ቤተ ክርስትያን እና አመራሮቿ

ቤተ ክርስቲያን በምን ዓይነት የአመራር ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች?

አመራር ሲባል የአንድን አካል እሴት፣ እምነት፣ በጎ አስተሳሰብና ጠባይ በተመሪዎች ውስጥ በማሳደር አርአያ በሚሆን አግባብ በጎ ተጽእኖ ማሳረፍ ማለት ነው። ወደ ቤተ ክርስቲያን በቀረበ መልኩ ሲተረጎም ደግሞ መልካም አርአያነት ባለው ሕይወትና በዕውቀት ምእመናን መመገብና ለሰማያዊ ሕይወት ማብቃት ማለት ነው። የሚያሠራና ተደራሽ መዋቅር መዘርጋት፣ አቅም ያለው የሰው ኃይል ማፍራት፣ አገልጋይና አገልግሎትን ማገናኘት፣ የተማከለ የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋት፣ አሳታፊነት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ መሥራት የመልካም አመራር መገለጫዎች ናቸው። እነዚህን መገለጫዎች ለሚመሩት ተቋም በሚሆን እና ዘመኑን በዋጀ አግባብ ተግባራዊ የሚያደርጉ ደግሞ መሪዎች ይባላሉ። በዚህ አግባብ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን የአመራር ሁኔታ ስንመለከት ብዙ ፈተናዎች ያሉበት ሆኖ እናገኘዋለን። ዋና ዋናዎቹም፡-

  1. በሕይወትና በዕውቀት የሚመሩ አባቶች ቁጥር መቀነስ

አመራርነት በዓለሙም ውስጥ አርአያነት ያለው ሕይወትን እንደሚሻ ይታመናል። አታርፍዱ፣ ሥራ አትበድሉ፣ የተሰጣችሁን ሥራ በጊዜው አጠናቅቃችሁ አቅርቡ ብሎ ሌሎችን ለማዘዝ ሆኖ/አድርጎ መገኘት ያስፈልጋል። በቤተ ክርስቲያን ሲሆን ደግሞ በእጅጉ ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ “በሕግ የዕውቀትና እውነት መልክ ስላለህ፣ የዕውሮች መሪ፣ በጨለማም ላሉ ብርሃን፣ የሰነፎችም አስተማሪ፣ የሕፃናትም መምህር እንደሆንህ በራስህ ብትታመን፣ እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን?” (ሮሜ 2፡19-23) እንዳለ ሌላውን በአግባብ ለመምራት ራስን መምራት መቅደም አለበት። ቅዱስ ጳውሎስ በወቅቱ የነበሩ አይሁዳውያንን ለመገሠጽ ብቻ ሳይሆን ዛሬ በእኛ ዘንድ እየሆነ ያለውን በትንቢት መልክ የተናገረ በሚመስል መልኩ በቤተ ክህነት ከፍተኛው መዋቅር ውስጥ ሳይቀር አትስረቁ የሚሉ ግን የሚሰርቁ፣ አታመንዝሩ እያሉ የሚያመነዝሩ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚመዘብሩ “መሪዎች” እየታዩ ነው። አባቶች በመንፈሳዊ ሕይወትም ሆነ በነገረ ሃይማኖት ዕውቀት እንደ ስማቸው አንቱ የሚባሉ ሊሆን ይገባል። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ሃይማኖትና ምግባር ከዕውቀትና ጥበብ ጋር የተስማማላቸው አባቶችን በአመራርነቱ ቦታ ላይ ማግኘት እየቸገረ መጥቷል። የሚፈሩ፣ የሚከበሩና የሚታፈሩ የዐደባባይ አባቶች ቁጥር ጥቂት ነው። በቅዱስ ሲኖዶስና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ የሕይወትና የዕውቀት ጥያቄ የሚነሣባቸው አካላት ካሉ አጠቃላይ እንደ ቤተ ክህነት መዋቅር የአመራር ችግር ውስጥ ነን ማለት ነው።

2. ዓለማዊነትና ጎጠኝነት ያጠላባቸው አመራረሮች

ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥጋዊ አስተሳሰብ፣ ጎጠኝነት፣ ገንዘብንና ሥልጣንን መውደድ፣ ለወገኔ ይበጃል ብሎ ማድላት ተንሠራፍቷል። የአሕዛብ መምህር የተባለው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “በአንድ አሳብ ተስማሙ፣ አንድ ፍቅር፣ አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ አንድ ስንኳን አታድርጉ። ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት ለባልንጀራውም ደግሞ እንጂ” (ፊል. 2፡2-4) ብሎ እንደተናገረው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሊመራ የሚገባው በዚህ ሥርዓት ነው። ነገር ግን በዓለሙ ደረጃ በሕግ የሚከለከሉ ጉዳዮች ስንኳ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲፈጸሙ ይታያሉ። በተለይም መንጋውን በርትዕ ይጠብቃሉ የሚባሉት ጳጳሳት ለወገኔ በሚል አንደኛውን አካል በማቅረብ ሌላውን በማራቅ ሊሠሩ አይገባም፤ ሥልጣነ ክህነት የሚያስቀማ ድርጊት ነውና። ማንነትን/ዘውግን መሠረት ያደረጉ ሢመቶች፣ ጎጥን ያማከሉ ቅጥሮች እንዲሁም በገንዘብና በአማላጅ የሚፈጸሙ ምደባዎች አገልጋይና አገልግሎት እንዳይገናኝ አድርገዋል። በቤተ ክህነት የሚፈጸመው አንዳንዱ ድርጊት በዓለማዊ መሥሪያ ቤቶች ስንኳ ሊፈጸም ይችላል ተብሎ የሚታሰብ ሆኖ አይታሰብም። ክርስትና ብልጫው ምንድን ነው ብሎ ለመጠየቅ በሚያስደፍር መልኩ የቤተ ክህነቱ መዋቅሮች ከዓለማዊ መሥሪያ ቤቶች ተለይተው የሚታወቁበት በጎ መዓዛ የላቸውም።

3. የጳጳሳት ገደብ አልባ አስተዳዳራዊ ሥልጣን

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉት ሦስቱም አካላት ማለትም ሠራዔ ሕግ፣ ፈጻሜ ሕግ እና ፈታሔ ሕግ በጳጰሳት የተያዙ ናቸው። በሕገ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ደንብ ጳጰሳት ያላቸው ሥልጣን ገደብ አልባ ነው። የሲኖዶስ አባል ሆነው ሕግ ያወጣሉ፤ ጠቅላይ ቤተ ክህነትን በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያንን እና መምሪያዎችን በበላይ ጠባቂነት በማስተዳደር የአስፈጻሚነቱን ቦታ ይዘዋል። በሕግ ተርጓሚነትም የመጨረሻ ውሳኔ/ፍርድ ሰጪ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው። ሊቃነ ጳጳሳት ሁሉንም ሥልጣን ጠቅልለው መያዛቸው ብቻ ሳይሆን በአግባቡ መጠቀም አለመቻላቸውም ሌላው ክፍተት ነው። ካህኑ ዮቶር ለሙሴ የነገረው የአስተዳደር ተዋረድ በመዋቅር እንጂ በተግባር እየጠፋ ከመጣ ቆይቷል። ጳጰሳት ውክልና ሰጥተው የሚተዉት ሥልጣን የለም፤ ከገንዘብ እንቅስቃሴ እስከ አጥቢያ አገልጋይ ቅጥር ድረስ ውሳኔ ይሰጣሉ። በዚህ ምክንያት ምእመናን ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ብቻ እንደሆነች እንዲያስቡ አድርጓል። የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች፣ የገዳማት አበምኔቶችም ሳይቀር በጳጳሳት ፈቃድ እና/ወይም ውሳኔ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው እንዲዛወሩ ይደረጋሉ።

4. የምእመናን ሱታፌ የሌለበት አሠራር

ቤተ ክርስቲያን የምእመናን ናት። በገቢር ግን እያንዳንዱ መዋቅር በመዋቅሩ ላይ ያሉ አካላት ቤት ሆኗል። የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መተዳደሪያ ደንብ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ መዋቅሩ በካህናት፣ በሰንበት ትምህርት ቤት እና በምእመናን ተወካዮች መደራጀት እንዳለበት ቢገልጽም የድንጋጌው አተገባበር በአጥቢያ ደረጃ ብቻ ተወስኖ ቀርቷል። ይህም ሕግ ከማውጣት ያለፈ ተግባራዊ የማድረግ ክፍተት መኖሩን ከማሳየቱም በላይ ምእመናንን ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ባይተዋር እንዲሆኑ አደርጓል። ምእመናንን በሙያቸው ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ድረስ በአማካሪነት እና በባለድርሻነት ሱታፌ ሊኖራቸው የሚገባ ቢሆንም ይህ ሲደረግ አይስተዋልም። ምእመናን ቅዳሴ አስቀድሰው ከመመለስ ያለፈ ሚና እንዳላቸው ግንዛቤ አልተፈጠረም ወይም ከጉዳዩ መራቅን እንደ መፍትሔ ለመቁጠር የሚያስገድዳቸው ገፊ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ አለ። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን የጳጰሳት ብቻ ሳትሆን የሁሉም አማኞች እንደመሆኗ መጠን ሁሉም ድርሻውን ይወጣ ዘንድ ሥራውን ለሠሪው መስጠት ያስፈልጋል።

5. በመዋቅር እንጂ በገቢር ተደራሽ ያለመሆን

ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱ የሚፈስበት ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ድረስ መዋቅር አላት። ግን በዚህ መዋቅር ውስጥ የሚፈጸሙ አገልግሎቶች ምእመናንን የሚያሳትፉ አይደሉም። በመዋቅሩ ውስጥ ምእመናን የነበራቸው ሱታፌ በሕግ ደረጃም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንዲመጣ ተደርጓል። በሕግ ተቀምጦ የማይተገበር፣ በጠቅላላ ጉባኤያት የምእመናን ተሳትፎ አለመኖሩ እና ውክልናው አግባብነት የሌለው መሆኑ በቤተ ክህነቱ መዋቅርና በምእመናን መካከል ሰፊ ክፍተት እንዲኖር አድርጓል። ከፓትርያርኩ ጀምሮ እስከ መደበኛው ምእመን ድረስ የንስሐ አባት የትስስር ሰንሰለት አላት። ግን ይህን ሰንሰለት የምእመናንን የአገልግሎት ሱታፌና ቀኖናዊ ሕይወት መጠበቂያ መንገድ አድርጎ የሚጠቀም/የሚቆጣጠር መዋቅር የለም።

6. መርሕ አልባ የሰው ሀብት አስተዳደር

ከጵጵስና ሢመት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ቅጥር ድረስ የመመልመያ መስፈርት ኖሮት የሚፈጸም ሳይሆን ዘፈቀዳዊ ነው። የሰው ሀብት አስተዳደር ሥርዓቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምግባር ሳይሆን የእምነት ጥያቄ የሚነሣባቸው ሰዎች እንዲገቡ የሚፈቅድ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት የእግዚአብሔርን ቃል ትተን መዓድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ አይደለም ብለው ሕዝቡን የሚያገለግሏቸው ሰባት ዲያቆናት በመረጡበት ወቅት “ወንድሞች ሆይ፣ በመልካም የተመሰከረላቸውን፣ መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን መርጣችሁ አምጡ” (ሐዋ. 6፡3) ነበር ያሉት። ከዚህ ባነሰ መስፈርት ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዳደር ወደ ከፍተኛው መዓርግ የሚመጡ ተሿሚዎች ሊኖሩ አይገባም። ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን የሚያገለግሉ ጳጳሳትን የምትመርጥበት የጸና ሥርዓት ያላት ናት። በጰጵስና ደረጃ ያለውን የምርጫ ሥርዓት ማስተካከል ከታች ያሉትን ጉድለቶች ለማስተካከል መንገዱን ቀና ያደርገዋል።

7. ያልተማከለና ለምዝበራ የተጋለጠ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት

ቅዱስ ሲኖዶስ ወይም ጠቅላይ ቤተ ክህነት የቤተ ክርስቲያንን ገቢ በተማከለ ሁኔታ የሚያስተዳድርበት፣ ገቢ ሰብስቦና በጀት መድቦ የሚመራበት ሥርዓት የለውም። አህጉረ ስብከት ከሁሉም አጥቢያዎች 20 በመቶ ሰብስበው፣ ከሰበሰቡት ገቢ ላይ 20 በመቶውን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ይልካሉ። በከተማ ያሉ አጥቢያዎች ገቢ ከፍተኛ ቢሆንም ለሀገረ ስብከት ከ20 በመቶ በላይ ፈሰስ አያደርጉም። ምንም ገቢ የሌላቸው የገጠር አብያተ ክርስቲያናትም በተመሳሳይ ገቢያቸው ዝቅተኛ መሆኑ ግምት ውስጥ ሳይገባ ካላቸው ገቢ 20 በመቶ ፈሰስ እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። ገንዘቡ የሚሰበሰብበት አግባብ ለምዝበራ በእጅጉ የተጋለጠ ነው። ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አጥቢያዎች ገቢ የሌላቸውን፣ በንዋያተ ቅድሳትና በአገልጋይ እጥረት የተዘጉትን፣ በተለያዩ ችግሮች የተፈቱ ገዳማትንና የጉባኤ ቤቶችን ማገዝ የሚቻልበት ሥርዓት የለም፤ ለመዘርጋትም አሳቡ የለም።

በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞ የነበራት ተሰሚነትና በጎ ተጽእኖ ቀንሷል። በትምህርት፣ በአስተሳሰብ፣ በሥልጣኔ መሪ የነበረች ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን ዋጅቶ ባለመራመድ የነበራትን የመሪነት ቦታ በማጣት ሒደት ላይ ትገኛለች። ሠራዔ ሕግ የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት፣ የሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የመድኃኒት ምንጭ ጤና ሚኒስቴር፣ አገር ጠባቂ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የተተኪ አመራር ማፍሪያ የልሕቀት ማእከል፣ የአገር አንድነት ማሠሪያ ገመድ፣ ለአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ጥቁር ሰው መሆኑ ቅቡል ሆኖ በሰውነቱ እንዲከበር ያደረገውን ድል የአሸናፊነትን ልቡና በመሥራት የነጻነት ቀንዲል የሆነች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በብዙ መስፈርቶች ወደ ኋላ እንድትቀር የቤተ ክህነቱ ዘመኑን ያልዋጀ አካሔድ አሳሪ ሆኖባታል። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ካለችበት ሊሻሻል የሚገባው የአመራር ሁኔታ ልትወጣና ዘመኑን ወደዋጀ የአመራር ሥርዓት መሸጋገር ይኖርባታል።