እርሱን የምሾመው ለመንበሩ ክብር እንዲሰጠው ነው

እርሱን የምሾመው ለመንበሩ ክብር እንዲሰጠው ነው

እርሱን የምሾመው ለመንበሩ ክብር እንዲሰጠው ነው

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከእኔ በኋላ ለመንጋዪቱ የማይራሩ ነጣቂዎች ተኵላዎች እንደሚመጡ እኔ አውቃለሁ። ደቀ መዛሙርትንም ወደ እነርሱ ይመልሱ ዘንድ ጠማማ ትምህርትን የሚያስተምሩ ሰዎች ከእናንተ መካከል ይነሣሉ። ስለዚህም ትጉ፤ እኔ ሁላችሁንም ሳስተምር ሦስት ዓመት ሙሉ ሌትም፣ ቀንም እንባዬ እንዳልተገታ አስቡ። አሁንም ለእግዚአብሔርና ሊያነጻችሁ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ሊሰጣችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ” (ሐዋ. ፳÷ ፳፰-፴፪)¹ በማለት ያስተማረው ትምህርት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶሳትን ስትመርጥ በጣም እንድትጠነቀቅ የሚያሳስብ ቃል ነው።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለጳጳሳት ምርጫ የምትጨነቀውም ለመንጋው የማይራሩ ክፉዎች ተሾመው ምእመናንን ከእግዚአብሔር እንዳያራርቋቸው ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የጳጳሳት ምርጫ የሚያሳስባት ዓላማው ሰማያዊ፣ ተልእኮው ሰውን ለመንግሥተ ሰማያት ማብቃት በመሆኑ ነው። ጳጳሳት ኖላዊ መሆናቸውን የተረዱ አባቶችም መንበራቸው ክፍት በሆኑ አህጉረ ስብከት ላይ የሚመድቧቸው አባቶች ማንነት ያሳስባቸዋል። ጉዳዩ አሳሳቢ የሚሆንበት የመጀመሪያው ምክንያት ለጵጵስና የሚመረጡ አባቶች ምግባረ ብልሹ ከሆኑ ሰዎችን ለድኅነት ማብቃት ሲገባቸው ከድኅነት ስለሚያርቋቸው ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በእነርሱ ምግባረ ብልሹነት ቤተ ክርስቲያን  እንዳትተች ነው። እንዲህ ያሉ አባቶች ቢመረጡ ክርስቲያኖችን የሚፈልጓቸው ለጊዜያዊ ነገር መጠቀሚያነት ብቻ ይሆናል ።

የክህነትን ተግባር በሚገባ የተረዳው ታላቁ አባት ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ቀጰዶቅያንና አካባቢውን ግኖስቲኮችና አርዮሳውያን ተቈጣጥረውት በነበረበት ዘመን የሁለቱንም ወገኖች ኑፋቄ ከሥሩ ነቅሎ ለመጣል በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም፣ በዕውቀታቸውም የተመሰከረላቸውን አባቶች እየመረጠ በተጓደሉ መናብርት ላይ ሲያስቀምጥ ወንድሙን ቅዱስ ጎርጎርዮስን ዐሥራ ሦስት ክርስቲያን ቤተ ሰቦች ብቻ ይገኙባት በነበረችው ኑሲስ በምትባለው ሀገረ ስብከት ሊሾመው መሆኑን የተረዱ ሰዎች ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ቀርበው “ቅዱስ ጎርጎርዮስን ያህል ታላቅ አባት እዚህ ግባ በማትባል ከተማ እንዴት ትሾመዋለህ? በሚል ላቀረቡለት ጥያቄ ቅዱስ ባስልዮስ ሲመልስ ወንድሜን በኑሲስ የሾምኩት ከመንበሩ መዓርግና ክብር እንዲያገኝ ሳይሆን ለመንበሩ መዓርግና ክብር እንዲያመጣለት ነው ” በማለት መልስ ሰጥቷል።²

ቅዱስ ባስልዮስ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ሊያቀኑ፣ ከአርዮሳውያንም ሊጠብቁ የሚችሉ ሊቃውንትን እንዲፈልግ ያስገደደው በኑፋቄ በመታወራቸው ምክንያት ለመንጋው የማይራሩ ሰዎች መንበሩ ላይ ተቀምጠው ክርስቲኖችን እንዳያሳስቱ ነው። ዘመኑም እንደ ወርቅ የጠሩ ኦርቶዶክሳውያን በመብራት ተፈልገው የሚገኙበት የመከራ ዘመን ነበር። ሰዎች በብዙ ድካም ታላቅ ባደረጉት ሀገረ ስብከት ላይ ተሾሞ መቀመጥ የሚያሳየው የተተኪውን ታላቅነት ሳይሆን ሰዎች በደከሙበት መግባቱን ነው። “ነቢያት በገረገሩት ሐዋርያት ማገሩት” የሚባለውም አንዱ በደከመበት ሌላው ሲገባ ነው። ቅዱስ ባስልዮስ የመረጠው ግን ወንድሙ ደክሞ መንበሩን ታላቅ እንዲያደርገው ስለነበር ትንቢቱ ተፈጽሟል፤ አሳቡም ተሳክቷል።

ቅዱስ ባስልዮስ ስለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ የተናገረው በተግባር መፈጸሙን ግብፃዊው ቄስ ያዕቆብ ማላቲ “ስብከት ድኅረ ዘመነ ሐዋርያት” በተሰኘ መጣጥፋቸው “Itissaid thatwhenSt. GregoryofNyssawasordainedas abishoptherewereonly13familiesinhisdiocese,and onhis departure fromthis world there wereonly 13 pagan families፡- ቅዱስ ጎርጎርዮስ ጵጵስና ተሹሞ ወደ ኑሲስ በሄደ ጊዜ በሀገረ ስብከቱ የነበሩ ዐሥራ ሦስት ክርስቲያን ቤተሰቦች ሲሆኑ ሌሎቹ ኢአማንያን ነበሩ። ቅዱሱ አባት ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፎ ወደ አምላኩ ሲጠራ በሀገረ ስብከቱ ክርስትናን ያልተቀበሉት ዐሥራ ሦስት ቤተሰቦች ብቻ ነበሩ”³ ብለዋል።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶችን ለኤጲስ ቆጶስነት ስትመርጥ መመሪያዋ ለመንበሩ ክብር የሚሰጡትን በመፈለግ እንጂ ምድራዊ ሀብት በተትረፈረፈባቸው አህጉረ ስብከት በመሾማቸው ክብር ለማግኘት የሚደክሙትን ለመመደብ መሆን የለበትም የሚባለውም ለዚህ ነው። የአባትነት ስሙን ብቻ ይዘው በግብሩ የማይገኙትን፣ የባለሥልጣናትን መዓድ ለመባረክ አገረ ስብከታቸውን ትተው በመዞር ቤተ ክርስቲያን እንድትተች ምክንያት የሚሆኑትን መመደብ ክርስቲያኖች ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ በሩን እንደ መዝጋት ይቈጠራል።

መማለጃ በመስጠት ወይም ኤጲስ ቆጶስ ከመሆን የሚገባቸውን አባቶች ፈልገው እንዲያቀርቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ኃላፊነት የተሰጣቸውን አባቶች ደጅ በመጥናት ካላሾማችሁኝ የሚሉትንና ታላቁ ቅዱስ ጳውሊ እንደ ቁራ ጠቁረው ባያቸው ጊዜ ያለቀሰላቸውን አይነት ሰዎች መምረጥ አይገባም። እንዲህ ያሉት በስም እንጂ በግብር አባት መባል አይገባቸውምና። እንዲህ ያሉ ሰዎች ቢሾሙም የቤተ ክርስቲያንን ቍጥርንም፣ የክርስቲያኖችን ምግባርንም ስለማያሻሽሉ የሚሾሙት አባቶች ለመንበሩ ክብር የሚሰጡት፣ ክርስቲያኖችን ለምግባርና ትሩፋት እንዲነሣሡ ምክንያት የሚሆኑት ብቻ መሆን ይገባቸዋል።

 

ማጣቀሻ መጻሕፍት

  1. የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ መጽሐፍ ቅዱስ፤ ብሉያትና ሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት፣ (፳፻ ዓ.ም.)
  2. ዳንኤል ክብረት፣ መንፈሳዊ ሕይወት ምንድን ነው?ሕይወቱ ለሙሴ፣ ( ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.)
  3. FR.Tadros Y, Malaty, Preaching in the post Apostolic Era. (2002)