ሦስተኛው የአህጉረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና የምርቃት መርሐ ግብር ተከናወነ።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት) ሐምሌ 21 / 11 / 2017 ዓ.ም

ሦስተኛው የአህጉረ ስብከቶች የሰ/ት/ቤቶች መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና የምርቃት መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ተከናውኗል። በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የሸገር ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የምስካየ ኅዙናን ገዳም የበላይ ጠባቂ እና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ፣ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋኒዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ በርናባስ የዋግህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ ፣ ዲ.ን ስንታየሁ ምስጋናው የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ተ/ም/ሰብሳቢ ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች ፣ መምህራነ ወንጌል ፣ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የሥራ አመራር አባላት ተገኝተዋል።

ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ባስተላለፉት መልእክት “ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ለ3 ዓመት ከ3 ወር ሐዋርያትን ከተለያየ ግብርና ክፍል መርጦ ካስተማራቸው በኋላ ሂዱና አስተምሩ በሀገር ሁሉ ቋንቋ አስተምሩ ብሎ እንዳዘዛቸውና አልጫ የሆነውን ዓለም በማስተማር እንዳጣፈጡ ሁሉ እናንተም በተማራችሁት ትምህርት ሄዳችሁ እንድታስተምሩ ፣ እንድታሰለጥኑ ፣ ፍሬ እንድታፈሩ” በማለት አባታዊ ምክርና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል።

ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም እንዲሁ “ከእግዚአብሔር የተላከ ከእግዚአብሔር የተመረጠ የአምላኩ የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል” በሚል ኃይለ ቃል ተነስተው እርሱን ለማገልገል የሚጠራ ማንኛውም አገልጋይ የእግዚአብሔርን ዓላማ ፣ ሐሳብ የእርሱን ዕቅድና እርሱ ለሰው ያለውን አምላካዊ ጥበብ ፣ መግቦት በፍጥረቱም ላይ እንዴት እንደሚሠራና ጥልቅ የሆነውን ፍቅሩን ሁሉ ይናገራል። ብለው ወደ መጣችሁበት ስንቃችሁን ያዛችሁ በመሄድ በሚገባ አገልግሎታችሁን እንድትፈጽሙ ይሁን በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈው ቋጭተዋል።

በዕለቱ ሌላኛውን አባታዊ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ በርናባስ የዋግህምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም እንዲሁ “በአባቶች ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ” የሚለውን የልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ቃል መነሻ አድርገው እናንተም በአባቶቻችሁ ፈንታ የተተካችሁ እንደመሆናችሁ አባቶቻችሁን መስላችሁ ቤተ ክርስቲያንን ልታገለግሉ ይገባል በማለት ለተመራቂ መምህራን የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወልደ ትንሣኤ “መጻሕፍት እግዚአብሔርን ወደ ማድነቅ ልብህን ይመሩታልና” በሚል ኃይለ ቃል በመነሣት የማደራጃ መምሪያውን መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ተ/ም/ሰብሳቢ ዲያቆን ስንታየሁ ምስጋናው በሥልጠናው ጊዜ አጠቃላይ የተከወኑ ተግባራትና በቀጣይ እንዲሠሩ የሚፈለጉ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል። ሠልጣኝ መምህራኑም የነበራቸውን የ15 ቀን ቆይታ የተመለከተ ዘገባ እና አቋማቸውንም እንዲሁ በተወካያቸው በኩል አቅርበው ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እጅ የዕውቅና የምስክር ወረቀታቸውን ተቀብለው የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።

ሥልጠናው ከሐምሌ 7 እስከ ሐምሌ 20 ቀን ድረስ በተከታታይ ለ15 ቀናት የተሰጠ ሲሆን በሥልጠናውም ላይ ከ30 አህጉረ ስብከት የተወጣጡ 209 መምህራን ተከታትለው አጠናቅቀዋል። ከነዚህም መካከል 106 ቀሳውስትና ዲያቆናት እንዲሁም 8 ሴቶች ይገኙበታል።

(የሰ/ት/ቤቶች አንድነት)