ተሿሚዎችን ለምእመናን አለማሳወቅ የሚያስከትለው መዘዝ
በዘመናችን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሚፈጸሙ ጉዳዮች በርክተዋል። አባቶች የሠሩትን ቀኖና እያፈረሱ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ አስጠብቃለሁ ብሎ መናገር አይቻልም። ከእግዚአብሔር ይልቅ ቄሳርን ለማስደሰት የሚደረገው ሙከራ በእግዚአብሔር የሚያስጠይቅ በታሪክም የሚያስወቅስ ነው። ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ከለባት ብላ በምትጠራው የኬልቄዶን ጉባኤ እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ንጉሥ ለማስደሰት ብለው እንደ ሌሎቹ መለካውያን ቢሆኑ ኖሮ ርትዕት የሆነችው ሃይማኖት ከዘመናችን ባልደረሰች ነበር።
ቅዱስ ሲኖዶስ በያዝነው ዓመት የግንቦት ርክበ ካህናት ጉባኤው በተጓደሉ መናብርት ላይ ኤጲስ ቆጶሳትን እንዲሾሙ በመወሰን ለሢመት የሚመጥኑትን አባቶች በማፈላለግ ለጉባኤው እንዲያቀርብ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ያካተተ ኮሚቴ መሠየሙ ይታወቃል። ይህ ተግባርና ኃላፊነት የተጣለበት ኮሚቴ ሥራውን ሁሉ እያከናወነ ያለው በድብቅ ነው። ጥቆማዎችን የተቀበለው ከሊቃነ ጳጳሳት ብቻ ነው። የተሰጡት ጥቆማዎችን ለሕዝብ ይፋ አድርጎ አስተያየት አልተቀበለም። ተጠቋሚዎችን የሚመርጥበት መስፈርት ምን እንደሆነ በምልዓተ ጉባኤውም ሆነ በአስመራጭ ኮሚቴው ለምእመናን አልተገለጸም። ለሹመት የሚቀርቡት አባቶች በቤተ ክርስቲያን ጸንቶ በቆየው ሥርዓት መሠረት ስለ ትምህርታቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ መንፈሳዊ ሕይወታቸውና ንጽህናቸው ደግሞ ምእመናን የመሰከሩላቸው እንዲሆኑ አልተገለጹም። ኮሚቴው ይህን በማድረጉም በመጽሐፈ ሲኖዶስ “ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ሊሾም የቀረበ ሰው ካለ ይህ በሀገረ ስብከቱ ሰዎች ሁሉ ስምምነት መሆን አለበት” (ሲኖዶስ፣ ገጽ ፻፵፭) ተብሎ የተሠራውን ሥርዓት ተገዳድሯል። በኮሚቴው ውስጥ ያሉ አባላት ይህን ቀኖና አያውቁትም ማለት ከባድ ነው። ቀኖና እያፈረሱ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ማስፋት አይቻልም። ሊቃነ ጳጳሳት ሕግና ሥርዓትን ካላከበሩ ምእመናንን ለሕግና ለሥርዓት ተገዥ ሁኑ ብሎ ለማዘዝ የሚችሉበት መንፈሳዊ ልዕልና ያጣሉ። ዐዲስ ኤጲስ ቆጶስ የሚሾሙባቸው አህጉረ ስብከት ክርስቲያኖች በእኔ አውቅልሃለሁ የተሾሙባቸውን አባቶች አንቀበልም ቢሉ በግድ ሊጫንባቸው አይገባም። በተለይም የሃይማኖት ሕጸጽ፣ የምግባር ጉድለት፣ የታወቀ ነውርና ነቀፋ ያለባቸው አባቶች ቢሾሙባቸው ምእመናን አንቀበልም ማለታቸው አይቀርም። በዚህ ወቅት ቅዱስ ሲኖዶስ በግድ ተቀበሉ ሊላቸው ነው ወይስ ምርጫውን ሊከልስ?
እንዲህ ያለው ተግባር ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን መጣስ ብቻ ሳይሆን የኮሚቴውን አባላት በገንዘብ ደልለው፣ በትውውቅና በቅርርብ ተጠቅመው ወይም በኃይል አስፈራርተው ለመሾም በር እንደሚከፍት መረዳትም ይገባል። በዚህ መንገድ ሥልጣን የያዙ አባቶች መንፈስ ቅዱስ መረጠን ብለው ሊናገሩ እንደማይችሉም መረዳት ያስፈልጋል። እንዲህ ባሉት መፍቀሬ ሢመት አባቶች ላይም መንፈስ ቅዱስ እንደሚያድር ቤተ ክርስቲያን አታስተምርም። ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷ በግልጽ ነው። በተለይም ለአንድ ቀንና ለወራት ሳይሆን እስከ ዕድሜ ልክ ድረስ የሆነውን የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ በግልጽ አሠራር፣ በጸና ቀኖናዊ ሥርዓት አለመፈጸም ቤተ ክርስቲያንን አሳልፎ እንደ መስጠት ይቆጠራል። ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና በድብቅ ኤጲስ ቆጶስነት ተሾመናል ሲሉ የነበሩ፣ ይህን ሕገ ወጥ ሢመት ተከትሎ ለብዙ ምእመናን ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ እስርና እንግልት ምክንያት የሆኑ፣ የሊቃነ ጳጳሳት ቀራቢዎች ስለሆኑ ብቻ የተጠቆሙ፣ መደለያ በመስጠት በዕጩነት የቀረቡ አባቶች ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠፏት እንጂ ሊያሰፏት አይችሉም።
አሁን እየተፈጸመ ያለው የምርጫ ሒደት ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በቤተ ክርስቲያን ላይ ለተከሠተው ታሪካዊ ስሕተት መፍትሔ የሚሆን ሳሆን ሌላ ችግር ይዞ የሚመጣ ነው። ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ አጋጥሟት የማያውቀውን ጥቁር ጠባሳ ለመፍታት የሔደበት መንገድ ማስታመምን መሠረት ያደረገ ነው። የተከሰተውን ችግር መፍታት መልካም ሆኖ ዘላቂ መፍትሔ የማያመጣ አካሔድ መጓዝ ደግሞ ከእግዚአብሔር እንደሚያጣላ፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስወጣ መዘንጋት የለበትም። ለተከሰተው ችግር መፍትሔው በዘላቂነት ችግሩን ሥር ነቅሎ የሚያወጣውን ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ ተግባር መፈጸም ነው።
ስለሆነም በዕጩነት የቀረቡ አባቶችን ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይፋ ማድረግ በኑፋቄ የተበከሉ ሰዎች ተመሳስለው እንዳይገቡ መፍትሔ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ምእመናንን ለመጠበቅ ብቃት ያላቸው አባቶች ከሢመት እንዳይታለፉ ያደርጋል። ይህን ማድረግ ኮሚቴው ያለበትን ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚያቀልል እንጂ ሥልጣኑን የሚጋፋ አይደለም። ኮሚቴው አካሔዱን እንደ ሐበሻ መድኃኒት ምሥጢር ማድረጉ ቤተ ክርስቲያንን ለሚያፈርሱ ወገኖች መዶሻ ማቀበል መሆኑን ሊረዳው ይገባል። በመሆኑም የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ከምልመላ እስከ ሹመት ድረስ ቅርበትን፣ ዝምድናን፣ ቋንቋንና ጎሣን መሠረት ያደረገ መሆን የለበትም የሚለው የቆየው ጩኸት መታለፉ ያስከተለውን ችግር እያየን ሌላ ችግር መጨመር ግልጽ በደል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩ የጎጥ፣ የትውውቅና የመደለያ መሳሳቦች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቆም አለባቸው። ይህ ጩኸት በአስመራጭ ኮሚቴውም በቅዱስ ሲኖዶስም ሊደመጥ ይገባል። በመጨረሻም አስመራጭ ኮሚቴው ሒደቱን የሚከልስበት አግባብ ከሌለ ቅዱስ ሰኖዶስ ጉዳዩን በጽኑዕ ሊመረምረውና እልባት ሊያስቀምጥበት ይገባል እንላለን።