ለአገራችን ኢትዮጵያ ሰላምን ስጣት

ለአገራችን ኢትዮጵያ ሰላምን ስጣት

ለአገራችን ኢትዮጵያ ሰላምን ስጣት

ሊቀ ነቢያት ሙሴ እስራኤላውያን ከአሕዛብ ነገሥታት ጋር ጦርነት በሚያደርጉበት ወቅት ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት ሔደው እናንተ ከቤታችሁ ተቀምጣችኋል ሲላቸው “እኛ ባሪያዎችህ ሁላችን ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ጌታችን እንደተናገረ ወደ ጦርነት እንሔዳለን” (ዘኁ. ፴፪፡፳፯) የሚል መልስ ሰጥተውታል። በዓለም ላይ ሰላም ሲታጣ  አገራት ሰላም አስከባሪ ኃይል በመላክ ሰላምን በፈረስ አንገት፣ በጦር አንደበት ሊያመጧት ይሻሉ። የተከሠተውን የሰላም እጦት ወደ ነበረበት ለመመለስ ጦርነት ያውጃሉ። ሰላምን የሚሹ ሁሉ ለጦርነት እንዲዘጋጁ ዐዋጅ ይነግራሉ። ሰላም የጦርነት አለመኖር ቢሆንም የሚለካው በውጤቱ ነውና የተባለው ሰላም እስከሚመጣ ሕዝቡ በጦርነት ይሳተፋል። ይህ የዕለት ከዕለት የየአገራት አነዋወር መገለጫ ነው።

ምክንያታቸው ምንም ቢሆን ጦርነቶች የሚካሔዱት የጋራ ትውውቅ እንኳን በሌላቸው አካላት መካከል የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው። ዣን ዥሮዱ የተባለ ፈረንሳያዊ ደራሲ እንደ ተናገረው በአብዛኛው ጦርነት እርስ በርሳቸው በሚተዋወቁና በሚጠላሉ ሰዎች ውሳኔ ለመጠላላት ቀርቶ ለመተዋወቅ እንኳ ዕድል በሌላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ ነው። በጦርነቱ ሒደት በውጊያው ዐውድ ላይ የሚገኙት የጦርነትን አስከፊነት ስለሚያውቁት ጦርነትን ይጸየፉታል፤ ይጠሉታል። ከዐውደ ውጊያው ርቀው ያሉት የጦርነቱ ዘዋሪዎች ደግሞ ሞት ከደጃቸው እንደሚደረስ በመዘንጋት የጦርነቱን መግፋት ይፈልጉታል። ጦርነቱ በአንደኛው አሸናፊነት ካልተጠናቀቀ ደግሞ ‘ወታደሩ ያልቃል፤ መሪ ይታረቃል’ በሚለው ብሂል ከጦርነት በፊት ሊሔድባቸው ይገባል ተብለው በዐዋቂዎች የተነገሩ የዕርቅና የሰላም መንገዶች አማራጭ ተደርገው ሲወሰዱ ይታያል።

ጦርነት አስከፊ ነው። የሚጎዳው በጦርነት የተሰለፉ ወታደሮችን ብቻ ሳይሆን ሕፃናትን እና አዛውንቶችን ጭምር ነው። ጦርነት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው። አገር ሊያፈርስ፣ ሃይማኖት ሊያረክስ ከመጣ ጠላት ጋር እንጂ ከማንም ጋር ጦርነት ሊኖር አይገባም ነበር። ይህም ሆኖ ሰው ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊና ሕጋዊ መብት ስላለው አንድ ሰው፣ ማኅበረሰብ፣ ሕዝብ ወይም አገር የተከፈተበትን ጦርነት ለመመከት ወደ ጦርነት ሊገባ ይችላል። ወደ ጦርነት ከመግባት በፊት ግን ሁሉንም የሰላም በሮች ሁሉ ማየት ይገባዋል። ጦርነትን እንደ አንድ የሥራ ዕቅድ መያዝ ተገቢ አይሆንም። የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ ብሔራዊና ዓለም አቀፍ የሰላምና ደኅንት ተቋማትም ሰላምን ለማስከበር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

በተለይም ዓለም ከሚሰጠው ሰላም የተለየው ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ የምታድለው ቤተ ክርስቲያን ሰላምን በእጅጉ ልትሰብክና ወደ ጦርነት የሚገቡ አካላትን ከጦርነት ባሻገር ያሉ መፍትሔዎችን እንዲያማትሩ ልትመክር ይገባታል። ይህን የሰላም መንገድ እውን ማድረግ ግን ቀላል ተግባር አይደለም። መታመን፣ መከበርና መፈራት ይጠይቃል። ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ። እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም” (ዮሐ. ፲፬፡፳፯) ብሎ የቤተ ክርስቲያን ሰላም ከዓለሙ ሰላም የተለየ መሆኑን ነግሮናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሰላም የገለጠው “አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ፣ ልባችንን እና አሳባችንን የሚጠብቅ የእግዚአብሔር ሰላም” በማለት ነው (ፊል. ፩፡፪)። እንዲህ ዐይነቱ ሰላም በቀላሉ አይገኝም። ፈተናውም ከባድ ነው። የዓለሙ ሰላም ግን እግዚአብሔር በኤርምያስ አድሮ “የሕዝቤን ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን፣ ሰላም ሰላም ይላሉ” (ኤር. ፮፡፲፬) በማለት የተናገረው ዐይነት ነው።

“ሰላምን የሚፈልግ ለጦርነት ይሰናዳ” እንደሚለው የዓለሙ ብሂል “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” (ኤፌ. ፬፡፫) የተባሉ ክርስቲያኖች በተለይም የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሰላም ይመጣ ዘንድ ከሥጋዊ ፍላጎታቸውና መሻታቸው ጋር ጦርነት ሊገጥሙ፣ ሊያሸንፉና ለዓለሙ የሚተርፍ ሰላምን ሊሰብኩ ይገባል። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳያስ “የምሥራች የሚናገር፣ ሰላምንም የሚያወራ፣ የመልካምንም ወሬ የምሥራች የሚናገር፣ መድኀኒትንም የሚያወራ፣ ጽዮንንም አምላክሽ ነግሦአል የሚል እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው (ኢሳ. ፶፭፡፲፪) በማለት የሰላም መልእክተኞችን መልካምነት ነግሮናል።

የቤተ ክርስቲያን አባቶች የቤተ ክርስቲያን ዓላማና ግብ የሆነውን ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም የመስጠት ተልእኮ በአግባቡ ቢወጡ በዓለም ላይ የምናያቸው ችግሮች ሁሉ ይቃለሉ፤ ምናልባትም ይጠፉ ነበር። ይህን ሥራ ለመሥራት ብቁ የሚሆኑት ግን የራሳቸውን ጦርነት ማሸነፍ የቻሉት ብቻ ናቸው። ከሥጋዊና ደማዊ ትግል ወጥተው በሰማይ ቦታ ካላቸው ርኵሳን መናፍስት ጋር የሚያዋጉ ብሎም የሚያሸንፉ መሆን አለባቸው። ዓለምን የናቁ እንጂ በዓለሙ የተሸነፉ መሆን የለባቸውም። እነዚህ የተናገሩት ብቻ ሳይሆን ዝምታቸው ይሰማላቸዋል። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በነበራት ክብርና ተሰሚነት ልክ ሰላም የማምጣት፣ ዕርቅ የማውረድ፣ መስተጻርራንን የማስታረቅና አገራዊ ሰላምን የማስከበር ዙፋን ላይ የማስቀመጥ ኃላፊነት በአባቶቻችን እጅ ላይ ነው። የሚናገሩትን የሚኖሩ፣ የማይኖሩትን የማይናገሩ፣ የሚፈሩና የሚከበሩ፣ በሕዝብ የሚታመኑና ለአገር ሰላም የሚለምኑ አባቶችን ፈልጎ ማግኘት የሚያሻበት አጣብቂኝ ጊዜ ላይ መሆናችን ሊታወቅ ይገባል። እንዲህ ዐይነት የአገር ዋርካዎች በሌሉን መጠን የኀጢአተኞችን ሰላም በማየት በዓመጸኞች ድርጊት በመቅናት ሰላምን በመግፋት፣ ሽማግሌዎችንም በመጥላት የሚኖሩት ጥቂት አይሆኑም።

የምንንኖርበት ዓለም ብርቱ ሰልፍ የሚካሔድበት መሆኑን በሕይወቱም፣ በትምህርቱም የነገረን ትዕግሥተኛው ኢዮብ “አንድ ሰው በሰላም ተዘልሎ ሲቀመጥ በሙሉ ኃይሉ ሳለ ይሞታል” (ኢዮ. ፳፩፡፳፫) ይለናል። ገዳይ ጦርነት ብቻ ሳይሆን የሚገድል ሰላምም እንዳለ ከዚህ ቃል መረዳት እንችላለን። ለዓለሙ መድኀኒት እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ የተመረጡ አባቶች ለመድኀኒትነት የሚያበቃቸውን ግብር ገንዘብ ለማድረግ የራሳቸውን ጦርነት በድል ካልተወጡ ሞት ነው። ለሕዝቦች ሰላምና አንድነት ካልጸለዩ፣ ጦርነት የሚጎስሙትን ካልገሠጹ፣ እምቢተኞችን ካላወገዙ፣ እንደ ሰማዕተ ጽድቅ ቅዱስ ጴጥሮስ ለእውነትና በእውነት ለመንጋዎቻቸው ካልቆሙ ሞት ነው።

ስለሆነም የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዋና ስብከቷ ሁሉ “ከክፉ ሽሽ መልካምን አድርግ፤ ሰላምን እሻ፤ ተከተላትም” (መዝ. ፴፬፡፲፬) የሚል ነውና በአገራችን ሰላም እንዲመጣ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ድርሻ ልትወጣ ይገባል። ሐዋርያው ያዕቆብም “የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል” (ያዕ. ፫፡፲፰) እንዳለ የሰላም ዘር መዝራት ይገባል። ይህን ማድረግ ባልተቻለ መጠን “ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፣ መልካምም አልተገኘም’ የሚሉት ብዙ ይሆናሉ። ከእግዚአብሔር ጽኑ ቁጣ የተነሣም የሰላም በረት ይፈርሳልና ከቁጣው እንዲመለስልን ከማሳሰብ ጋር “ምሕረትና እውነት ተገናኙ፣ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ” (መዝ. ፹፭፡፲) የምንልበት ጊዜ እንዲቀርብ መሥራት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው። ሰላም እንዲመጣ መሥራት እና ማስታረቅ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ የሰጠው ሥልጣን ነው። “የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (ማቴ. ፭፡፲)። በተለይም የቤተ ክርስቲያን አባቶች የማስታረቅ ሥልጣናቸው ሰውን ከሰው ብቻ ሳይሆን ሰውን ከራሱ እና ከእግዚአብሔር ጭምር ነው። ስለሆነም ይህን ሥልጣን በማቃለል፣ በተንኮልና በሴራ እርቅ የሚያደርጉ በራሳቸው ላይ የእሳት ክምር ይጨምራሉና ሊጠነቀቁ ይገባል። አባቶችም ይህን ኃላፊነታቸውን ሲወጡ እግዚአብሔር በሰጣቸው ጥበብ “ሲታጠቡ ከክንድ፣ ሲታረቁ ከሆድ” የሚለውን ብሒል የተከተለ መሆኑን መመርመር አለባቸው። “በዘመኑ ፍጹም ሰላምን እግዚአብሔር ይሰጣት ዘንድ እግዚአብሔርን ስለምትወድ ስለ አገራችን ኢትዮጵያ እንማልዳለን” (በእንተ ቅድሳት)።

መልካም በዓል