አዝልፍኬ አንብቦ መጻሕፍት እስመ እማንቱ ይመርሃሁ ለልብከ ኀበ አንክሮተ እግዚአብሔር- መጻሕፍትን አዘውትረህ አንብብ፤ መጻሕፍት እግዚአብሔርን ወደማድነቅ ልብህን ይመሩታልና፡፡ (ማር ይስሐቅ)

ማር ይስሐቅ መጻሕፍትን ማንበብ በውስጣቸው ያለውን እውቀት ከማግኘት ባለፈ ወደ ተመስጦ፣ እግአብሔርንም ወደማድነቅ እንደሚያደርስ ይነግረናል፡፡ ለማወቅም ሆነ ያወቁት ለማስተማር ከጉባኤ ከዋሉ ምስጢር ካደላደሉ ሊቃውንት እግር ስር ቁጭ ብሎ ለሚማሩት ትምህርት በቂ ጊዜ ሰጥቶ መማር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ጉባኤ ቤት ገብቶ በቂ ጊዜም ሰጥቶ መማር ለሁሉ የሚቻል አይደለምና በማደራጃ መምሪያችን በየዓመቱ በክረምት ወቅት የሚሰጥ እንደዚህ ዓይቱ የአጭር ጊዜ ሥልጠና መነቃቃትን የሚፈጥር ለተጨማሪም ትምህርትና ንባብ የሚያነሳሳ ስለሆነ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል “መከሩ ብዙ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡” ብሎ እንዳስተማረ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በሁሉም ሰንበት ት/ቤቶች ተግባራዊ እንዲሆን የተጋጀው ወጥ ሥርዓተ ትምህርት በሁሉም አህጉረ ስብከት በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ መምህራን ያስፈልጉናል፡፡ ይህንን የመምህራን ፍላጎት በአንድ ጊዜ ማሟላት የሚቻል ስላልሆነ እንደዚህ ያሉ ሥርዓተ ትምህርቱን መሠረት ያደረጉ አጫጭር ስልጠናዎች በጣም አስፈላጊዎች ናቸው፡፡

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጋር በመሆንና አህጉረ ስብከትን በማስተባበር ሥርዓተ ትምህርቱ በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ በክረምት ወቅት ከየአህጉረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤት መምህራንን ወደማዕከል በማስመጣት በዚህ መልኩ ሥልጠና ሲሰጥ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ሲሆን በቀጣይም ከአህጉረ ስብከት ጋር በመነጋገርና የሥልጠና ማዕከላቱን በማብዛት የተሻለ ሥራ ለመሥራት ታስቧል፡፡ በዘንድሮው ለሁለት ሳምንታትና ለ200 ሰዓታት በታወቁ የቤተ ክርስቲያናችን መምህራን የተሰጠው ሥልጠና እጅግ የተሳካ ሠልጣኞችም ጥሩ እውቀትና ልምድ የቀሰሙበት እንደነበር እናምናለን፡፡

ስለሆነም ውድ ተመራቂዎች የተማራችሁት ትምህርት መጻሕፍትን በማንበብና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊቃውንትን በመጠየቅ አዳብራችሁ ሥራ ልትሠሩበት ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በትምህርት የወለደው የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስን “ወተዐቀብ እስከ እመጽእ በአንብቦ ወበምሂር ወበገሥጾ ወበጸልዮ – እስክመጣ ድረስ በማንበብና በመምከር በማስተማርም ተጠንቀቅ።” 1ጢሞ. 4፡13 ብሎ እንዳስተማረው እግዚአብሔር ቢፈቅድ ወደፊት ወደጉባኤ ቤትና ወደ መንፈሳዊ ኮሌጆች ገብታችሁ ከዚህ የበለጠ ትምህርት እስክታገኙ ድረስ ከጸሎት ጋር በማንበብና በመምከር በማስተማርም አብዝታችሁ ልትተጉ ይገባል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ  አፈ ወርቅ  “ቅዱሳት መጻሕፍትን አለማወቅ የስህተት ሁሉ ምንጭ ነው፡፡” ብሎ እንዳሰተማረ መጻሕፍትን ባለማወቅ የሚመጣን ስሕተት ቅዱሳት መጻሕፍት አብዝቶ በማንበብና በመመርመር መከላከል ይቻላልና ለማንበብ እንድትተጉ ማደራጃ መምሪያችን አጥብቆ ያሳስባል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቈላስይስ መልእክቱ “ወይኩን ነገርክሙ በጸጋ ወቅሱመ በጼው – ነገራችሁ በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ይሁን በማለት መናፍቃን አብዝተው ቢጠቅሱ እናንተም አብዝታችሁ ጠቅሳችሁ በለጋስነት መልሱላቸው፡፡ ንግግራችሁም በፍቅርና በትሕትና የጣፈጠ ይሁን ብሎ እንዳስተማረ አሁን ያለንበት ዘመን ሐሳውያን የበዙበት መጽሐፍ ቅዱስን እየጠቀሱ የዋሃን ምእመናንን የሚያደናግሩ ሰዎች እንደ አሸን የፈሉበት ዘመን ስለሆነ በየምትሄዱበት አካባቢ ወጣቶችና ሕጻናትን ከመናፍቃን ቅሰጣ ጠብቆ በቃለ እግዚአብሔር ማሳደግ ይቻል ዘንድ የተማራችሁትን ትምህርት በሥራ ላይ በማዋል ዛሬ የተቀበላችሁትን አደራ በአግባቡ ልትወጡ ይገባል፡፡

በእነዚህ ሁለት ሳምንታት በነበራችሁ ቆይታ በተማራችሁት ትምህርት ሳትወሰኑ ሁል ጊዜ ለማንበብና ለመጠየቅ የተዘጋጃችሁ በመሆን ክህደትንና ኑፋቄን የምትቃወሙ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲን ዶግማዋን ቀኖናዋንና ሥርዓቷን ጠብቃችሁ የምታስጠብቁ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃዎች ልትሆኑ ይገባችኋል፡፡

ሰዎችን ለመለወጥ በብዙ የትምህርት ተቋማት አልፎ ብዙ ዕውቀት መሰብሰብ ብቻው በቂ አይደለምና ከማስተማር ጋር አርአያ የሚሆን ሕይወት ሊኖረን ይገባል፡፡ እንዲህ ሲሆን በአገልግሎታችን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ብዙ ኢማንያንን ወደ እምነት እንዲመጡ እናደርጋለን በእምነት ያሉ ወጣቶችና ሕጻናትም በዕውቀት እናሳድጋለን፡፡

በመጨረሻም ውድ ተመራቂዎች ለዚች ቀን እንኳን አደረሳችሁ እያልኩ ያለንበት ወቅት ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እጅግ የፈተና ወቅት እንደሆነ ተድተን ወጣቶችና ሕጻናት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ አገልግሎታችንም ለዘመኑ እንደሚገባ በጥበብና በእውቀት ልናደርግ ይገባል በማለትና አገልግሎታችሁ የተሳካ እንዲሆን በመመኘት መልእክቴን በዚሁ አጠቃልላለሁ፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መጋቤ ሐዲስ ጸጋ ወ/ትንሣኤ

የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሐላፊ