ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳትና የምእመናን ሱታፌ
የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምእመናንን ማእከል ያደረገ ነው። ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን የሰጣቸው ዋናው ትእዛዝ “አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸውና ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው” (ማቴ. 28፡19-20) የሚል ነው። ስለሆነም ሐዋርያትና በሐዋርያት እግር የተተኩት ሐዋርያውያን አበው፣ ዐቃብያነ እምነት፣ ሊቃውንት በአጠቃላይ በየዘመኑ የተነሡ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዋና ግብራቸው ይህን ታላቁን ተልእኮ መፈጸም ነበር። ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ለሐዋርያት ለሦስተኛ ጊዜ በተገለጠላቸው ወቅት ስምዖን ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ትወደኛለህን? ብሎ እየጠየቀ የሰጠው ትእዛዝም በተመሳሳይ “ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ” (ዮሐ. 21፡15-17) የሚል ነው። ቅዱስ ጳውሎስም “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጰሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (ሐዋ. 20፡28) በማለት ተናግሯል። ከእነዚህ ትእዛዝት መረዳት እንደሚቻለው ጳጳሳት በመንጋው ላይ እንዲሾሙ የሚመርጣቸው መንፈስ ቅዱስ መሆኑንና ዋና አገልግሎታቸውም ምእመናንን ማስተማር፣ መጠበቅ፣ ለሕይወታቸው መጠንቀቅ መሆኑን ነው። ይህን ግብር በአግባቡ ለመወጣት ደግሞ የሚሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት በዕውቀታቸውና በሕይወታቸው የተመሰከረላቸው፣ እንደ አብርሃም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኙ፣ እንደ ነቢዩ ዳንኤል በፊቱ ቅንነት የተገኘባቸው መሆን አለባቸው። በአጭሩ በመንጋው ላይ ሊሾሙለት እንጂ ሊሾሙበት አይገባም።
ምእመናን መንጋውን ለመጠበቅ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልግል በሚመረጡ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ላይ ያላቸው ሱታፌ ከፍተኛ ነው። ተሿሚዎች ይገባቸዋል ተብለው ለሹመቱ ብቁ መሆናቸው የሚረጋገጠው በምእመናን ምስክርነት ነው። ምእመናን በሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት የነበራቸው ተሳትፎ የመምረጥና የምስክርነት ብቻ ሳይሆን በመመረጥም ጭምር ነበር። ይህንም በእነ ዲሜጥሮስ ታሪክ ማስታወስ የምንችለው ነው። ጳጰሳት ድናግላን እንዲሆኑ ውሳኔ ያገኘው በቀድሞው አልቫሪዝ (የአሁኗ ግራናዳ) በ306 ዓ.ም በተደረገ አካባቢያዊ ጉባኤ ሲሆን በጉባኤው “ከዲያቆናት እስከ ጳጰሳት ያሉት ሁሉም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ደናግላን መሆን አለባቸው” በሚል ተወስኖ ቆይቶ በጉባኤ ኒቂያ የዲያቆናትን እና ቀሳውስትን በማሻሻል “ጳጳሳት ደናግላን መሆን አለባቸው” የሚለው እንዲጸድቅ ተደርጓል።[1] ምእመናን ሱታፌያቸው በምስክርነት ላይ ብቻ የቆመ አይደለም። በቀሌምንጢጦስ ቀኖና እንደተገለጸው “ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ እንዲሾም የመረጡት ሰው ሹመቱ የሚሰጠው በሀገረ ስብከቱ ሰዎች ስምምነት ይሁን”[2] ይላል። ኤጲስ ቆጶሱ የሚሾመው ለሕዝብ በቁዔት እንጂ ለግል ክብር ስላልሆነ የሚሾምበት ሀገረ ስብከት ሕዝብ ይገባቸዋል ብሎ ምስክርነት መስጠትና በአባትነት መቀበል አለበት። ይህ ካልሆነ ግን ክህነት ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ እንጂ ግላዊ ሥልጣን ስላልሆነ ሹመትን መፈለግ አይገባም።
በዚህ አግባብ ኤጲስ ቆጶሳት በየሀገረ ስብከቱ ሲሾሙ ምእመናን ሥነ ምግባራቸውን፣ ትምህርታቸውን መስክረውላቸው በአባትነታቸው ተቀብለዋቸው መሆን ይገባዋል። አስቀድሞ ከመመረጣቸው በፊት ስማቸውና አገልግሎታቸው ለሕዝብ ተገልጾ ምእመናንን በታችኛው የክህነት መዓርግ እያሉ ስለነበራቸው ሕይወት፣ አገልግሎት፣ ትጋት፣ ቅንነትና ከፍ ላለው መዓርግ ሊታጩ የሚገባቸው ስለመሆናቸው ሊጠየቁና በአባትነት ሊቀበሏቸው የሚችሉ መሆናቸው መረጋገጥ ይኖርበታል። ኤጲስ ቆጶስ ሹመቱን በገንዘብ፣ በልመና፣ በመደለል፣ በባለሥልናት አስገዳጅነት ያገኛት ከሆነ ከሹመት መሻር እንደሚገባው በሐዋርያት ሲኖዶስ ተገልጿል። ሹመቱ ሰማያዊት እንጂ ምድራዊት አይደለችም። ስለሆነም ከሥርዓት ውጪ በሆነ መንገድ ሊያገኛትም ሆነ ለወደደው ሰው በውርስ ሊያስተላልፋት አይችልም። ይህ የጸና የሹመት ሥርዓት በአኃት አብያተ ክርስቲያንም ሆነ በምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ዘንድ የሚሠራበት ነው።
ወደ አገራችን ስንመጣም ይህ ሥርዓት ሲፈጸም የቆየ መሆኑን እንመለከታለን። በተለይም ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከተቋቋመበት ከ1964 ዓ.ም ጀምሮ የነበረው ሲታይ አገልግሎቱ በካህናት፣ ሰንበት ትምህርት ቤት እና ምእመናን ሱታፌ የሚከናወን ሆኖ እናገኘዋለን። ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የአገልግሎት መዋቅሮች በእነዚህ ከሦስቱ አካላት ተዋጽዖ የተደራጀ ነው። ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ሕግጋቱ በሚሻሻሉበት ወቅት የሰንበት ትምህርት ቤትና የምእመናን ሱታፌ እየቀነሰ፣ የጳጳሳት ሥልጣን እየጨመረ እንዲሔድ ተደርጓል። ምእመናን በጳጰሳት ሢመት ላይ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ እየሆነ መምጣቱ፣ ስለ ትምህርታቸውና መልካም አርአያነታቸው የምእመናን ምላሽ ምን እንደሆነ ሳይጠየቅ ወደ ከፍተኛው መዓረግ የሚመጡ አገልጋዮች ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል። በዚህም ምክንያት ጵጵስና የእግዚአብሔር ጥሪ፣ መንጋውን ለመጠበቅ መሰጠት ሳይሆን እንጀራ ማብሰያና ምድራዊ ፍትወትን መፈጸሚያ እስከሚመስል ድረስ የሚናጠቋት እንዲበዙ ሆኗል። ቀደም ባለው ሥርዓት ምእመናን በሕይወታቸው አርአያነት እንዲሾሙላቸው የሚጠይቋቸው አገልጋዮች እኔ ለዚህ ኃላፊነት አልበቃም በማለት ሲሸሹና ሲርቁ የሚታየውን ያህል አሁን ደግሞ ሊሾሙ አይገባቸውም ተብለው በግድ ለመሾም የሚወዱ አካላት ተበራክተው ይታያሉ።
ምእመናን ቤታቸው በሆነች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጸንተው ለመኖር የሚሾምላቸውን አካል የማወቅ፣ የመምረጥ፣ የማይገባው መሆኑን ካወቁ ደግሞ ሊሾምብን አይገባም ብለው የመናገር ፈቃዱና ነጻነቱ ስላላቸው፣ ይህም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጸንቶ ሲሠራበት የኖረ ስለሆነ ይህ ሥልጣናቸው ሊከበርላቸው ይገባል። ይህ የሚሆነው ደግሞ ጳጰሳት ሲመረጡ ምእመናን በአስመራጭነት ሲወከሉ፣ የዕጩዎች ጥቆማ ላይ እንዲሳተፉ ሲደረግ እና በቀረቡት ዕጩዎች ላይ የሕዝበ ክርስቲያኑን አሳብ መቀበል ሲቻል ነው። ስለሆነም በቀጣይ በሚደረገው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ላይ ምእመናን ከአስመራጭ ኮሚቴ ጀምሮ ሱታፌ እንዲኖራቸው ማድረግ ከፍ ወዳለው መዓርግ ሊመጡ ያሉትን ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው፣ ፈቃደ ነፍሳቸውን ለእግዚአብሔር የሚያስገዙ መልካም አገልጋዮችን ለማግኘት ያግዛል። ጉቦ በመስጠት፣ በዝምድና፣ በልዩ ልዩ ጥቅም ኤጲስ ቆጶስነት የሚሹ አካላትን ለመከላከል ይጠቅማል። ለመንጋው የሚራሩ፣ ሕይወታቸውንና ቤተ ክርስቲያንን በመልካም የሚመሩ፣ ወንጌል የሚሰፋበትን ምእመናን የሚጸኑበትን ሥራ የሚሠሩ፣ ደሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ብለው በድፍረት ሹማምንትን ለመገሠጽ የሚችሉ አባቶችን ማግኘት የሚቻለው በዚህ መልክ የአሿሿም ሥርዓቱን ሁሉንም ያሳተፈ በማድረግ ነው። ይህ ካልሆነ ዘውግና ቋንቋን መሠረት በማድረግ በተዋቀረች አገር ውስጥ ከዚህ አካባቢ የተወለደ ለመሾም በሚል በስርዋጽ የሚገቡ አሳቦችን በመምዘዝ የእግዚአብሔርን ፈቃድና የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ በመዘንጋት ለወገኔ ይጠቅማል የሚለውን ወደ ማድረግ ሊያመራ ይችላል። ኤጲስ ቆጶስ የሚሾምበትን ሀገረ ስብከት ሕዝብ ባህልና ቋንቋ ቢያውቅ መልካም ነው። ግን ሕዝቡ ያለ ማንም መሪነት አስገዳጅነት ለዚህ ሹመት የሚበቃ መሆኑን መመስከርና በአባትነት መቀበል አለበት የሚለው መሠረታዊ መስፈርት ሆኖ መቀመጥ አለበት። ቋንቋውንና ባህሉን ማወቁ ቅሉ ጥቅሙ ምእመናንን በሚያውቁት ቋንቋ ለማስተማር እንጂ ቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ ተወካይ እንዲኖራቸው አይደለም።
ዋቤ
[1] መጋቤ ምሥጢር ስማቸው ንጋቱ፣ መጽሐፈ ሲኖዶስ ዘሐዋርያት የሀዋርያት ሲኖዶስ፣ 2012 ዓ.ም፣ ፋር ኢስት ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ገጽ 8-10
[2] ዝኒ ከማሁ ገጽ 319