለች ብሏል፤ ኤልያስም በሠረገላው ወደየመጡበት ተመልሰዋል፡፡ ሦስቱ ሐዋርያትም ደንግጠው ወድቀው ነበርና ጌታ ዳስሶ በአስነሳቸው ጊዜ ከእርሱ በቀር ሌላ ሰውን አላዩም፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዝዟቸው ከተራራው ወርደዋል፤ (ማቴ 17፥1-9)።
ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ሲሆን ነብያት እና ሐዋርያት በተራራው ላይ መገኘታቸው ቤተ ክርስቲያን የነብያትንም የሐዋርያትንም ትምህርት ይዛ የመገኘቷ፡፡ ሙሴ ከሞት ተነስቶ በተራራው ላይ ተገኘ ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን መጣ፡፡ ይህም በሰማይ ያሉትም ይሁኑ በምድር ያሉት በአንድነት የሚያመሰግኑባት ቦታ እንደሆነች ሲያስተምረን ነው፡፡
ምሥጢረ መንግሥቱን ለምን በታቦር ተራራ ገለጸው?
መድኃኔዓለም ሌሎች ተራሮች እያሉ ክብሩን ለመግለጥ ስለምን ደብረ ታቦርን መረጠ ቢሉ ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡
1/ ትንቢቱን ለመፈጸም
“ታቦርና አርሞንኤም በስምህ አምነው በተደረገላቸው ነገር ደስ ይላቸዋል፣ ስምህን ያመሰግናሉ፣ ለስምህም ምስጋና ያቀርባሉ” እንዲል /መዝ. 88፡12/፡፡
2./ ምሳሌውን ለመፈጸም
ይህ ተራራ ባርቅ ሲሳራን ድል አድርጎበታል /መሳ.4፡6/፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፡፡ “የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደገና ክፉ ሥራ ሠሩ፡፡ እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቡስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ በአሕዛብ አሪሶት የተመረጠው ሲሣራ ነበር፡፡… ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና የእስራኤልንም ልጆች ሃያ ዓመት ያስጨንቃቸው ነበር” /መሳ 4.1-3/፡፡ ሁሌም ቢሆን የሰውን በደል ዐይቶ እንደወጣችሁ ግቡት፣ እንደገባችኋት ውጧት የማይልና “ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” የተባለለት እግዚአብሔር ከዚህ ቀንበር የሚላቀቁበትን መላ ራሱ አመለከታቸው /1ቆሮ. 10-13/፡፡ እስራኤላውያን ወደ ፈጣሪያቸው በጮኹ ጊዜ የለፊዶት ሚስት የሆነችውንና እስራኤልን በነቢይነትና ዳኝነት ታገለግል የነበረችው ነቢይቱን ዲቦራን ተጠቅሞ የማሸነፊያ መላውን አመለከታቸው፡፡ ነቢይቱ ዲቦራ ትንቢት ከመናገር አልፋ የእስራኤልን ንጉሥ ባርቅ ከእኔ ጋር ወደ ጦርነቱ ውጪ ብሎ ባስጨነቃት ጊዜ በጦር አዝማችነትም ተሳተፈች፡፡ እግዚአብሔር በነቢይቱ በዲቦራ በኩል ለእስራኤል ንጉሥ “ሔደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጡ” ብሎ አዞት ነበርና ንጉሡ ዐሥር ሺሕ ብረት ለበስ ያልሆነ እግረኛ ሠራዊት ይዞ ደብረ ታቦርን ተማምኖ በተራራው ላይ መሸገ፤ ጦርነቱም ሳይጀመር አለቀ፡፡ ምክንያቱም “እግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፡፡ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ” /መሳ. 4.15/፡፡ እስራኤል በእግዚአብሔር አጋዥነት በታቦር ተራራ ላይ የሃያ ዓመት የግፍና የሰቀቀን አገዛዝ ቀንበራቸውን ከትከሻቸው አሽቀንጥረው በምትኩ የድል ካባን ደረቡ፡፡ “በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩ” ተብሎም ጀግንነታቸው ተጻፈላቸው፡፡ የታቦር ተራራ ያኔ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ባለውለታቸው ነበር /ዕብ. 11.32-34/፡፡
ጌታም በልበ ሐዋርያት ያለ ሰይጣንን ድል ያደርጎበታልና ማለትም በልባቸው ጥርጥርን እና ፍቅረ ሢመትን (የሥልጣን ፍቅር) ያሳደረ ዲያብሎስን ድል ነስቶላቸዋል ፡፡ ከዚህም በመነሣት ነው “በዓለ ደብረታቦር የደቀመዛሙርት ተማሪዎች በዓል ነው” የሚባለው ፡፡
ኤልያስና ሙሴን ለምን አመጣቸው?
1/. በአንድ ወቅት ሙሴ እግዚአብሔርን ፡- “በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴ እውነት ከሆነስ ፊት ለፊት ተገልጸህልኝ ልይህና በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴን ልወቀው” ሲል ጠይቆት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም “ጀርባዬን ታያለህ ፊቴን ግን አታይም” ብሎት ነበር /ዘጸ. 33.13፣23/፡፡ የዚህ ኃይለ ቃል ትርጓሜና ሐተታ በደብረ ታቦር ተፈጽሟል፡፡ እንዲህ ማለቱ “አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ሰው ሆኜ ሥጋ ለብሼ ኋላ በደብረ ታቦር እስክገለጽልህ ድረስ አንተ በመቃብር ተወስነህ ትኖራለህ” ማለቱ ነበርና፡፡ ይህን ማለቱ እንደሆነ የታወቀው ግን በደብረ ታቦር ሙሴን ከብሔረ ሙታን አምጥቶ ባቆመው ጊዜ ነበር፡፡
2/ ልዑል እግዚአብሔር ነቢዩ ኤልያስን፡- “አንተ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትሆነኛለህ” ብሎት ነበር፡፡ ይኸውም ኃይለ ቃል ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ “የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ነው ይልሃል? እግዚአ ኤልያስ፤ አምላከ ኤልያስ ይበሉህ እንጂ” ሲል በደብረ ታቦር ተፈጸመ፡፡ ታያለህ የተባለው ሙሴም አየ፣ ትመሰክራለህ የተባለው ኤልያስም መሰከረ፡፡
3/ በፊልጶስ ቂሳርያ ጌታ ሐዋርያትን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?” ብሎ በጠየቃቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ሙሴ ነው ይሉሃል ፤ እንዲሁም የኃይል ሥራህን ተመልክተው ኤልያስ ነው ይሉሃል” ብለው ነበርና ሙሴን ከመቃብር ፤ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ እግዚአ ሙሴ ፤ አምላከ ሙሴ ፤ እግዚአ ኤልያስ ፤ አምላከ ኤልያስ መሆኑን ለማስመስከር፡፡
4/ አይሁድ ፈሪሳውያን ጌታን እንደ ሕግ ተላላፊና የእግዚአብሔርን ክብር ለራሱ የሚወስድ አድርገው ያስቡት ስለነበረ /ዮሐ.9፡16፣ 10፡33/ ሕግን የሰጣቸው ሙሴንና ለሕገ እግዚአብሔር ቀናተኛ የነበረው ኤልያስን አምጥቶ ሕግ አፍራሽ አለመሆኑን የእግዚአብሔር ተቃዋሚም አለመሆኑን ለማስረገጥ፡፡
5/ ጌታችን በሙታንና በሕያዋን ላይ ሥልጣን ያለው እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ ሞተው ከተቀበሩት ሙሴን ከብሔረ ሕያዋንም ደግሞ አልያስን አምጥቶ ሲነጋገር ታየ፡፡
6/ የሐዋርያቱን የወደፊት አገልግሎት ሲነግራቸው፡፡ ይኸውም ሙሴ እና ኤልያስ ለሕዝበ እስራኤል በጣም ታማኝ እንደነበሩ ሁሉ እነርሱም ለሚያገለግሉት ሕዝብ ታማኝ እረኞች እንዲሆኑ፡፡ ሆኖም ግን አገልግሎታቸው ከሙሴና ከኤልያስ ይልቅ ጠንከር እንደሚልም አሳይቶአቸዋል፡፡ ምክንያቱም ውጊያቸው እንደ ሙሴ ከፎርዖን እንደ ኤልያስም ከአክዓብ ጋር ሳይሆን ከክፋት መናፍስት ጋር ነውና፡፡
# የበዓሉ መጠሪያ ስሞች (ደብረ ታቦር / ቡሄ/ ቡሔ መባሉ ስለምንድ ነው ?
• ደብረ ታቦር የተባለው ጌታ ክብሩን የገለጠበት ስፍራ ደብረ ታቦር ስለሆነ በዚሁ በዓሉ ስያሜውን አግኝቷል፡፡
• ቡሔ ይባላል ፡- ቡሄ ብርሃን ማለት ነው በደብረታቦር ቧ ብሎ የተገለጠውን የጌታችንን የፊቱን ብርሃን ጸዳል፤ የልብሱንም እንደ ነጭ በረዶ ጸዓዳ መሆን ያስረዳል፡፡
አንድም፡- ቡሔ ማለት መላጣ (ገላጣ) ማለት ነው፡፡ ይኸውም በበዓሉ ዋዜማ ልጆች ‹‹ ቡሔ በሉ፤ ቡሔ መጣ ፣ ያ መላጣ፣ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ›› ይላሉ እዚህ ላይ ቡሄ ያለው ዳቦውን ነው፡፡
• አንድም፡- ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለምሌሊት›› እንደሚባል ወቅቱ በሃገራችን የጸዓተ ክረምት ዋዜማ ስለሆነ የክረምቱ አፈናው ተወግዶ /ተጋምሶ/ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት ፤ በዶፉና በጎርፉ ተሸፍና የነበረች መሬት የምትገለጥበት በመሆኑ ነው፡፡
• አንድም፡- ቡሔ (ቡሔእየ) ተብሎ ይተረጎማል ይኸውም የደብረታቦር እለት እርሾ ሳይገባበት ተቦክቶ የሚጋገረውን ኅብስት ያሳያል፡፡
# “ችቦ የመብራቱ ፣ የሙልሙል ዳቦ የመጋገሩና የጅራፍ ማጮኽ ምክንያት፡-
ችቦ የሚበራው 12 ለ13 ዋዜማ ሌሊት በ3 ሰዓት ነው ።
• የጌታችን ክብሩ በተገለጠበት ጊዜ ብርሃኑ የሌሊቱን ጨለማ ገፍቶት እስከ አርሞንዔም ደርሶ ነበርና በዚያ አካባቢ የነበሩ እረኞች በሁኔታው ተገርመው ቀንም መስሎኣቸው ሌሊቱም ተዘንግቷቸው በዚያው ቆይተው ነበርና ቤተሰዎቻቸው ምን አግኝቷቸው ይሆን በማለት መብራት አብርተው (ችቦ ይዘው)፣ የሚመገቡትን ይዘው ወገኖቻቸውን ፍለጋ ወጥተዋል እረኞችም ያሉበትን ቦታ ለቤተሰዎቻቸው ጅራፍን በማጮኸ አመልክተዋቸዋልና ይህን ለማሰብ ነው፡፡
• ዋናው ምሥጢሩ ግን፡- የችቦው ብርሃን የጌታ ክብር መገለጡን፣ የጅራፋ ጩኸት ሓዋርያትን ያስደነገጣቸው የአብ የምስክርነቱ ቃል ምሳሌ ሲሆን፣ ኅብስቱ ጌታችን በመስቀል ላይ መሥዋዕት የመሆኑ (የሥጋወደሙ) ምሳሌ ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር