“ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ።” ዳን 10፡13

እንኳን ለተራዳኢው መልአክ ለቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ መታሰቢያ በሰላም አደረሳችሁ!
#ሚካኤል ማለት መኑ ከመ አምላክ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማነው የሚል ትርጉም አለው። ይህም እንደ እግዚአብሔር ያለ በባሕርይው ቅዱስ የሆነ ፣ እንደ እግዚአብሔር ያለ ንጹሐ ባሕርይ ፣ እንደ እግዚአብሔር ያለ ፍጹም ማነው የሚል ነው። ቅድስና ፣ ንጽሕና እና ፍጹምነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ከእግዚአብሔር በቀር የለምና። ዘዳ 33፡26
ሰኔ 12 በዚህች ቀን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በዓለ ሲመቱ ይታሰባል። እንዲሁም የባህራንን የሞቱን ደብዳቤ ወደ ሕይወት የቀየረበት እንዲሁም ቅድስት አፎምያን ከሰይጣን ያዳነበት መታሰቢያ ነው። “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ።” ዘጸ 23፡20 ይህ መልአክ በብሉይ እስራኤል ዘሥጋን ከግብጽ ባርነት መርቶ ነጻ እንዳወጣቸውና ምድረ ርስት ከንዐንን እንዲወርሱ በመንገዳቸው ሁሉ እንደረዳቸው፤ እንደጠበቃቸው ሁሉ ባሕራንም ይሄድ ከነበረበት የሞት መንገድ ሕይወትን ሰጥቶ ፤ አፎምያን ደግሞ ከጥንተ ጠላታችን ከዲያብሎስ እጅ በተራዳኢነቱ አድኖ ለክብር አብቅቷቸዋል።
በባሕራን እና በቅድስት አፎሚያ ታሪክ ውስጥ የምናገኘው የመልአኩ ተራዳኢነት ዛሬ ላይ ላለነው ለክርስቲያኖች በሕይወታችን ውስጥ የመልአኩን ተራዳኢነት አምነን እንድንጠቀም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ቅዱስ ሚካኤል ወይም ቅዱሳን መላእክት በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ መዳን መንግሥተ ሰማይን ለመውረስ በሚደረጉ ሒደቶች ሁሉ የሚራዱና የሚያግዙ ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ላይ “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስ አይደሉምን?” ብሏል። ዕብ 1፡14 ዛሬም እኛ ከቅዱሳን መናፍስት ወገን አንዱና አለቃቸው የሆነ ቅዱስ ሚካኤል መዳን መንግሥተ ሰማይን እንወርስ ዘንድ የሚላክ የሚያገለግል አይደለምን እንላለን። ማመን መጠመቅ በጎ ሥራ መሥራት ሕጉን ትዕዛዙን መጠበቅ ንስሐ መግባት እነዚህ በሙሉ ወደ መዳን / መንግሥተ ሰማያት / የሚያደርሱን መንገዶች ናቸው ፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል
ለሰዎች የሚራራ ፣ በተጨነቁም ጊዜ የሚያረጋጋ ፣ በደከሙ ጊዜ የሚያበረታ ፣ ባዘኑ ጊዜ የሚያጽናና ነው። ሉቃ 22፡43 ፣ ዳን 10፡20
የሰው ልጆችን ከመከራ ሥጋ እና ከመከራ ነፍስ የሚያድን የሚታደግ ነው። መዝ 33፡7 ፣ ዘፍ 48፡16 ፣ ዕብ 1፡14
ሰውን ከሚገጥመው ክፉ ነገር ሁሉ ይራዳል። ዳን 10፡13 ፣ ዳን 12፡1
ስለ ሰዎች ይማልዳል ከአምላካቸው ያስታርቃል። ዘካ 1፡12-13
ለሰው ሁሉ በጎን የሚያደርግ መልአክ ነው። ሔኖክ 6፡1-2
የከበረ መልአክ ነው። ከክብሩ የተነሳም ምድር ሁሉ ትበራለች። ራእ 10፡1 ፣ ራእ 18፡1
ትሕትናን የሚያስተምር ትሑት መምህረ ትሕትና ነው። ይሁ 1፡9
በሰዎች ድኅነት ሀሴት ደስታን የሚያደርግ ነው። ሉቃ 15፡7
የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነቱ አማላጅነቱ በዚህም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም ይጠብቀን።
ይቆየን!
መልካም በዓል!

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ በ14ኛው ዓለም አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ላይ ያስተላለፉት መልእክት

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ በ14ኛው ዓለም አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ላይ ያስተላለፉት መልእክት

“ወይረድአነ ለነ ድካመነ በመንፈስ ቅዱስ – ድካማችንን በመንፈስ ቅዱስ ያግዛል፡፡ ሮሜ 8፡26

ከሁሉ በማስቀደም አምላካች ቅዱስ እግዚአብሔር እንደ ሐዋርያት በተስፋ ለምንጠብቀውና ኃይል መንፈሳዊም አግኝተን ለበለጠ ሥራ ለምንነሳበት ለበዓለ ጰራቅሊጦስ፣ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን እና ለ14ኛው ዓለም ዐቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ፡፡ እንኳን ደህና መጣችሁ።

መንፈስ ቅዱስ የደከሙትን የሚያበረታ ያዘኑትን የሚያጽናና የታወኩትን የሚያረጋጋ ኃጢአተኞችን የሚያነጻ መንፈስ ነውና በደከምን ጊዜ ብርታትን፣ በመከራ ጊዜ ጽናትን፣ በፍርሐት ጊዜ ጥብአትን፣ በሁከት ጊዜ መረጋጋትን ይሰጠናል፡፡
በዘመነ ሐዋርያት የነበረው አገልግሎት በሰይፍና በስለት ውስጥ አልፎ የጠፉትን መፈለግ፣ በሞት ተወራርዶ በጎችን፣ ጠቦቶችንና ግልገሎችን መጠበቅን የሚጠይቅ ነበርና የሚያደክሙና የሚያፍገመግሙ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች በርካቶች ቢሆኑም ሲፍገመገሙ ያጸናቸው በድካማቸውም ሁሉ ያገዛቸው የብርታታቸውና የጽናታቸው ምክንያት መንፈስ ቅዱስ ነውና “ወይረድአነ ለነ ድካመነ በመንፈስ ቅዱስ-ድካማችንን በመንፈስ ቅዱስ ያግዛል” በማለት ሐዋርያው ተናገረ፡፡
ይህ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን የሆነው በዓለ ጰራቅሊጦስ በ፭ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን ተብሎ ከተሰየመ እነሆ ዛሬ ፲፬ኛ ዓመት ላይ እንገኛለን፡፡ ባለፉት 14 ዓመታት መንፈስ ቅዱስ ድካማችንን እያገዘ ብዙ መልካም ሥራዎችን ለማከናወን በመቻላችን የጅማሬም የፍጻሜም ባለቤት የሆነውን ልዑል እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡
ዕለተ ጰራቅሊጦስ ሐዋርያት በአንድ ሐሳብ በአንዲትም ልብ ሆነው በተሰበሰቡባት ጽርሐ ጽዮን መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሁሉም የራሱን ቋንቋ በሚሰማበት ልሳን እንዲያስተምሩ የተለያዩ ልሳኖች ለሐዋርያት የተገለጡባት፣ ፍርሐት ጠፍቶላቸው ጥብአትን ገንዘብ ያደረጉባት ዕለት ናት።

ይህችን ዕለት መነሻ በማድረግ በየዓመቱ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን የሚያከብረው የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያም እንደ ሐዋርያት አንድ ልብ በመሆን ከመምሪያው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጋር የሊቃውንት ጉባኤ አባላትን፣ የመንፈሳዊ ዩንቨርስቲና የኮሌጆች መምህራንን እንዲሁም የሥርዓተ ትምህርት ባለሙያዎችን በማሳተፍ በተዘጋጀው ወጥ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ሁሉም እንደ እድሜው ደረጃ ሊረዳው በሚችለው ልክና አቅም በተለያዩ ልሳናት መጻሕፍትን በማዘጋጀት ስያሜውን በተግባር በማሳየት ላይ ይገኛል።
ይህም ውጤት ከዚህ ቀደምም በተግባር የታየና ዛሬም በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ታትመው ለምረቃ በተዘጋጁት መጻሕፍት የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ ወደ ፊትም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቋንቋዎች መጻሕፍቱን ለማሳተም በዝግጅት ላይ ነን፡፡

ይህ ሁሉ ዘመን ተሸጋሪ የሆነና በዘላቂነት ትውልድን የሚታደግ ሥራ የተሠራውና እየተሠራም ያለው “ወሀሎ ምስሌሆሙ ኅቡረ መንፈስ ቅዱስ” መንፈስ ቅዱስ በጉባኤያቸው ሁሉ አብሯቸው ነበር እንዲል መጽሐፈ ምስጢር በሥራችን ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ስላልተለየን በድካማችንም ስላገዘን ነው።
ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ በሁሉም ቋንቋ ባስተማሩት ትምህርት ብዙ ነፍሳትን ማርከው “ምንተ ንግበር አኃዊነ” እንዳሰኙ ሁሉ በእነዚህ ፲፬ ዓመታት በተለይም ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በትኩረት በተሠራው ሥራ እና በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰንበት ት/ቤት አገልግሎት በሰጠው ትኩረትና በፈቀደው በጀት በ2016 ዓ.ም ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል በአማርኛ፣ በዚህ ዓመት በ2017 ዓ.ም ከ5ኛ እስከ 7ኛ ክፍል በአማርኛ እና ከ1ኛ እስከ 4ኛ በአፋን ኦሮሞ የሰንበት ት/ቤት መማሪያ መጻሕፍት በመታተማቸው ያለቋንቋ ገደብ ወጣቶችንና ሕጻናትን በማስተማር ግልገሎችንና ጠቦቶችን የመጠበቅ የመምሪያውን ተልእኮ ለማስፈጸም ትልቅ በር ተከፍቷል፡፡ በሥርዓተ ትምህርቱም ቤተ ክርስቲያናቸውን በሚገባ ያወቁና የተረዱ፣ በሥነ ምግባርም አርዓያ፣ “ምንተ ንግበር” በማለትም የቤተ ክርስቲያን ተስፋ የሚሆኑ ወጣቶችን ለማፍራት የተሻለ ዕድል ተገኝቷል፡፡

ወደፊትም በቤተ ክርስቲያናችን በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድና በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ በጸደቀው የ5ዓመት ሥልታዊ ዕቅድ እየተመራን የበለጠ ለመሥራት የምንጥር መሆናችንን እየገለጽኩ እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ልዩ ክትትልና የቅዱስነትዎ አባታዊ መመሪያ፣ ጸሎትና ቡራኬ እንዳይለየን በታላቅ ትሕትና እየጠየቅሁ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት የማደራጃ መምሪያው ሠራተኞችና የመምሪያውን ተልዕኮ ለማስፈጸም በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ከተዋቀረው የመምሪያው የሀገር አቀፍ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልጋዮች ጋር በመሆን፣ በመምሪያው ሊቀ ጳጳስ መመሪያ ሰጪነት ታግዘን ከምንጊዜው በተሻለ ውጤታማ ሥራ በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡

በአጠቃላይ በዘንድሮው የጉባኤያችን መሪ ቃል “የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡” ብሎ ሐዋርያው እንደተናገረው የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ሕጻናት መንፈሳዊ ሰይፍ የሆነውን ቃለ እግዚአብሔርን በአግባቡ ታጥቀው ክህደት ጥርጥርና ኑፋቄን ቆርጠው ይጥሉበት ዘንድ በ2017 ዓ.ም ዕቅዳችን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተነው የነበረው የሰንበት ት/ቤት መማሪያ መጻሕፍትን ቀጣይ ኅትመት የማከናወን ተግባር ተሳክቶ በዕቅዳችን መሠረት ከ5ኛ እስከ 7ኛ ክፍል በአማርኛ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል በአፋን ኦሮሞ ማሳተም በመቻላችን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡

በሚቀጥለው በ2018 በጀት ዓመት እግዚአብሔር ቢፈቅድ ቀሪዎቹ ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ መጻሕፍት የአርትዖት ሥራን በልዩ ትኩረት በማጠናቀቅ ለማሳተምና በተመሳሳይ በአፋን ኦሮሞም ቀጣይ የትርጉም፣ አርትዖትና የኅትመት ሥራን ለመሥራት ከወዲሁ ዝግጅት ጀምረናል፡፡

በመጨረሻም በ10 ዓመቱ የቤተ ክርስቲያናችን መሪ ዕቅድ መሠረት የተዘጋጀውን የ5 ዓመቱ ስልታዊ ዕቅድ አግባቡ በለመተግበር እንችል ዘንድ በእነዚህ ሁለት ቀናት በሚኖረን የምክክር መድረክ በዓለ ጰራቅሊጦስንና ዓመታዊ የሰንበት ት/ቤቶችን ቀን እያከበርን በቀጣይ ሥራዎቻችን ዙሪያ በትኩረት ተመካክረን የሚጠብቀንን ሰፊ አገልግሎት ባገናዘበ መልኩ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሚጠቅም፣ የወጣቱንም ሕይወት የሚታደግ ምክክር እንድናደርግ በትሕትና አሳስባለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወ/ትንሣኤ
የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ

ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት)

 

የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!

Youtube
https://www.youtube.com/@eotc-gssu

Facebook
https://www.facebook.com/gssu.eotc

Telegram
https://t.me/eotcgssu21

Tiktok

@eotc_gssu

የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ፲፬ኛው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ የቃለ ጉባኤ ማጠቃለያ እና የጋራ የውሳኔ ሐሳብ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ፲፬ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ግንቦት 30 እና ሰኔ 1/ 2017 ዓ/ም ከየአህጉረ ስብከቱ የተወከሉ የሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አባላት፣ የዐዲስ አበባ ሀ/ስብከት አጥቢያ ሰ/ት/ቤቶች አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተካሔዷል። በመሆኑም በጉባኤው ከቀረቡ ዓመታዊ ሪፖርቶች፣ ተዘጋጅተው ከቀረቡ ጥናታዊ ሰነዶች፣ ከየአህጉረ ስብከት ከቀረቡ አስተያየቶች እና ከጉባኤው ተሳታፊዎች ከተነሡ የውይይት ሐሳቦች ግብዓት በመነሣት ባለ 12 ነጥብ የቃለ ጉባኤ ማጠቃለያ እና የጋራ የውሳኔ ሐሳብ በማውጣት ተጠናቋል፡፡

1.በጠቅላላ ጉባኤው የቀረበውን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነትና የአህጉረ ስብከት አንድነቶች የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና የተሰጡ የሥራ አቅጣጫዎችን ጠቅላላ ጉባኤው ተቀብሎ ያጸደቀ ሲሆን የሰንበት ት/ቤቶች የ5 ዓመት መሪ ዕቅድ አፈጻጸም በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ጉባኤው ወስኗል።
2.በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀው መሪ ዕቅድን በተመለከተ በትኩረት የምንከታተለውና የብዙ ምሁራን ጊዜ፣ ዕውቀትና ጉልበት የፈሰሰበት ሥራ ወደ ተፈለገው ውጤት እንዳይመጣ የሚደረገው የማሰናከል ሥራ በእጅጉ ያሳዘነን ከመሆኑም ባሻገር እናት ቤተ ክርስቲያናችን ዘመኑን የዋጀ ስልታዊ አካሔድ እንዳትከተል አሉታዊ ተጽዕኖ እና ከፍተኛ ሥጋት አሳድሯል። የመሪ ዕቅድ ትግበራውን በተያዘበት አግባብ ማፋጠን፣ የሊቃውንቱ፣ የካህናት የምእመናን የሰ/ት/ቤት አባላትና ባለድርሻ አካላትን ሚና በሕግ ማውጣት ሥራ ላይ ከፍ እንዲል በአጽንዖት እንጠይቃለን።
3.በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በቃለ ዐዋዲ የተደነገገው የምእመናን፣ የካህናትና የሰንበት ት/ቤቶች ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ሊኖራቸው የሚገባ የሰበካ ጉባኤ ሱታፌ በጽኑዕ እንዲተገበር እንዲሁም የሰ/ት/ቤት አባላት በጊዜ በጉልበትና በዕውቀት ከሚሰጡት የጎላ አስተዋጽዖ አንጻር ውክልናችን በቁጥር ከፍ እንዲል አበክረን እንጠይቃለን።
4.ልዩ ልዩ የአስተዳደርና የቀኖና ጥሰት እየተፈጸመ የቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነቷ እንዲሸረሸር የሚደረጉ ድርጊቶችን በጽኑዕ እንቃወማለን። የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና እንዲከበር፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲጸና፣ መለያየት እንዲወገድ ፣በዚህም የተፈጠሩ ልዩነቶች ተቀራርቦ በመነጋገርና የበደለ ክሶ፤ ያጠፋ በቀኖና ታርሞ እንዲስተካከሉ፣ በሀገር ሰላምና አንድነት ላይም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቀደመ ሚናዋን እንድትወጣ እንጠይቃለን።
5.በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው የሀብት ሥርጭት ፍትሐዊነት መጉደል ቤተ ክርስቲያን ከገጠር ወደ ከተማ እየተሰደደች መሆኗ በግልጽ የሚታይ በመሆኑ ለዚህ ችግር ትኩረት በመስጠት የአጥቢያ ዐቢይ ጉባኤን በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገባ እና በተደጋጋሚ እንደሚነሣው የፋይናንስ አስተዳደሩን የተማከለ የሚደረግበት ሥርዓት እንዲዘረጋ እንጠይቃለን።
6. አብዛኛው የቤተ ክርስቲያኗ ሀብት የሚመነጨው አጥቢያ ላይ በመሆኑ አስፈጻሚ አካላት ገንዘብ መልቀምና መጠበቅ ላይ በሀብት ምደባም ይሁን ለአስተዳደር ሥራ ብቻ ትኩረት በማድረጋቸው ሕፃናትን የማሠማራት፣ ወጣቶችንና ምእመናንን የመጠበቅ ሥራው በአብዛኛው ተዘንግቷል፣ ስለዚኽ ይኽ ጉዳይ በአስቸኳይ እንዲስተካከል እንጠይቃለን።
7.የሰንበት ትምህርት ቤቶች መዋቅር የበጀት ዕጥረት ከፍተኛ በመኾኑ፣ ሥርዓተ ትምህርቱን ማስፈጸም፣ የመጽሐፍ ስርጭቱንና ሌሎችንም ዘርፈ ብዙ የሰንበት ትምህርት ቤት ሥራዎች ከፍተኛ እንቅፋት በመፍጠሩ መፍትሔ እንዲሰጠው እንጠይቃለን።
8.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት የጠነከረ የኢኮኖሚ አቅምና ማኅበራዊ መስተጋብር ፈጥረው ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁና ለሀገርም ረብ ያለው ነገር ማበርከት እንዲችሉ የማድረግ ሚናዋን ዘንግታለች፣ ስለዚህም ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በቂ ሀብት በመመደብና ተገቢ አመራር በመስጠት በአባላት ሁለንተናዊ ሕይወት ዙሪያ አስፈላጊ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል ጥረት ይደረግ ዘንድ በአጽንዖት እንጠይቃለን።
9.የሰንበት ት/ቤቶችም ኾነ ሌሎች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን የቅርብ ክትትል የሚፈልግ ኾኖ እያለ ሀገረ ስብከቶቻቸውን በዓመት ለውስን ጊዜያት አንዳንዴም አንዴ ብቻ በሚጎበኙ ሊቃነ ጳጳሳት የተነሣ አገልግሎቶች እየታወኩ ይገኛሉ፤ ስለዚህ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳቱ ሀገረ ስብከቶቻቸውን በተገቢው መልኩ እንዲከታተሉ የሚመለከተው አካል ተገቢ ቁጥጥር እንዲያደርግ በአጽንዖት እንጠይቃለን።
10.የሰንበት ት/ቤቶች ጠቅላላ ጉባኤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነቶች ተወካዮች ተሰባስበው የሚመክሩበት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚወያዩበት ቀጣይ ሥራዎች የሚተልሙበት ጉባኤ ነው። ይኽ ጉባኤ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ከቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ከሌሎች የሥራ ሓላፊዎች ጋር የሚወያዩበትም ጭምር ነው። ይኹን እንጂ ይኽ ጉዳይ በትክክል ተፈጻሚ እየሆነ አይደለም። ስለዚኽ ይኽ ጉባኤ ከዚህ በኋላ የሚካሔዱ ጠቅላላ ጉባኤያት በቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎተ ቡራኬ ተከፍቶ፤ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ ምዕዳን የሚዘጋ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ተገኝተው የሚመሯቸው እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች እና የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ተገኝተው የሰ/ት/ቤቶችን ጉዳይ በሓላፊነት የሚከታተሉባቸው እንዲኾኑ በአጽንዖት እንጠይቃለን።
11.. በዚኸ ጉባኤ ላይ በተለያዩ ምከንያቶች ያልተገኙ የአህጉረ ስብከት ተወካዮች እንዳሉ ቢታወቅም በተለይ ግን በትግራይ ከልል ከሚገኙ አህጉረ ስብከት ጋር በተፈጠረዉ እጅግ አሳዛኝ መለያየት የተነሣ የክልሉ አህጉረ ስብከት ተወካይ ወንድሞች እና እኅቶች ባለመገኘታቸዉ ጉባኤው ከፍተኛ ኀዘን ተሰምቶታል። ከዚህም በላይ ችግሩ ወደ ምእመናን እየሰፋ መሔዱ ጉባኤውን በእጅጉ አሳስቦታል፡፡ በ13ኛው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አበክረን፣ ከወንበራችን በመነሣት በልመናና በልጅነት መንፈስ መፍትሔ እንዲያገኝ ብንጠይቅም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባለማየታችንና ይኸ መለያየት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ሔዶ በአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ አደጋና የማይጠገን ስብራት እያደረሰ በመሆኑ ልዩነቶችን አስወግዶ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አግባብ የክልል ትግራይ አህጉረ ስብከት ወደ መዋቅራቸው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ይመለሱ ዘንድ፤ በእኛ በኩል የተቻለንን ኹሉ እንደምናደርግ ቃል በመግባት አሁንም ችግሩን ለመፍታትና እርቀ ሰላሙን ለማምጣት ከፍተኛዉን ድርሻ ሊወጡ የሚችሉት ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን እንደኾኑ እናምናለን፡፡ ይኽንኑ ለመፈጸም ቅዱስነትዎ ቃል ይገቡልን ዘንድ የቤተ ክርስቲያን ልደት ተብሎ በሚታወቀው በዛሬው በዓለ ጰራቅሊጦስ ስም ልክ እንደ አምናው ኹሉ ከመቀመጫችን በመነሣት በታላቅ አከብሮት እና ትሕትና እንጠይቃለን።
12.እነዚህ የ14ኛው ሀገር ዐቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የጋራ የውሳኔ ሐሳብ በቀጣይ የሲኖዶስ ስብሰባ አጀንዳዎች እንዲሆኑ አበክረን እንጠይቃለን።

ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ/ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በ14ኛው ዓለም አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያስተላለፉት መልእክት

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ። አሜን

እንኳን ለ14ኛው ዓለም አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ እና የሰንበት ት/ቤቶች ቀን አደረሳችሁ

“ተዘከሮ ለፈጣሪከ በመዋዕለ ውርዙትከ ዘእንበለ ይመጻእ መዋዕል እኩይ ወይመጽእ ዓመታተ በእለ ትብል ኢኮነኒ ቦቶን ፈቃድየ፦ የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ።” መክ 12፥1 ጠቢቡ ሰሎሞን ጭንቅ ቀን የመከራ ቀን ሳይመጣ የጉብዝና ወራት በተባለ የወጣትነት ዘመንን ለእግዚአብሔር መስጠት እንዲሚያስፈልግ ያስተምራል፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያን የጉብዝናን ዘመን በቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤት እንዲሆን ታስተምራለች።
ሰንበት ትምህርት ቤት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ ሥፍራ ካላቸው ተቋማት አንዱ ነው። ዘመን ተሻጋሪዋ ቤተ ክርስቲያናችን ቀድማ የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ትውልድን ስብስባ፣ ታላላቅ ሥራዎችን የምትሠራበት፣ ትውልዱን በማስተዋል በእውቀት በሃይማኖት በሥነ ምግባር በልዩ ልዩ ጸጋ የምትቀርጽበት የተወደደ ሥፍራ ሰንበት ት/ቤት ነው፡፡ ከሰንበት ትምህርት ቤት ብዙ ሊቃውንት፣ ብዙ መሪዎች፣ ብዙ መምህራን፣ ብዙ አገልጋዮች፣ ብዙ ባለሙያዎች እና ጠንካራ አማኞች ተገኝተዋል።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆቿ ጽድቅን ይማሩ ዘንድ በሰንበት ት/ቤት አሰባስባ እግዚአብሔርን አውቀው እንዲያመልኩ፣ ሕጉን ጠብቀው፣ በሃይማኖት፣ በምግባርና በትሩፋት ጸንተው አምላካቸውን መስለው እንዲኖሩ፣ የእርሱ የሆነችውን መንግሥተ እግዚአብሔርን እንዲወርሱ በብሉይ ከአምላኳ የተቀበለችውን ሕግጋተ እግዚአብሔርን አስተምራ በሐዲስ ኪዳንም በ40ና በ80 ቀን እያጠመቀች ለምዕመናን እንደ እድሜያቸው ቃለ እግዚአብሔርን በስብከት፣ በዝማሬ፣ በቅዳሴ፣ በሰዓታት፣ በማሕሌት፣ በቅኔ፣ በትርጓሜው እያስተማረች ምዕመናንን በሃይማኖት አንፃ ለመንግሥተ ሰማያት እያዘጋጀች ዛሬ ላይ ደርሳለች።

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና የዚህ ጉባኤ ታዳሚዎች

ሰንበት ት/ቤት ሕጻናት ወጣቶች የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቅኖና፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚማሩበት እና በእምነት፣ በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚያጠነክሩበት ታላቅ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ነው:: በመጽሐፍ ቅዱስ ሰንበት ት/ቤት ተብሎ የተፃፈ ቀጥተኛ የሆነ ስም ባይገኝም ዛሬ ላይ በሰንበት ትምህርት ቤት የሚተገበረው መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ልጆችን በቤተ እግዚአብሔር ማስተማር በብሉይ ኪዳን ዘመንም ይፈጸም እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል። የሰንበት ት/ቤት ፅንሰ ሀሳብም ከዚያ የመነጨ ነው። ኦሪት ዘዳግም 11÷18-21

በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው መካከል ሕፃናት (ወጣቶች) ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጡ ዘንድ ነበር። በዚህም ለሰንበት ትምህርት ቤት መነሻ የሆነ እና መሠረቱም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን ያረጋግጥልናል። (ማቴ 18፥3፣ 21፥16፣ ማር 9፥37)። በዚህ መነሻነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮዎቿ _ ሳይበረዙ _ ለትውልድ እንዲተላለፉ በተለይ በሕጻናት እና በወጣቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ለመሥራት ተሞክሯል።

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና የዚህ ጉባኤ ታዳሚዎች

ይህ የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልዕኮ ቅድሚያ የሚሰጠው ሐዋርያዊ ተግባር ሆኖ ሳለ እነዚህን የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ የሰንበት ት/ቤት ልጆቻችንን በአግባቡ ባለመመልከታችን፣ እንደ አባት ለልጅ የሚደረገውን ባለማድረጋችን፣ የሚገባውን ሥፍራ ሰጥተን ባለመሥራታችን ምክንያት ከበረቱ የተበተኑ፣ ከቤቱ የራቁ፣ ከአገልግሎት የጠፉ፣ ጀመረው ያልጨረሱ፣ ወድቀው ያልተነሱ ያለአስታዋሽ የቀሩ ጥቂት የማይባሉ ናቸው።

በተጨማሪም በዚህ ዘመን መሰማማት፣ መደማመጥ፣ መታዘዝ፣ መከባበር፣ ትህትና እና ፍቅር የጎደለው ቤተሰብን፣ ቤተ ክርስቲያንን፣ ሀገርን፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን እና ሽማግሌዎችን የሚያከብር ትውልድ አጥተናል፡፡ በየዕለቱም ፍቅር ሳይሆን ጥላቻ፣ ርሕራሄ ሳይሆን ጭካኔ፣ መረዳዳት ሳይሆን መገፋፋት፣ ክብር ሳይሆን ማዋረድ፣ ምርቃት ሳይሆን እርግማን፣ ምስጋና ሳይሆን ስድብ እየበዛ ከመሄዱ አንጻር ትውልዱን እያጠፋ ይገኛል።

ስለዚህ ሰንበት ት/ቤት ይህን እና ተመሳሳይ ጉዳዮችን ለመቅረፍ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅሙና አስፈላጊነቱ የጎላ በመሆኑ ከየትኛውም ሥራችን አስቀድመን በዚህ ትውልድ ላይ በትኩረት አስፈላጊውን በጀት በመበጀት በገጠር በከተማ በሙሉ ኃይላችን ነፍሳችን ጭምር ሰጥተን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
እግዚአብሔር ቢፈቅድ እኛ ከእናንተ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጋር ከወጣቱ ጋር ቤተ ክርስቲያንን ከፍ የሚያደርጉ ታላላቅ ሥራዎችን እቅድ አቅደን፣ ተገቢውን ጥናት አጥንተን፣ ተመካከረን፣ … ተወያይተን ሥራዎችን መሥራት ይገባናል፡፡ እንሥራለን እግዚአብሔርም ይረዳናል።

ሰንበት ት/ቤቶች እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ሊቃውንት፣ አገልጋዮች፣ መምህራን እና ጽኑ አማኞች መገኛ እንደመሆኑ መጠን በየአጥቢያው ሰበካ ጉባኤው የአብነት መምህራን በመቅጠር ሰንበት ትምህርት ቤቱን በማጠናከር ትውልዱን በኦርቶዶክሳዊ የሃይማኖት ትምህርት በማነጽ፣ ዶግማን፣ ቀኖናን እና ትውፊትን በማስተማር በየሀገረ ስብከቱ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰንበት ት/ቤቶች እንዲቋቋሙ፣ የተቋቋሙትም እንዲጠናከሩ ማድረግ ያስፈልጋል።

በተጨማሪም የሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎትን የበለጠ ለማጠናከር ሆነ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በመስጠት ወጣቱን ትውልዱ በዘመናዊነት ተፅዕኖ ውስጥ ወድቆ ከመንፈሳዊ ሕይወት እንዳይወጣ ልዩ ክትትል ማድረግ የሰንበት ት/ቤቶች ለተቋቋሙበት ዓላማና ተግባር እንዲንቀሳቀሱ ማገዝ መርዳት እንደሚያስፈልግ መዘንጋት የለብንም፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የዚሁ ጉባኤ ታዳሚዎች

ቤተ ክርስቲያን በባሕርይዋ አንዲት፣ ሐዋርያዊት፣ ቅድስት እና ኩላዊት (ዓለም አቀፋዊት) እንደመሆኗ መጠን ትውልዱ ይህን በተግባር ማየት ይሻል። እውነት ነው ብዙ ያንቀላፋንበት፣ በእውነት በዓላማ ያልተንቀሳቀስንበት፣ ትኩረት ሰጥተን ያልሠራንበት፣ ተግተን ያላገለገልንበት፣ ጊዜ ብዙ ነፍሳት እና ብዙ ትውልድ አሳጥቶናል። ቀላልም የማይባል ዋጋም ጭምር አስከፍሎናል፡፡ ስለሆነም ከየትኛውም ጊዜ በላይ በቤተ ክርስቲያናችን፣ በቤተሰብ፣ በማኅበራዊ፣ በሀገራዊ፣ በአንድነታችን፣ በጠፋው ሰላማችን፣ በቀዘቀዘው ፍቅራችን፣ በደከመው እድገታችን፣ ትጋት በሌለው መንፈሳዊ አገልግሎታችን እና በሃይማኖታችን ጉዳዮች ላይ ይሄ የእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ ነውና በፍቅር፣ በሰላም፣ በአንድነት፣ በመከባበር፣ በመተባበር፣ በትሕትና እና በመናበብ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ በመሆን በተሰጠን ኃላፊነት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብር እና እድገት ልንሠራ ያስፈልጋል።

የሰንበት ት/ቤቶችን አገልግሎት ያስፋልን፡፡

እግዚአብሔርበመንፈሳዊ በረከት ይባርካችሁ።

ተባረኩ ብሩክ ሁኑ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

ግንቦት 3ዐ ቀን 2017 ዓ.ም

አባ ሳዊሮስ

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ሓላፊ

ብፁዕ አቡነ ቀለሜንጦስ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በ14ኛው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ያስተላለፉት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ አሜን።

“ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ-በአንተ ሕልውና ባለ መንፈስ ቄዱስ አንድ እንሆን ዘንድ አንድ መሆንን ስጠን” (ቅዳሴ ሐዋርያት ምዕ ፪ ክፍል ፪፥፴፬)

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የምስራቅ ትግራይ ራያ ሀገረ ስብከትና የማሕበራት ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ፣

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አሀጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣

የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎች፤

እንዲሁም ሰንበት ትምህርት ቤቶቻችሁን ወክላችሁ ከየ ሀገረ ስብከቱ የመጣችሁ የሰንበት ት/ቤ/ቶች ክፍል ሓላፊዎችና የአንድነት አመራሮች

በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተገኛችሁ ውሉደ ቤተ ክርስቲያን በሙሉ፤

“አቀድም አእኵቶቶ ለእግዚአብሔር በእንተ ኵልክሙ እስመ ተሰምዐት ሃይማኖትክሙ ውስተ ኵሉ ዓለም”። መሰብሰባችን፣ ጽንዐ ሃይማኖታችን በዓለም ሁሉ ተሰምቶዋልና  በዚህ ጉባኤ ላይ እንድንገኝ እንድናመሰግነውም የፈቀደልንን ልዑል እግዚአብሔርን ከሁሉ በማስቀደም እናመሰግናለን።

እንኳን ለ፲፬ኛው ዓለም አቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤና በዓለ ጰራቅሊጦስ አደረሳችሁ!! እንኳንም ደህና መጣችሁ ለማለት እወዳለሁ።  በመቀጠልም፦ቅዱሳን ሐዋርያት “ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ በማለት የአንድነታቸው ማኀተም በሆነው መንፈስ ቅዱስ ኀብረታቸው እንዲጸና ለምነዋል የዚህም ታላቅ ጉባኤ ዓላማ ሕብረተ መንፈስ ቅዱስን አጽንቶ ትውልድን በቀናች ሃይማኖት ለማነጽ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የተሰጠንን ኃላፊነት ለመወጣት ነው። እንደሚታወቀው ሕብረት ማለት የእርስ በርስ ግንኙነት ማለት ሲሆን ሕብረት ማድረግ ያስፈለገው አንድ ሰው ብቻውን ምንም ማድረግ ስለማይችል ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎቷ ሁሉን አሳታፊ ነው። ቅ.ዳዊት “ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይሄልዉ አኃው ሕቡረ” ወንድሞች በኅብረት ቢኖሩ መልካም ነው በማለት ኅብረት መልካምና የተወደደ መሆኑን ገልጦልናል። ሕብረታችንን ደግሞ የሚያጸናው ፍቅር ነው ያለ ፍቅር ሕብረት ትርጉም የለውም በሕብረት ውስጥ የፍቅርን የበላይነት ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳን በልሳን ብናገር ትንቢትንም ሁሉ ባውቅ ሥጋዬንም ለእሳት አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ በማለት ግልጹን ነግሮናል።1ኛቆሮ ፲፫፥፪ ቅዱሳን ሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስ የወረደላቸው አብረው ስለተሰበሰቡ ብቻ አይደለም በአንድ ልብ በአንድ ሀሳብ በፍቅር ጸንተው ስለጠበቁት ነው።(ግሐ ፪፥፵፪) የተከበራችሁ የዚህ ታላቅ ጉባኤ ተሳታፊዎች እንዲሁም በመላው ዓለም ያላችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፦ ይህን የሚያክል ታላቅ ሕብረት ፈጥረን በመካከላችን መለያየት ካለ ትርፉ ድካም ብቻ ነው እግዚአብሔርም በመካከላችን አይገኝም። መለያየት ዲያብሎስ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ከሚጠቀምበት  መሣሪያ አንዱ ስለሆነ፤ሀበነ ንሕበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ እያልን በመማጸን ሕብረታችንን እናጽና።

ቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣

ክቡራን የዚህ ታላቅ ጉባኤ እድምተኞች ይህ በየ ዓመቱ በእለተ ጰራቅሊጦስ እየተከናወነ ያለው ጠቅላላ ጉባኤ ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ ፍሬ ያፈራ ጉባኤ ነው፤ ባሳለፍናቸው 3 ዓመታት እንኳን ለረዠም ዓመታት የተደከሙባቸው ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ እና የመማሪያ መጻሕፍት ሕትመት ተግባራዊ ሆኖ ፍሬውን ለማየት በቅተናል፦ በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተጠናክሮ ዘመኑ በፈቀደልን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ተናቦ ለመስራትም ተችሎዋል። ይህም የሆነው የቅዱስ ሲኖዶስ የቅርብ ክትትል ስላልተለየን የቅዱስ አባታችን ጸሎት እረድቶን የመንፈስ ቅዱስ እገዛ ተጨምሮበት ነው። በተጨማሪም፦ ያላቸውን ጥሪው ሸጠው በአንድነት ለመኖር ወስነው የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እንደጎበኛቸው  መቶ ሃያው ቤተሰብ በሀገር አቀፍ ደረጃና በውጭው ዓለም እያገለገሉ ያሉ ልጆቻችን ያላቸውን እውቀት፣ጉልበት፣ገንዘብና ጊዜአቸውን ያለ ምንም ስስት  በማዋጣት እያበረከቱ ያለው የአንድ ልብ አገልግሎትም ውጤት ነው። ለዚህም መንፈሱን ልኮ ዘወትር ከሕብረታችን ያልተለየው እግዚአብሔርን ሳመሰግን በታላቅ ደስታ ነው። ወደ ፊትም ከዚህ የበለጠ ሰፊ ሥራ የሚጠብቀን መሆኑን ለአፍታ እንኳን የምንዘነጋው አይደለም ጀመርን እንጂ አልጨረስንምና።

ቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣

ትውልዱ በጥያቄና በብዙ ፍላጎት የተሞላ ስለሆነ ዘመኑም ውስብስብና አስጨናቂ በመሆኑ በትውልዱ ላይ የተጫነው ዓለም አቀፍ ጫና ያለ እግዚአብሔር ቃል የሚታለፍ ስላልሆነ ከሥራችን ጎን ለጎን ብርቱ ጸሎትና ያላሰለሰ ክትትል ከምን ጊዜውም በላይ ያስፈልገናልና በጸሎታችሁ ይህን ጉባኤ እንድታስቡት እማጸናለሁ። በመጨረሻም የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥሪ አክብራችሁ የትውልዱ ባለ አደራነታችሁን ተረድታችሁ በዚህ ታላቅ ጉባኤ ላይ ከሩቅም ከቅርብም የተገኛችሁ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች እናንተንም የወከላችሁንም ሀገረ ስብከት በታላቅ አክብሮት እናመሰግናለን። በምትቆዩባቸው ጊዜያት ሁሉ ዓለም እንደ ሚያገሳ አንበሳ ዙሪያውን በተለያዩ ርኩሰቶች አድብታ ለምትጠብቃቸው የዚህ ዘመን ትውልድ የሚጠቅም ፍሬአማ ውይይት እንድታደርጉ እያሳሰብኩ መልእክቴን አጠቃልላለሁ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

የሦስት ወር የክረምት ፕሮጀክት ሥራ ማስታወቂያ – የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት

፩. ለሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት የትግሪኛ ትርጉም ባለሙያ
ተፈላጊ ልምድ/ችሎታ
▶️ በሰንበት ት/ቤት እና ግቢ ጉባኤያት ሥራ አስጻሚነት ወይም ክፍል ተጠሪነት ያገለገለ/ለች
▶️ በሰንበት ት/ቤት በማስተማር መምህርነት ልምድ ያለው
▶️ቢያንስ በሰንበት ት/ቤት የሚሰጡ ትምህርቶችን ያጠናቀቀ/ች
▶️በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ የተመረቀ/ች
▶️የኮምፒወተር አጠቃቀም መሠረታዊ ዕውቀት ያለው/ያላት

፪. ለሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት የእንግሊዝኛ ትርጉም ባለሙያ
ተፈላጊ ልምድ/ችሎታ
▶️ በሰንበት ት/ቤት እና ግቢ ጉባኤያት ሥራ አስጻሚነት ወይም ክፍል ተጠሪነት ያገለገለ/ለች
▶️ በሰንበት ት/ቤት በማስተማር መምህርነት ልምድ ያለው
▶️ቢያንስ በሰንበት ት/ቤት የሚሰጡ ትምህርቶችን ያጠናቀቀ/ች
▶️በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ የተመረቀ/ች
▶️የኮምፒወተር አጠቃቀም መሠረታዊ ዕውቀት ያለው/ያላት

፫.  የሥልጠና  አስተባባሪ 

ተፈላጊ ልምድ/ችሎታ
▶️ በሰንበት ት/ቤት እና ግቢ ጉባኤያት ሥራ አስጻሚነት ወይም ክፍል ተጠሪነት ያገለገለ/ለች
▶️ በሰንበት ት/ቤት በማስተማር መምህርነት ልምድ ያለው
▶️ በሰንበት ት/ቤት አሰልጣኝነት ልምድ ያለው/ያላት

▶️በመምህርነትና በአሰልጣኝነት ስልጠና የወሰደ
▶️በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ የተመረቀ/ች
▶️የኮምፒወተር አጠቃቀም መሠረታዊ ዕውቀት ያለው/ያላት

፬.  የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ
ተፈላጊ ልምድ/ችሎታ
▶️በሰንበት ት/ቤት እና በግቢ ጉባኤያት ያገለገለ/ለች
▶️በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ኮምፒዩተር ሳይንስ፣ ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀ/ች

፭.  የግራፊክስ ዲዛይን ባለሙያ
ተፈላጊ ልምድ/ችሎታ
▶️በሰንበት ት/ቤት እና ግቢ ጉባኤያት ያገለገለ/ለች
▶️በሰንበት ት/ቤት ሥነ ጽሑፍና ሥነ ጥበባት፣ መዝሙር፣ ሚዲያ ክፍሎች ያገለገለ/ለች
▶️በዘርፉ ስልጠና የወሰደ እና  ፍላጎት ያለው/ያላት
▶️በዘርፉ ሙያ ወይም ተመሳሳይ የተመረቀ/ች

፮.  የሥዕል ባለሙያ
ተፈላጊ ልምድ/ችሎታ
▶️በሰንበት ት/ቤት እና ግቢ ጉባኤያት ያገለገለ/ለች
▶️በሰንበት ት/ቤት ሥነ ጽሑፍና ሥነ ጥበባት፣ መዝሙር፣ ሚዲያ ክፍሎች ያገለገለ/ለች
▶️በዘርፉ ስልጠና የወሰደ እና  ፍላጎት ያለው/ያላት
▶️በዘርፉ ሙያ ወይም ተመሳሳይ የተመረቀ/ች
▶️ከምፒዩተር ዕውቀት ያለው/ያላት

፯.  ዳታ ኢንኮደር 
ተፈላጊ ልምድ/ችሎታ
▶️በሰንበት ት/ቤት እና ግቢ ጉባኤያት ያገለገለ/ለች
▶️በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተመረቀ/ች

ለኹሉም የሥራ መስኮች፡-

✳️ ጾታ አይለይም፣
✳️የስራ ቦታ:-  አዲስ አበባ፣
✳️የፕሮጀክቱ የቆይታ ጊዜ ከሐምሌ 1/2017 እስከ መስከረም 30/2018

አመልካቾች ሊያሟሉዋቸው የሚገቡ መስፈርቶች፡-
✳️  የሰ/ት/ቤት አባል የሆነ/የሆነች ብቻ፣
✳️ በአባልነት ከተመዘገቡበት አጥቢያ ሰንበት ት/ቤት የአባልነት ማረጋገጫ ማቅረብ ፣

ለመመዝገብ ከዚህ በታች የተቀመጠውን የመመዝገቢያ ቅጽ እስከ ሰኔ 25/2017 ዓ/ም ድረስ  ሞልተው ይላኩ፡፡ 

የክረምት የሦስት ወር ፕሮጀክት ሥራ ማስታወቂያ
Click or drag files to this area to upload. You can upload up to 2 files.

 

ወቅታዊ መልእክት

ግንቦት ፯ ቀን ፳፻፲ወ፯ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት !!
በቅድሚያ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንኳን ለ፳፻፲ወ፯ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ። በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ የሆነ ውይይት እንድታከናውኑ የልጅነት ጸሎታችን ነው።
የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ የሚወያይበትን አጀንዳ ተመልክተነዋል። የተያዘውም አጀንዳ ጠቃሚ እንደሆነ ተረድተናል። ነገር ግን አሁን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ የሚስተዋሉ ቁልፍ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበዋል ብለን አናምንም። ምክንያቱም ከአጥቢያ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ የሚስተዋሉ፤ በቅዱስ ሲኖዶስ በቁርጠኝነት ዘላቂ መፍትሔ ሊበጅላቸው የሚገቡ ዘርፈ ብዙ አስተዳደራዊ እና ተያያዥ ጉዳዮች ለውይይት ሳይቀርቡ ታልፈዋል።
በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተለይተው፣ በማስረጃ ዳብረው እና በመጨረሻም ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲ወ፯ ዓ.ም የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ከበርካታ አህጉረ ስብከት ከተውጣጡ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር አባላት እና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከተውጣጡ የክፍለ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት አመራሮች፣ የገዳማት እና አድባራት ሰንበት ት/ቤት ሊቃነ መናብርት ጋር በአካልና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በመሆኑም በአካልና በቴክኖሎጂ በአመራሮች ውይይት የተደረገባቸው፤ የጋራ አቋም የተያዘባቸው እንዲሁም በቀጥታ የኦርቶዶክሳዊያን ምእመናንና ምእመናት ጥያቄም ጭምር የሆኑትን፤ እኛ የነገይቱ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ወጣቶች በልጅነት አንደበት እንደሚከተለው ለማቅረብ እንወዳለን ።
እነርሱም፦
1. የቤተ ክርስቲያንን ሲኖዶሳዊ ልዕልና እና አንድነትን ማስጠበቅ ፤
ሀ. ታላቂቱ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከትናንቱ ይልቅ ዛሬ ተቋማዊ ህልውናዋ እና ልዕልናዋ አስጊ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገ ቤተ ክርስቲያን እና መዋቅራዊ አሠራርን በመፈተሽ እና በማስጠበቅ የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ፈተና በፍጥነት ሊያስቆም ይገባል፡፡
ለ. በነገረ ሃይማኖት ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ሐሰተኛ ትምህርቶች ቤተ ክርስቲያን የጠራ ትምህርቷን በተገቢው ሁኔታ፣ በሚገባው ዐውድ እና በሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጥባቸው፤
ሐ. ሐሰተኛ ትምህርት ያስተላለፉ ከመምህራን እስከ ሊቃነ ጳጳሳት ያሉ አካላት ላይ ተገቢው ቀኖናዊ ሥራ እንዲሠራ፤
መ. እየተድበሰበሰ ያለው የነገረ ቅብዓት ጉዳይ የማያዳግም እልባት ሊሰጠው ይገባል።
ሠ. በትግራይ ክልል የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ነፍስ ጉዳይ በእጅጉ ያሳስበናል። በክልሉ ከሚገኙ አህጉረ ስብከት አስተዳደራዊ ግንኙነት መቋረጥ እና እስከ አሁንም ይኽ ችግር ተገቢ የኾነ መፍትሔ ባለማግኘቱ፤ መለያየቱ ሥር ሰዶ፤ የጥፋቱ ጉዳት እየጨመረ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ለማይፈልጉ አካላት ሰርግና ምላሽ ሆኖ ነፍሳት በኑፋቄ እየተነጠቁ ይገኛሉ። ከተፈጠረው የአስተዳድር ልዩነት በኋላ የተስተዋሉ የኑፋቄ እና ስልታዊ ጥፋትን አስመልክቶ ያዘጋጀነውን ዝርዝር የማስረጃ ሰነድ ለቋሚ ሲኖዶስና ለቅዱስ ፓትርያርኩ ብናቀርብም ተጨባጭ ምላሽ አልተሰጠም። በመሆኑም በትግራይ ያለ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን በሚያስደነግጥ ፍጥነት በኑፋቄ እየተነጠቀ መሆኑን በመረዳት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው በፈጣሪ ፊት፣ በኅሊና እና በታሪክ ያስጠይቃል። አደገኛ ሰብራትም የሚያስከትል በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሠጥበት፤
ረ. በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት ወቅታዊ ችግር፣ ሌሎች የከረሙ አስተዳደራዊ ችግሮች እና ተያያዥ ምክንያቶች አብያተ ክርስቲያናት እየተዘጉ አገልጋይ ካህናት እና ተከታይ ምእመናን ወደ ሌላ እየፈለሱ እና እየተሰደዱ መሆናቸው የሚታይ የአደባባይ ሐቅ ነው። ይኸንኑ ችግር በጥናት ላይ ተመሥርቶ ከመመለስ ይልቅ ጳጳስ በመሾም ጥያቄዎቹ እንደተመለሱ የመቁጠር ከፍተኛ ዝንባሌ ተስተውሏል። በእርግጥ እርሱም ውጤታማ አይደለም። ችግሩን ከሥሩ ተረድቶ ምላሽ ባለመሰጠቱ የክልሉን ኦርቶዶክሳዊ በሌላ ዐውቅልሀለው ባይ አካል እንዲናወጽ ሆኗል:: በቅዱስ ሲኖዶሱም ለቋንቋዎች አገልግሎት የተመደበው በጀት እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሲሠራበት አልታየም። በአጠቃላይ በክልሉ የሚገኘውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት በማጠናከር የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የካህናት ማሠልጠኛ ማዕከላትን ማስፋፋት፣ መምህራንና አገልጋዮችን በማፍራት ተደራሽነትን የማስፋት ተጨባጭ ሥራ መሥራት ይገባል።
2. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግሮችን (ለጥፋት የዳረገንን ብልሹ አሠራርን) በተመለከተ፦
የሰበካ መንፈሳዊ ሥራ አስፈጻሚ ፣ ጠቅላላ ጉባኤ እና ከመንፈሳዊ ዘርፍ ውጪ ያሉ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በቃለ ዐዋዲው እና በተገቢው የዘርፉ ባለሙያ እንዲመሩ አለማድረግ ለጥፋት እና ለብልሹ አሠራር ዳርጎናል።
ታላቂቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከማይመጥን እና ብዙ ዋጋ ካስከፈላት አስተዳደራዊ ድክመት በመላቀቅ እና ዘመኑን በመዋጀት እናት ቤተ ክርስቲያንን መታደግ ለነገ የማያድር ሥራ ነው ። በመሆኑም :-
ሀ. የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ተደራሽ እንዳይሆን፣ የምእመናን ነፍስ እንዲነጠቅ፣ የኢኮኖሚ አስተዋጽዖዋ እንዲደበዝዝ ፣ ተሰሚነቷና ተቀባይነቷ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት የሆነው በብቁ የአስተዳደር ባለሙያ የመፈጸም ችግር የገነገነ ነው። መንፈሳዊ ዕውቅት ብቻ ባላቸው ነገር ግን የአስተዳደር ክህሎት በሌላቸው፣ ዘመኑን የመዋጀት ክፍተት ባለባቸው ሊቃነ ጳጳሳት እና በዘመድ አዝማድ ደጅ ጥናት ሙያ ሳይኖራቸው በተመደቡ ሓላፊዎች መመራቱ ዋናው የችግሩ አካል ስለሆነ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት፣ የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች የአስተዳደር ዘርፍ ከሊቃነ ጳጳሳት ውጪ በብቁ ባለሙያዎች እንዲመሩ እና ሊቃነ ጳጳሳት በሕግ አውጪነት እና ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ ፤ ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ፤ሕገ ቤተ ክርስቲያን ላይ ማሻሻያ ማድረግ ይገባል ::
ለ. በሕገ ቤተ ክርስቲያን እና በቃለ ዐዋዲ የተደነገገው የሰበካ ጉባኤ የአስፈጻሚነት እና የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤያት ሚና መገሰስ ፦ በቃለ ዐዋዲው የተደነገገው የካህናት፣ የምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የአስፈጻሚነት ተሳትፎ ማለትም በወረዳ ቤተ ክህነት፣ በሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና እና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተግባራዊ እንዳይደረግ ተገፍቷል። በዚህም ምክንያት የክፍል እና የመምሪያ ሓላፊዎች በቤተ ክርስቲያን ሕግ በግልጽ ከተደነገገው ከሦስቱ አካላት ተዋጽዖ ውጪ በሕግ የማይታወቅ የመደበኛ ቅጥር ሠራተኞች ስብስብ ” የአስተዳደር ጉባኤ ” የሚባል መሥርተው ቤተ ክርስቲያኒቱን እየበደሉ ይገኛሉ። ካህናት፣ ምእመናን ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የአስፈፃሚነት ሚናቸውን እንዲወጡ በሕገ ወጥ ስብስብ የተነጠቀው የአስፈጻሚነት ድርሻ በየመዋቅሩ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተመልሶ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ።
ሐ. የሀብት ብክነት፦ ንጽሕናን ገንዘብ ያደረጉ አባቶቻችን ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ብለው የገነቧቸው እና ለአገልግሎት ያበቋቸውን ሕንፃዎች ፣ ድርጅቶች እና ቤቶች ዛሬ በአያያዝና በቁጥጥር ሥርዓት ጉድለት ከፍተኛ ዘርፋና ግፍ የሚፈፀምባቸው ሆነዋል፤ ለብክነትም ተዳርገዋል። ለዚህም ጤናማ የሥራ አፈፃፀም ታሪክ የሌላቸው አካላት እየተፈራረቁ የመዘበሩት የቤቶች ድርጅት አንዱ ማሳያ ነው። ከአጥቢያ ጀምሮ በዘመናዊ አስተዳደር እጦት ምክንያት ለኪራይ አገልግሎት የዋሉ ሕንፃዎች ፣ ቤቶች እና ይዞታዎች በረቀቀ የሙስና ስልት ከሚጠበቅባቸው ገቢ በታች እየሰበሰቡ አብላጫውን አስተዳዳሪ ተብለው በሚሾሙ አካላት ይዘረፋሉ። በመሆኑም አሁን ላይ የአጥቢያዎች ቁመና የሠራተኞች ደሞዝ መክፈል ላይ ብቻ ተቸክሎ የምእመናን ሕይወት፣ ስብከተ ወንጌል ማስፋፋትና ልማት የማይታሰብ ሆኗል።
በመሆኑም ለወንጌል ልማት መዋል የሚገባው ሀብት ለምዝበራ ተዳርጓል። ቤተ ክርስቲያን መንፈንሳዊ ዕውቀትን ከዘመናዊው ዕውቀት ጋር ያጣመሩ ፈሪሐ እግዚአብሔር ያላቸው ልጆች የሌሏት ይመስል፤ የለየላቸው ጨካኝ ወንበዴዎች የሚቀራመቷት ሆናለች። በአያያዝ እና በብቁ አስተዳደር እጦት ሀብቷ ለብክነት ተዳርጓል ፤ ለጥቅመኞችም ሲሳይ ሆኗል።
ይህን የአደባባይ ምሥጢር መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ አይቶ እንዳላየ፤ ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፍ ቤተ ክርስቲያንን ለወንበዴዎች አሳልፎ መስጠት ነውና በቁርጠኝነት ሥር ነቀል ለውጥ ሊደረግ ይገባል።
መ. ከአጥቢያ ጀምሮ በሁሉም መዋቅር ዘመኑን የዋጀ የአስተዳደር ፣ የፋይናስ የግምገማ ፣ የቁጥጥር እና የምዘና ሥርዓት አለመኖር :- በሁሉም መዋቅር የሥራ ግምገማ ፣ የሥራ አፈጻጸም እና የሀብት አጠቃቀም ቁጥጥር ሥርዓት የለም። አጥፊ አይጠየቅም፤ በአጥፊዎች ላይ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አይተገበርም፤ ሹመት፣ ዕድገት፣ ዝውውር ያለ ምዘና ሥርዓት በዘፈቀደ ይከናወናል። የሠራተኞች የሥራ መደብ በከፍተኛ የብር መጠን ይቸበቸባል ፤ ሌብነት ፣ ሥርዓት አልበኝነት ነግሠው መንፈሳዊነት ከቦታው ጭራሹኑ ጠፍቷል። የሥራ ዋስትና የለም፤ ከኢአማኒያን እንኳ በማይጠበቅ መልኩ የካህናት፣ የዲያቆናት እና የስብከተ ወንጌል የሥራ መደብ ላይ የአየር ላይ ሽያጭ ፣ የወንዘኝነት መጠቃቀም የመሳሰሉት ዘግናኝ የግፍ ግፎች ይፈጸማሉ። ይህ ችግር በብዙ ሀገረ ስብከቶች መጠኑ ይነስም ይብዛ የሚስተዋል ሲሆን በተለይ ዋነኛ መገለጫው የሆነው እንደ አዲስ አበባ ባለ ሀገረ ስብከት ጎልቶ ይታያል። እንደ ማሳያ በተለያየ ጊዜ የተሾሙ ብፁዓን አባቶችም ሆነ በተለያየ እርከን ያሉ ሓላፊዎች የግላቸው የአሠራር ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ አንዱ የችግሩ ምንጭ እንደ ሲኖዶስ አብረው የሚወስኑ ጥቂት የማይባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ቅጠርልኝ፤ አዛውርልኝ፣ መድብልኝ፣ አታዘዋውርብኝ፣ አትቅጣብኝ የሚሉ ጫናዎች እንደሚያሳድሩባቸው ሁሉም በሚባል ደረጃ የሚገልጹት ለተበላሸ አሠራር ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ይህ የመልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የቅዱስ ሲኖዶስ ቁርጠኛ አቋም ከሆነ አባቶች ለወዳጅ ዘመድ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ማስቆም ያስፈልጋል ።
ረ. ውስን ሊቃነ ጳጳሳት በእርግና ምክንያት በግልፅ አስተዳደራዊ ሥራ ማከናወን እንደማይችሉ እየተስተዋለ ስለ ነፍሳቱ እረኛ ማጣት ደንታ ቢስ በመሆን መፍትሔ ሳይሰጥ ቀርቷል፤ እንዲሁም ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ሊቃነ ጳጳሳት ከምእመናን ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው ሀገረ ስብከቱ ታውኮ፤ ምእመናን አዝነው እና ከበረቱ ተገፍተው ወጥተው ሲቀሩ ሲኖዶስ በዝምታ ተመልክቶታል። ሀገረ ስብከታቸውን በሚገባ በማያስተዳድሩ ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተደነገገው መሠረት አስተዳደራዊ እርምጃ አለመወሰዱ እና የበዛ ዳተኝነቱ ቤተ ክርስቲያንን ክፉኛ ጎድቷታል። በመሆኑም በእርግና ላይ ለሚገኙ ብፁዓን አባቶች ረዳት መሾም ፣ የታወቀ የአስተዳድር ድክመት ያለባቸውን አባቶች ተገቢውን የተጠያቂነት አሠራር በተግባር ላይ ማዋል ይገባል።
ሸ. በመንፈሳዊ አገልገሎት ማለትም በፍትሐት፣ በሥርዓተ ተክሊልና በሥርዓተ ቀብር ላይ ከመንፈሳዊ አሠራር ያፈነገጠ የለየለት ንግድ ምእመናንን አስመርሯል። በቅዳሴ ሰዓትና አገልግሎት፣ ማሕሌት፣ ሰዓታት እና በሌሎች መንፈሳዊ አገልገሎቶች ላይ እየተሰተዋለ ያለው ከመጻሕፍትም ከአባቶችም ያላገኘነው ዐዲስ ባዕድ ልምምድ ተበራክቷ ። በፍቅር እና በረከትን ሽቶ ማገልገል ሞኝነት መስሎ፤ ከመንፈስ ቅዱስ አሠራር ውጪ እንደ መደበኛ ሥራ የማየትና ከፍቅር ይልቅ በሥራ መንፈስ የማገልገል አዝማሚያ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል።
ከ. በከተማ ልማት እና መስፋፋት ምክንያት ምእመናን ከአምልኮ ሥፍራ እንዳይለዩ እና አድባራቱና ገዳማቱ ተገልጋይ እንዳያጡ፣ ዘመኑ በመዋጀት ከአምልኮ ሥፍራና መልሶ ማልማት ጋር የተጣጣማሙ ስልታዊ የተቀናጁ የልማት ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት በአድባራቱ ቦታ እና ከመንግሥት ቦታን በመጠየቅ ምእመናን ተኮር የልማት ሥራ መሥራት ምእመናን ከቀያቸው ሣይርቁ አምልኮተ እግዚአብሔርን መፈጸም ያስችላቸዋል። በመሆኑም ነገን አሻግሮ በመመልከት ዛሬ ላይ ወደ ሥራ መግባት ይገባል።
3. የሥነ ምግባር ግድፈት ክብረ ክህነት፣ ክብረ ምንኩስናን የሚያስነቅፍ የተገለጠ የቀኖና ጥሰት መበራከት:-
የታወቀ፣ የተገለጠ የሥነ ምግባር ግድፈቱ ትውልዱን ከቤተ ክርስቲያን እያራቀው ነው። ትናንት ለቀሳውስት እና ለሊቃነ ጳጳሳት የሚሰጠው ክብር ተሸርሽሮ ጀርባ መሥጠት ተጀምሯል። በከተማ መነኮሳት እና መነኮሳይያት ኢክርስቲያናዊ ምግባር ምእመናንና ወጣቱን የማያንጽ አሰናካይ፤ ከሥርዓተ አበው፣ ከሥርዓት ምንኩስና ያፈነገጠ አሳፋሪ ልምምድ ተበራክቷል።
መንፈሳዊ ሕይወት ተዘንግቶ ፤ ቦታ ተነፍጐት ዓለማዊነትና ሥጋዊ ፍላጎት ነግሧል። ከታወቀ ደሞዝ በላይ ኑሮ ፤ ምንጩ የማይታወቅ፤ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረት ማካበት፣ ከገዳማት እና አድባራት ሠራተኛ እስከ ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ ሕጋዊ እስኪመስል በአደባባይ ተገልጧል። ይኸ አደገኛ በሽታ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፤ ባለቤት የሌለው ይመስል ልቅ የሆነውን ጉዳይ ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ ሁሉም በየተዋረዱ ለሥነ ምግባር ጥሰቱ ተጠያቂነት የሚሰፍንበት ሥርዓት ሊበጅለት ይገባል ።
4. በሀገራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳይ ላይ ተሳትፎን በተመለከተ
ሀ. በሀገር ግንባታ፣ በሰላም እና እርቅ ክዋኔ የካበተ እና ተጠባቂ ልምድ እና አስተዋጽዖ ያላት ቤተ ክርስቲያን ፣ በሊቃውንቷ አዎንታዊ አስተዋጽዎ ማበርከት ሲገባት በግልጽ፤ ከታወቀው አዎንታዊ ሚናዋ ተናጥባለች። በየዕለቱ የሂስና ግለሂስ አስተምህሮን የምትተገበር ቤተ ክርስቲያን ፣ በጸሎትና በውይይት ችግሮች የመሻገር ሰፊ ልምድ ያላት ቤተ ክርስቲያን፤ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ያላትን ግንኙነት በጥበብ በማስኬድ፣ በውይይት ፣ በምልዐት በመመካከር ማስኬድ ይገባታል። በሀገራዊ ጉዳይ ተቋማዊ ተሳትፎና ድርሻን መወጣት ዐቢይ ተግባር መጠናከር ይገባል ።
ለ. በመንግሥት በኩል እየተዘጋጁ ባሉ ልዩ ልዩ ረቂቅ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ተገቢነት ያለው ተቋማዊ ተሳትፎን በማጠናከር፤ ልዩ ልዩ ረቂቅ የሕግ ፣ የደንብ ዝግጅቶች ላይ መሳተፍ፣ ክትትል ማድረግ እነዚህ መመሪያዎች ከመውጣታቸው አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያኒቱና በአማኞቿ ላይ የሚያመጣውን በጎም ይሁን ክፉ ተጽእኖ በባለቤትነት መንፈስ በመመርመር ተገቢነት ያለው ሱታፌ እንዲኖራት የሚያስችል አግባብነት ያለው የውክልና ተሳትፎዎች ማድረግ እንድትችል በባለ ሙያዎች በተደራጀ ቡድን ክትትል እና ተቋማዊ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል።
ሐ . በሀገራችን የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ እና ሀገራዊ ሰላም እንዲረጋገጥ አዎንታዊ የቤተ ክርስቲያን ሚናን በተመለከተ ፦ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሀገራዊ ሰላም ፣ በህዝቦች ስደት፣ ሞት እና አለመረጋጋት ዙሪያ ፤ አስቀድሞ ለዘመናት መገለጫዋ ከሆነው ልምዷ በመነሣት ችግሩ እንዲቀረፍ ፍሬ ያለው ተግባር አልተከናወነም:: ከመግለጫ በዘለለ የተቀናጀ ፣ ውጤት ሊያመጣ የሚችል አዎንታዊ ሚናዋ ደብዝዟል። በመሆኑም ችግሩን ከመቅረፍ እና በወንድማማቾች መሀል የተፈጠረን ልዩነት በማጥበብ ሀገራዊ ሰላም እንዲሰፍን ቤተ ክርስቲያን ተጠባቂ ሚናዋን ከመወጣት አንፃር ሰፊ ሥራ ይጠበቃል ፡፡
መ. ቤተ ክርስቲያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ የሃይማኖት እና ሰብዓዊ ክዋኔዎች ላይ በአግባቡ አለመሳተፍ፤ በአኃት አብያተ ክርስቲያናት መደበኛ እና ልዩ ልዩ ጉባኤያት አለመወከል እንዲሁም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተገቢውን ተሳትፎ እና መብቷን የማስከበር ሥራዎች አለማከናወን ይስተዋላል:: ቅዱስ ፓትርያርኩ ከሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርቲያን ከምትወከልበት መድረክ መሄድ ካቋረጡ ሰነበቱ። በመሆኑም ይኸ ታላቋን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስትያን የማይመጥን ድርጊት ተገቢው ማስተካከያ ሊሰጠው ይገባል።
ከላይ በዝርዝር የተገለጠው በዋነኛነት የብልሹ አስተዳደር ውጤት፤ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቷን እንዳታስፋፋ፣፤የነፍስ ድኅነትን እንዳታውጅ፤ መንግሥተ እግዚአብሔርን እንዳትሰብክ እንቅፋት የሆነ፤ ነፍሳትን ከበረቱ ያስኮበለለ፤ የቀሩትም ለቀቢፀ ተስፋ የዳረገ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ፤ ከአሁኑ የከፋ ጥፋት ሳይከሰት ሥር ነቀል መፍትሔ በመሥጠት እና የምእመናንን የአስፈፃሚነት ሱታፌ በማረጋገጥ የምንረከባትን ቤተ ክርስቲያን እንዲታደግልን እና ሐዋርያዊ አደራውን እንዲወጣ በልጅነት መንፈስ ዝቅ ብለን እንማፀናለን ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!
(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)

ወቅታዊ መልእክት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ (ሀገር አቀፍ) የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከውጪና ከውስጥ የሚቃጡባትን ፈተናዎች በመቋቋም ከውጭ የሚቃጡባትን ፈተናዎች ሰማዕትነትን በሚቀበሉ ልጆቿ ምስክርነት፣ ምንፍቅናን በቃል የመጣውን በቃል በመጻሕፍት የመጣውን በመጻሕፍት በመመከት ሐዋርያዊ ቅብሎሿን ጠብቃ መሠረተ እምነቷን፣ ዶግማና ቀኖናዋን ቅዱስ ትውፊቷን ለትውልዱ እያስተማረች ጸንታ ቆይታለች፤ ወደ ፊትም ትኖራለች፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ በልዩ ልዩ ውጫዊ ፈተናዎች ዋጋ እየከፈለች ያለች ቢሆንም ከሁሉ የከፋው ግን ከክብር በላይ የላቀ ክብር ባጎናጸፈቻቸውና እረኛና ጠባቂ እንዲሆኑ ባሰማራቻቸው ልጆቿ በተደጋጋሚ እየገጠማት ያለው የቀኖና ጥሰት ነው። የጥር ፲፬ ጳጳሳት ሹመት፣ የትግራይ ሲኖዶስ፣ የቅባት ጳጳሳት ሹመት ፤ ፖለቲካን ተጠግቶ ቤተክርስቲያንን የማጥቃት ክፉ ግብር ሳያንሳት ፤በተገኘው አጋጣሚ ኹሉ የምንፍቅና ትምህርቶች የሚያስተላፉትን በዝምታ መመልከት እየበዛና በዚህም በጎቿን ከበረቷ ለማስነጠቅ ለሚሠሩ ሁሉ ተባባሪ በመሆን የሚኬድበት ርቀት ቤተክርስቲያኒቱን ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ በቃ ሊባል ይገባዋል፡፡ ለማሳያ ይሆን ዘንድ በአቡነ በርናባስ መባልእትንና ነገረ ክርስቶስን አስመልክቶ፤ በአቡነ ፊልጶስ እመቤታችንና ሥላሴን አስመልክቶ የተናገሩትን የስሕተት ትምህርቶች ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ የሊቃውንት ጉባኤ በወቅቱ ማስጠንቀቂያም ሆነ የእርምት እርምጃ ባለመውሰዳቸው ዛሬ በአቡነ ገብርኤል እመቤታችንንና ነገረ ክርስቶስን አስመልክቶ ያውም በዐውደ ምሕረት፣ እንዲሁም በዕለተ ስቅለት በተደረገ የአዳራሽ ጉባኤ ለተናገሩት የኑፋቄ ትምህርት አድርሶናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን ገፊ እንደሆነች እና ስለክርስቶስ የሚዘምሩትን እንደምታባርር እርሷም ስለ ክርስቶስ እንደማትዘምር በአደባባይ በጉባኤ ያለምንም ፍርሀት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የማኅበራት ምዝገባ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያን ጨምሮ የተለያዩ ሊቃነ ጳጳሳት በኑፋቄ ትምህርት ማስፋፋት ላይ የተሰማራውን “ፍኖተ ጽድቅ” ማኅበርን በገንዘቡ በሚሠራቸው የስቱዲዮ ግንባታ፣ የመጽሐፍ ኅትመት እና የመሳሰሉት ተግባራት በመማረክ የቤተክርስቲያንን ክብር አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ሂደት ላይ አንዳንድ መምህራን እና ማኅበራትም ተሳታፊ መሆናቸው በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡

ይህ እንዲሆን ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከል የሚከተሉት በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው።

1. የአስተዳደር ብልሹነት የወለደው ዘርፈ ብዙ ችግር
በእኛ መረዳት አሁናዊው ፈተና እና ችግር ከውጪያዊው የዝግጅት ጥቃትና ፈተናም በላይ የበረታው የውስጥ ችግር ነው። ለዚህም ዋናውና አንደኛው የሁለንተናዊ ድካማችን ምክንያት የቤተ ክህነቱ ብልሹ አስተዳደር ነው።
አሁን ላይ ያለው የቤተ ክህነት አስተዳደር ዘመኑን በመዋጀት የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ተልዕኮ በማስፈፀም ነፍሳትን ለመንግሥተ እግዚአብሔር ለማብቃት የሚያስችል ቁመና እና ብቃት ላይ አይገኝም ። ሕግ አውጪ፣ ሕግ ፈፃሚ እና ሕግ ተርጓሚ አንድ አካል በመሆን፣ ተጠቅልሎ በተያዘ ሥልጣን ቤተ ክርስቲያኒቱ እጅ ተወርች ተቀፍድዳ ወደ ትውልዱ እንዳትደርስ እየተሠራ ይመስላል።

ቤተ ክርስቲያን በማይመጥናት ደካማ አስተዳደር ምክንያት ከተመሠረተችበት ነፍስ የማዳን መንፈሳዊ ተግባር ተናጥባለች። አስተዳደሩ ምእመናንን ለመንፈሳዊ ፍሬ ከማብቃት ይልቅ ለውድቀታቸው ምክንያት ሆኗል። በተለያዩ ጊዜያት ተጠንተው የቀረቡ ልዩ ልዩ የአስተዳደር ማሻሻያዎች እየተኮላሹ ጉዞው ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል:: በ ፳፻ወ፬ ዓ.ም ለሲኖዶስ የቀረበው የመሪ ዕቅድ ትግበራ ጥያቄ ፲፫ ዓመታት ሲገፋ ቆይቶ አሁንም ቦታ ተነፍጐታል። አስተዳደራዊ ለውጥ ጠልነቱ ተባብሶ ቀጥሏል። እኔ ብቻ በሚሉ ፣ ቤተ ክርስቲያን እንደ ግል ተቋማቸው በሚያዩ አካላት ተወራለች:: በሃይማኖት ችግር ፣ በቀኖና ጥሰት እና በሙስና ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው አካላት የተሻለ ሹመትና ሽልማት ይሰጣቸዋል፡፡

2. ለሊቃውንት ጉባኤ ትኩረት መነፈጉ
የሊቃውንት ጉባኤ ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው በመቅረቱ ፣ እንዲሁም ሊቃውንት ክብራቸው ባለመጠበቁ እና ከውሳኔ ሰጪነት ድርሻ በመገለላቸው ፤ ለስሑት ትምህርት በሚገባው መልኩ ምላሽ መስጠት የማይችል ሆኗል:: እንዲሁም በቤተክርስቲያኒቱ ስም ለሚታተሙና ለሚሰራጩ መጻሕፍትና ልዩ ልዩ የምስልና የድምፅ እንዲሁም የኅትመት ውጤቶች የመገምገምና ዕውቅና የመስጠት ሥልጣኑ ተነጥቋል። የአደረጃጀትና የመከላከል አቅሙ በመዳከሙ፤ በመዋቅሩ ውስጥ የተሰገሰጉ ሐሰተኛ መምህራን በአፍም በመጽሐፍም ስሁት ትምህርታቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት እያሰራጩ ይገኛሉ።

ትናንት አባቶች ያቆዩትን ሀብት መንዝሮ መጠቀም እንጂ የራሳቸውን አሻራ የማያኖሩ፣ ሀብት ንብረቷን ጠብቀው ከማቆየት ይልቅ ለግል መዝብረው ቀሪውን ለዘራፊ አሳልፈው የሰጡ ከመንፈሳዊ ክብር በጐደሉ፣ በሥጋ ሐሳብ ጨርሶውኑ በተወሰዱ፣ ምግባር በጎደላቸው ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ ባሉ አገልጋዮች እየተፈተነች ትገኛለች።
ያለ ዋጋ ከሚሰጠው መንፈሳዊ ሹመት ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚጎዳ እኩይ ተግባር በእጅ መንሻ የሚፈጽሙ አካላት በሁሉም መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበትን ዓላማ እንዳታሳካ ሳንካ ሆነውባታል።

ስንዱዋ እመቤት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሕግ እና በሥርዓት ዝግጅቷ እንከን አይወጣላትም። ነገር ግን ከሕግና ከሥርዓት ባፈነገጡ፣ ሐሰተኛ ትምህርት በሚያሰራጩ እና ኢ-ክርስቲያናዊ በሆነ ሕይወት ወስጥ በሚመላለሱ በተለይ በሁሉም መዋቅር ወስጥ በሚገኙ አገልጋይ ሠራተኞች ላይ ተግባራዊ ርምጃ አለመወሰዱ ለምእመናን ተስፋ መቁረጥ እና ፍልሰት ምክንያት ሆኗል።

3. በሕግ ከተሰጣቸው መብት ውጪ በማስተማር የሚሰማሩ ማኅበራትን በሕግ አግባብ ወደ መስመር አለማስገባት
የሰሞኑ ስሁት ትምህርት በሕጋዊ ዕውቅና ስም የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት እኩይ ተግባር ከትናንት የቀጠለ የብልሹ አስተዳደር መገለጫ ነው። የማኅበራት አስተዳደር ደንብ ፀድቆ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ደንቡ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስረጃ በማስደገፍ የማሻሻያ ሐሳብ ብናቀርብም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። በመሆኑም የፈራነው ደርሶ ፤ ደንቡን ለማስፈፀም የተቀመጠው የማኅበራት ምዝገባ ክትትል እና ቁጥጥር መምሪያ፤ በማኅበራት አስተዳደር ደንብ አንቀጽ ፲ ላይ የማኅበራት ዓለማ “ለትምህርት ተጠሪ ተቋማት ድጋፍ መስጠት ነው” በሚል የተደነገገ ቢሆንም እንደ ‹‹ፍኖተ ጽድቅ›› ያለ ማኅበር ድጋፍ ሰጪ ሳይሆን ፈፃሚ ሆኖ፣ ማኅበሩ ከተመሠረተበት ዓላማ ውጭ ትምህርተ ወንጌልን በአዳራሽ ውስጥ ሲሰጥ፤ በሚዲያ ትምህርት ሲያስተላልፍ አልፎ ተርፎ የቤተ ክርስቲያን መዝሙሮቿን ከሥርዓቷና ከቀኖናዋ ውጪ በሆነ ሁኔታ በሚዲያ እያቀናበረ ሲያስተላልፍ ተገቢው አስተዳደራዊም ሆነ ቀኖናዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከማድረግ ይልቅ በማኅበርነት በመመዝገብ እንዲሁም በደንቡ የተሰጠውን የመቆጣጠር ሓላፊነት የማኅበራት ማደራጃ ምዝገባ ክትትል እና ቁጥጥር መምሪያ ባለመወጣቱ ዛሬ ለደረሰው ስሑት ትምህርት ዝግጅትና ስርጭት አብቅቶናል፡፡
ይኽ ማኅበር ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተህምሮ ውጪ ስሑት ትምህርት የሚሰጥበት ተቋም እንደሆነ በተጨባጭ እየታወቀ እና በአካል ቀርበው አረጋግጠው እንኳን ቅዱስ ፓትርያርኩን በዚያ ሥፍራ እንዲገኙ በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን አሳልፈው የሰጡ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች መኖራቸው የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡

በመሆኑም ከዚህ በታች የዘረዘርናቸው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተገቢው ትኩረት እንደሚሰጣቸው እና የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው እናምናለን።

1. የሊቀ ጳጳሱ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት ብናምንም በሚገባ እና በትኩረት ጉዳዩ እንዲታይና መፍትሔ እንዲሰጠው፡፡ እንዲሁም በተመሳሳይም ስሑት ትምህርቶችን የሚያስተምሩ እና ያስተማሩ ሌሎች ጳጳሳት እና መምህራን ጉዳይም አብሮ እንዲታይ፣ ይኽን አጋጣሚ ተጠቅሞ የሊቃውንት ጉባኤም በስሑት አስተምህሮዎች ላይ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ቢደረግ፡፡

2. ሓላፊነቱን በአግባቡ ያልተወጣው የማኅበራት ምዝገባና ክትትል እና ቁጥጥር መምሪያ ከሊቀ ጳጳሱ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ሓላፊዎች እንዲጠየቁ፡፡

3. የማኅበራት ምዝገባ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ የዕውቅና ሰርተፊኬት ከመቸርቸር ወጥቶ፣ ደንቡና አሠራሩን ዳግመኛ በመፈተሽ፣ የዕውቅና አመዘጋገብ፣ ክትትልና ቁጥጥር ሒደቱም ንጥር ያለ እና መስፈርቶች የወጡለት እንዲሆን፡፡

4. ቅዱስ ፓትርያርኩን በማሳሳት ” ፍኖተ ጽድቅ ” በተባለው ማኅበር ዝግጅት ላይ እንዲገኙ ያደረጉ የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ሓላፊና የፖትርያርኩ የፕሮቶኰል ሹም እንዲጠየቁ፡፡

5. ‹‹ፍኖተ ጽድቅ›› የተሰኘው ማኅበር በቤተክርስቲያን ላይ እያደረሰ ያለውን የተሐድሶ ኑፋቄ ትምህርት ባለማረሙ ምክንያት ማኅበሩ የምዝገባ ፈቃዱ ተሰርዞ ባስተላለፈው ትምህርቶች በቀኖና እንዲጠየቅ እና በዚሁ አጋጣሚ ከመምህራን እስከ ሊቃነ ጳጳሳት “ፍኖተ ጽድቅ” ከተባለ ማኅበር ጋር የጀመሩት በነዋይ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲደረግ። እንዲሁም በቤተ ክህነቱ የበላይ ሓላፊዎች በኩል እናት ቤተ ክርስቲያናችን አንዳች ሳይጎድልባት ባልተገባ መሻት ከባለ ጸጋ እጅ ለማኝ በማድረግ ቅድስት ቤተክርስቲያንን የማዋረድ እና አሳልፎ የመስጠት እኩይ ተግባር እንዲቆም።

6. የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎቷን እንዳታሰፋ እጅ ተወርች ቀፍድዶ የያዛት ደካማ፣ ብልሹ አስተዳደር እንዲስተካከል በልጅነት መንፈስ በተደጋጋሚ የችግሮቹን ማሳያና መፍትሔዎቹን፣ ሥርዓተ መዋቅርን በመጠበቅ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ድረስ ቢያቀርብም ተጨበጭ ምላሽ አልተሰጠውም ። ይህም ጉዳይ ከግንዛቤ ገብቶ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል።

ነገር ግን አሁንም እንደ ቀድሞው ተሸፋፍኖ የሚታለፍ እና መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ታላቋን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስትያን የማይመጥነው ብልሹ አስተዳደር የሚቀጥል ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ሊቃውንት፣ ምእመናን፣ እና የሰንበት ት/ቤት አባላት ጋር በመሆን የምንረከባትን እና ለትውልድ የምናሰረክባትን እናት ቤተ ክርስቲያን የምንታደግበትን መንገድ የምንከተል መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለፅ እንወዳለን።

የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
ሚያዚያ ፳፩ቀን ፳፻፲ወ፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!

(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)

Youtube

https://www.youtube.com/@eotc-gssu

Facebook

https://www.facebook.com/gssu.eotc

Telegram

https://t.me/eotcgssu21

Tiktok

@eotc_gssu

“ኢሀሎ ዝየ ዳእሙ ተንሥአ በከመ ይቤ – ከዚህ የለም እንደ ተናገረው ተነሥቷል፡፡” ማቴ.28፡6

በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር በራስጌና በግርጌ የነበሩ ቅዱሳን መላእክት ማልደው ወደ ጌታ መቃብር ለሄዱ ሴቶች ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ ከዚህ የለም እንደ ተናገረው ተነሥቷል በማለት መልሰውላቸዋል፡፡ ሴቶቹ ወደ መቃብሩ መሄድ የጌታችንን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ጠበቁት ሦስት ቀን የሞላው ጠረኑ የተቀየረ ሥጋ ሳይሆን ባዶ መቃብር ነበር ያገኙት፡፡ ማስተዋል አቅቷቸው እንጂ ጌታችን ከሞቱ አስቀድሞ “ይህንን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አነሣዋለሁ” ብሎ በሥልጣኑ በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ነግሯቸው ነበር፡፡ (ዮሐ.2፡18) በሌላም የወንጌል ክፍል “ያለ እኔ ፈቃድ ነፍሴን ከሥጋዬ የሚለያት የለም፤ እኔ ወድጄ እለያታለሁ እንጂ በመቃብር ላኖራት አዋሕጄም ላስነሣት ሥልጣን አለኝ፡፡” በማለት ስለሞቱና ስለ ትንሣኤው ተናግሮ ነበር፡፡ (ዮሐ.10፡18)

የጌታችን ሥጋ በመቃብር መፍረስ መበስበስን ሊያጠፋል ወደ መቃብር ወረደ እንጂ እስከ ክርስቶስ ድረስ በነበሩ ሙታን ሲሆን እንደነበረው መፍረስ መበስበስ ያለበት በሦስተኛውም ቀን ሽቱ መቀባት የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ አይሁድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ካንተ ምልክት ማየት እንሻለን ባሉት ጊዜ “አመጸኛና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ትሻለች ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጣትም፡፡ ዮናስ በአሳአንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት እንደቆየ የሰው ልጅም በምድር ሆድ ውስጥ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ይቆያል፡፡” በማለት መቃብር እንደማያስቀረው ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፡፡ (ማቴ.12፡39)

ወደ መቃብሩ የሄዱ ሴቶች በተደጋጋሚ በሰሙት የአይሁድ የውሸት ወሬ ምክንያት አስቀድሞ የሰሙትን የጌታ የትንሣኤውን ነገር በሙሉ እምነት መቀበል አልቻሉም ነበርና ሽቱ ለመቀባት ሄዱ፡፡ በለሊት ከወንዶቹ ቀድመውና ጨክነው ወደ መቃብሩ የሄዱበት ጥንካሬ ግን የሚደንቅ ነው፡፡ ቀድመው በመሄዳቸው ቀድመው የትንሣኤውን ብስራት ሰሙ፤ በዓይናቸውም አይተው አረጋገጡ፡፡ ጌታችን ከሙታን መካከል እንደሌለ፣ መሞቱ ሞታችንን ሊያጠፋ፣ ወደ መቃብር መውረዱም በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን ሊያስወግድ እንደሆነ ተረዱ፡፡

የጌታችን የሞተው ሞታችንን ለመግደል የተነሣውም እኛን ለማሥነሳት ነውና የጌታችን ትንሣኤን ስናከብር የምናከብረው ትንሣኤያችንን እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ዘተሰቅለ በእንተ ኃጢአትነ ከመ ያጽድቀነ ወትንሥአ ከመ ያንሥአነ – ሊያጸድቀን ስለኃጢአታችን ተሰቀለ፤ ሊያነሣንም ተነሣ” ይላል፡፡ (ሮሜ.4፡25) ስለዚህ የትንሣኤን በዓል ስናከብር የተነሣንበት በዓል እያከበርን ነውና በዓሉ ሙት በሆነ ሕይወት እንዳናከብር በትንሣኤ ልቡና ተነሥተን ስለእኛ ሕይወት የተቆረሰውን የክርስቶስ ሥጋን በመብላት ደሙንም በመጠጣት ሊሆን ይገባል፡፡ በዓለ ትንሣኤ የመነሣት በዓል ነውና ለፍቅር ለአንድነት ለሰላም ከመነሣት ጋር በዓሉን ማክበር ይገባል፡፡

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ “ወአድኃነነ በርደቱ እመስቀሉ ውስተ ሲኦል ወፈትሐ እለሀለዉ ሕየ ጻድቃነ ሙቁሐነ በኃጢአተ አዳም አቡሆሙ – ከመስቀሉ ወደ ሲኦል በመውረዱ አዳነን በዚያም በአባታቸው አዳም ኃጢአት ምክንያት የታሰሩ ጻድቃንን ፈታ፡፡ ብሎ እንዳስተማረ የምናከብረው በዓል የመፈታት በዓል ስለሆነ ከኃጢአት፣ ከክፋት ከዘረኝነትና መሰል እስራቶች ተፈትተን ልናከብረው ይገባል፡፡
በመጨረሻም በመላው ዓለም የምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን፣ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ያላችሁ በሰንበት ትምህርት ቤት የምታገለግሉ ወጣቶችና ሕጻናት በዓሉ ለንስኃ፣ ለአገልግሎትና ለመልካም ነገር የመነሣትና ከተለያዩ የዓለም እስራቶች የመፈታት በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ! መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንላችሁ!

መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወ/ትንሣኤ
በመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ

የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!

(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)

Youtube

https://www.youtube.com/@eotc-gssu

Facebook

https://www.facebook.com/gssu.eotc

Telegram

https://t.me/eotcgssu21

Tiktok

@eotc_gssu

፵፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጀመረ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የሚደረገው የመንበረ ፖትርያርክ የጠቅላይ ቤተክህነት ፵፫ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤበዛሬው ዕለት ተጀመረ። በመክፈቻው ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያት ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት “እንደ ዐስራ ኹለቱ ሐዋርያት መንጋውን ትጠብቁት ዘንድ መንገዱን አሳምሩ” በሚለው በቅዱስ ያሬድ ቃል ተነስተው በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መልዕክትን አስተላልፈዋል።

የመጀመርያው መልዕክታቸው አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን “በዚህ ዘመን በሐዋርያት መንበር ላይ ለመንጋውና ለመንግሥተ እግዚአብሔር የተሾምን እንደመሆናችን በመልካም አስተዳደርና በቀና እምነት ልናስተዳድር ይገባል። በአሁን ሰዓት የቤተክርስቲያን አስተዳደር ችግር በብዛት የሚስተዋልበት እንደመሆኑ ይህን ችግር ለመቅረፍ በጥናት ላይ በመመስረት በፍጥነት መስራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።

ኹለተኛው መልዕክታቸውም የምዕመናንና የአገልጋዮች ሰቆቃና ሞት ላይ ያተኮረ ነው። በምዕመናንና በአገልጋዮች ላይ እስከ አሁኗ ሰዓት እያጋጠመ ያለውና ያልተቋረጠው እንግልትና ሞት እንደ ምሳሌ በምስራቅ ሸዋ ከነቤተሰቦቻቸው የተገደሉትን አባት በማንሳት እንዲህ አይነቱ ተግባር ሊቆም እንዲገባ መልዕክትን በማስተላለፍ ስብሰባው በይፋ መጀመሩን አብስረዋል።

በመቀጠል ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕርዳርና ምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የሰበካ ጉባኤን ጅማሮና አሁን እስካለበት ድረስ ያለውን ታሪክ በማንሳት ይህን ሥርዓት ላበጁ አባቶች ክብርና ለዚህ ያደረሰንን አምላክ ልናመሰግን ይገባል ብለዋል። በመቀጠልም የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችን ሪፖርት አቅርበዋል።

ጉባኤውም እስከ ጥቅምት 10 የሚቀጥል ሲሆን የየሀገረ ስብከቶችን የሥራ ሪፖርትና በተለያዩ ጉዳዮች ውሳኔ ይተላለፍበታል ተብሎ ይጠበቃል።