ለክፉዎች መድኃኒት የሚሆን የጵጵስና አገልግሎት
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በክፋቱ በሚታወቀው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመነ መንግሥት ብፁዕ አባ ጢሞቴዎስ የሚባሉ በሀገረ ግብፅ የእንስና ወይም እንዴናው ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስ ነበሩ። የወንጌል ገበሬ ስለነበሩ በሀገረ ስብከታቸው እየዞሩ ወንጌለ መንግሥትን ለሰው ልጅ ሁሉ ያስተምሩ የነበረው ሳይታክቱ ነበር። የኤጲስ ቆጶሱ ዞረው ወንጌልን ማስተማራቸው የጠቅላይ ግዛቱን ገዥ ዕለት ዕለት ያበሳጨው ነበር። ሀገረ ገዥውም ስለተበሳጨ አስጠርቶ “በክርስቶስ ማመንህንና ወንጌልን ዞረህ ማስተማርህን ተው” በማለት አስጠነቀቃቸው (መጽሐፈ ስንክሳር ኅዳር ፲፫ የሚነበበው)።
አባ ጢሞቴዎስ ግን ድሆችን ከመደገፍ፣ ከማስተማር እና ከማጽናናት እንዲሁም አሕዛብን ከማስተማር የሚያቆሙት ሲሞቱ ብቻ መሆኑን እቅጩን ነገሩት። ከድርጊታቸው ባለመቆጠባቸውና ትእዛዙን ባለመፈጸማቸውም ገዥው ይዞ አሠራቸው። ማሠር ብቻ ሳይሆን ልዩ ልዩ ጽኑ ሥቃይ ያደርስባቸው ነበር። “መከራ ቢሉ ኃጢአት ሲበዛ ጸጋ እግዚአብሔር ይበዛልና (ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ) ቅዱሱ አባት በመከራ ውስጥ እያሉ ልዩ ልዩ ምሥጢራት ስለተገለጡላቸው አገረ ገዥውን ከመጥላት ይልቅ በጣም ይወዱት ነበር። ሀገረ ገዥው ለዚህ መከራ ባይዳርገኝ ኖሮ ይህ ሁሉ ጸጋ ከየት አገኘው ይሉም ነበር (ዝኒ ከማሁ)።
መከራን በደስታ መቀየር ልማዱ የሆነው አምላካችን ክፉውን ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስን አሳልፎ ደጉን ንጉሥ ቈስጠንጢኖስን በሮም አነገሠው። ቈስጠንጢኖስም የታሠሩት ክርስቲያኖች እንዲፈቱ፣ የተሰደዱት አባቶች ወደ መንበራቸው እንዲመለሱ፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያን እንዲከፈቱ፣ በአንጻሩ ደግሞ ተከፍተው የነበሩ አብያተ ጣዖታት እንዲዘጉ አደረገ።
በንጉሡ ዐዋጅ መሠረት አባ ጢሞቴዎስም ከእሥር ተፈትተው ወደ ሀገረ ስብከታቸው ወደ እንስና ወይም እንዴናው ተመለሱ። ከመንበረ ጵጵስናቸው እንደ ደረሱም የሀገረ ስብከታቸውን መነኰሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት እና ምእመናን ሰብስበው ለሀገረ ገዥው እንጸልይለት አሏቸው። ሰዎችም ወደ ቅዱሱ አባት ቀርበው እንዴት ላሰቃየህ ሰው እንጸልይለት ትላለህ አሏቸው? አባ ጢሞቴዎስም “እርሱ ባያሰቃየኝ ኖሮ እግዚአብሔርን አላገኘውም ነበር። በገዥው በመሰቃየቴም እግዚአብሔር የሚያስገርሙ ምሥጢራትን ገልጦልኛል” (ስንክሳር ዘኅዳር ፲፫) በማለት መለሱላቸው።
ክርስቲያኖች በቅዱሱ አባት መሪነት በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ከማታ እስከ ጠዋት ድረስ ሲጸልዩ ማደር ጀመሩ። የቅዱሱን አባት ድርጊት የተመለከቱ ሰዎችም ወደ ሀገረ ገዥው ሔደው “አባ ጢሞቴዎስ እየጸለየልህ ነው” አሉት። በዚህ ጊዜ ገዥው በጣም ተገረመ፤ “የክርስቲያኖች ሃይማኖት እንዲህ ነውን?” በማለት ተደነቀ። ከዚያም ወደ አባ ጢሞቴዎስ መልእክተኛ ልኮ አስወስዶ ስለ ሃይማኖቱ ጠየቀው። ቅዱሱ አባትም በየዋህነት ሲያጫውተው ሀገረ ገዥው ልቡ ተነካ።
በጨዋታቸው መካከል ሀገረ ገዥው አባ ጢሞቴዎስን “እኔ እኮ ያን ያህል ሥቃይ ስላጸናሁብህ የምትረግመኝ እንጂ የምትጸልይልኝ አልመሰለኝም ነበር” አለው። አባ ጢሞቴዎስም መልሶ “ክርስቲያኖች ማንንም አይረግሙም” በማለት መለሰለት። ቅዱሱ አባት ይህን የመለሰው በቅዱስ ወንጌል “የሚረግሟችሁን መርቁ፣ ክፉ ለሚያደርጉባችሁም ጸልዩ” (ማቴ. ፬፡፵፬-፵፭) የሚለውን በተግባር በመግለጥ ነው። ሀገረ ገዥውም “ስለሃይማኖትህ አስተምረኝ” በማለት ስለጠየቀው መሠረታዊውን ትምህርተ ሃይማኖት አስተምሮ አጠመቀው። ከዚያም ሀገረ ገዥው ስለ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በደንብ ተማረ። በመቀጠልም አገር ማስተዳደሩን ትቶ የነበረውን ገንዘብ ሁሉ ለድሆች ሰጥቶ በአባ ጢሞቴዎስ ሥር መኖር ጀመረ። አባ ጢሞቴዎስም ኅዳር ዐሥራ ሦስት ቀን ዐርፎ ወደ አምላኩ ሔደ (መጽሐፈ ስንክሳር)።
በዚህ ዘመን ለኤጲስ ቆጶስነት የሚሾሙ አባቶችም እንደ አባ ጢሞቴዎስ ለአሕዛብ ብርሃን፣ ለክፉዎች መድኃኒት የሆነ ተግባር የሚፈጽሙ መሆን ይገባቸዋል። ክርስቲያኖችም የእነርሱን በጎ ምግባር አርአያ አድርገን መልካም ነገር ከሠራን በሃይማኖት ያሉትን ከማጽናት በተጨማሪም ሌሎችን ስበን የሃይማኖት ሰዎች እናደርጋቸዋለን። ክርስቲያኖች ለሚገድሉን ልንጸልይላቸው እንደሚገባ ቅዱሱ አባት በወንጌል የተጻፈውን በተግባር ገለጠው። አርያኖስን ወደ ክርስትና አስገብቶ በሰማዕትነት እንዲያርፍ ያደረገ አምላክ ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ክርስቲያኖችን ለመግደል፣ በዘመናችን ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን በቋንቋ ለመከፋፈል እንቅልፍ የሚያጡትን ሊመልሳቸው እና ምርጥ ዕቃ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ማመን ይገባል።
አምላካችን እግዚአብሔር ከአራዊት የከፋ ጨካኝ የነበረን አንድ ሰው በጸጸት ልቡ እንዲነካ አድርጎ ተጋድሎው ለዓለም እንዲተርፍ እንዳደረገው በየካቲት ወር የሚነበበው ስንክሳር ይነግረናል። ባለጸጋ መሆኑን አውቀው ሊገድሉት ሔደው የነበሩትን አሥራ ሦስት ሽፍቶች በምግባሩ ስቦ፣ በተአምራት አሳምኖ ወደ ክርስትና ያስገባቸው የአስከናፍር ደግነትም (ስንክሳር ዘኅዳር) ለዚህ ዘመን ምእመናን ብቻ ሳይሆን ለሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳትም አርአያ የሚሆን በመሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ለሢመት የሚገቡትን አባቶች እንዲመርጡ ኃላፊነት የተጣለባቸው ጳጳሳት ለቤተ ክርስቲያን ውለታ ዋሉላት የሚባለው እንደነዚህ ያሉትን አባቶች መርጠው በተጓደሉ አህጉረ ስብከት እንዲሾሙ ኃላፊነት ለሰጣቸው አካል ሲያቀርቡ ነው።
ዋቢ መጻሕፍት
ሊቀ መዘምራን ላእከ ማርያም (ተርጓሚ)። መጽሐፈ ስንክሳር ከመስከረም እስከ የካቲት። ፲፱፻፱፫ ዓ.ም።
ቅዱስ ኤፍሬም። ውዳሴ ማርያም። ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት።
የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር። መጽሐፍ ቅዱስ የብሉያትን የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት። ፳፻ ዓ.ም።