ቤተ ክርስቲያን ለምን ለውጥ ያስፈልጋል?

ቤተ ክርስቲያን ለምን ለውጥ ያስፈልጋል?

ቤተ ክርስቲያን ለምን ለውጥ ያስፈልጋል?

በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን እጅግ በከፋ መንፈሳዊ ጉድለትና አስተዳደራዊ ግድፈት እየታመሰች ነው። ይህን ሐቅ በአገልግሎት ቀጥተኛ ሱታፌ ላላቸው ካህናትና ምእመናንን መንገር የዓዋጁን በጆሮ ይሆናል፡፡ ሀብተ ውልድ ያላቸው ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያላቸው ትሥሥር የላላ ነው ተብለው ለሚታሰቡት ክርስቲያኖች እንኳ ግድፈቱ ክሡት ነው፡፡ ይህ የተገለጸ እውነት ቤተ ክርስቲያን ለውጥ ያስፈልጋታል የሚለው ሐሳብ አከራካሪ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሣ አንዳች የማያከራክር መሠረታዊ እውነት አለ፤ እርሱም ምን ዓይነት ለውጥ ለሚለው ጥያቄ የሚሰጥ መልስ ይሆናል፤ አስተዳደራዊ ለውጥ፡፡

የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሥሪት በጥሩ መሠረት ላይ የቆመ ነው። የዘመነ ሰማዕታትን የመከራ ማዕበል መሻገር የቻለችው መሠረቷ፣ ራስ ጉልላቷ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለሆነላት ነው። ሐዋርያት፣ ሐዋርያውያን አበው እና በየጊዜው የተነሡት ሊቃውንቱ በጽኑ መሠረት ላይ የቆሙ ዓምዶቿ ስለነበሩ በደም በተከፈለ መሥዋዕትነት መከራውን የተሻገረ ክርስትና ዛሬም ድረስ እንዲኖረን አድርገዋል። እንከን የለሽ ክርስቶሳዊው አስተምህሮዋን ለመቀሰጥ የተደረገባትን ሙከራ ሁሉ ተቋቁማ እዚህ የመድረሷ ዋነኛው ምክንያት እውነት ላይ የቆመች የእውነት ምስክር በመሆኗ ነው፡፡ ይህ እውነቷ ዘላለማዊ ነውና ለውጥም መሻሻልም አያስፈልገውም፡፡ ይህን ተልእኮዋን የምታስፈጽምበት አስተዳደራዊ ሥርዓት ግን ዘመኑን በዋጀ መንገድ ለውጥን ይሻል፡፡

ከላይ በገለጽነው እውነት መሠረት በዚህ ጽሑፍ የምንዳስሰው ለውጥ ለምን ያስፈልጋል፣ የሚለውን ነጥብ ነው፡፡ ለውጥ የሚያስፈልግበትን በርካታ ጥናታዊ ሐሳቦችን መጋቤ ምሥጢር ስማቸው ንጋቱ «የለውጥ አመራር ለቤተ ክርስቲያን» በሚለው መጽሐፋቸው ይዘረዝራሉ (ገጽ ፪፻)። ለዛሬ ሁለቱ ላይ እናተኩር።

1ኛ. ለውስጥ ግፊት (internal pressure) ምላሽ ለመስጠት፤ ለውጥ የሚያስፈልግበት አንደኛው ምክንያት ለውስጥ ግፊት ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ መጋቤ ምሥጢር በመጽሐፋቸው ይገልጻሉ። እውነት ነው ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስተዳደራዊ ለውጥን እንዲመጣ የሚጠይቅ(ግፊት የሚያደርግ) ኃይል አለ። ይህኛው ግፊት የወዳጅ ግፊት ነው። ቤተ ክርስቲያኑን እናቴ ብሎ የተጠጋ ብቻ ሳይሆን ህልውናውን ከህልውናዋ ጋር ያስተሣሠረው ምእመን የሚያነሣው የለውጥ ጥያቄ ነው።

ቤተ ክርስቲያኑ ሁሌም ህልው ሁና ማየት የሚሻ፣ ሁሌም  የመንፈሳዊ ልዕልና ማዕከል እንደ ሆነች፣ ዓለምን እየዋጀች፣ ስብራቱን እየጠገነች ዕለት ዕለት እንድታድግ የሚሻ ለውጥ ፈላጊ ኃይል ነው። ለውጡን የሚፈልገው በፍጥነት እየተለወጠ ባለው ዓለም በአስተዳደራዊ ዕሳቤ ሳይለወጡ መኖር የሚያመጣውን ወደ ዳር የመገፋት፣ የመገዝገዝ እና የመገንደስ ሥጋት ስለሚያውቅ ነው። ማንኛውም ተቋም በተለወጠ ከባቢ ያልተለወጠ የአእምሮ ውቅር ይዞ መቀጠል ይከብደዋል። ይህ ኃይል ጳጳሳቱን አባቶቼ ብሎ በእግዚአብሔር እንደራሴነት የተቀበለ፣ ለቡራኬያቸው በፊታቸው የሚንበረከክ ነው።

በዚህ ለውጥ ፈላጊ የቤተ ክርስቲያኗ አካል ውስጥ ኦርቶዶክሳዊው ምእመን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና አገልጋይ ካህናት ይገኛሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ጥንቱ ፈቃደ ሥጋቸውን ያሸነፉ፣ ለመለኮታዊው ፈቃድ የተገዙ ጳጳሳት እጅ ማየት ይሻል፡፡ ለፍትሕ ቆሞ ድሃ ተበደለ፣ ፍርድ ተጓደለ የሚል አባት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ክብርና ስለ ወንጌል አገልግሎት ራሱን ለመስጠት ቁርጠኝነቱ ያላቸው አባቶች መንፈሳዊውን አገልግሎት ሲመሩት ማየት ይፈልጋል፡፡ በመንጋው ላይ የሚሾሙ እረኞች የሥልጣን ፆር ያሸነፋቸው ሳይሆኑ፣ የእግዚአብሔር ጥሪ የደረሳቸው፣ ለመንጋው የሚጠነቀቁ፣ በጎችም በመንፈሳዊ ብቃትና ንጽሕናቸው የሚተማመኑባቸው፣ በኖላዊነታቸው በመንጋው የሚታወቁ እንዲሆኑ የሚጠይቅ ለውጥ ፈላጊ ነው፡፡ በአድልኦ አልባ መርሕ አገልጋዮቿን ማለትም ካህናትን እና ምእመናንን የምታስተናግድ ቤተ ክርስቲያን እንድትኖረው ይሻል።

በውስጥ ያለው የለውጥ ፍላጎት ግፊት ዓላማው መንፈሳዊና አስታዳደራዊ ግድፈቶች ታርመው ማየት ነው፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔር የሰፈነበት፣ ከጉቦኝነት፣ ከዘውገኝነት የጸዳ ለዓለም አሠራር አርአያ የሆነ አስተዳደርን ማንበር ይፈልጋል፡፡ አድልዎን የምታወግዝ ቤተ ክርስቲያን በአድሏዊ አሠራር ስትታወክ ማየት አይሻም፡፡ የሥነ ምግባርና ሞራል ትምህርት  ምንጭ የሆነች ቤተ ክርስቲያን የሥነ ምግባር መምህሮቿ በሥልጣን ሽኩቻ ሲራኮቱ ማየትና መስማትን አይወድም፡፡ አባቶች በሀገረ ስብከታቸው እና በሚያስተዳድሯቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሌብነት፣ የግቦና የወገንተኝነት ተግባር መበራከቱ በውስጥ ላለው ለውጥ ፈላጊ ኃይል ሕመም ነው፡፡ ከዚህ ሕመም የተፈወሰች ቤተ ክርስቲያንን ለማየት አስተዳደራዊ ለውጥን መተግበር የሕክምናው አንዱ መንገድ እንደሆነ በጽኑ ያምናል፡፡

የሰፈነው አስተዳደራዊ ግድፈት መንፈሳዊነትና ሙያዊ ብቃት ያላቸውን አገልጋዮች ከዐጸደ ቤተ ክርስቲያን ገፍቶ እያስወጣ ነው፡፡ በበርካታ ምእመናንን ሕይወት ላይም አሉታዊ ተጽእኖው ከብዷል፡፡ በጎችን ከቤተ ክርስቲያን አስበርግጎ እያስወጣ እና ለነጣቂዎች ሲሳይ እያዳረገ ነው፡፡ በውስጥ የተነሣው የለውጥ ግፊት እነዚህን ሁሉ ሥጋቶች ሊቀርፍ የሚችል አስተዳደራዊ ለውጥ እንዲተገበር የሚሻ ነው፡፡ ለውጡ የምእመናንን መንፈሳዊ ሕይወት በሚያጎለምስ መልኩ መቃኘት አለበት፡፡ ክብረ ክህነት የተጠበቀበት፣ በምእመናን እና በእረኞች መካከል መተማመን የሰፈነበት ከአድልኦ የጸዳ ሥርዓትን ማስፈን አንዱና ዋነኛ ዓላማው ነው።

አስተዳደራዊ ብልሹነት ከመገንገኑ የተነሣ ካህናት ቀድሰው ወጥተው ዕጣን ዕጣን ብቻ አይደለም የሚሸቱት፣ ከምርፋቅ እስከ መኖሪያ ቤታቸው ብሶት ብሶት የሚሸቱ ድምፆችንም ያሰማሉ። ዕድሜ ልክ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ጠንቅቀው ተምረው ዕድሜ ልክ ደጅ ጠኝ የሆኑ አገልጋዮች ዕንባ በማኅሌቱ ድምፅ ተውጦ ሊጠፋ አልቻለም እኮ። አስቀድሰው ወደ ቤታቸው ከሚመመለሱ ክርስቲያኖች መካከል ለሕይወት የሚበጅ ስንቅ ከሰነቁት ይልቅ የልመና መድረክ በሚመስለው ዐውደ ምሕረት የተሰማቸውን መሰላቸት ይዘው የሚመለሱት እየበዙ ነው፡፡ በዕረፍተ ሥጋ የተለያቸውን ዘመድ አዝማድ ቀብረው ወደ ቤታቸው ከሚመለሱ መካከል በአገልግሎት አሰጣጥ በሚታይ መድልዎ በኀዘን ላይ ኀዘን የሚደርቡ ምእመናን ብዙ ናቸው።

የውስጥ ለውጥ ፈላጊ ግፊት ውጤት የሆነው ብዙኃኑ አገልጋይና ምእመናን የተዛባውን አስተዳደር ሥርዐት ታርሞ ማየት ብቻ ሳይሆን በማረም ሒደቱም ተሳታፊ የመሆን ዓቅሙም ፍላጎቱም አለው። ቤተ ክርስቲያንን ፍትሕ እና ርትዕ የሰፈነባት ደጀ ሰላም ሆና ማየትን ያልማል። ያንዣበበው አደጋ ገብቷቸው፣ ህልሙን ህልም አድርገው፣ የለውጥ መሪ ለመሆን ራሳቸውን ያዘጋጁአባቶች ቢጠሩት አቤት፣ ቢልኩት ወዴት ለማለት የተዘጋጀና በቤተ ክርስቲያን ዕቅፍ ውስጥ ያለ ኃይል ነው፡፡ ይህን በልጅነት መንፈስ የተነሣሣ በጎ የለውጥ ግፊት ተቀብሎ በአግባቡ ለማስተናጋድ ያልተከፈተ የቤተ ክህነት ደጃፍ መዶሻና ጅራፍ ከያዘ የለውጥ ኃይል ጋር መፋጠጡ አይቀሬ ነው፡፡

  1. ተፎካካሪ ለሆኑ ግፊቶች(Competitive pressure) ምላሽ ለስጠት፤ ሁለተኛው ለውጥ የሚያስፈልግበት ምክንያት ተፎካካሪ ለሆኑ ግፊቶች(Competitive pressure) ምላሽ ለመስጠት ነው።

በፉክክር መርሕ የምትመራ ዓለም ነው የምንኖረው፡፡ በዓለም ሳለን ይህን የፉክክር መድረክ የመጋፈጥ ግዴታ አለብን፡፡  መጋቤ ምሥጢር ስማቸው የፖለቲካውን እና የኢኮኖሚውን ዓለም የፉክክር አድማስ ይገልጹና የመንፈሳዊውን ዐለም ፉክክር እንዲህ ያስረዳሉ፤ ‹‹መንፈሳዊው ዓለም ደግሞ በነገረ መለኮት ዕውቀት፣ በሥርዓት፣ በቀኖና፣ በስብከት ዘዴ፣ በማኅበራዊ አገልግሎት፣ አባላትን በማብዛትና አንዱ የሌላውን በመንጠቅ ይወዳደራል፡፡ እኛ ሁል ጊዜ አስነጣቂ ሌላው ነጣቂ የሆነበት ግንኙነት እየተፈጠረ ነው፡፡›› (ገጽ ፪፻፩)

ከዚህ የሁል ጊዜ ተነጣቂነት ቦታ ለመውጣት ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ለውጡ በአግባቡ ከተመራ ቤተ ክርስቲያን ከተፈጥሯዊ ዕድገቷ ማለትም ከክርስቲያን ቤተሰብ በሚወለዱ ሕፃናት ያገኘቻቸውን ነፍሳት ብቻ አይሆንም ለሰማያዊ ክብር የምታበቃው፡፡ በወንጌል መረብነት በደጅ ያሉትን አጥምዳ የሰማያዊ ሕይወት ተካፋይ በማድረግ እየሰፋች እንድትሔድ ያስችላታል፡፡ ለውጡ ቸል ከተባለ ደግሞ የራሷን ልጆች ጠብቃ በዐጸዷ ለማቆየትም ከባድ ይሆንባታል፡፡

ከውጭ በኩል የለውጥ ግፊት የሚፈጥረው አካል ለውጡን የሚፈልገው ከውስጣዊው ግፊት በተቃርኖ ቆሞ እና ከራሱ ዓላማና ግብ አንፃር አስልቶ ነው፡፡ በእርሱ አስተሳሰብ የተቃኘች ለፍላጎቱ የተገዛች ቤተ ክርስቲያንን ለመፍጠር ነው። በዚህ ተፎካካሪ ውጫዊ ገፊ ኃይል የተቃኘች ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ርትእት ኦርቶዶክሳዊት ልትሆን አትችልም፡፡ ምክንያቱም ፈቃዱን ፈጻሚ ለማድረግ ባለው ፍላጎት አስተምህሮዋን ይቆነጽላል፣ መንፈሳዊ ዕሴቶቿን ያራክሳል፡፡ በዚህ ብቻ አይቆምም፤ ለራሱ ጥቅም ሲል የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ለማክሰም እንቅልፍ የለውም፡፡

ይህን ሁሉ ነባራዊ ሐቅ ተረድቶ እና የሁነት ትንተና ሠርቶ በረድኤተ እግዚአብሔር በመደገፍ መጭውን ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምቹ ማድረግ የሚችል ቤተ ክህነት ግን ያለን አይመስልም፡፡ ለውጡ መጀመር ያለበት እዚህ ላይ ነው፤ ቤተ ክህነቱ ዐይነ ልቡናውን እንዲገልጥ ከማድረግ፡፡ ነባራዊውን ሒደት እንዲያይ፣ ውስጣዊውን የለውጥ ግፊት በአዎንታ እንዲቀበል መጫን ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለውጡን የማስፈጽም ዓቅም ያላቸውን በዕውቀት የደረጁ፣ በልምድም የበለጸጉ ምእመናንን ልጆቿን አበርክቶት የምትጠቀምበትን መንገድ ማመቻቸት ለነገ የማይባል ሓላፊነት ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በተደጋጋሚ እንደታየው ለሚወዳት እና ሳይሳሳ ነፍሱን ለሚሰጥላት ቤተ ክርስቲያን ህልውና ሲል ቤተ ክህነቱ አስተዳደሩን ከአፍ በተሻገረ ሁኔታ ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት አሠራር በማስፈን እንዲያዘምን በተለያየ መንገድ ግፊት ማድረግ አለበት፡፡