አክሊል የሆነችው ሢመት መርጣ የምታርፍባቸው አባቶች

አክሊል የሆነችው ሢመት መርጣ የምታርፍባቸው አባቶች

አክሊል የሆነችው ሢመት መርጣ የምታርፍባቸው አባቶች

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጽሑፎች ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን የአመራር ሁኔታና የሚያስፈልጋትን አመራር ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ደግሞ የሚፈለገውን አመራር ለመስጠት የሚችለው ምን መስፈርቶችን የሚያሟላ አባት ነው የሚለውን እንመለከታለን። የኤጲስ ቆጶስነት ሢመት ለሚገባው አባት አክሊል ስትሆን ለማይገባው ደግሞ እሾህ እንደምትሆንበት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሲከሠት የኖረ እውነት ነው። መንፈሳዊት ሢመት አክሊል የምትሆነው ኖላዊነታቸውን አምነው የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ለሚተጉ አባቶች ሲሆን እሾህ የምትሆነው ደግሞ ሳይገባቸው ሰማያዊውን ምሥጢር ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘት ለሚሞክሩ ሲሞናውያን ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶሳትን የምትሾመው ምእመናንን ከአውሬ እንዲጠብቁ ለኖላዊነት ነው። ኖላዊደግሞ በበር የሚገባ ጠባቂ፣ ነፍሱን ስለበጎቹ አሳልፎ የሚሰጥ ዋስ፣ “ደጃፍ የመለሰውን፣ ማጀት የጎረሰውን” ለልጆቹ እንደሚያወርስ አባት ነው። መንፈሳዊ አባት ተብሎ የሽፍታ ተግባር የሚፈጽም፣ ኖላዊነቱን ዘንግቶ ምንደኛ የሚሆን፣ ሰማያዊውን ሢመት በጊዜያዊ ጥምቅ የሚለውጥ፣ አምላካዊውን አደራ ዘንግቶ ፈቃደ መንግሥትን ለመፈጸም የሚደክም ከሆነ ሢመት አክሊል መሆኗ ቀርቶ እሾህ ትሆናበታለች።

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት የሚናገረው ጵጵስና መንፈሳዊ አባትነት በመሆኑ ለሢመት የሚመረጡት በጥንቃቄ መሆኑን፣ በጥንቃቄ መመረጥ የሚኖርባቸውም ኃላፊነቱ ሰማያዊ፣ ሹመቱ አምላካዊ በመሆኑ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ለመንፈሳዊው ሹመት የሚታጩ አባቶች አምላክን የሚያስደስቱ፣ ሰዎችን ወደ አምላካቸው ለማቅረብ የማይታክቱ፣ ምድራውያንን ከሰማያውያን የሚያገናኙ መሆን እንዳለባቸው ነው (ሐመር መጽሔት ፴ ዓመት ቍጥር ፭፣ ግንቦት ፳፻፲፭ ዓ.ም)። የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ጥንቃቄ የሚያስፈልገውተሿሚዎች በምእመናን ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ሥልጣን የሚሰጥ፣ የተሰጡትን ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣትም ተጠያቂነቱ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ በመሆኑ ነው።ስለሆነም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶችን በጥንቃቄ መምረጥ የሚገባት ከእውነት ላለመውጣትና ከአምላክ ፈቃድ ላለመራቅ ነው። ቤተ ክርስቲያን “ጊዜ የወደደውን ዘመን የወለደውን” የምትከተል ከሆነ ተልእኮዋ የአምላክን ፈቃድ መፈጸም፣ አገልግሎቷም የአምላክን ቃል ለሰው ልጆች ሁሉ ማድረስ መሆኑ ይቀራል።

በየጊዜው በተካሔዱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ የተሰጠባቸው አንገብጋቢ ችግሮች ተፈጻሚ አለመሆናቸው፣ ምእመናን በአባቶቻቸው ተስፋ እንዲቆርጡ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንዲጠራጠሩ አንዳንዶችም ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው ሲባዝኑ በክፉ አውሬ እንዲበሉ ምክንያት ሆኗል። እንዲህ ያለውን ችግር ማስወገድ ከሚቻልባቸው ተግባራት አንዱ ለኤጲስቆጶስነት የሚመረጡ መነኰሳት የተጣለባቸውን መንፈሳዊ ኃላፊነት ለመወጣት ብቁ መሆናቸውን በማረጋገጥ ነው። ይህን ለማድረግ በዋናነት ሁለት ተግባራትን ማከናወን ይገባል።

በአንድ በኩል አምላካችን ለዚህ ለተቀደሰ ኃላፊነት ብቁ የሚሆኑትን አባቶች እንዲገልጥልን በጸሎት መጠየቅ ሲሆን ሁለተኛው ምርጫውን ከምንም ዓይነት ምድራዊ መስፈርት በማራቅ በቀኖና ቤተክርስቲያንን ብቻ እንዲከናወን ማድረግ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየታየ ያለው ደምና አጥንት ቆጥሮ፣ ገንዘብ ከፍሎና ተቀብሎ፣ ሥጋዊ አሳብና ፍላጎት ባጠላበት አግባብደጋፊ ለማብዛት እንጂ እግዚአብሔርን ለማስደስት እና ምእመናንም ትጉህ እረኛ እንዲያገኙ ከመሻት ያልሆነ ምርጫ ሊታረም የሚገባው ነው። እንዲህ ዐይነት ከአባት የማይጠበቁ፣ ከእግዚአብሔር ፈቃድ የራቁ ሥጋዊ ፍትወቶችን መዝጋት የሚቻለው ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን መነሻ በማድረግ የምርጫ መስፈርት በማዘጋጀት ነው።

የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ደንብ እንደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘርን ቀዳሚ መስፈርቱ ያላደረገ እንደ አይሁድ ከእኛ በላይ ለፈጣሪ በሚል ከንቱ ትምክህት ከዚህ አካባቢ ብቻ ይመረጥ የማያሰኝ ከየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆን መንፈሳዊነቱ፣ መንፈሳዊ ዕውቀቱ እና የአስተዳደር ብቃቱ ብቻ እየታየ የሚሾምበት መሆን ይገባዋል። በወንጌል አንተ አይሁዳዊ አንተ ግሪካዊ የሚል ክፍፍል ስለሌለ መንጋውን ለመጠበቅ ብቃት ያላቸውን ከማንኛውም ቋንቋ ተናጋሪ መፈለግ ይገባል። ይህ ሲባል ግን ቋንቋውን የሚችል ብቻ ሳይሆን የእኔ ዘውግ መሆኑ ተረጋግጦይሾምልኝ ከሚል ምድራዊ መስፈርትም መራቅ ያስፈልጋል።

በአገልግሎታቸው እና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እግዚአብሔር የሚደሰትባቸው አባቶች ከየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ ወገኖቻችን መካከል ሲመረጡ መስፈርቱ የጎሣ ወይም የአካባቢ ተዋጽዖ ሳይሆን የመንፈሳዊነትና የመምራት ብቃት ብቻ መሆን ይገባዋል። ዘመዴ፣ የጎጤ ልጅ፣ ወገኔ መመረጥ ይኖርበታል የሚል መስፈርት ማውጣት በአሮጌ አቅማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ለመያዝ እንደመሞከር ነው። አምላካችን እግዚአብሔር ሐዋርያትን የመረጠው የቋንቋ መስፈርት አውጥቶ ወይም የአካባቢ ተወካይ ያስፈልጋል ብሎ ሳይሆን ለመንፈሳዊው ሢመት ብቃት ያላቸው መሆናቸውን አውቆ ነው። አሁንም ሆነ ወደ ፊት ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው የብቃት እንጂ የውክልና መስፈርት አይደለም። ማወቅ የሚገባው ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሹመትን ሽተው “ሹመት በተርታ ሥጋ በገበታ” ያሉትም፣ ከእኛ ውጪ ማን ሊሾም ብለው ተመክተው“ወንጌል ካለ ኦሪት፣ ጥምቀት ካለ ግዝረት” ያሉትም መጥፋታቸውን ነው።

የጵጵስና አክሊል የምታርፍባቸው አባቶች ሲመረጡ መንፈሳዊ ሕይወት ያላቸው መሆናቸው ቀዳሚው የምርጫ መስፈርት ሲሆን የአስተዳደር ብቃት ደግሞ ሁለተኛው መስፈርት መሆን ይገባዋል። ለመንፈሳዊው ሹመት ብቁ የሆኑትን ማግኘት የሚቻለውም በብልጣ ብልጥነት ወይም እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል ግትርነትም አይደለም። ገንዘብ ሰጥተው ለመሾም የሚሞክሩትንም፣ ገንዘብ ተቀብለው ለማሾም የሚጣጣሩትንም. የእኔ ወገን ብቻ ይሾምልኝ የሚሉትም ድርጊታቸው ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ያፈነገጠ መሆኑን ማወቅ አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪም የዚህ ደም ያላቸው ካልተሾሙ ሞተን እንገኛለን ባዮችም ለቤተ ክርስቲያን አይጠቅሙም። ሢመቱ የሚገባው ትሕትናን ከግብረ ገብነት ለሠመረላቸው አባቶች ብቻ መሆኑን የኒቅያ ጉባኤ የመላጥዮስን ጉዳይ በተመለከተበት ጊዜ ደንግጓል (NPNF, second serious, vol. 3, 2012, P,46)።

በዘመናችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም መከተል የሚኖርባት መስፈርት ለሢመት የሚታጩ አባቶች ምግባር ከሃይማኖት የሠመረላቸው መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የአስተዳደር ብቃታቸው በጎሰኝነትና ሰውን በአካባቢና በቋንቋ ከመከፋፈል የጸዱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል መመሪያ ማውጣት ነው። ምግባር ከሃይማኖት ያልሠመረላቸው ቢሾሙ ምእመናን ማግኘት የሚገባቸው መንፈሳዊ አገልግሎት ይቋረጣል፤ ትክክለኛ ኖላዊ አጥተውምይባዝናሉ። የኢጲስ ቆጶሳት ሢመት እነ እገሌን እንዳይከፋቸው ተብሎ ሰዎችን ወይም መንግሥትን ለማስደስት መካሔድ የለበትም። ቋንቋና ዘርን ብቻ መሠረት በማድረግውክልናዊ ሢመትየሚሰጠው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንጂ ለቅዱስ ሲኖዶስ አለመሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ይገባል።

ዘመናችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ የወደቀችበት፣ ምእመናንም ከውጫዊ ፈተናው በተጨማሪ በአባቶቻቸው ድርጊት እየተማረሩ ቤተ ክርስቲያንን ሔደው ለመሳለም ከመሳቀቅ ደረጃ የደረሱት አንዳንድ አባቶች የተሰጣቸውን መንፈሳዊ ኃላፊነት በሚገባ ባለመወጣታቸው ነው። ምእመናንን ከሚያሳቅቁ ተግባራት አንዱ በመንፈሳዊ ሕይወትም በአስተዳደር ችሎታም አርአያመሆንየሚችሉ አባቶች ቁጥር እየሳሳ መምጣት ነው።

የምግባርና የአስተዳደር ጥያቄ የሚነሣባቸው አባቶች ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውለታ የሚውሉት እነርሱ መንፈሳዊ ሕይወት ከአስተዳደር ብቃት የሠመረላቸው ባይሆኑ እንኳ የጃፓኑንጉሥ ሚጂ ተስፋፊ የመሬት ከበርቴዎችን ድርጊት ለማራቅ የሚያስችለውን ተግባር በመፈጸም አገሩን ከኋላ ቀርነት እንደታደገው ያለ ሥራ በመሥራት ነው። በዘመናችን ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት ኃላፊነት የተጣለባቸውም እነርሱ መልካም መሥራት ቢያቅታቸው መሥራት የማይችሉት እየገቡ ለቤተ ክርስቲያንተጨማሪ ፈተና እንዳይሆኑባትአሻጋሪ ሆነው በመስፈርቱ መሠረትመርጠው መተካት መቻል አለባቸው።

በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ለምትሻው አመራር ወደፊት የሚመጡ ተሿሚዎችየሚቀበሉት ሹመት አምላካዊ አደራ መሆኑን የተረዱ፣የተበላሸውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለመለወጥ የሚተጉ፣ አምላካቸውን አጋዥ አድርገውና ምእመናንን ይዘው በረሃውን ገነት ለማድረግየሚፋጠኑ፣ እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ክህነት መክሊት መሆኑን ተረድተው ለማትረፍ የሚተጉ፣ ሰው ተክተው፣ ተተኪ አፍርተው ለማለፍ የሚሞክሩ፣ ከከተማው ይልቅ ሀገረ ስብከታቸው የሚናፍቃቸው፤ ከዋዛ ፈዛዛ ይልቅ መንፈሳዊ ሕይወት የሚያስቀናቸው፣ የተጨነቀ ክርስቲያንም ይሁን አረማዊ ቀርቦ ሲጠይቃቸው እንደ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ የችግሩን ምክንያት ተረድተው መፍትሔ በመስጠትየቤተ ክርስቲያንን ብርሃንነት ለዓለም የሚገልጡ(ስንክሳር ዘመስከረም)። ክርስቲያኖችአርአያነታቸውን ተከትለው በእምነት እንዲጸኑ ምክንያት የሚሆኑ፣ አሕዛብም ትሩፋታቸውን አይተው ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመቅረብ እንደ እኊ ቅዱስ ምክንያት የሚሆኑመሆን ይገባቸዋል። (ትርጓሜ ወንጌል)።

በካህናት፣ በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ በምእመናን ሱታፌ የሚመረጡ ኤጲስ ቆጶሳት በዘመናችን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ከሆኑ አባቶች መካከል በመንፈሳዊ ሕይወትም፣በዘመናዊ በዕውቀትም አርአያ የሚሆኑት ቍጥር ጥቂት በመሆናቸው ይህን የሚቀይሩ፣ ጎልቶ የሚታየውን ዓለማዊነትና ጎጠኝነት የሚያስተካክሉ፣ ገደብ የሌለው የሆነውን የጳጳሳት ሥልጣን በማስተካከል በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚመሩ፣ አመራራቸውም ሆነ አገልግሎታቸው ምእመናንን አሳታፊ እንዲሆን የበኩላቸውን የሚወጡ፣ በሕግና ሥርዓት የማይመራውን የሰው ሀብት አስተዳደር የሚለውጡ፣ ለምዝበራ የተጋለጠውን ያልተማከለየንብረትና ገንዘብ አስተዳደርኦርቶዶክሳውያን ባለሙያዎችን በማማከር የሚያስተካክሉ መሆን ይገባቸዋል። እንዲህ ያሉትን አባቶች አሁን የሚታማው በሁለትና በሦስት ጎራ ተከፍሎ ቃላት በመወራወር ማግኘት አይቻልም። አሁን ያሉ አባቶች በእግዚአብሔርም በታሪክም ተጠያቂ እንዳይሆኑ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚያዝዘውን ብቻ በመፈጸም፣ ጸንቶ በቆየው ቀኖና ከአድሎና ከወገንተኝነት ወጥተው ውግንናቸው ለእግዚአብሔርና ለምእመናን ሊሆን ይገባል።

በአገልግሎት ሒደት የሚታየውን የማስፈጸም አቅም ማነስ ለማስወገድ ዘመኑ የሚጠይቀውን አባት በተገቢው ቦታ ማስቀመጥ ከተቻለ አሁን ያለው ሁኔታ እየተቀየረ የማይሔድበት ምክንያት የለም። አባቶች መመሪያ ሰጭና ያዘዙት መፈጸሙን መቈጣጠርና መከታተል እንጂ ሲፈልጉ የአስፈጻሚነት ሚናውንም መጫወት፣ ሳይፈልጉ ደግሞ ከነጭራሹ መተው የሚታረመው ለመንበሩ የሚመጥኑት እየተተኩ የማይሠሩትና የማያሠሩት ከእነርሱ ሲማሩ፣ መልካም ከሚሠሩት ካልተማሩ ደግሞ ቦታቸውን ለቀው በጸሎት ተወስነው እንዲኖሩ መደረግ ይኖርበታል። መንፈሳዊው አገልግሎት የሚሠምረው ራሳቸውን ለአገልግሎት አሳልፈው በመስጠት እንጂ አንዱ በጎጥ ሌላው በገንዘብ ደጋፊ ለማብዛት በሚያደርገው ዓለማዊ አሠራር አይደለምና።