በትሕትና የሚሸሹት በፍቅር የሚሸከሙት

በትሕትና የሚሸሹት በፍቅር የሚሸከሙት

በትሕትና የሚሸሹት በፍቅር የሚሸከሙት

የክርስትናን ቀደምት ዘመናት ታሪክ ስናገላብጥ የአበው እና እማት የኑራቸው ፍሬዎች፣ የተጋድሏቸው ምስክሮች የሆኑ ድንቅ ድንቅ ታሪኮች ተመዝግበው እናገኛለን፡፡ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ብሎ ያዘዛቸውን አምላክ ቃል ሲተገብሩት እናያለን፡፡ ማስተዋል ለቻለ ትእዛዙን ጠብቀው፣ በፍጹም ልባቸው ፈጣሪያቸውን በማመን፣ በትሕትና፣ በመታዘዝ፣ ወንድማቸውን እንደ ራስ በመውደድ ቅድስናን ገንዘብ ሊያድርጓት ያለ መታከት የተጋደሉበት ፍኖት ትልቅ የወንጌል መዓድ ነው፡፡ ቢያነቧቸው ትምህርት የሚሆኑ፣ ቢተገብሯቸው በረከት የሚያሰጡ አስደማሚ የቅዱሳን ገድል ተከትበውባቸዋልና፡፡ ዛሬ አንዱን ቅዱስከድርሳንቀድተን እንዘክራለን፡፡

ለአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን መንበር በትሕትናው የታወቀው፣ በቅድስናው የተመሰገነው አባ አትናስዮስ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ይሾም ዘንድ በትውፊቱ መሠረት ምእመናን እና ካህናት በአንድ ድምፅ መረጡት፡፡ የጥቅምት ፱ ቀን ስንክሳር አትናስዮስ ከልጅነቱ ጀምሮ በምንኩስና እና በተባትሖ የኖረ ለበጎ ሥራ የማይደክም አባት እንደ ነበረ በመግለጽ ለታላቅ አባትነቱ ምስክርነት ይሰጣል፡፡ ኤጲስ ቆጶሳትም የፋርሱ ሊቀ ጳጳስ እልመፍርያን ከእነርሱ ጋር በአንጾኪያ ተገኝቶ አብረው በዓለ ሢመቱን እንዲያከናውኑ መልእክት ላኩበት፡፡ እርሱ ግን እጅግ ዘገየ፤ ከሃምሳ ቀናት በላይ ጠበቁት፤ አልመጣም፡፡ ከእርሱ ዘንድ ስለ መምጣት መቅረቱ መልእክትም እንኳ አልደርሳቸውም፡፡ መንበሩን ያለ ሊቀ ጳጳስ መተው ደግሞ መንጋውን ለተኩላ አሳልፎ እንደ መስጠት ሆነባቸው፡፡ እናም አባ አትናስዮስን የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ አድርገው ሹመውት ወደ አህጉረ ስብከታቸው ሔዱ፡፡

የአባ አትናስዮስ ሥርዐተ ሢመት ከተፈጸመ በኋላ ሲጠበቅ የውኃ ሽታ ሆኖ የቆየው አባ እልመፍርያን ወደ ሶሪያ ድንበር ደረሰ። ሥርዐተ ሢመቱ እርሱ በሌለበት የመከናወኑን ዜና በሰማ ጊዜ ነፍሱ በብስጭት ታወከች፤ እጅግ ተቆጣ፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር መሆን አለመሆኑን ለመመርመር የጥሞና ጊዜ አልወሰደም፡፡ ተበሳጨ፤ ከብስጭት ስሜቱ ሳይወጣ አትናስዮስን አወገዘ። የአትናስዮስን ስም በቅዳሴ የሚጠራውን ካህን፣ እንደ አባት የሚቀበለውን ምእመን ሁሉ አውግዞ ወደ ሀገረ ስብከቱ ተመለሰ፡፡

የፋርሱን ሊቀ ጳጳስ ቁጣና ውግዘት የሰማው አባ አትናስዮስ በእርግጥም ትሑት ነበርና ሰከን ብሎ ዐሰበ፡፡ ፍቅረ ቢጽን እና ፍቅረ ሢመትን በወንጌል ሚዛን ላይ አስቀመጣቸው፡፡ ያለ ኤጲስ ቆጶስነት ከክርስቶስ ጋር መኖር፣ ክርስቶስንም ማገልገል እንደሚችል ያውቃል፡፡ ኤጲስ ቆጶስነት ግን ፍቅር በሌለበት የሠመረ የአገልግሎት መሥዋዕት ለማቅረብ ዓቅም እንደማይኖራት ተገነዘበ፡፡ በእርሱ ሹመት ምክንያት በክርስቶስ ወንድሙ ከሆነው አባ እልመፍርያን ጋር ሊኖረው የሚገባው ፍቅር ስለታወከበት አዘነ፡፡ ሹመቱ ቀርቶበት ፍቅሩን ማትረፍ እጅግ ማለፊያ እንደ ሆነ አመነ፡፡ ፍቅረ ሢመትን ፆር አድርጎ ሊዋጋው እንደሚያገሣ አንበሳ በዙሪያው የሚዞረው የፍቅር ጠላት በአባ አትናስዮስ ልብ ባለው በጎ ሐሳብ አፈረ፡፡ ፍትወተ ሢመትን ካሸነፈው መነኮስ ከአባ አትናስዮስ ፊት መቆምም አልተቻለውም፡፡

ሊቀ ጳጳስ አትናስዮስ ረዳቱን ጠርቶ ‹‹ልቤ ትባርክህ ትመርቅህ ዘንድ ታዘዝልኝ፤ ሕዝቡ የፈለገኝ እንደሆን በዋሻ ሱባኤ ውስጥ ነው በላቸው፡፡… አንተም ሊሆን በሚገባ ሥራ ሁሉ እዘዛቸው፡፡ በእኔም ፈንታ እሠር ፍታ፤›› ብሎ ተማጸነው፡፡ መልካም እረኛ ነውና የመንጋውን ነፍስ በመልካም እረኛ እጅ አደራ ሰጠ፡፡ የረዳቱን እሺታ ካገኘ በኋላ አባ አትናስዮስ ጵጵስናውን ደብቆና አልባሌ ልብስ በመልበስ ራሱን ለውጦ ወደ ፋርስ በእግሩ ተጓዘ።

ፋርስ ሲደርስ ወደ ሊቀ ጳጳስ እልምፍርያን ቤት ሔዶ በአገልጋይነት እንዲቀበሉት ተማጸነ፡፡ በአወገዘው ሊቀ ጳጳስ ቤት ተቀጥሮ ውኃ እየቀዳ አዛባ እየጠረገ ማገልገል ጀመረ፡፡ ስንክሳሩ እንዴት ራሱን ስለ ፍቅር ሲል ከሊቀ ጳጳስነት ወደ አልባሌነት እንደ ቀየረ የአትናስዮስን መሳጭ ገድል ልብን በሚያስደምም አቀራረብ ይተርከዋል፡፡ የአትናስዮስን ቅን ታዛዥነትና መንፈሳዊነት የተመለከቱ ሁሉ የሚሰጡት በጎ ምስክርነት ሊቀ ጳጳሱ ዘንድ ይደርሳል፡፡ በእርግጥም መልካም አገልጋይነቱ ለሊቀ ጳጳሱ ብቻ ሳይሆን በመንበረ ጵጵስናው ላሉ መነኮሳት ሁሉ ነበር፡፡ በፍጹም ታዛዥነቱ የተነሣ አብዝተው ወደዱት እንደ መልአክም ተመለከቱት፡፡

ከረጅም ጊዜ የትጋት አገልግሎት በኋላ እልምፍርያን አንድ ነገር አስተዋለ፤ ይህ ሰው ለእርሱ ቤት ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይነት የሚያበቃ ጸጋ የበዛለት እንደሆነ፡፡ አትናስዮስን አስጠርቶም ማዕረገ ዲቁና ሊሰጠው መወሰኑን ነገረው። የትናንቱ ሊቀ ጳጳስ የዛሬው የፈረስ እና የበቅሎ ጋጥ ጽዳተኛ፣ የመነኮሳት ምግብ አብሳይ አትናስዮስ ግን በፍጹም ብሎ አስቸገረ። ከቤተ ክርስቲያናችን ምሥጢራት መካከል ክህነት ከማይደገሙት ውስጥ ነውና የሊቀ ጳጳሱ ውሳኔ የማይታለፍ ወጥመድ ሆነበት፡፡ ተጽእኖው ሲጠናበት ወደ ሊቀ ጳጳሱ ቀርቦ “አባቴ ይቅርታ አድርግልኝ ዲቁና አለኝ፤›› አለኝ አለው፡፡ እንዲህ አድርጎ የመጀመሪያ ክህነቱን ገለጠና ለሰባት ወራት በዲቁና እንዲያገለግል በታዘዘው መሠረት እያገለገለ ኖረ።

በአገልግሎቱ የተደሰተው ሊቀ ጳጳሱ እልመፍርያን ዳግም በቤተ መቅደስ ሆኖ ጠራውና ‹‹መንፈስ ቅዱስ ቅስና ሊሾምህ ጠርቶሃል፤›› አለው፡፡ አትናትዮስም እያለቀሰ እንዲተወው ማለደው፡፡ ነገር ግን ሊቀ ጳጳሱ ከውሳኔው እንደማይመለስ ሲያውቅ ይቅር እንዲለው እየተመጸነ ቅስናውን ገለጸለት፡፡ ጳጳሱም መነኮሳቱም አደነቁ፡፡

ከቆይታ በኋላ የአባ አትናስዮስ አስተዋይነት፣ ታዛዥነትና አገልጋይነት ለጵጵስና የተገባ ሰው ስለመሆኑ መነኮሳቱም፣ ሊቀ ጳጳሱም ሕዝቡም በአንድነት አመኑ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ እልመፍርያን ኤጲስ ቆጶስነት ሊሾመው ሲዘጋጅ ከፊቱ የተሠወረች ጵጵስናን ብቻ ሳይሆን የትናንት ስሕተቱን የሚያጋልጥ የታርክ ሐቅ ከተቀበረበት ቆፍሮ እያወጣ እንደነበር አልተረዳም፡፡ አልቅሶም ሆነ ሸሽቶ ማምለጥ እንደማይችል ያወቀው ትሑቱ አገልጋይ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ አትናስዮስ እርሱ መሆኑን በመግለጽ ደብቆት የቆየውን ሰሚውን ሁሉ ያስገረመ ምሥጢር ተናገረ።

አባ እልመፍርያን እጅግ ደነገጠ፤ አስኬማውን አውልቆ፣ በምድር ላይ ወድቆ፣ ከድንጋጤው የተነሣ ለረጅም ጊዜ ራሱን ስቶ ቆየ፡፡ በተነሣም ጊዜ በምሬት ራሱን ወቀሰ፤ በሠራው ጥፋት ምክንያት እንዳይጠፋ ጸሎት እንዲያደርጉለት በዙሪያው ያሉትን ተማጸነ፡፡ በአባ እልምፍርያ ትእዛዝ መሠረት ለአትናስዮስ ልብሰ ተክህኖ አለበሱት፣ አርዌ በትሩንና መስቀሉን በእጁ አስያዙት፤ በመንበር ላይ አስቀምጠው ከመንበሩ ጋር ተሸከሙት እና አኪዮስ አኪዮስ እያሉ ወደ መቅደስ አስገቡት፡፡ ቀድሶ  አቆረባቸው፡፡ ምድር በይቅርታ ድምፅ ተሞላች። ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን በኑሮው የመሰል ትሑት ደቀ መዝሙር አግኝታለችና ደስ አላት።

በመጨረሻም ሊቀ ጳጳሱ እልመፍርያን አባ አትናስዮስን የጵጵስና ልብስ አለበሰው፤ በበቅሎ ላይም አስቀመጠው። በቅሎዋን እራሱ አባ እልመፍርያን እየጎተተ፣ በጳጳሳት ታጅቦ ወደ አንጾኪያ ወሰዱት፡፡ አብሮት በበቅሎ እንዲቀመጥ ቢጠይቀው በእርሱ ምክንያት በእግሩ ያደረገውን ጉዞ ዐስቦ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ‹‹አንተ በእግርህ ወደ እኔ እንደ መጣህ እኔም በእግሬ ወደ አገርህ አደርስሃለሁ፤›› ብሎ አሻፈረኝ አለ በተፀፀተ ልብ ሆኖ፡፡ በመንገድ ላይ በደረሱበት ሀገር ሁሉ የአትናስዮስ የትሕትና ነገር እየተነገረ አትናስዮስን ወደ መንበረ ጵጵስናው አደረሰው፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሕዝብም ለአትናስዮስ ታላቅ ትዕግሥት እና ትሕትና ሰጥቶ በታላቅ ሞገስ ወደ መንበሩ ለመመለስ ያበቃውን እግዚአብሔርን እያመሰገነ ተቀበለው።

አባ አትናስዮስ ተሸንፎ አሸነፈ፡፡ በመሸነፉ በትሕትናው ሦስት አካላትን አሸንፏል፡፡ አስቀድሞ ዲያቢሎስን የጠብ አባት ነውና ለጠብ የሚበቃን መግፍኤ በበጎ ኅሊና አሸነፈ፡፡ በኋላም ራሱን አሸነፈ፤ ሥጋ እልከኛ ነውና። በመጨረሻም ላወገዘው በፍቅር ተገዝቶ ባርከኝ ብሎ እስኪንበረከክ ድረስ በፍቅር አሸነፈው።

በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሹመት የማይሻሙት የሚሸሹት፣ የእግዚአብሔር ጥሪ ሲሆን ደግሞ በፍቅር የሚሸከሙት ሓላፊነት ነበር፡፡ ጵጵስና በጌታ ወንድማማቾች የሆኑ አበው በውርስ ንብረት እንደሚጣሉ ወንድማማቾች የሚፋጠጡበት ሳይሆን በትሕትና አይገባኝም ብለው የሚርቁት ሢመት እንደ ነበር እንዲህ በኑሯቸው በተግባር ተመስክሯል፡፡

የአባቶቻችን የከበረች በረከታቸው፣ ድል የማትነሣ ረድኤታቸው ከእኛ ጋር ትሁን፡፡