ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊው ለውጥ መቼ?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ያልተበረዘ ክርስቶሳዊ ትምህርት ምንጭ ናት፡፡ ነቅ አልባ አስተምህሮዋ መቼም ቢሆን ለድርድር አይቀርብም፡፡ ከጥንትም መሥሯቿ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ፍጽምት አድርጎ ነው የሠራት። መንገድ እና ሕይወት እኔ ነኝ ያለው ጌታ የመሠረታት ሕይወት የሚገኝባት መንገድ ናት ተዋሕዶ፡፡ ሐቁ ከእርሷ የተሻለ መንገድ የለም ሳይሆን ከእርሷ ሌላ የሕይወት መንገድ የለም ነው። አስተዳደራዊ ሥርዐትን በተመለከተ ግን ነገሮች የሚከወኑበት ሁልጊዜም ከዘመን ዘመን የተሻሻለ መንገድ ይመጣል።
ሐዋርያት መጀመሪያ የክርስቲያኖች ቁጥር አነስተኛ በነበረበት ሰዓት የዘረጉትን የአስተዳደር ሥርዓት የአማኙ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ቀይረውታል። ‹‹ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም፤›› ብለው ሁኔታውን ያገናዘበ አስተዳደራዊ ለውጥ አደረጉ። ውሳኔው የምእመናንን ሱታፌ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከፍ ያደረገ፣ አዳዲስ የወንጌል መልእክተኞችን ወደ አገልግሎቱ የሳበ የለውጥ ውሳኔ ነበር፡፡ የክርስትናን ፋና ወጊ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን ያስገኘ እና አገልግሎቱን ያሰፋ አስተዳደራዊ ለውጥ ነበር፡፡
የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያንም ገፊ ምክንያቶችን በመመዘን አይቀሬውን አስተዳደራዊ ለውጥ መቼ ማድረግ እንደሚገባት ልትማርበት የምትችል የታሪክ ዐውድ ነው፡፡ ቀደም ባለው ጽሑፋችን ‹‹ለቤተ ክርስቲያን ለምን ለውጥ ያስፈልጋታል?›› በሚል ርእስ ለውጥን ግድ የሚሉ ውስጣዊና ውጫዊ ግፊቶችን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ደግሞ ይህ ለውጥ መቼ ነው መተግበር የሚኖርበት የሚለውን ሐሳብ በመጠኑ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ለመዳን ቀጠሮ መስጠት እንደማይገባ ሲያስረዳ ‹‹የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤›› (፪ቆሮ. ፮፥፪)ይላል፡፡ ለወንጌል አገልግሎት፣ ለቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ተልእኮ የሚበጅ ሥምሪት ለማድረግ ዕለተ ኅሪት ዛሬ ናት፣ ከዛሬም አሁን፤ ከዚህ የተሻለ የተመረጠ ጊዜ የለም፡፡ ቀን ሳለ ነው ልንሠራ የሚገባን፡፡ የእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ በጎ ነው፤ በጎውን ነገር ለመሥራት ደግሞ ከዛሬ ያውም ከአሁን የተሻለ ጊዜ የለም፡፡ እግዚአብሔር ለለውጥ እንድንዘጋጅ በተለያየ መንገድ እየነገረን ያለበት ይህ ጊዜ ለእኛ የተወደደ ሰዓት ነው፡፡ ‹‹ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፤›› (ማር.፲፮፥፳) እንደ ተባለ ጌታ ከእኛ ጋር የሚሠራበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ነገ በእጃችን አይደለምና፡፡ በይፋ የሚታየው አስተዳደራዊ ብልሹነት እና መንፈሳዊ ጉድለት ለለውጥ የሚቀጠር ጊዜ መኖር እንደሌለበት የሚያስገነዝብ የማንቂያ ደወል ነው፡፡ የውስጥና የውጭ ግፊቶች እየከበዱ መምጣት ዕለተ ኅሪት አሁን እንደሆነ አፍ አውጥተው ይናራሉ፤ ጠቢብም ይሰማቸዋል፡፡
ርትዕት የሆነችው ቤት ርቱዐን የማይኖሩባት፣ ርትዕ ሐሳብ ያላቸው የሚሳደዱባት ከሆነች ውላ አድራለች። የተበላሸው አስተዳደር የበለጠ ለመዝቀጥ ርቱዐኑን ማሳደድ፣ ሐሳውያኑን መሰብሰብ ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። ይህን አሠራር ማሻሻልና መለወጥ ካልተቻለ እየተደራረበ የመጣው እንከን ከመሰናክልነት ወደማይገፋ ጋራነት ብሎም ወደ አይበገሬ የችግር ተራራነት እንዲያድግ እየፈቀድንለት ነው። እዛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ደግሞ ላፍርስህ ቢሉት መዶሻውም ይለግማል። ማፍረስ ቢቻል እንኳ ናዳው ይዞት ገደል የሚገባ፣ የሚያዳፍነው ነገር ብዙ ነው።
የሮም ካቶሊክ ሥር ሰድዶ በቆየው አስተዳደደራዊ ዝቅጠት እና በጳጳሳቷ ዓለማዊነት የበዛበት የተቀማጠለ አኗኗር ምክንያት በሕዝቡ ዘንድ የተጠራቀመውን ምሬት ለማየት አልፈቀደችም፡፡ የካርዲናሎቿን ብልሹ ሥነ ምግባር በማረም የለውጥ ግፊቱን በጊዜውና በአግባቡ ማስተናገድ ተሳናት፡፡ ለለውጥ ዝግጁ ባልሆነ ድንዛዜ ውስጥ በመቆየቷ ፲፮ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈላትን መነሻውን አስተዳደራዊ ጥያቄ አድርጎ ወደ አስተምህሮ ልዩነት ያመራውን ሉተራዊውን አብዮት ለማስተናገድ ተገደደች፡፡ ከካቶሊክ እና ከመሰል ታሪኮች ለመማር ጊዜው አልረፈደም፡፡ አለበለዚያ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የሚታየው መፋዘዝ እና በውስጥ ያለውን የለውጥ ጥያቄ በጊዜው ለማስተናገድ ያለመፈለግ ቅጥያ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ነብይነትን አይጠይቅም፡፡ ለዛም ነው ለበጎ ሥራ ዛሬያችንን እየተጠቀምን ነገን ያማረ ማድረግ የሚኖርብን፡፡ ዛሬን ካልሠራንበት ነገ ምን ይዞ እንዲመጣ ዐናውቅም፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ፊሊክስ ለተባለው ሀገረ ገዢ ስለ ክርስቶስ በነገረው ጊዜ ሀገረ ገዢው አምኖ ለመጠመቅ በፊቱ የነበረን የተወደደ ሰዓት ጥሪ ቸል አለ፣ የመዳን ቀን ዛሬ እንጂ በይደር ቀጠሮ የሚተላለፍ እንዳልሆነ ዐላወቀም። «በተመቸኝ ጊዜ አስጠራሃለሁ፤» (ሐዋ. ፳፬፥፳፭) ብሎ ቀጠሮ ያዘ። ነገር ግን ሌላ ዕድል አግኝቶ ጳውሎስን አስጠርቶ ሲጠመቅና ከመንፈስ ቅዱስ ሲወለድ፣ ለሰማያዊ ሕይወት ራሱን ዕጩ ሲያደርግ የሚተርክ ምዕራፍ አላነበብንም።
ቤተ ክህነት ግልጸኝነት ያልሰፈነበትን፣ ተጠያቂነትን ከፍርድ ቀን ጋር ብቻ ያስተሣሠረ አመለካከትን እንዳነገበ ይህን ዘመን መሻገር እንደማይችል ለማወቅና ለመታረም ጊዜው አሁን ነው፡፡ የዘመኑን ተግዳሮት ዐውቆ ከውስጥ ለመጣው የለውጥ ግፊት አዎንታዊ እና አስቸኳይ ምላሽ መስጠት አማራጭ የሌለው ምርጫ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ቤተ ክህነት የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ከራሱ ህልውና ጋር በጥብቅ ያስሣሠረውንና ለነገ በጎነቷ ሲባል ዘመኑን የዋጀ ለውጥ በቤተ ክርስቲያን እንዲተገበር የሚመክረውን ልጇን ወደ ዳር መግፋ ማቆም አለበት፡፡ የለውጥ ደወል እየደወሉ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጉድለቶች እንዲታረሙ የሚጠይቁ ልጆቿ ጉትጎታ አሁንም ሰሚ ጆሮ አጥቷል፡፡ ከነገ ዛሬ የቤተ ክህነቱን ጆሮ ለማግኘት የሚደክሙትን ድምፅ መስማት ግድ የሚልበት ሰዓት ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ ቀርቧል፡፡ ቤተ ክህነቱ ይህን የተወደደን ሰዓት ባልተወደደ ተግባር ላይ ማዋል መቀጠሉ የቤተ ክርስቲያንን ዘመኑን የመዋጀት ተልእኮ ያጨናግፋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በለውጥ ስም ነውጥ ለደገሰላት በጥላቻ ላበደ ባዕድ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል። ለክብርዋ ቀንተው ለውጥን ሲሹ የነበሩት ልጆቿ ምሬት ሲበዛ የሚወስዱት የተናጥል ውሳኔ ምን እንደሚሆን አይታወቅም፡፡ ቤተ ክህነት እያሳየው ያለው ለውጥ ጠል መንገድ የማይነካ ከፍታ ላይ የተቀመጡ ለሚመስላቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሳይቀር አደገኛ እንደሚሆን መገመት ግን አይከብድም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ ‹‹ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ ሚጀምርበት ጊዜ ደርሷልና፤›› ይላል፡፡