እነርሱ እያቃጠሉ እኛ ስንሠራ አንኖርም
እነርሱ እያቃጠሉ እኛ ስንሠራ አንኖርም
ዘመናችን “መታዘዝ እንደ ድካም፣ ትሕትና እንደ ውርደት፣ ራስን መግዛት ራስን እንደ መጨቈን፣ በሥርዓት ማደር እንደ ኋላ ቀርነት፣ ክህነታዊ ተዋረድን የጠበቀ አገልግሎት ዘመን እንዳለፈበት የጭቆና መሣሪያ፣ ሃይማኖተኛነት እንደ ተራ ወግ አጥባቂነት ተፈርጆ ይዘመትበታል፡፡ ነባር ሃይማኖትን መቃወምን እንደ ሃይማኖት የያዘ መስተጻርርነት አየሩን ሞልቶታል” በማለት በአማን ነጸረ የጻፈው በተግባር ተገልጦ የሚታይበት ነው። ፀረ -ኦርቶዶክሶችም ይባል አክራሪዎች በኦርቶዶክሳውያን እንደሚሸነፉ ሲረዱ እግር ላይ ወድቀው የሚለምኑት በኦርቶዶክሳውያን መልካም ዕሴት ላይ ተሸጋግረው አዘናግተው ለማጥቃት ወይም ጊዜ ለመግዛት እንጂ በሚልኩት ሽምግልናም ሆነ በሚያቀርቡት ተማጽኖ አምነውበት አይደለም።
የአክራሪዎች መርሕ ራስ ብቻ ደኅና የሚል ነው። የራሳቸው ደኅንነት ከሌላው ደኅንነት ጭምር እንደሚመነጭ አመዛዝነው መረዳት የሚችሉበት አእምሮ የተነሣቸው ናቸው። መደጋገፍ የሚባለው አብሮ የመኖር ባህል፣ መከባበር የሚሉት መልካም ዕሴት አይገባቸውም። ሁሉ ነገር የእኛ፣ ሁሉን እኛ ይዘነው ሌላው ከገጸ ምድር ይጠፋ የሚል ነው። ለቀጣይ ትውልድ ማሰብ የሚባል ነገር አያውቁም። ሌላው የለፋበትን ነጥቆ መውሰድ ወይም ማውደም ሃይማኖት ብለው የያዙት እኩይ ድርጊት ነው። እግዚአብሔር የፈጠረውን ትውልድ በማጥፋት “የፈጠርከውን አጠፋንልህ” ብለው ለባለቤቱ ሪፖርት የሚያቅርቡ ናቸው። እንዲህ ያለው መረን የለቀቀ አስተሳሰብ ክቡር የሆነውን ፍጡር ከእንስሳ ተራ የሚያስመድብ ነው።
እንዲህ ያለው መጥፎ ድርጊት የሚፈጸመው በአክራሪ ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆን በፖለቲከኞች ጭምር ነው። ድርጊቱን ገራሚ የሚያደርገውም ሕዝብ ሊያገለግሉበት የተሰጣቸውን ሥልጣን ሀገር ለማፍረስ መጠቀማቸው ነው። በዲሞክራሲ ስም ምለው እየተገዘቱ የሚሠሩት ግፍ ኋላ ቀር ብለው በሚጠሩት የፊውዳል ሥርዓት መንግሥት ይፈጸም እንደ ነበር ማስረጃ ማግኘት አይቻልም። ነውር የሚባል ነገር አያውቁም፤ ዞሮ ለማየት የሚያስችል አንገት አልተፈጠረባቸውም። እንደ አሕዛብ ሁሉ-በአፌ ናቸው። በእንዲህ ያለ ዘመን ሃይማኖተኛ ሆኖ መገኘት የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ ቢሆንም ጸንቶ ለተቀበለው የሚያስገኘው ክብርም ያንኑ ያህል ከፍተኛ ነው።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አዲሱን ዓመት አስመልክተው “በቂምና በበቀል፣ በጥላቻና በመናናቅ እንደዚሁም ማቆሚያ በሌለው የራስ ወዳድነት ክፉ መንፈስ ተይዞ እርስ በርስ የሚጋጭባቸው፣ እግዚአብሔርንም ቸል የሚልባቸው፣ ለሥጋዊና ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ዘላቂ የጋራ ጥቅም የማይጠቀምባቸው፣ ሁለንተና ሕይወቱን በንስሓ የማይታደስባቸው፣ በፍቅርና በሰላም የማይኖርባቸው ከሆኑ ዓመታቱ መጥፎዎች ይሆኑበታል” በማለት ያስተላለፉት መሠረታዊ ጉዳይ ቢሆንም ሰሚ ግን የለም። እንዲህ ያለው ምግባረ ብልሹነት በአክራሪ ሙስሊሞች እና የዓይንህ ቀለም አላማረኝም በሚሉ ፖለቲከኞች የሚከፋ ቢሆንም በቤታችንም ውስጥ የሚንጸባረቅ እኩይ ድርጊት መሆኑ መታወቅ አለበት። በቂምና በበቀል እየተነሣሡ ሲመቻቸው እያሳደዱ፣ ቀን ሲጎድልባቸው ከእግር ሥር እየወደቁ መኖር የሚችሉት እስከ መቼ እንደ ሆነ የሚያዉቁት ፈጻሚዎች ብቻ ቢሆኑም ርግጠኛ የሚሆኑት እሳቱን መለኮሳቸውን እንጂ የለኮሱት እሳት ማንን እንደሚፈጅ ርግጠኛ መሆን አይችሉም።
ቅዱስነታቸው “ በወሰን እና በርእዮተ ዓለም ምክንያት የምናደርገው ክርክርስ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን የሚለውን መርሕ በትክክል ከተገበርን የሚያከራክረው ምኑ ነው? የሀገሪቱ ሕግስ ይህንን መፍታት አይችልም ነበርን ? በወሰን ምክንያት ጠብ የሚነሣውስ መላዋ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆንዋን እየረሳን ይሆንን ? በአንድ የበላይ መሪ፣ በአንድ የሀብት ቋት የምንተዳደር የአንድ ኢትዮጵያ ልጆች አይደለንም ወይ? ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሶ እየሠራ እንዳይኖር የከለከለ ሕግ እና ሥርዓትስ አለ ወይ ? ካለስ እርሱን በምክክር ፈትቶ ስለታላቋ ኢትዮጵያ ብቻ በጋራ መቆም አይበልጥም ወይ? እውነቱ ይህ ከሆነ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተፎካካሪዎች፣ ልኂቃን፣ የስቪክ ማኅበራት እና ምሁራን የሆናችሁ፣ የሆነው ሁሉ ትክክል አልነበረም እና እባካችሁ ወደ ልባችሁ መለስ በሉና ምርጫችሁን ኢትዮጵያ፣ ሰላምና አንድነት ብቻ አድርጉ” በማለት ጨምረው ያስተላለፉት መልእክት የሚመለከተው ፖለቲከኛውን ብቻ ሳይሆን ሰላም በሰፈነበት አካባቢዎች ተዘዋውረው ሠርተው ሀብት እያካበቱ አካባቢየ ወደሚለው ሄደው ሠርተው የሚለወጡትን የሚያሳድደውን አክራሪ ጭምር ነው።
እንዲህ ያለውን እኩይ ተግባር የሚፈጽመው የሃይማኖት ክፍልም ይባል የፖለቲካ ፈረስ ጋላቢ መረዳት የሚገባው እርሱ እንግድነት የሚሄዱበትን አላሳድርም ካለ ወገኖቹን ባዶ እጃቸውን ሊሰድ የሚችል ተግባር ሊፈጸምባቸው የሚችል መሆኑ ነው። የሐድያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ፣ አላባ እንዲሆም የደቡብ እና ምዕራብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በሚገባ ገልጠውታል። በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እና ክርስቲያኖች በእሳት እየተቃጠሉ፣ መንግሥት ባለበት ሀገር ዕለት፣ ዕለት መከራ እየተቀበሉ የሚኖሩት እስከ መቼ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ታላቅነት ነው። የሚጠቅመው እንግድነት የሚሄዱበትን አቅፎ መያዝ፣ የራስንም መርቆ መሸኘት እንጂ እኔ እያሳደድኩ ሌላው እኩይ ድርጊቴን አይረዳውም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።
ብፁዕነታቸው “እነርሱ እያነደዱ እኛ መልሰን መልሰን ስንሠራ የምንኖርበት መንገድ አይኖርም። ሕዝባችን እና ታቦታችንን ይዘን ከተማቸውን ለቀንላቸው እንወጣለን መልሱ ግን ከባድ ነው” በማለት ያስተላለፉትን መልእክት ደጋግሞ አዳምጦ ራስን ከጥፋት፣ ሀገርን ከውርደት የሚታደግ ተግባር መፈጸም ታላቅነት ነው። አላዋቂዎች የብፁዕነታቸውን ንግግር ጦር ከማወጅ ጋር ሊያያዙት ቢችሉም መታወቅ ያለበት ፍቅር ካላሸነፈውና ሀገሬ የሚለው ዕሴት አስሮ ካልያዘው ጦር ሰብቆ ውጊያ ውስጥ ከመግባት የበለጠ አጥፊዎችን የሚጎዳ ተግባር ማከናወን ይቻላል። እንዲህ ከመደረጉ አስቀድሞ ግን አክራሪዎች እና በፖለቲከኞች ጀርባ የታዘላችሁ የጥፋት መልእክተኞች ራሳችሁን ገዝታችሁ ሌላውንም በትግዕሥት ለማሸነፍ ጥረት ብታደርጉ መልካም ነው። የኦርቶዶክሳውያን ትሕትና ፍርሃት የሚመስላቸው፣ ለሀገር ማሰባቸው አላዋቂነት ሆኖ የሚታያቸው አካላት ድርጊታቸው ከአውሬ የከፋ መሆን ደጋግመው መመርመር ቢችሉ መልካም ነው።
ብፁዕነታቸው በስልጤ ዞን የሚኖሩ አክራሪ ሙስሊሞች ምቹ ሁኔታ እየጠበቁ በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሱትን ተደጋጋሚ ጥቃት በተመለከተ “ይህን የምናገረው የስልጤ ሕዝብ እንዲሰማው ነው። ከዚህ በኋላ በስልጤ ዞን የሚገኙ ቤተ ክርስቲያኖችን በእሳት እያነደዱብን፣ እኛ መልሰን ስንሠራ የምንኖርበት መንገድ አይኖርም። ሕዝባችንን እና ታቦታችንን ይዘን ከተማቸውን ለቀንላቸው እንወጣለን። እንዲህ ካደረግን መልሱ ከባድ ነው” በማለት ያስተላለፉት መልእክት የኦርቶዶክሳውያን ትዕግሥት የተሟጠጠ መሆኑን ያስገነዝባል። ትዕግሥቱ የተሟጠጠ ሕዝብ ምን እንደሚያደርግ ደግሞ በየዘመናቱ ሲታይ ኖሯል።ሰው ተስፋ ሲኖረው እንጂ ሁሉም የመኖር አማራጮች ከተዘጉበት የፍርሃትንም፣ የይሉንታንም ገመድ ቆርጦ የጣለ እንደ ሆነ ማጣፊያው ያጣራል። ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ተከባብሮ መኖር ታላቅነት ነው። በብዙ አካባቢዎች ሙስሊሞች በቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ሲሰጡ፣ ክርስቲያኖችም የሙስሊም ወገኖቻቸውን የአምልኮ ቦታ ሲሠሩ ይታያሉ። ከዚህ ተነሥቶ በስልጤ የሚኖሩ ሙስሊሞችን የሚጋልባቸው ምን ዓይነት የክፋት ፈረስ ነው? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው። በእርግጥ በስልጤ ውስጥ የሚገኙ ሙስሊሞች ሁሉ እንዲህ ያለውን ሰይጣናዊ ድርጊት ይፈጽሞታል ብሎ ማሰብ ይቅርና አሳቡን ይጋሩታል ብሎ መቀበል ባይቻልም በእምነቱ የተጠለሉ አክራሪዎች የሚፈጽሙትን እኩይ ድርጊት ለማስቆም መረባረብ ይገባቸዋል።
ሰላም ፈላጊ ሙስሊሞች ማድረግ የሚገባቸው እኩዮችን ለሕግ ማቅረብ፣ ሕግ አስጠባቂ አካላት ኃላፊነታቸውን ከዘነጉም በባህልና በወጋቸው መሠረት ተገቢውን ማስተካከያ ማድረግ ይኖርባቸዋል። መታወቅ የሚኖርበት ብፁዕነታቸው “የስልጤ ሕዝብ ከመቶ ስድሳ የሚሆነው ሀብት አፍርቶ የሚኖረው ባልተወለደበት ቀየ፣ በሌላ ቦታ በሰው ሀገር እየነገደ እየሸጠ እያተረፈ፣ መንገድ እየዘጋ፣ እየሰገደ፣ ሃይማኖቱ ተከብሮለት የሚኖረ ሕዝብ ነው። የስልጤ ሕዝብ በእኔ ተወለደኩበት በሚለው ቀዬ ግን? ቤተ ክርስቲያን አናስነድድም የሚሉ የክርስቲያኖችን መኖሪያ ቤት እና ሱቅ መርጦ ያቃጣላል። ከእንግዲህ ግን ክርስቲያኖችን ማሳደድ ዋጋ ያስከፍላል” በማለት የተናገሩትን ነው።
ሰፊ በሆነችው አገራችን ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ለዘመናት ተከባብረን ብቻ ሳይሆን ተቃቅፈን ኖረናል። ዓለም የሚቀናብንም ልዩነታቸው እስከ እዚህ ነው ተብሎ ማመልከት እስከማይቻል አንድ ሆነን በመኖራችን ነው። በዘመናችን ጥፋትን ከሊቢያም፣ ከግብፅም፣ ከሶርያም፣ ከሊባኖስም፣ ከየመንም እየተጫኑ በሚመጡ አክራሪዎች እየተመሩ ኦርቶዶክሳውያንን ማሳደድ ሰላምን ያናጋል። እነ ሶርያ ክርስቲያኖችን አንይ በማለት የጀመሩት የእርስ በርስ መጨፋጨፍ ከምን ደረጃ እንዳደረሳቸው እያየን ነው። ሊቢያ የሌላ እምነት ተከታይ ባይኖርባትም በሰላም ውሎ ማደር ብርቅ ሆኖባታል። የአገራችን አክራሪዎች ከመልካሙ ነገር ትምህርት መቅሰም ሲያቅታቸው ጥፋት ተጭነው የሚመጡት አገራችንን ለመበተን ካልሆነ መችም እንዲህ እያደረጉ እሳቱ ወደ እኛ አይዞርም ብለው አስበው ከሆነ በጣም የዋሆች ናቸው። ለሁላችንም የሚበጀው እንደ እስከ አሁኑ ተከባብሮ መኖር ብቻ ነው። በሚያደጋግፈው እየተባበርን በሚያለያየን ደግሞ በየራሳችን መሥራት ሀራችንን ሰላም የሰፈነባት ያደርጋታል።