“ንጹሐንን ከርኩሳን ጋር አታጥፋቸው”
ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ በግዞት ካለበት ወደ እስክንድርያ እንደማይመለስ ያረጋገጠው አርዮስ የእስክንድርያ ክርስቲያኖች ሊቀበሉት እንደሚችሉ ተስፋ በማድረግ ወደዚያ ሔዶ ነበር። የአርዮስ ወደ እስክንድርያ መመለስ በቀላሉ ሊበርድ የማይችል ሁከት አስነሣ። የሁከቱ ምክንያትም የእስክንድርያ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ አባታቸውን ቅዱስ አትናቴዎስን በስደት ማጣታቸው አንሶ በአርዮስ መመለስ እጅግ መበሳጨታቸው ነበር (አዶንያስ ብርሃነ፣ ገጽ ፪፻፴፭)።
በአርዮስ ወደ እስክንድርያ መመለስ ምክንያት የእስክንድርያ ክርስቲያኖች ተቃውሞ ማስነሣታቸውን የሰማው ንጉሡ ቈስጠንጢኖስ የተቀሰቀሰውን ሁከት ለማርገብ በማሰብና አርዮስ ወደ ቍስጥንጥንያ ቢሄድ አውሳብዮሳውያኑ (የአርዮስ ተከታዮች አርዮሳውያን እንደተባሉት የአውሳብዮስ ዘቂሣርያ ተከታዮች ደግሞ አውሳብዮሳውያን ተብለዋል። እነዚህም መንፈቀ አርዮሳውያን ናቸው) በክብር እንደሚቀበሉት በማመን ወደ ቍስጥንጥንያ እንዲመለስ መልእክት ላከበት። በዘመኑ በቍስጥንጥንያ መንበር ላይ ከሜትሮፌን በመቀጠል ሊቀ ጵጵስና ተሾሞ የነበረው ቅዱስ አሌክሳንደር (ኢትዮጵያውያን ምንጮች እለ እስክድሮስ በማለት ይጠሩታል) የሚባለው አባት በአውሳብዮሳውያኑ አሳብ አልተስማማም ነበር። አውሳብዮሳውያኑ አርዮስን ካልተቀበለው ከመዓርጉ እንደሚሽሩት ቢዝቱበትም ጽኑ ሃይማኖት ስለነበረው ቅዱስ አሌክሳንደር አሳባቸውን ሳይቀበለው ቀረ (አዶንያስ ብርሃነ፣ ገጽ ፪፻፴፭)።
ቅዱስ አሌክሳንደርን አውሳብዮሳውያን ቢያባብሉትም ከዓላማው ፍንክች አልል አለ። ማባበሉ አልሠራላቸው ሲል ለስደት እንደሚዳርጉት አስፈራሩት። ነገር ግን በማስፈራራታቸው አልተርበደበደም። ቅዱስ አሌክሳንደር የቀናችው ሃይማኖት ጠበቃ ነውና በአውሳብዮሳውያን ዛቻና ማስፈራሪያ ሳይሸበር ‘አርዮስን ወደ ቤተ ክርስቲያን ማስገባት ክሕደቱን ማስገባት ነው’ በማለት በአቋሙ ጸና።
በሊቀ ጳጳሱ በአሌክሳንደር በአቋም መጽናት ምክንያት አርዮስ ለሁለተኛ ጊዜ የሚያምንበትን ጽፎ ለንጉሡ እንዲያቀርብ ተደረገ። ንጉሡ ስለሃይማኖቱ በጠየቀው ጊዜ አርዮስ በቅዱስ እለ እስክንድሮስ የተወገዘባቸውን ኑፋቄዎች በመሰወር የቀናቸውን ሃይማኖት እንደሚከተል በማስመሰል እየማለና እየተገዘተ የማምንበት ነው በማለት በጽሑፍ አቀረበ። ቀጥሎም እለ እስክንድሮስ እርሱን ያወገዘባቸውን ኑፋቄዎች ፈጽሞ እንደማይመለስባቸው በመሐላ ባረጋገጠ ጊዜ ንጉሡ ቈስጠንጢኖስ “እምነትህ የቀናች ብትሆን በመማልህ ደግ አደረግህ፤ እምነትህ የረከሰች መሆኑን እያወቅህ ሰውረህ ምለህ ከሆነ ግን እግዚአብሔር እንደ መሐላህ ይፍረድብህ” በማለት አሰናበተው (አዶንያስ ገጽ ፪፻፴፭-፪፻፴፮)።
አውሳብዮሳውያን በተለመደ ተንኮላቸው አርዮስን በግድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊያስገቡት ቢሞከሩም ቅዱስ አሌክሳንደር ተቃወማቸው። መልካም ምስክር የሆነው የቍስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አሌክሳንደር ርእስ መናፍቅ የሆነው አርዮስ ወደ ምእመናን አንድነት ሊመለስ አይገባውም በማለቱም አውሳብዮሳውያኑ በግድ ለማስገባት መዛት ጀመሩ። አንተ ሳትፈቅድ በንጉሡ እንዲጠራ እንዳደረግነው ሁሉ አንተ ወደድክም ጠላህም ነገ በቤተ ክርስቲያን ከእኛ ጋር የምሥጢራት ተካፋይ ይሆናል በማለት ቁርጥ ውሳኔያቸውን አሳውቀውት ሄዱ። አውሳብዮሳውያን በቅዱስ አሌክሳንደር ላይ ዝተውበት የሄዱበት ዕለትም ቅዳሜ ነበር።
ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ረዳት የሌለው መሆኑን የተረዳው ቅዱስ አሌክሳንደር ወደ ቅድስት ሄራኒ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ፣ ከመሠዊያው ሥር በግንባሩ ተደፍቶ በጽኑ ኀዘን ወደ አምላኩ ይጸልይ ጀመር። በዚህ ዕለት ከአጠገቡ ያልተለየው መቃርዮስ የሚባል የእስክንድርያ ካህን ነበር። ሊቀ ጳጳሱ አሌክሳንደር አምላኩን ከተማጸነባቸው ቃላት መካከል ካህኑ መቃርዮስ የሚያስታውሳቸው “አርዮስ ነገ ወደ ምእመናን አንድነት የሚጨመር ከሆነ እኔን ባርያህን አሰናብተኝ” የሚለውና “ንጹሐኑንም ከርኩሳን ጋር አታጥፋቸው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያንህን የምትታደጋት ከሆነ፣ እንደምትታደጋትም አምናለሁ፤ አርዮስንና ኑፋቄውን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ ከልክላቸው” የሚሉት ይገኙበታል። ይህ የቅዱስ አሌክሳንደር ጸሎት እስራኤልን የምታጠፋቸው ከሆነ እኔን ከሕይወት መጽሐፍህ ደምስሰኝ ያለውን የሊቀ ነቢያት የሙሴን ጸሎት የሚያስታውስ ነው (ዘጸ. ፴፪፣፴፪)።
አርዮስ በቀጣዩ ቀን ማለትም እሑድ ከምእመናንና ከካህናት ጋር አንድ በሚያደርገው ሥጋውና ደሙ እንደሚተባበር አስቦ በዝግጅት ላይ ሳለ ገና በዋዜማው ቅዳሜ ፀሐይ እንኳ ሳትጠልቅ ፈራጁ እግዚአብሔር በክፉዎች ላይ ፍርዱን አሳየ። ታሪክ ጸሐፊው ሩፊኖስ ድርጊቱ የተፈጸመው እሑድ ጠዋት መሆኑን ሲጽፍ ሌሎች ቅዳሜ ወደ ማታ መሆኑን ገልጠዋል። አርዮስ በዚያች ቀን ማለትም ቅዳሜ ወደ ማታ ድንገተኛ ከባድ የሆድ ሕመም ተሰምቶት ወደ አንበሳ መደብ (መጸዳጃ ቤት) ለመሔድ ፈለገ። ሰዎችን እንዲያሳዩት ጠይቆም አሳይተውት በፍጥነት ሮጦ ገባ። አርዮስ አንበሳ መደብ ገብቶ ረዘም ያለ ጊዜ በመቆየቱም ይጠብቁት የነበሩት ሰዎች ወደ ውስጥ ቢገቡ አርዮስ በተቀመጠበት ቦታ የውስጥ አካሉ ተዘርግፎ አገኙት። ብዙ ደም በመፍሰሱና የውስጥ አካሉ በመዘርገፉ ወዲያው ሞተ።
በዕለቱ በአርዮስ ላይ በተፈጸመው ተአምር ምክንያት ንጉሡ አርዮስ በእውነት መናፍቅ እንደ ነበረ ተረድቶ የኒቅያ ጉባኤ አባቶች እምነት ትክክለኛ መሆኑን አረጋገጠ። አርዮስ የሞተበት ቦታም በነሶቅራጥስ ዘመን በቍስጥንጥንያ ሰዎች በአዕማዱ መካከል በእጃቸው እየጠቆሙ የሚያሳዩት በጣም የታወቀ ቦታ ነበር። በዚያ ቦታም ለረጅም ዘመን ሰው አይጠቀምም ነበር። በተፈጥሮ ግዳጅ ምክንያት ወደዚያ የሚገቡ ሰዎችም እርስ በርሳቸው በዚያ መቀመጫ አንጠቀምም ይባባሉ እንደ ነበር ይነገራል። በኋላ ዘመንም የአርዮስን ኑፋቄ የሚደግፍ አንድ ባለጸጋ ሰው ድርጊቱ እንዲረሳና የአርዮስም ክፉ አሟሟት በትውልዱ ሁሉ ሲዘከር እንዳይኖር ቦታውን ገዝቶ ታላቅ ሕንፃ ሠራበት (አዶንያስ፣ ገጽ ፪፻፴፯)።
አውሳብዮሳውያን በመቅሰፍት በተደመደመው የአርዮስ ፍጻሜ በጣም አፈሩ። ቅዱስ አሌክሳንደር ዘቍስጥንጥንያ ደግሞ በዚህ የቤተ ክርስቲያን የደስታ ቀን ከንጹሐን ምእመናን ጋር በጸሎትና በመሥዋዕት እግዚአብሔርን አመሰገነ። የሊቀ ጳጳሱ ደስታ አርዮስ ሞተ ብሎ ሳይሆን ከሕሊና በላይ በሆነው በእግዚአብሔር ርትዕ ፍርድ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር በቅዱስ አሌክሳንደር ተማጽኖ አርዮሳዊው ክሕደት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገባ አድርጓልና ነው።
በንጉሡና በአውሳብዮሳውያን ድጋፍ አግኝቶ የነበረውና ቤተ ክርስቲያን ያወገዘችው የአርዮስ ኑፋቄ ርትዕት ከሆነው አስተምህሮ ጋር እንዳይደባለቅ በማድረጉ ቅዱሱ አባት አምላኩን ሲያመሰግን ውሏል። በአርዮስን ድንገት መቀሰፍ ምክንያት ክደው ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶች ወደ ርትዕት ሃይማኖት ተመልሰዋል። ቤተ ክርስቲያንን በጎሣና በጎጥ ለመከፋፈል እና በኑፋቄ ለመበከል የሚሞክሩ አካላት ሁሉ መጨረሻቸው እንደ አርዮስ መሆኑን መረዳት ይገባል። ለመንጋውና ለራሳቸው በመጠንቀቅ ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ጳጰሳት ደግሞ እጅጉን አርአያነት ባለው ሕይወት፣ ፈቃደ እግዚአብሔርብ በማስቀደም መምራት ይገባቸዋል። የተሰጣቸው መንፈሳዊ ኃላፊነት ሸክም እንጂ ማጌጫ አይደለም። ስለሆነም የተሾሙበትን ዓላማ በመዘንጋት ሥጋዊ መሻታቸውን ለማስፈጸም መሥራት አይገባቸውም። ይህን በሚያደርጉ ሁሉ ላይ ሰዎች አቅም አጥተው ዝም ሲሉ እግዚአብሔር ሥራውን እንደሚጀምር ከዚህ ታሪክ መረዳት አዋቂነት ነው።
ዋቢ መጻሕፍት
- መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ መጽሐፍ ቅዱ የብሉያትና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት፣ ፳፻ ዓ.ም።
- አዶንያስ ብርሃነ። ጉባኤያተ ቤተ ክርስቲያን (ከ፶- ፫፻፹ ዓ.ም) ቅጽ ፩። አዲስ አበባ፤ ዘካርያስ ማተሚያ ቤት፣ ፳፻፲፬ ዓ.ም።