“ክርስቲያኖች መተት አደረጉብን”

“ክርስቲያኖች መተት አደረጉብን”

“ክርስቲያኖች መተት አደረጉብን”

መቼም በየዘመኑ የማይሰማ ጉድ የለም። ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አንሥቶ በየሀገሩ ይኖሩ የነበሩ አረማውያን እና አሕዛብ ክርስቲያኖችን ተከራክረው ማሸነፍ እንደማይቻላቸው ሲረዱ አንድ መላ ዘይደው ነበር። ይኸውም “ክርስቲያኖች የሰው ሥጋ ይበላሉ” ብለው በማስወራት ስለክርስትና የማያውቁ የሰው ልጆች እንዲርቁ በሌላ በኩልም ሃይማኖቱ ሕገ ወጥ ተብሎ ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ማስደረግ ነበር። ይህም ሐዋርያት ወንጌልን ለመላው ዓለም ለማዳረስ በሚሰማሩባቸው ቦታዎች ሁሉ እንደ በግ እንዲታረዱ የሱ ምክንያት ነበረው። የአረማውያኑ አሳብ መከራውን ተሰቅቀው ሌሎች እንዲሸሿቸው ማድረግ ቢሆንም ውጤቱ ግን በተቃራኒው ነበር።

ድርጊቱም በአንድ በኩል ቤተ ክርስቲያን በሰማዕታት ደም እንድታሸበርቅ ምክንያት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ዕለት ዕለት ወደ ክርስትና የሚገቡት አሕዛብ ቁጥር እየጨመረ ሄደ። “የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን ዘር ነው” ያስባለውም እንዲህ ያለው ተግባር ነው። የክርስቲያኖችን ስም ማጥፋቱ በመላው ዓለም በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በሀገራችንም የተለመደ እንደ ነበር ገድለ ተክለ ሃይማኖትን እና ገድለ ቀውስጦስን ስናነብ የምናረጋግጠው ሐቅ ነው። አቡነ ተክለ ሃይማኖት ኢትዮጵያን ዞረው ሲያስተምሩ ኖረው ወደ መጨረሻ አካባቢ ደብረ አስቦ ገብተው፣ በአት አጽንተው ተጋድሎ በመጀመራቸው አካባቢውን ወደ ክርስትና ይቀይሩብናል ብለው የሰጉ ጣዖት አምላኪዎች መነኰሳት የሰው ሥጋ ይበላሉ ብለው ማስወራት ጀመሩ።

ድርጊቱ ጎልቶ የወጣው ትውልዱ ከምዕራብ ሸዋ የሆነው አባ ፊልጶስ ገና ልጅ ሳለ ወደ ደብረ አስቦ ገዳም በሄደ ጊዜ የፈጠራውን ድርሰት ከወላጆቻቸው የሰሙት እረኞች ወደ “እነርሱ አትሂድ፤ እነርሱ እኮ ሰው ይበላሉ” ብለው ለመከልከል በሞከሩበት ጊዜ ነው። ሕፃኑ ፊልጶስ ወደ ገዳም የሚሄድበትን ምክንያት ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር መንገዱን አሳዩኝ እንጂ ስለ እኔ መበላት አትጨነቁ አላቸው። እነርሱም ለራስህ ብለን እንጂ ምን ገዶን ብለው፣ መንገዱን መርተው ወደ ገዳሙ አደረሱት። በገዳሙ ውስጥ በተጋድሎ በመኖርም መንኵሶ ሦስተኛው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ ለመሆን በቃ።

ሰሞኑን ከስልጤ ሀገረ ስብከት የተሰማውም እንደ ተለመደው ተመሳሳይ ስም የማጥፋት ዘመቻ መሆኑን መረዳት ይገባል። አክራሪዎች ቤተ ክርስቲያን ለማቃጠል ሲሔዱ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዳይቃጠልባቸው የተከላከሉ ክርስቲያኖች ቤቶች ተመርጠው ተቃጠሉ። ይህን ድርጊት ሕጋዊ ለማስመሰል የፈጠሩት የሐሰት ምክንያት ደግሞ “ክርስቲያኖች መተት ስላደረጉብን ነው ቤቶቻቸውን ያቃጠልንባቸው” የሚል ነው። ይህ የሐሰት ድርሰት የአክራሪዎች ይሁን የፖለቲከኞች ወደ ፊት የሚጣራ ቢሆንም ክርስቲያኖችን ያሳደድናቸው በመተት ስላፈዘዙን ነው ማለት ግን በእጅጉ አሳፋሪ ነው። የራስን እምነትም ማቅለል ነው። አክራሪዎች አስገድደውና ደልለው እንጂ አስተምረው እና አሳምነው ሰውን ወደ ራሳቸው ሃይማኖት የመሳብ አቅም የላቸውምን ያሰኛል። ይህ የአክራሪነት አንዱ መገለጫ ነው። በአክራሪነት ውስጥ እኔ ብቻ ልኑር እንጂ በአሳብ የሚለይም ይኑር የሚል መርሕ የለም። በዚህም ምክንያት ከእነርሱም ሲወሰድባቸው አስተምሮ ከመመለስ ይልቅ በሰይፍ ማስፈራራትን የአስተምህሯቸው አንድ አካል ያደርጉታል። ክርስቲያኖች መተት አደረጉብን የሚለው አሳብም ክርስቲያኖችን ለማሳደድ አንዳንድ አክራሪዎች እና መለያየትን የሚሰብኩ ፖለቲከኞች የተጠቀሙበት ክርስቲያኖችን የማሳደጃ ስልት እንጂ የስልጤ ሙስሊሞች አሳብ እንዳልሆነ መግለጥ ይገባል።

ማንም ሰው በፈጣሪ ሲያምን ሌላ ሰው መተት አድርጎ ይጎዳኛል ብሎ ሊያምንና በዚያም ተነሣሥቶ ጥቃት ሊፈጽም አይገባውም። ምክንያቱም እምነት በመተት የሚፍረከረክ አይደለም። እንዲያ ካልሆነ ደግሞ መተትን ማፍረስ የማይችል እምነት ነው ያላችሁ? የሚል ጥያቄ ያስነሣል። ክርስቲያኖች በየዘመናቱ ለሐዋርያዊ ተልእኮ ወደ አሕዛብ ወይም አረማውያን ወደሚበዙባቸው አካባቢዎች ሲገቡ የአረማውያኑ የመጀመሪያ ሙከራ ወንጌልን በመተት ለማሰር መሞከር ነበር። የሚያስገርመው ደግሞ ራሳቸው ከመቶ እስከ አንድ ሽሕ የሚደርሱ ጣዖታትን አቁመው እየሰገዱ ክርስቲያኖችን መተተኛ ብለው መስደባቸው ነበር። የተሰበሰበው ጣዖት ሁሉ አንድ ነገር ማድረግ ሲሳነው ዞረው ክርስቲያኖችን አስማተኛ በማለት ስም አስጠፍተው ተከታይ እንዳያገኙ ጥረት ቢያደርጉም ውጤቱ በተቃራኒው ሲሆን ኖሯል። ሐሰተኛ ወሬ ለጊዜው እንጂ በዘላቂነት አሳምኖ ማስቀረት ስለማይቻለው “ክርስቲያኖች የሚያምኑት በትክክለኛው አምላክ ነው” ብለው የነገሥታቱን ዛቻ፣ ሰይፍና መደለያ ወደ ጎን በማለት ተጠምቀው የቤተ ክርስቲያን አባል፣ የክርስቶስ አካል ይሆኑ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚነግረን እውነታ ነው።

ሰሞኑን እየተነገረ ካለው አንድ ነገር መረዳት ይገባል። ይኸውም በስልጤ የችግሩ ፈጣሪ የሆኑ አክራሪዎች ጠንካራ ክርስቲያኖች መኖራቸውን አለመረዳታቸውን። በአካባቢው የሚኖሩ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወታቸውና አገልግሎታቸው ፍሬ አፍርቶ ሌሎችንም ስቦ እስከ ማምጣት ደርሷል ማለት ነው። ብዙ ፈተና እና መከራ ባለበት አካባቢ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በቁጥራቸው ኅዳጣን ቢሆኑም የሕይወታቸው ብርሃን በሌሎች ላይ ፈንጥቆ ወደ ቤቱ ስቦ ማምጣት መጀመሩ አክራሪዎችን አስደነግጧቸዋል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ እያሉ ወደስደው ሳይጨርሱን በሰይፍ እንጨርሳቸው ወደሚል ሰይጣናዊ ቅንዓት ተሸጋግረዋል።

በስልጤው ድርጊት የክርስቲያኖች መደብደብና ንብረታቸው መቃጠሉ ያላረካቸው አንዳንድ አክራሪዎች በአንድ እጃቸው መጽሐፍ፣ በሌላኛው እጃቸው ደግሞ ፖለቲካውን ተደግፈው ከተማ ተቀምጠው የጦርነት ነጋሪት ይጎስማሉ። በክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን በደል በሚናገሩ አባቶች ላይ ይዝታሉ። በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን ቅዱስ ሲኖዶስ ጦርነት አውጆብናል በማለት ጀሌዎቻቸውን ተጨማሪ ጥቃት ይቀሰቅሳሉ። ይህን ሲያደርጉ መቼም እነርሱ እና ተከታዮቻቸው ሎሚ እየወረወሩ አለመሆናቸው ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም። ክርስቲያኖች ልንገደል እና ልንሳደድ አይገባም ብለው ሲናገሩ ጦርነት ማወጅ በአንጻሩ አክራሪዎቹ ምክንያት እየፈለጉ ክርስቲያኖችን ሲገድሉና እና ሲያፈናቅሉ መብት ማስከበር የሚባለው በምን መስፈርት እንደሆነ የሚያውቁት እነርሱ ብቻ ናቸው።

ሌላው መታወቅ ያለበት ዐቢይ ጉዳይ መተት ሠሩብን የሚሉት ክርስቲያኖች አስተምረው በማጥመቅ ክርስቲያን ማድረጋቸውን ነው። ምክንያቱም ተናጋሪዎቹ “ቤተ ክርስቲያን ወስደው ጠበል ማጥመቃቸውንም” እንደ መተት በመቁጠር ሲያብራሩ ተሰምተዋል። ማስተማር፣ ማጥመቅና መቀደስ ግን የቤተ ክርስቲያን ዋና ተግባራ እንጂ መተት ማድረጓ አይደለም። ያላመኑትን ማስተማር፣ ያመኑትን ማጥመቅ፣ የተጠመቁት በሥጋ ወደሙ መቀደስ (ማተም) መተት የሚባልበት ምንም ምክንያት የለም። በማስተማር ማሳመን የሚያስደነግጣቸው አካላት ካሉ እርሱ የራሳቸውን የቤት ሥራ አለመወጣታቸውን ከሚያሳይ በስተቀር በሰባኪው በኩል ወንጀል ተደርጎ የሚቆጠርበት አግባብ የለም። ተከራክሮ መርታት፣ ሰብኮ ማሳመን እየተቻለ በደመ ነፍስ እና በስሜት እየተነዱ በሰይፍ ማስፈራራት ክርስቲያኖችን ወንጌልን ከመስበክ ሊያስቆማቸው አይችልም። እንዲህ ያለው ድርጊት እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የነበሩ አረማውያን እና ዓላውያን ነገሥታት ይፈጽሙት የነበረ ነገር ግን ውጤት ያላመጣ እኩይ ምግራበር ነው። እውነትን የያዘ በጦር አንደበት፣ በፈረስ አንገት ሳይሆን፣ በምልክት ነው የሚያስፋፋው። ሰይፍ የሚያነሡ ግን በሰይፍ ይጠፋሉ።

ስለሆነም ለወገኖቻችን የምንመክረው ለሁላችንም የሚበጀን እስከ አሁን እንደኖርነው ተከባብረን ለመኖር የሚያስችለንን ተግባር እንዲፈጽሙ እንጂ ሰይፍ እንዲያነሡ አይደለም። ሕግ ባለበት አገር አንደኛው አሳዳጅ፣ ሌላኛው ተሳዳጅ ሆኖ መኖር እንደማይችልም መረዳት ይኖርባቸዋል። እኛ እንዳሻን እንሁን፣ እናንተ ያልናችሁን ብቻ ፈጽሙ ማለት  አብሮ አያኗኑርም። አክራሪዎች የሚጭሩት እሳት ብዙ ጥፋት ሳያደርስ የሚቆመው “ቢቻላችሁስ ከሁሉም ጋር በሰላም ኑሩ” በሚለው አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት ክርስቲያኖች ታግሠው ነው። ነገር ግን በደል ሲበዛ ትዕግሥትን ሊፈታተን እንደሚችል መረዳት ይገባል። ለሁላችንም የሚበጀው  መከባበሩ ነው። የተፈጸመው እኩይ ደርጊት የሁሉም የስልጤ ሙስሊሞች እንዳልሆነ በውል እንረዳለን። ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ አሳቦችን ተጭነው የሚበጠብጡ አክራሪዎችን ዕረፉ ማለት፣ የክፉዎቹን ድርጊት መስመር ማስያዝ ይገባል።

ለአገራችን የሚጠቅመው ለዘመናት እንደኖርነው በመከባበር መቀጠል ብቻ ነው። መንግሥትን ተገን አድርገንም ሆነ የውጭ ርዳታን ተደግፈን እናጥፋችሁ ማለት አይቻልም። የተፈጸመው እኩይ ድርጊት ክርስቲያኖችንም፣ ሙስሊሞችንም የሚጎዳ ነው። “ክርስቲያኖች መተት አደረጉብን” የሚሉትም በእምነታቸው የማይተማመኑ መሆናቸውን ራሳቸው እየመሰከሩ በመሆኑ እምነታቸውን ባያስተቹ መልካም መሆኑንም ማስገንዘብ እንወዳለን። መተትና አስማት የሚያደርጉ ካሉም ከማንም ጋር ሳይዳበሉ ጥፋተኞችን በሚገባው አግባብ ወደ ሕግ በመውሰድ ተገቢው ርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል። በግለሰብ ደረጃ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ወይም የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ አስተምህሮ ባለመረዳት ማስተማር እና ማጥመቋን እንደ ድግምት በመቁጥር በሰይፍ መፍትሔ ለማምጣት ማሰብ ክርስትና የቆመበትን መሠረት አለመረዳት ነው።

ከሱዳን እና ከፋርስ ለሚመጣው መተት ሙስሊም ወገኖቻችንን በሙሉ ተጠያቂ እንደማናደርግ ሁሉ እነርሱም መተት ተደርጎባቸው ቢሆን እንኳ መተት አድራጊውን ለይቶ መናገር እንጂ ክርስቲያኖችን ሁሉ ለማጥፋት መሞከር መብረጃ የሌለው ግጭት ያስከትላል። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሚታወቁ አስማተኞች አንዱ በሰሜን አፍሪካ የኖረው ቆጵርያኖስ ነው። በመተቱ ክርስቲያኞችን ለማጥፋት ቢሞክርም በቅድስት ዮስቲና አማካኝነት አምኖ ተጠምቋል። እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት ሲበድሉ ራሱ ማጥፋት የተሳነው ይመስል “አንተ አልቻልህ ያለውን በሰይፍ አጠፋንልህ፤ ደስ ይበልህ” ማለት ቀልድ መሆኑ መታወቅም አለበት። በእምነቱ የተማመነ አስተምሮ፣ ተከራክሮ እና ረትቶ እንጂ በሰይፍ እና በማስገደድ የድኅነትን መንገድ ማሳየት አይቻልም። መግደል የማንንም ቤት አይሠራም።