ቤተ ክርስቲያን የአንድ አካል ብቻ አይደለችም፤ የካህናት፣የምእመናን እና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ጭምር እንጂ!

ከሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት የተላለፈ ወቅታዊ መልእክት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዋና ተግባሩ የሆነውን ሐዋርያዊ ተልእኮ በትጋት እና በስፋት ከማስፈጸም ይቅል በሥጋ ሐሳብ ተቀፍድዶ ጥንታዊቷን እና አማናዊቷን ቤተ ክርስቲያን በማይመጥን ደረጃ ላይ መገኘቱን የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተገንዝቧል። በተለይ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ አደረጃጀቱን ለማዘመን እና የሥራ አፈጻጸም ስልትን ከዘመኑ ጋር ለማጣጣም እንዲያስችል በተለየዩ ጊዜያት በባለሙያዎች ተጠንተው የተዘጋጁ መፍትሔ አመላካች ሰነዶች ልዩ ልዩ ምክንያት እየተለጠፈባቸው ተገፍተው መወገዳቸውን ታዝበናል። ስለሆነም አስተዳደራዊ ክፍተቱ በከፍተኛ ደረጃ የወለደው ችግር የአደባባይ ምሥጢር ሆኖ ተገልጧል::
ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ድክመት ጋር ተያይዞ እየተስተዋሉ ያሉ ዘርፈ ብዙ የውስጥ ችግሮች እና የሥነ ምግባር ጥሰቶች መንፈሳዊ አገልግሎቱን ያቀጨጩ፣ በመንፈሳዊነት ዐውድ አንገታችን ያስደፉ፣ በሌሎች ዘንድ ለስላቅ መንገድ የከፈቱ፣ ለትችት የዳረጉን የትውልዱ ስብራቶች እንደ ሆኑ ተገንዝበናል  ::

ቤተ ክርስቲያን ጥንተ ሥርዓቷን አስጠብቃ ዘመኑን የዋጀ መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ ብቃት ያለው አስተዳደር እና ሐዋርያዊ አገልግሎቷን የምትመራበት መሪ ዕቅድ ትግበራ እውን እንዲሆን በተደጋገሚ ስንጠይቅ ይሁንታ ባገኘ ጊዜም በዝግጅቱ በመሳተፍ በርካታ ዓመታትን በተስፋ አሳልፈናል:: በያዝነው ዓመትም በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታ በተሰጠው ዘላቂ መፍትሔ ቋሚ ኮሜቴ ውስጥ በመሳተፍ የሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ቅድመ ምልመላ መሥፈርት፣ የሀገረ ስብከት አደራጃጀት እና ምደባን አስመልክቶ አስፈላጊና ጠቃሚ የጥናት ሰነዶች እንዲዘጋጅ ተራድተናል። በዚህም ተገቢ ሰነድ ተዘጋጅቶ ቀርቧል።
የሁሉም የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለይ በዚህ አስጨናቂ ወቅት አባቶች የልጆችን ድምፅ በመስማት፣ እርስ በእርስ በመደማመጥና በመናበብ፣ አቃፊ በመሆን፣ በጥበብ መጓዝ ያስፈልጋል ብለን የምናምን ሲሆን እኔ ብቻ አውቅልሀለሁ ብሎ የልጆችን ቀና የአስተዳደር ለውጥ ሐሳብ መግፋትና ከተሳትፎ ማግለል ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል መረዳትም ያስፈልጋል ብለን እናምናለን:: ቤተ ክርስቲያን በሁሉ ልብ ውስጥ ያለች ናት። በመሆኑም የጥቂት ጳጳሳት ብቻ ሳትሆን የካህናት፣ የምእመናን እና የሰንበት ትምህርት ቤት ድርሻ ተሰናስሎ የሚገለጥባት መንፈሳዊ ተቋም ናት::
በሕገ ቤተ ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አንድነትና አስተዳደር ለማጠናከር በወጣው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ደንብ (ቃለ ዓዋዲ) መሠረት የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር መመራት ያለበት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ ከካህናት፣ ከምእመናን እና ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በተውጣጡ መዋቅሮች ነው፡፡ በዚህም አግባብ ይህን ታሳቢ ያደረገ አሳታፊ አሠራርን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን እንገለጻለን።
ሀገራዊ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ቤተ ክርስቲያን የሚኖራት ሱታፌ በትክክል ሊሠራበት ይገባል። ከዚህ በፊት እንደሚደረገው ወሳኝ አስተዋጽኦ ማድረግ በማያስችል ሁኔታ ከአንድ አካል ብቻ ኮሚቴ አቋቁሞ ለዜና ግብአት ከመሆን  ባለፈ እውነተኛ ተሳትፎ እንዲኖረን አግባብነት ያላቸውን ሊቃውንት፣ ምሁራን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች እና ማኅበራትን በማሳተፍ ወደ ሥራ እንዲገባ እንጠይቃለን፡፡
– በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታ በተሰጠው ዘላቂ መፍትሔ ጠቋሚ ኮሜቴ የሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ቅድመ ምልመላ መሥፈርትን፣ የሀገረ ስብከት አደራጃጀትን እና ምደባን አስመልክቶ ካህናት፤ ምእመናን እና ሰንበት ትምህርት ቤቶች የተሳተፉበት ጠቃሚ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቧል። ይሁንና ለምልዐተ ጉባኤው ገንቢ ግብዓት እንዳይሆን አለመቅረቡ የቀደመ ለውጥ ጠል በሽታ ማሳያ ነው። ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ዘመኑን ያልዋጀና የሰነበተ ደዌ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ቆርጦ እንዲጥል እና የተዘጋጀው ጥናት እና አቅጣጫ ጠቋሚ የመፍትሔ ሐሳብ በመሆኑ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀኖና፣ ክብር እና አንድነት ቅድሚያ በመስጠት እንዲጠቀምበት፣ ግልፅና መርኀን የተከተለ የምልመላ፣ የምርጫ እና የምደባ ሥርዓት ለመከተል የሚያስችለው የጥናት ሰነድ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አርፎበት ተግባራዊ እንዲሆን በልጅነት መንፈስ እንጠይቃለን።
*በተደራቢነት የተያዙ አኅጉረ ስብከቶች እና በቁጥራቸው ብዙ የሆኑ አድባራትና ገዳማት ያሉባቸው አኅጉረ ስብከቶችን ተገቢ እና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት በሚያስችል መልኩ ተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በቀረበው መሥፈርት መሠረት በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እና ሕግ መሠረት እንዲከናወን እናሳስባለን፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በውጪያዊ እና በውስጣዊ ግፊት፣ ከሲሞናዊነት እኩይ ተግባር፣ ለውጥ ጠልና ጎታች በሆኑ አመለካከቶች እንዳይያዝ በመጠንቀቅ ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታውን እንዲወጣ እንጠይቃለን። እንዲሁም ጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. በግልጽ ደብዳቤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረብነውን የመፍትሔ ሐሳብ በአግባቡ በመመልከት በግብዓትነት እንድትጠቀሙበት በፍጹም ትሕትና እና በልጅነት መንፈስ እንጠይቃለን።

የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት

ግንቦት ፭፣ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም