ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በ14ኛው ዓለም አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያስተላለፉት መልእክት

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ። አሜን

እንኳን ለ14ኛው ዓለም አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ እና የሰንበት ት/ቤቶች ቀን አደረሳችሁ

“ተዘከሮ ለፈጣሪከ በመዋዕለ ውርዙትከ ዘእንበለ ይመጻእ መዋዕል እኩይ ወይመጽእ ዓመታተ በእለ ትብል ኢኮነኒ ቦቶን ፈቃድየ፦ የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ።” መክ 12፥1 ጠቢቡ ሰሎሞን ጭንቅ ቀን የመከራ ቀን ሳይመጣ የጉብዝና ወራት በተባለ የወጣትነት ዘመንን ለእግዚአብሔር መስጠት እንዲሚያስፈልግ ያስተምራል፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያን የጉብዝናን ዘመን በቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤት እንዲሆን ታስተምራለች።
ሰንበት ትምህርት ቤት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ ሥፍራ ካላቸው ተቋማት አንዱ ነው። ዘመን ተሻጋሪዋ ቤተ ክርስቲያናችን ቀድማ የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ትውልድን ስብስባ፣ ታላላቅ ሥራዎችን የምትሠራበት፣ ትውልዱን በማስተዋል በእውቀት በሃይማኖት በሥነ ምግባር በልዩ ልዩ ጸጋ የምትቀርጽበት የተወደደ ሥፍራ ሰንበት ት/ቤት ነው፡፡ ከሰንበት ትምህርት ቤት ብዙ ሊቃውንት፣ ብዙ መሪዎች፣ ብዙ መምህራን፣ ብዙ አገልጋዮች፣ ብዙ ባለሙያዎች እና ጠንካራ አማኞች ተገኝተዋል።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆቿ ጽድቅን ይማሩ ዘንድ በሰንበት ት/ቤት አሰባስባ እግዚአብሔርን አውቀው እንዲያመልኩ፣ ሕጉን ጠብቀው፣ በሃይማኖት፣ በምግባርና በትሩፋት ጸንተው አምላካቸውን መስለው እንዲኖሩ፣ የእርሱ የሆነችውን መንግሥተ እግዚአብሔርን እንዲወርሱ በብሉይ ከአምላኳ የተቀበለችውን ሕግጋተ እግዚአብሔርን አስተምራ በሐዲስ ኪዳንም በ40ና በ80 ቀን እያጠመቀች ለምዕመናን እንደ እድሜያቸው ቃለ እግዚአብሔርን በስብከት፣ በዝማሬ፣ በቅዳሴ፣ በሰዓታት፣ በማሕሌት፣ በቅኔ፣ በትርጓሜው እያስተማረች ምዕመናንን በሃይማኖት አንፃ ለመንግሥተ ሰማያት እያዘጋጀች ዛሬ ላይ ደርሳለች።

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና የዚህ ጉባኤ ታዳሚዎች

ሰንበት ት/ቤት ሕጻናት ወጣቶች የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቅኖና፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚማሩበት እና በእምነት፣ በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚያጠነክሩበት ታላቅ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ነው:: በመጽሐፍ ቅዱስ ሰንበት ት/ቤት ተብሎ የተፃፈ ቀጥተኛ የሆነ ስም ባይገኝም ዛሬ ላይ በሰንበት ትምህርት ቤት የሚተገበረው መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ልጆችን በቤተ እግዚአብሔር ማስተማር በብሉይ ኪዳን ዘመንም ይፈጸም እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል። የሰንበት ት/ቤት ፅንሰ ሀሳብም ከዚያ የመነጨ ነው። ኦሪት ዘዳግም 11÷18-21

በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው መካከል ሕፃናት (ወጣቶች) ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጡ ዘንድ ነበር። በዚህም ለሰንበት ትምህርት ቤት መነሻ የሆነ እና መሠረቱም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን ያረጋግጥልናል። (ማቴ 18፥3፣ 21፥16፣ ማር 9፥37)። በዚህ መነሻነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮዎቿ _ ሳይበረዙ _ ለትውልድ እንዲተላለፉ በተለይ በሕጻናት እና በወጣቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ለመሥራት ተሞክሯል።

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና የዚህ ጉባኤ ታዳሚዎች

ይህ የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልዕኮ ቅድሚያ የሚሰጠው ሐዋርያዊ ተግባር ሆኖ ሳለ እነዚህን የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ የሰንበት ት/ቤት ልጆቻችንን በአግባቡ ባለመመልከታችን፣ እንደ አባት ለልጅ የሚደረገውን ባለማድረጋችን፣ የሚገባውን ሥፍራ ሰጥተን ባለመሥራታችን ምክንያት ከበረቱ የተበተኑ፣ ከቤቱ የራቁ፣ ከአገልግሎት የጠፉ፣ ጀመረው ያልጨረሱ፣ ወድቀው ያልተነሱ ያለአስታዋሽ የቀሩ ጥቂት የማይባሉ ናቸው።

በተጨማሪም በዚህ ዘመን መሰማማት፣ መደማመጥ፣ መታዘዝ፣ መከባበር፣ ትህትና እና ፍቅር የጎደለው ቤተሰብን፣ ቤተ ክርስቲያንን፣ ሀገርን፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን እና ሽማግሌዎችን የሚያከብር ትውልድ አጥተናል፡፡ በየዕለቱም ፍቅር ሳይሆን ጥላቻ፣ ርሕራሄ ሳይሆን ጭካኔ፣ መረዳዳት ሳይሆን መገፋፋት፣ ክብር ሳይሆን ማዋረድ፣ ምርቃት ሳይሆን እርግማን፣ ምስጋና ሳይሆን ስድብ እየበዛ ከመሄዱ አንጻር ትውልዱን እያጠፋ ይገኛል።

ስለዚህ ሰንበት ት/ቤት ይህን እና ተመሳሳይ ጉዳዮችን ለመቅረፍ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅሙና አስፈላጊነቱ የጎላ በመሆኑ ከየትኛውም ሥራችን አስቀድመን በዚህ ትውልድ ላይ በትኩረት አስፈላጊውን በጀት በመበጀት በገጠር በከተማ በሙሉ ኃይላችን ነፍሳችን ጭምር ሰጥተን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
እግዚአብሔር ቢፈቅድ እኛ ከእናንተ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጋር ከወጣቱ ጋር ቤተ ክርስቲያንን ከፍ የሚያደርጉ ታላላቅ ሥራዎችን እቅድ አቅደን፣ ተገቢውን ጥናት አጥንተን፣ ተመካከረን፣ … ተወያይተን ሥራዎችን መሥራት ይገባናል፡፡ እንሥራለን እግዚአብሔርም ይረዳናል።

ሰንበት ት/ቤቶች እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ሊቃውንት፣ አገልጋዮች፣ መምህራን እና ጽኑ አማኞች መገኛ እንደመሆኑ መጠን በየአጥቢያው ሰበካ ጉባኤው የአብነት መምህራን በመቅጠር ሰንበት ትምህርት ቤቱን በማጠናከር ትውልዱን በኦርቶዶክሳዊ የሃይማኖት ትምህርት በማነጽ፣ ዶግማን፣ ቀኖናን እና ትውፊትን በማስተማር በየሀገረ ስብከቱ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰንበት ት/ቤቶች እንዲቋቋሙ፣ የተቋቋሙትም እንዲጠናከሩ ማድረግ ያስፈልጋል።

በተጨማሪም የሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎትን የበለጠ ለማጠናከር ሆነ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በመስጠት ወጣቱን ትውልዱ በዘመናዊነት ተፅዕኖ ውስጥ ወድቆ ከመንፈሳዊ ሕይወት እንዳይወጣ ልዩ ክትትል ማድረግ የሰንበት ት/ቤቶች ለተቋቋሙበት ዓላማና ተግባር እንዲንቀሳቀሱ ማገዝ መርዳት እንደሚያስፈልግ መዘንጋት የለብንም፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የዚሁ ጉባኤ ታዳሚዎች

ቤተ ክርስቲያን በባሕርይዋ አንዲት፣ ሐዋርያዊት፣ ቅድስት እና ኩላዊት (ዓለም አቀፋዊት) እንደመሆኗ መጠን ትውልዱ ይህን በተግባር ማየት ይሻል። እውነት ነው ብዙ ያንቀላፋንበት፣ በእውነት በዓላማ ያልተንቀሳቀስንበት፣ ትኩረት ሰጥተን ያልሠራንበት፣ ተግተን ያላገለገልንበት፣ ጊዜ ብዙ ነፍሳት እና ብዙ ትውልድ አሳጥቶናል። ቀላልም የማይባል ዋጋም ጭምር አስከፍሎናል፡፡ ስለሆነም ከየትኛውም ጊዜ በላይ በቤተ ክርስቲያናችን፣ በቤተሰብ፣ በማኅበራዊ፣ በሀገራዊ፣ በአንድነታችን፣ በጠፋው ሰላማችን፣ በቀዘቀዘው ፍቅራችን፣ በደከመው እድገታችን፣ ትጋት በሌለው መንፈሳዊ አገልግሎታችን እና በሃይማኖታችን ጉዳዮች ላይ ይሄ የእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ ነውና በፍቅር፣ በሰላም፣ በአንድነት፣ በመከባበር፣ በመተባበር፣ በትሕትና እና በመናበብ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ በመሆን በተሰጠን ኃላፊነት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብር እና እድገት ልንሠራ ያስፈልጋል።

የሰንበት ት/ቤቶችን አገልግሎት ያስፋልን፡፡

እግዚአብሔርበመንፈሳዊ በረከት ይባርካችሁ።

ተባረኩ ብሩክ ሁኑ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

ግንቦት 3ዐ ቀን 2017 ዓ.ም

አባ ሳዊሮስ

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ሓላፊ