ኢ-ቀኖናዊ የሆነውን “ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት” አስመልክቶ ከሀገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት የተሰጠ መግለጫ
ቀኖናዊ ሥርዓቷን ጠብቃና አስጠብቃ አያሌ ዘመናትን የተሻገረቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየደረሰባት ካለው ፈተና፣ መሰናክል፣ መከራ እና ውጣ ውረድ በእግዚአብሔር ቸርነት ተጠብቃ አሁን ካለንበት ዘመን ደርሳለች :: ዛሬ ግን ከፈተናዎች ሁሉ የከፋው ፈተና የበጐች እረኛ አድርጋ ሾማ እስከ ማዕረገ ጵጵስና ባከበረቻቸው ልጆቿ ተፈጽሞባታል። መንጋውን እንዲጠብቁ የመረጠቻቸው ልጆቿ ሊያፈርሷትና ሊከፍሏት መነሳታቸው በእጅጉ አሳዝኖናል ::ይኸንን ኢ -ቀኖናዊ ተግባርም በጽኑ እንቃወማለን። በመሆኑም ፦
- ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ በሕገወጥ መልኩ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም እና ሲኖዶስን ለመክፈል የተደረገውን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ አጥብቀን እንቃወማለን :: ድርጊቱ ታላቋን ፣ ጥንታዊቷን፣ ታሪካዊቷን ፤ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለማዳከም የተሸረበ ሴራ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። በመሆኑም ከሙሉ ክብሯ፣ ሥርዓቷ እና እሴቶቿ ጋር የምንወርሳትን ቤተ ክርስቲያን በእኛ ዘመን ለመክፈል የተነሱ የውስጥ እና የውጪ ጠላቶቿን በፍፁም አንታገሰም ::
- ቅዱስ ሲኖዶስ በድፍረትና በማን አለብኝነት የተፈፀመውን ኢ- ቀኖናዊ ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳትን አስመልክቶ ሕጋዊ እና የታላቋን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ክብር እና መብት የሚያስከብር እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን።
- ቅዱስ ሲኖዶስ ኢ- ቀኖናዊ ለሆነው የመንደር ኤጲስ ቆጶሳት ሲመት መነሻ የሆነውን ምክንያት በማጥናትና በመለየት ተገቢውንና አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ መንፈሳዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን :: ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዋነኝነት የብዙ ችግሮች ምክንያት መሆኑ በጉልህ የሚስተዋለው አስተዳደራዊ ክፍተት ዘላቂና አስተማማኝ ተግባራዊ መፍትሔ እንዲሰጠው አበክረን እንጠይቃለን።
- ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የተለመደውን አካሄድ መከተል ነገሩን ከማዳፈን የዘለለ እልባት ስለማያስገኝ ዘግይቶ ለሚፈጠረው ችግር አባቶች ቀዳሚ ተጠያቂ እንደምትሆኑ በልጅነት አንደበት እየገለጥን የአስተዳዳር አካላት ፣ምዕመናን ና ምዕመናት የጀመራችሁትን ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ ኃላፊነት እያደነቅን ፤ አሁንም በበለጠ በጋራ ሆነን ክርስቲያናዊ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ጥብቅ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
- መንግስትም ሀገረ መንግስቱን በኃይል ለመናድ የሚንቀሳቀስ ኃይል ቢኖር ሕግ የማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ ሁሉ ሕጋዊ ሰውነት ላላት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሕግ በማስከበር ሥራው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ፤በግልጥ እና በስውር የሚደርሰው ጥቃት እና ትንኮሳ የማያባራ የእርስ በእርስ ችግር የሚያስከትልና ሰላምና መረጋጋትን በሀገራቸን የሚያሳጣ በመሆኑ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን በመሆን ፤አፍራሽ እና እኩይ ዓላማ ያነገቡ የበግ ለምድ ለባሽ ኃይሎች ላይ በቁርጠኝነት ሕጋዊ እርምጃ በመውስድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በጥብቅ እንጠይቃለን ::
በመጨረሻም ወቅታዊ የአስተዳደር ክፍተቶች ፣ ግለሰባዊ ፍላጎቶችን እና ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ በቤተ ክርስቲያናችን ችግር መፍትሔ ላይ በማተኮር እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በኅብረት እንዲቆም እንጠይቃለን።