ከአዲስ ተሿሚዎች የሚጠበቅ ተግባርና ኃላፊነት

ከአዲስ ተሿሚዎች የሚጠበቅ ተግባርና ኃላፊነት

ከአዲስ ተሿሚዎች የሚጠበቅ ተግባርና ኃላፊነት

ሥርዓተ ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሐምሌ 09 2015 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷ ልጆች ኤጲስ ቆጶስነት እንዲሾሙላት ባደረገች ጊዜ የተፈጸመውን መንፈሳዊ ተግባር በዘመኑ ታትሞ የወጣው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ የዘገበው “አመራረጡ ግን በዕጣ እንዲሆን ምክር ተቈርጦ ስለነበር በዕጣው ላይ ሰባት ቀን ሙሉ በቤተ ክርስቲያን ጸሎት እየተጸለየበት እና ቅዳሴ እየተቀደሰበት ቆይቶ ለአምስቱ መምህራን ዕጣ ወጣላቸው። ስማቸውም መምህር ደስታ፣ መምህር ኃይለ ማርያም፣ መምህር ወልደ ኪዳን፣ መምህር ኃይለ ሚካኤል ናቸው። አምስተኛው ግን ወደ ግብፅ አልወረዱም” በማለት ነበር (ብርሃንና ሰላም ሰኔ 6 ቀን 1921 ዓ.ም፣ ገጽ 189)።

ኢትዮጵያውያን የፈጸሙት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚያዝዘውን ነበር። ከሌሎች እጩዎች ጋር በአንድ ሆኖ ለሰባት ቀን ሱባኤና ጸሎት ተደርጎበት ‹‹እግዚአብሔር ሆይ ከእነዚህ መካከል የመረጥከውን ለኤጲስ ቆጶስነት መዓርግ አብቃ›› ተብሎ እጣ ሲወጣ የአምስቱ ተሿሚዎች ወጣላቸው። እነርሱም ትውፊቱን ጠብቀው ወደ ግብፅ ወርደው ተሹመው ተመለሱ። ምንም እንኳ የመንግሥት ተጽዕኖ በዘመኑም የነበረ ቢሆን የተመረጡት መምህራን እንከን የሚወጣላቸው አልነበሩም።

አባቶች ግብፅ ወርደው ተሹመው ከተመለሱ በኋላ የተፈጸመውን ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል መዝግበውት የምናነበው “መምህር ደስታ ይባሉ የነበሩት አቡነ አብርሃም ተብለው ጵጵስና ከተሾሙ በኋላ አራቱም ጳጳሳት ለሦስት ወራት አዲስ አበባ ላይ ሆነው ከሊቀ ጳጳሱ ከአቡነ ቄርሎስ ጋር በአንድነት ቆይተው ነበር። የዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያውያን ጵጵስና መሾማቸው አዲስ ነገር ስለሆነበት ባለማወቅ ሕዝቡ ክፉ ነገር እየተናገረ እንዳይጎዳ ሲሆን በሌላ በኩል እነርሱም አስተዳደር እንዲለምዱ ነበር” ይላል (ዝክረ ነገር፤ 1963 ዓ.ም ገጽ 536)።

ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ለሦስት ወራት መቆየታቸውን ቢገልጡም ሥርዓተ ጵጵስና ሲማሩ አዲስ አበባ የቆዩት ለስድስት ወራት ነበር። ከማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ጽሑፍም መረዳት የሚቻለው አንድ አባት ሕዝብ ለመምራት አባት ተደርጎ በኖላዊነት ሲመረጥ አስተዳደር መማር የግድ መሆኑን ነው። አንባብያን ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ ከመመረጣቸው በፊት በጸሎትና በሱባኤ ከተመረጡ በኋላ ደግሞ የአስተዳደር ሥርዓት ተምረው ሲያጠናቅቁ ወደ ተመደቡባቸው አህጉረ ስብከት መሔዳቸው አባቶቻችን ምን ያህል ጠንቃቆች እንደነበሩ ትምህርት የምናገኝበት መሆኑን ነው። በምንገኝበት አስቸጋሪ ዘመን መፈጸም የሚገባው ከዚህ የበለጠ እንጂ ያነሰ መሆን አልነበረበትም።

የአስተዳደር ሥርዓት ሲማሩ ጎን ለጎን በተመደቡባቸው አህጉረ ስብከት የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ባህል፣ ለአባቶች ያላቸውን አመለካከት፣ ማኅበረሰቡ ችግር ሲገጥመው እንዴት እንደሚፈታው አስቀድመው ጠይቀው እየተረዱ ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት፣ የተቀበሉት ኃላፊነት ለታይታ ሳይሆን ለመከራ ጭምር የሚዳርግ መሆኑን አምነው የሚገቡበት ነው።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጥር ፲፫ ቀን ፲፱፻፸፩ ዓ.ም ፲፫ ኤጲስ ቆጶሳትን በሾሙ ጊዜ ውጭ ሀገር ሔደው እስከ ሦስተኛ ድግሪ ተምረው የመጡት ታጭተው የነበረ ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነው “የዘመናዊ ትምህርት ዶክትሬት ወዘተ በሚል በወቅቱ ውጭ ሀገር ተምረው የመጡት ዶክተሮች ቆሞሳት ለጊዜው ሚዛን ስላልደፉ ቦታ ሳይገኝላቸው በመቅረቱ የመምሪያ ኃላፊ ሆነው ይለማመዱ” በማለት ነበር (ዝክረ አበው፣ ፳፻፲፩ ዓ.ም፣ ገጽ ፳፻፭)። ከዚህ አሳብ መረዳት የሚቻለውም አባቶች ኤጲስ ቆጶስነት ከመሾማቸው በፊት አስቀድሞ አስተዳደር መማር፣ የሕዝቡን ባህልና አኗኗር ማወቅ የሚኖርባቸው መሆኑን ነው። ይህ ማለት መንፈሳዊነቱ ይዘነጋል ማለት አይደለም። ሃይማኖት ድርድር ውስጥ የማይገባ መስፈርት ሲሆን ትምህርት ይውሰዱ የተባለው ተጨማሪ ዕውቀት እንዲያገኙ ዕድል ተሰጥቷቸው ይታዩ ማለት ነው።

አንድ አባት ኤጲስ ቆጶስነት ከተሾመ በኋላ የአስተዳደር ተግባርም ሆነ ሌላ ኃላፊነት ከመጀመሩ አስቀድሞ መፈጸም የሚገባውን ዝክረ አበው የሚያስነብበን “በቤተ ክርስቲያን ሕግ (ትውፊት) መሠረት አንድ ኤጲስ ቆጶስ ሢመተ ጵጵስናው ከተፈጸመ በኋላ በተመደበበት አልያም ቀድሞ በሚሠራበት ደብር ሦስት ቀን ሱባኤ መያዝ እንዳለበት ያዝዛል” በማለት ነው (ገጽ ፳፻፱)። ተሿሚው እንዲህ የሚያደርገው በአንድ በኩል የአምላኩን ፈቃድ ለመጠየቅ ሲሆን በመቀጠልም የአስተዳደር ሥራ ከጀመረ በኋላ የሚጎትተው ብዙ በመሆኑ ጊዜ ስለማያገኝ ጭምር ነው። በሌላ በኩል መንፈሳዊ ተግባር መጀመር የሚኖርበት በጾም በጸሎት መሆኑን ያስገነዝባል። ቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከጎበኛቸው በኋላ ሀገረ ስብከት ተከፋፍለው ከመሔዳቸው አስቀድሞ ጾም ጸሎት መያዛቸው ተከታዮቻቸው ሁሉ አሠረ ፍኖታቸውን እንዲከተሉ አብነት ለመሆን ነው።

ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የተሾሙ አባቶችም ወደ አህጉረ ስብከቶቻቸው ከመሔዳቸው አስቀድሞ ከነባሮቹ አስተዳደርን ተምረው መሔድ ይገባቸዋል። አስተዳደሩን ጠንቅቀው የሚያውቁት ቢሆኑ እንኳ ደግመው መማር ይኖርባቸዋል። አገልግሎታቸውንም በትውፊቱ መሠረት በጾም በጸሎትና በሱባኤ መጀመር አለባቸው። እንዲህ ማድረጋቸው ስለትሕትናቸው አምላካችን እግዚአብሔር የኤጲስ ቆጶስነት ዘመናቸውን የተባረከ ያደርግላቸዋል። ምእመናንም በአገልግሎታቸው ይረካሉ፣ ዘመኑን የሚዋጅ አባት የሰጣቸውን አምላካቸውንም ያመሰግናሉ። ማስተዳደር ከትምህርት ይልቅ ልምድ እንደሚጠቅም በመረዳት እና የተጣለባቸውን ኃላፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ራሳቸውን ማዘጋጀት የሚገባቸው በመንፈሳዊ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን በአስተዳደርም ጭምር ነው።

ዋቢ መጻሕፍት

  1. ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ፣ ፭ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፳፬፣ ሐሙስ ሰኔ ፮ ቀን ፲፱፻፳፩ ዓ.ም
  2. ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ ዝክረ ነገር፣ አዲስ አበባ፣ ፲፱፻፷፫ ዓ.ም
  3. ወሰን ደበበ፣ ዝክረ አበው፡- ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም። ራምፕ ፕሪንቲንግ፣ ግንቦት ፳፻፲፩ ዓ.ም