ከወርቃማው ሕግ አትንሸራተቱ (የነገረ ሰብእ ትምህርት ጉድለት የወለደው አገራዊ ቀውስ ክፍል ሁለት)

የነገረ ሰብእ ትምህርት ጉድለት የወለደው አገራዊ ቀውስ

የነገረ ሰብእ ትምህርት ጉድለት የወለደው አገራዊ ቀውስ

የተከበራችሁ የማኅበራዊ ሚዲያችን ተከታታዮች አስቀድምን ባስነበብነው የዚህ ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ሰው በእግዚአብሔር አርአያ እና ምሳሌ የተፈጠረ የፍጥረታት ንጉሥ፣ ከሌሎች ፍጥረታት ተለይቶ ዐዋቂ እና ሕያውነት ያለው፣ በፍጥረታት ላይ የሠለጠነ ባለጸጋ ፍጡር መሆኑን አቅርበን ነበር። በዚህም ምክንያት ሰው ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ ሲጠፋ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ “እስመ በፈቃዱ፣ ወበሥምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጽዐ አድኀነነ” እንደ ተባለው ሰው ሆኖ ሰውን ከውድቀት አነሣው። ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ትቶ አንዱን ነገድ ሰውን ለመፈለግ ሰው የሆነው ለሰው ካለው ጽኑ ፍቅር የተነሣ ነው።

ሰውን ያዳነውም ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ በሚበልጥ ጥበብ ነው። በከብቶች ግርግም የተወለደው፣ ረኃቡን እና ጥሙን ታግሦ ወደ ግብፅ የተሰደደው፣ ሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት ዞሮ ያስተማረው፣ በአይሁድ መከራ የተቀበለው፣ የተገረፈው፣ የተጎተተው፣ በመስቀል የተሰቀለው፣ በሚስማር የተቸነከረው፣ ነፍሱን በገዛ ፈቃዱ የሰጠው እና ወደ መቃብር የወረደው ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ለመግለጥ ነው። ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ቢሆንም ክርስቶስ ሞትን የተቀበለው በራሱ ፈቃድ ለሰው ልጆች ካለው ፍቅር ነው። በመስቀል ላይ እንዲሰቀል ያደረገው፣ ያስገረፈው ጲላጦስ ቢሆንም ግርፋቱን የተቀበለው በፈቃዱ ለሰው ልጅ ካለው ፍቅር የተነሣ ነው። በመስቀል ላይ የተቸነከረው በሚስማር አይደለም በፍቅር ነው። እርሱ ሁሉን ቻይ አምላክ ሲሆን በፈቃዱ ለድኅነተ ዐለም መከራውን ታግሷል።

ለሰው ልጅ ይህ ሁሉ የተደረገለት፣ ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለለት ክቡር ፍጥረት ነው። ሰው አምላክ ለመሆን ፈልጎ በእግዚአብሔር ላይ ዐምጾ ከእባብ ጋር የማይገባ ምክር ተመካክሮ ነበር። እግዚአብሔር ግን ሰው ሆኖ የሰውን የአምላክነት ተምኔት ፈጸመለት። አዳም በበደለው ተበዳዩ ራሱ ቤዛ ሆኖ ከፈለለት። ቅዱስ ጳውሎስ “ጠላቶቹ ሳለን በልጁ ሞት ታረቀን” በማለት እንደ ገለጠው ሕግ አፍራሾች ብሆንም ቸል ብሎ ይተውን ዘንድ አልፈቀደም። በራሳችን መሻት ተቅበዝብዘን ከክብር ብንጎድል፣ በሞቱ ከሞት እስራት ፈትቶ ወደ ቀደመ ክብራችን መለሰን። ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ “አምላክ ሰው የሆነው ሰውን አምላክ ለማድረግ ነው” በማለት ያስተማረው ለዚህ ነው። አምላክ ሰው ሲሆን ከእመቤታችን የነሣውን ሥጋ የባሕርይ አምላክ፣ እኛን ደግሞ የጸጋ አማልክት አደረገን። በዚህም ቅዱሳን “የጸጋ አማልክት ለመሆን የተጠራን ድንቅ ፍጡራን ነን” ብለው ለመናገር በቁ። በቅድመ ፍጥረት ለሰው ልጅ ምድራዊ ምግብን ሁሉ ያዘጋጀ አምላክ በዳግም ፍጥረት ሰማያዊ ምግብና መጠጥ አዘጋጀለት። አትብላ የሚል ትእዛዝ ሰጥቶት መጠበቅ ቢከብደው ሥጋውን ቆርሶ፣ ደሙን አፍስሶ ብላ ጠጣ ብሎ የሕይወት እንጀራ እና የሕይወት ውኃን ሰጠው። ከዚህ የምንረዳው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያልሰጠው ክብር አለመኖሩን ነው።

ከዚህ በተቃራኒው ዐለም ሰውን ግብ ያደረገ ፍልስፍና፣ ሳይንስ፣ ርእዮተ ዓለም እና ሥርዓት ስትከተል አትታይም። እንዲያውም በተቃራኒው ሰው ቁሳቁስ ለማምረት እንደ አንድ ግብዓት ነው የሚቆጠረው። የሳይንስ ግቡ የሰውን ሕይወት ማቅለል ነው ቢባልም ቅሉ አጠቃላይ ሥሪቱ ግን ሰውን በቁሳቁስ ሊተካ የሚችል “ተራ ፍጡር” እንጂ ክብር እና ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ፍጥረት መሆኑን መረዳት አይችልም። የሰው ሞት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ነጻነት መገፈፍና ሌሎች ሰው ሠራሽ ችግሮች ሁሉ በዚህ ምድር ላይ ለሰው የተሰጠው ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑን የሚያስገነዝቡ ናቸው።

ሰዎች በተለያዩ በሽታዎች ሲጠቁና ሲሞቱ “በሽታው አምራቹን የሰው ኃይል እያሳጣን ነው” የሚል ዜና ሲሠራ የምንሰማው የሰውን ክብር ከመግለጥ ይልቅ ከሟቹ ይገኝ የነበረውን ጥቅም ብቻ አስልቶ ኀዘንን መግለጥ የሰውን ታላቅነት አለመረዳት ነው። የጉዳዩ ትኩረት አምራችነቱ ላይ እንጂ ሰውነቱ ላይ ሲያርፍ አለመታየቱም ክብሩን ካለመረዳት የመነጨ ነው። ሰውን የሚገፋ እና የበይ ተመልካች ያደረገ ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለም፣ ለሰው ሳይሆን ሰው ለሚያስገኘው ነገር ቅድሚያ የሚሰጥ የትምህርት ሥርዓት፣ ለብዙኀን ሳይሆን ለኅዳጣን ቅድሚያ የሚሰጥ የአስተዳደር ፍልስፍና በዐለም ላይ የተንሰራፋው ሰው የራሱን ክብር ባለመረዳቱ ምክንያት ነው።

ሰው በሰው ላይ በደል ሲፈጽም፣ ሰውን ሲያሳድድ፣ ንብረቱን ሲቀማ እና ሲያወድም አልፎ ተርፎም ሰውን ሲገድል የማይሳቀቀው ሰው እንስሳ ነው ተብሎ የተነገረውን አምኖ ተቀብሎ በዚያው ስለሚመራ እንጂ ሰውን ሲበድል የራሱንም ክብር እያዋረደ መሆኑን ስለማይረዳው ነው። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “ሰው ጅምር ፍጡር ነው፤ የሚሞርዱት እና አስተካክለው የሚቀርፁት መጻሕፍትና መምህራን ናቸው” የሚሉት ያለ ምክንያት አይደለም። በዚህም ምክንያት ሰው የአካባቢው ፍጡር ነው ይባላል። ሰውን ዐውሬም፣ ሰውም አድርጎ በማሳደጉ ረገድ ሁሉም የራሱ ድርሻ አለው። የሰው ጠባይ እና ማንነት በቤተሰቦቹ፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ፣ በአጠቃላይ በአገር ዕሴት ላይ ተመሠረተ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ለሰው ክብር በመስጠት እና የሰውነትን ዋጋ በመረዳት አንጻር ጥያቄ የሚነሣበት ማንነት አልነበረም። ካለፉት አርባ ዐመታት ጀምሮ እየተከተልነው ያለነው የዘውግ ፖለቲካ ግን ሰውን በሰውነቱ ሳይሆን በንኡስ ማንነቱ የሚለካ ሆነ። በዚህም ምክንያት ዘውግ ተኮር የፖለቲካ አራማጆች እና ጭፍሮቻቸው ከእነርሱ ጎሣና ቋንቋ ውጭ ያለውን በሙሉ እንደ ሰው የማይቆጥሩ፤ ጉዳታቸውና ሞታቸውም የማይገዳቸው ሆኑ። እንዲህ ያለው አመለካከት ሰብእናን የሚያዋርድ ከመሆኑ በተጨማሪ አገርን የሚያጠፋና አደገኛ ከመሆኑም በላይ ማቆሚያ ለሌለው ቂምና እልቂት የሚዳርግ ነው። አንድ ሰው ቋንቋ ከመቻሉ በፊት፣ የእገሌ ዘውግ ነኝ ከማለቱ በፊት ሰው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

በዚህ ምድር ላይ ያሉት ፍልስፍናዎች ሁሉ በኦርቶዶክሳዊው የነገረ ሰብእ ዕሳቤ ሊቃኙ እና ሊጠመቁ ይገባል የምንለውም ፍልስፍናው ጎደሎ በመሆኑ ነው። ኦርቶዶክሳውያንም ለዚህም አስተምህሮ ቅርብና ተገዢ መሆን አለብን። ከኦርቶዶክሳዊው የነገረ ሰብእ አስተምህሮ መራቅ እና መውጣት በአገራችን ብሎም በዐለም ላይ እያመጣ ያለውን ቀውስ እየተመለከትነው ነው። ሰውን መግደል፣ የሰው ነፍስ ማጥፋት ዶሮ የማረድ ያህል ቀላል ተደርጎ መታየት የጀመረው የሰው አመለካከት በመብዛቱ ነው። የግፍ አገዳደል በየዕለቱ የምንሰማው መደበኛ ዜና ከሆነ ሰነባበተ። የሰው ክቡርነታ እና የተፈላላጊ ጾታዎች በጋብቻ መዋሐድ ግንዛቤ በመንሸዋረሩም ግብረ ሰዶማዊነት ሕጋዊ እየሆነ መጥቷል። ጾታን መቀየር የዘመናዊነትና የሥልጣኔ መገለጫ ተደርጎ ተቆጥሯል። ሰዎች በመረጡት መንገድ በመሔድ ሰላም ለማግኘት ይጥራሉ። ይህን ሁሉ እያደረጉም ግን ሰላም ማግኘት አልቻሉም። ምክንያቱ ደግሞ ሰላም የሚገኘው ለሕሊና የሚስማማ ተግባር በመፈጸም እንጂ ከሥነ ፍጥረት ሕግ ውጪ በመሆን አይደለም። ሰው የሚያደርገው ነገር ትክክል ስለመሆን አለመሆኑ ለማወቅ መምህር አያስፈልገውም፤ የራሱ ሕሊና ያውቀዋል።

የአሕዛብ መምህር የተባለው ቅዱስ ጳውሎስ ሕግ ያላቸው በሕግ፣ ሕግ የሌላቸው ደግሞ በልቡናቸው ሕግ እንደሚፈረድባቸው እንዲህ ተናግሯል። “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፣ ሕግ ባይኖራቸው አንኳን ለራሻቸ ኽግ ናቸው። እነርሱ ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፣ አሳባቸውም እርስ በእርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ” (ሮሜ ፪፡፲፬-፲፭)። ክፉን በሚያደርግ ሰው መከራና ጭንቀት ሆንበታል እንደሚል ሰዎች የሚያደርጉት ከንቱ ተግባር ዕረፍት ይነሣቸዋል። ለዚህም ነው በተለይም በምዕራቡ ዐለም ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ የሚያሻቅበው። ከሰዎች መሸሸግና መራቅ ይቻል ይሆናል። ከሕሊና ግን ወዴትም መሸሽ አይቻልም። የሕሊና ወቀሳን የሰሙት ወደ ልቡናቸው ይመለሳሉ። ለመስማት ያልፈለጉ ደግሞ ራሳቸውን እስከወዲያኛው በማጥፋት ከወቀሳ መዳን እንደሚቻል በማሰብ ራሳቸውን ያጠፋሉ። ራሳቸውን ለማጥፋት ካነሣሣቸው ድርጊት ጀምሮ ራሳቸውን እስከ ማጥፋት ድረስ የፈጸሟቸው ተግባራት ሰውነትን በአግባቡ ካለመረዳት፣ የተፈጠሩበትን ዓላማ ካለመገንዘብ የመጡ ናቸው።

ወንድም በወንድሙ ላይ የሚነሣው ከሰው ይልቅ ገንዘብን በማስቀደም፣ ከሕይወት ይልቅ ቁስን በማስበለጥ ነው። እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ኃይሉና በፍጹም አሳቡ እንዲወድ የታዘዘው ሰው፣ ሰውን እንደራሱ እንዲወድም ይህ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው። ወንድም ማለትም በሰውነት የሚመስለንን ሁሉ ማለት ነው። ሰው ሌላውን እንደ ራሱ ሲወድ ሊገድለው፣ ሊሰርቀው፣ በሐሰት ሊመሰክርበት፣ ገንዘቡንና ንብረቱን ሊመኝና ሊቀማ፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ክብር ሊነፍገው አይችልም። ስለሆነም ሰው የተፈጠረበትን ዐላማ ሊገነዘብ፣ የተሰጠውን ክብርና ልዕልና ሊረዳ፣ በራሱም ላይ ሆነ በሌላው ላይ ሥልጣን የሌለው መሆኑን ሊያውቅ፣ ከዚህ እውነት በተቃራኒ የሚነገሩ ፍልስፍናዎች፣ ርእዮተ ዐለማት፣ “ትምህርቶች” እና “አመክንዮዎች” ሁሉ ከንቱ ልፍለፋዎች መሆናቸውን ሊያስተውል ይገባል።

በተግባር ባይመራበትም ዐለሙም ወርቃማ ሕግ በማለት የሚጠራው “በአንተ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን በሌላው ላይ አታድርግ” የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ነው። “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና” (ማቴ. ፯፡፲፪)። ይህን ሕግ ማክበር ቢቻል እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን ከብር መረዳት፣ የእግዚአብሔርን ሕግ ሁሉ መፈጸም ማለት ነበር። በእርግጥ ክርስትና ከዚህም በላይ ነው። “በሰማይ ላላ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ፣ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አደርጉ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ። እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፤ በጻድቃንና በኀጢአተኞች ላይ ዝናቡን ያዘንባልና” (ማቴ. ፭፡፵፬-፵፭) ተብለናል። ፍጹም እንዲሆን የታዘዘ ሰው ቢያንስ ሰው መሆን ሊከብደው አይገባም። ሰው ሕይወቱን ሊመራበት የሚገባው ብቸኛው መንገድም ይህ ነው። ከማስተዋል ጎዳና በመውጣት እንደ ውኃ ሌሎች በመሩት መንገድ መንጎድ ግን መዳረሻው ሞት ነው። ይህ ደግሞ በየዕለቱ ሕይወታችን የምናየው ሐቅ ነው። በዐዲሱ ዐመት ከዚህ የጥፋት፣ የስሕተትና የሞት መንገድ ወጥተን፣ ሕይወት በሚገኝበት የእግዚአብሔር ቃል አሳባችንን እና ልቡናችንን ሁሉ እንድንቃኝ እግዚአብሔር ይርዳን።