መዋቅሩ ለወንጌል ወይስ ወንጌሉ ለመዋቅሩ?

መዋቅሩ ለወንጌል ወይስ ወንጌሉ ለመዋቅሩ?

መዋቅሩ ለወንጌል ወይስ ወንጌሉ ለመዋቅሩ?

ኤፍሬም እንዳለ የተባለ ደራሲ “እንጨዋወት” በሚል ርእስ ያዘጋጀው ትኩረቱን ማኅበራዊ ሂስ ላይ ባደረገው መጽሐፍ አንድ ታሪክ እናገኛለን። ታሪኩ እንዲህ ነው። አንድ ድርጅት ከከተማ ወጣ ባለ ቦታ ያከማቻቸው አሮጌ መኪናዎች፣ የወላለቁ ብረታ ብረቶች እና ከጥቅም ውጭ የሆኑ የተለያዩ ቁሰቁሶች ነበረው፡፡ ክምችቱ ያለ ጥበቃ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል፡፡ በኋላ ግን የድርጅቱ ባለ ሥልጣናት መጠበቅ አለበት ብለው ስላመኑ ሁለት የጥበቃ ሠራተኞች እንዲቀጠሩ ወሰኑ።

 

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጥበቃዎቹ በሰዓት መግባት መውጣታቸውን ከዋናው መሥሪያ ቤት ሆኖ በርቀት መከታተል እንዳልተቻለ ዘገባ ቀረበ፡፡ እነርሱን በፈረቃ የሚከታተሉ ሁለት ሰዎች ተቀጠሩ፡፡ ከቆይታ በኋላ ለአራቱ ሠራተኞች ደመወዝ ከፋይ እንደሚያስፈልግ ታመነበትና ተቀጠረ፡፡ ከዚያም የሰው ኃይል አስተዳደር መኖር አለበት ተብሎ እርሱም ተቀጠረ፡፡ የሰው ኃይል አስተዳደሩ ጸሐፊ ስላስፈለገው ጸሐፊ ተጨመረ፡፡ ይህን ሁሉ ያለ ሥራ አስኪያጅ ማስተዳደር እየከበደ ስለመጣ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተሾመለት፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ቀስ በቀስ ብዙ ሠራተኞች ያለው ድርጅት ሆነ፡፡

 

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዋናው ድርጅት ትልቅ በጀት የሚጠይቅ ነገር ግን ምንም ገቢ የማያመነጭ ድርጅትን ተሸክሞ መቀጠል እየከበደው ሄደ፡፡ ስለዚህ የሠራተኛ ቅነሳ መደረግ እንዳለበት ተወሰነ፡፡ የሚገርመው መጀመሪያ እንዲቀነሱ የተወሰነባቸው መጀመሪያ የተቀጠሩት የጥበቃ ሠራተኞች መሆናቸው ነው፡፡ ለድርጅቱ ህልውና ምክንያት የሆኑት እነርሱ መሆናቸው ተዘነጋ፡፡ ብዙ ሰው የያዘው ድርጅት ዋና ዓላማ የተከማቸውን አሮጌ ቁሳቁስ መጠበቅ ነበር፡፡ ኋላ ግን የዓላማው አስፈጻሚዎች ዋጋ ተረሳና ጥበቃዎቹ ቀዳሚ ተባራሪ ሆኑ፡፡

 

በቤተ ክህነት ሲፈጸም የሚታየው ነገር ከዚህ ድርጅት ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ሺሕ ዘመናት ሁል ጊዜ አዲስ  የሆነውን ቅዱስ ወንጌልን እየሰበከች ኖራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከጥንትም ለወንጌል አገልግሎት የተዘጋጀ ጽኑ ፍቅር እና መንፈሳዊ ቁርጠኝነት የሚታይበት ሥርዐት ነበራት፡፡ ነገር ግን ዘመናዊ የቤተ ክህነት መዋቅር ከመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዘመን በኋላ ነው መደበኛ በሆነ አደረጃጀት የተዋቀረው ( ስማቸው ንጋቱ፣ 2013 ዓ.ም፣ 199)፡፡ ቤተ ክህነቱ የተዋቀረው ወንጌለ መንግሥትን ለሰው ልጅ ሁሉ ለማድረስ ነው፡፡ መዋቅሩ ያስፈለገው ቤተ ክርስቲያን ለቆመችለት ዋነኛ አገልግሎት አጋዥ እንዲሆን ነው።

 

ዛሬ ቤተ ክህነቱን ከተቀዳሚው የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ጋር እንዳይራመድ እንቅፋት የሚሆኑ ምንደኞች ወርረውታል፡፡ ወንጌልን ማስተማር የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ተልእኮዋ መሆኑን ከመጻሕፍት ሆድ፣ ከመዛግብት ገጽ እናገኘው እንደ ሆነ እንጂ በቤተ ክህነት እንዲያገለግሉ ከተመደቡ ሰዎች ልብ ውስጥ የተጻፈ አይመስልም፡፡ ሹመት፣ ደመወዝ፣ መኪና እና ቤት የሚያማርጡ፣ የምእመናን ቍጥር በቅሰጣና በስደት መቀነሱ የማያስጨንቃቸው ወረውታል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የሚፈልጓት ለደመወዛቸው እንጂ  እንዴት ውላ እንዳደረች አይጨነቁም። ለምእመናን የሕይወት ቃል የሚመገቡባት ሰማያዊ መዓድ፣ የቃልን ወተት የሚጠጡባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለምንደኞች የማትነጥፍ  ጥገት ሆናለች።

 

ቤተ ክርስቲያን በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ስትሆን ተልእኮዋም  የሕይወትን ቃል ለዓለም ሁሉ ማዳረስ ነው፡፡ የሰሙት እንዲያምኑ፣ ያመኑት ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደው፣ በመልካም ምግባርና ትሩፋት አጊጠው የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ወራሾች እንዲሆኑ ማጽናት። ከአናጎንስጢስ ጀምሮ እስከ ጳጳሳቱ “በጎቼ፣ ጠቦቶቼና ግልገሎቼ” በማለት ጌታችን የጠራቸው ምእመናንን መጠበቅ ያለባቸው መሆኑን ረስተውታል።

 

ለቤተ ክህነቱ መዋቅር አንቀሳቃሽ የሆኑ ምእመናን ተረስተዋል፡፡ የሚፈለጉት ጥላ ሲዘቀዘቅ ገንዘብ እንዲሰጥ ብቻ ነው፡፡ ምእመኑን የሚፈለጉት የደብሩ አለቃ ጓዳ ወይም  በአስተዳደር መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ የሥም አገልጋዮች ኪስ ሲራቆት ነው። በጎቹን፣ ጠቦቶቹንና ግልገሎቹን ዓለም ያስነሣችው ማዕበል ሲያናውጣቸው ፣ ዕረፍት የለሽ ሩጫ የሚጠይቀው የዓለም ኑሮ ሥነ ልቡናቸውን ሲያውከው ፈጥነው ደርሰው የሚያረጋጉ ጥቂት ናቸው፡፡ ከልጆቻቸው ጉሮሮ ነጥቀው መባ ሰጥተው፣ ድንጋይ ተሸክመው፣ ባለሥልጣናትን አድሏዊ አሠራር እና ማዋከብ ተቋቁመው በሚተክሏት ቤተ ክርስቲያን በሚሾሙ ሰዎች ምግባረ ብልሽነት፣ ሙዳየ ምጽዋት በሚያራቁቱ ምንደኞች ተማረዋል፡፡

 

ሠራኤ ሕግ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ሕግ አፍራሾች እንደ ሊባኖስ ዛፍ ከፍ ከፍ ብለው ሲታዩ  መንፈሳቸው የሚታወክ ምእመናን ብዙ ናቸው፡፡ በተረበሸ መንፈስ ከአምላካቸው ጋር የኅሊና ሙግት ሲገጥሙ ዐይናቸውን ለጽድቅ በተሰለፉት እውነተኛ ጳጳሳት እና ካህናት ላይ እንዲያደርጉ መንገድ የሚያሳያቸው ከወዴት አለ? በአንድ ሰው ነፍስ መመለስ ታላቅ ደስታ የሚደረግባት የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳያ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን የሚመሩ ጳጳሳት እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በመከራቸው ሰዓት አልደረሱላቸውም፡፡ አንዳንድ ካህናት፣ ሰባክያትና ጳጳሳት የሚያሳዩት ምግባር የጎደለው ድርጊት  ብዙዎች ጥያቄ እንዲያነሡ ያደርጋል። የአገልጋዮች ድርቀት በቤተ ክርስቲያን ላይ ከባድ ፈተና ደቅኗል፡፡ ይህ ሁሉ ለምን ሆነ? ብለን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን  ወደ ራሳችን በመመልከት ለተበላሸው አሠራር የእያንዳንዳችን ድርሻ ሊኖር እንደሚችል መረዳት  ይኖርብናል፡፡

 

ቤተ ክህነቱ አባቶቻችን በተጓዙበት የጽድቅ ፍኖት በሚጓዙ አገልጋዮች ድርቅ ተመትቷል፡፡ ለዚህ ድርቅ የተዳረግነው እውነተኛ አገልጋዮችን ለማገዝ እና የተበላሸውን አሠራር ለማረም ዳተኛ በመሆኑ ነው።  ችግሮች የበዙት ልጆቿ ግዴለሽነት ምክንያት እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ከግዴለሽነት አዚም በመውጣት አገልግሎቱን በአስተማማኝ መሠረት ማቆም ይገባል። ቤተ ክህነትን ከምንደኞች መሻኮቻነት ነፃ ማድረግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሚገባ የሚወጡ የወንጌል መልእክተኞች ብቻ እንዲያገለግሉበት ማድረግ ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው።