ወቅታዊ መልእክት
ግንቦት ፯ ቀን ፳፻፲ወ፯ ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት !!
በቅድሚያ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንኳን ለ፳፻፲ወ፯ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ። በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ የሆነ ውይይት እንድታከናውኑ የልጅነት ጸሎታችን ነው።
የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ የሚወያይበትን አጀንዳ ተመልክተነዋል። የተያዘውም አጀንዳ ጠቃሚ እንደሆነ ተረድተናል። ነገር ግን አሁን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ የሚስተዋሉ ቁልፍ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበዋል ብለን አናምንም። ምክንያቱም ከአጥቢያ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ የሚስተዋሉ፤ በቅዱስ ሲኖዶስ በቁርጠኝነት ዘላቂ መፍትሔ ሊበጅላቸው የሚገቡ ዘርፈ ብዙ አስተዳደራዊ እና ተያያዥ ጉዳዮች ለውይይት ሳይቀርቡ ታልፈዋል።
በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተለይተው፣ በማስረጃ ዳብረው እና በመጨረሻም ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲ወ፯ ዓ.ም የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ከበርካታ አህጉረ ስብከት ከተውጣጡ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር አባላት እና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከተውጣጡ የክፍለ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት አመራሮች፣ የገዳማት እና አድባራት ሰንበት ት/ቤት ሊቃነ መናብርት ጋር በአካልና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በመሆኑም በአካልና በቴክኖሎጂ በአመራሮች ውይይት የተደረገባቸው፤ የጋራ አቋም የተያዘባቸው እንዲሁም በቀጥታ የኦርቶዶክሳዊያን ምእመናንና ምእመናት ጥያቄም ጭምር የሆኑትን፤ እኛ የነገይቱ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ወጣቶች በልጅነት አንደበት እንደሚከተለው ለማቅረብ እንወዳለን ።
እነርሱም፦
1. የቤተ ክርስቲያንን ሲኖዶሳዊ ልዕልና እና አንድነትን ማስጠበቅ ፤
ሀ. ታላቂቱ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከትናንቱ ይልቅ ዛሬ ተቋማዊ ህልውናዋ እና ልዕልናዋ አስጊ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገ ቤተ ክርስቲያን እና መዋቅራዊ አሠራርን በመፈተሽ እና በማስጠበቅ የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ፈተና በፍጥነት ሊያስቆም ይገባል፡፡
ለ. በነገረ ሃይማኖት ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ሐሰተኛ ትምህርቶች ቤተ ክርስቲያን የጠራ ትምህርቷን በተገቢው ሁኔታ፣ በሚገባው ዐውድ እና በሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጥባቸው፤
ሐ. ሐሰተኛ ትምህርት ያስተላለፉ ከመምህራን እስከ ሊቃነ ጳጳሳት ያሉ አካላት ላይ ተገቢው ቀኖናዊ ሥራ እንዲሠራ፤
መ. እየተድበሰበሰ ያለው የነገረ ቅብዓት ጉዳይ የማያዳግም እልባት ሊሰጠው ይገባል።
ሠ. በትግራይ ክልል የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ነፍስ ጉዳይ በእጅጉ ያሳስበናል። በክልሉ ከሚገኙ አህጉረ ስብከት አስተዳደራዊ ግንኙነት መቋረጥ እና እስከ አሁንም ይኽ ችግር ተገቢ የኾነ መፍትሔ ባለማግኘቱ፤ መለያየቱ ሥር ሰዶ፤ የጥፋቱ ጉዳት እየጨመረ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ለማይፈልጉ አካላት ሰርግና ምላሽ ሆኖ ነፍሳት በኑፋቄ እየተነጠቁ ይገኛሉ። ከተፈጠረው የአስተዳድር ልዩነት በኋላ የተስተዋሉ የኑፋቄ እና ስልታዊ ጥፋትን አስመልክቶ ያዘጋጀነውን ዝርዝር የማስረጃ ሰነድ ለቋሚ ሲኖዶስና ለቅዱስ ፓትርያርኩ ብናቀርብም ተጨባጭ ምላሽ አልተሰጠም። በመሆኑም በትግራይ ያለ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን በሚያስደነግጥ ፍጥነት በኑፋቄ እየተነጠቀ መሆኑን በመረዳት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው በፈጣሪ ፊት፣ በኅሊና እና በታሪክ ያስጠይቃል። አደገኛ ሰብራትም የሚያስከትል በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሠጥበት፤
ረ. በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት ወቅታዊ ችግር፣ ሌሎች የከረሙ አስተዳደራዊ ችግሮች እና ተያያዥ ምክንያቶች አብያተ ክርስቲያናት እየተዘጉ አገልጋይ ካህናት እና ተከታይ ምእመናን ወደ ሌላ እየፈለሱ እና እየተሰደዱ መሆናቸው የሚታይ የአደባባይ ሐቅ ነው። ይኸንኑ ችግር በጥናት ላይ ተመሥርቶ ከመመለስ ይልቅ ጳጳስ በመሾም ጥያቄዎቹ እንደተመለሱ የመቁጠር ከፍተኛ ዝንባሌ ተስተውሏል። በእርግጥ እርሱም ውጤታማ አይደለም። ችግሩን ከሥሩ ተረድቶ ምላሽ ባለመሰጠቱ የክልሉን ኦርቶዶክሳዊ በሌላ ዐውቅልሀለው ባይ አካል እንዲናወጽ ሆኗል:: በቅዱስ ሲኖዶሱም ለቋንቋዎች አገልግሎት የተመደበው በጀት እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሲሠራበት አልታየም። በአጠቃላይ በክልሉ የሚገኘውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት በማጠናከር የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የካህናት ማሠልጠኛ ማዕከላትን ማስፋፋት፣ መምህራንና አገልጋዮችን በማፍራት ተደራሽነትን የማስፋት ተጨባጭ ሥራ መሥራት ይገባል።
2. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግሮችን (ለጥፋት የዳረገንን ብልሹ አሠራርን) በተመለከተ፦
የሰበካ መንፈሳዊ ሥራ አስፈጻሚ ፣ ጠቅላላ ጉባኤ እና ከመንፈሳዊ ዘርፍ ውጪ ያሉ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በቃለ ዐዋዲው እና በተገቢው የዘርፉ ባለሙያ እንዲመሩ አለማድረግ ለጥፋት እና ለብልሹ አሠራር ዳርጎናል።
ታላቂቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከማይመጥን እና ብዙ ዋጋ ካስከፈላት አስተዳደራዊ ድክመት በመላቀቅ እና ዘመኑን በመዋጀት እናት ቤተ ክርስቲያንን መታደግ ለነገ የማያድር ሥራ ነው ። በመሆኑም :-
ሀ. የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ተደራሽ እንዳይሆን፣ የምእመናን ነፍስ እንዲነጠቅ፣ የኢኮኖሚ አስተዋጽዖዋ እንዲደበዝዝ ፣ ተሰሚነቷና ተቀባይነቷ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት የሆነው በብቁ የአስተዳደር ባለሙያ የመፈጸም ችግር የገነገነ ነው። መንፈሳዊ ዕውቅት ብቻ ባላቸው ነገር ግን የአስተዳደር ክህሎት በሌላቸው፣ ዘመኑን የመዋጀት ክፍተት ባለባቸው ሊቃነ ጳጳሳት እና በዘመድ አዝማድ ደጅ ጥናት ሙያ ሳይኖራቸው በተመደቡ ሓላፊዎች መመራቱ ዋናው የችግሩ አካል ስለሆነ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት፣ የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች የአስተዳደር ዘርፍ ከሊቃነ ጳጳሳት ውጪ በብቁ ባለሙያዎች እንዲመሩ እና ሊቃነ ጳጳሳት በሕግ አውጪነት እና ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ ፤ ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ፤ሕገ ቤተ ክርስቲያን ላይ ማሻሻያ ማድረግ ይገባል ::
ለ. በሕገ ቤተ ክርስቲያን እና በቃለ ዐዋዲ የተደነገገው የሰበካ ጉባኤ የአስፈጻሚነት እና የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤያት ሚና መገሰስ ፦ በቃለ ዐዋዲው የተደነገገው የካህናት፣ የምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የአስፈጻሚነት ተሳትፎ ማለትም በወረዳ ቤተ ክህነት፣ በሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና እና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተግባራዊ እንዳይደረግ ተገፍቷል። በዚህም ምክንያት የክፍል እና የመምሪያ ሓላፊዎች በቤተ ክርስቲያን ሕግ በግልጽ ከተደነገገው ከሦስቱ አካላት ተዋጽዖ ውጪ በሕግ የማይታወቅ የመደበኛ ቅጥር ሠራተኞች ስብስብ ” የአስተዳደር ጉባኤ ” የሚባል መሥርተው ቤተ ክርስቲያኒቱን እየበደሉ ይገኛሉ። ካህናት፣ ምእመናን ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የአስፈፃሚነት ሚናቸውን እንዲወጡ በሕገ ወጥ ስብስብ የተነጠቀው የአስፈጻሚነት ድርሻ በየመዋቅሩ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተመልሶ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ።
ሐ. የሀብት ብክነት፦ ንጽሕናን ገንዘብ ያደረጉ አባቶቻችን ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ብለው የገነቧቸው እና ለአገልግሎት ያበቋቸውን ሕንፃዎች ፣ ድርጅቶች እና ቤቶች ዛሬ በአያያዝና በቁጥጥር ሥርዓት ጉድለት ከፍተኛ ዘርፋና ግፍ የሚፈፀምባቸው ሆነዋል፤ ለብክነትም ተዳርገዋል። ለዚህም ጤናማ የሥራ አፈፃፀም ታሪክ የሌላቸው አካላት እየተፈራረቁ የመዘበሩት የቤቶች ድርጅት አንዱ ማሳያ ነው። ከአጥቢያ ጀምሮ በዘመናዊ አስተዳደር እጦት ምክንያት ለኪራይ አገልግሎት የዋሉ ሕንፃዎች ፣ ቤቶች እና ይዞታዎች በረቀቀ የሙስና ስልት ከሚጠበቅባቸው ገቢ በታች እየሰበሰቡ አብላጫውን አስተዳዳሪ ተብለው በሚሾሙ አካላት ይዘረፋሉ። በመሆኑም አሁን ላይ የአጥቢያዎች ቁመና የሠራተኞች ደሞዝ መክፈል ላይ ብቻ ተቸክሎ የምእመናን ሕይወት፣ ስብከተ ወንጌል ማስፋፋትና ልማት የማይታሰብ ሆኗል።
በመሆኑም ለወንጌል ልማት መዋል የሚገባው ሀብት ለምዝበራ ተዳርጓል። ቤተ ክርስቲያን መንፈንሳዊ ዕውቀትን ከዘመናዊው ዕውቀት ጋር ያጣመሩ ፈሪሐ እግዚአብሔር ያላቸው ልጆች የሌሏት ይመስል፤ የለየላቸው ጨካኝ ወንበዴዎች የሚቀራመቷት ሆናለች። በአያያዝ እና በብቁ አስተዳደር እጦት ሀብቷ ለብክነት ተዳርጓል ፤ ለጥቅመኞችም ሲሳይ ሆኗል።
ይህን የአደባባይ ምሥጢር መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ አይቶ እንዳላየ፤ ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፍ ቤተ ክርስቲያንን ለወንበዴዎች አሳልፎ መስጠት ነውና በቁርጠኝነት ሥር ነቀል ለውጥ ሊደረግ ይገባል።
መ. ከአጥቢያ ጀምሮ በሁሉም መዋቅር ዘመኑን የዋጀ የአስተዳደር ፣ የፋይናስ የግምገማ ፣ የቁጥጥር እና የምዘና ሥርዓት አለመኖር :- በሁሉም መዋቅር የሥራ ግምገማ ፣ የሥራ አፈጻጸም እና የሀብት አጠቃቀም ቁጥጥር ሥርዓት የለም። አጥፊ አይጠየቅም፤ በአጥፊዎች ላይ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አይተገበርም፤ ሹመት፣ ዕድገት፣ ዝውውር ያለ ምዘና ሥርዓት በዘፈቀደ ይከናወናል። የሠራተኞች የሥራ መደብ በከፍተኛ የብር መጠን ይቸበቸባል ፤ ሌብነት ፣ ሥርዓት አልበኝነት ነግሠው መንፈሳዊነት ከቦታው ጭራሹኑ ጠፍቷል። የሥራ ዋስትና የለም፤ ከኢአማኒያን እንኳ በማይጠበቅ መልኩ የካህናት፣ የዲያቆናት እና የስብከተ ወንጌል የሥራ መደብ ላይ የአየር ላይ ሽያጭ ፣ የወንዘኝነት መጠቃቀም የመሳሰሉት ዘግናኝ የግፍ ግፎች ይፈጸማሉ። ይህ ችግር በብዙ ሀገረ ስብከቶች መጠኑ ይነስም ይብዛ የሚስተዋል ሲሆን በተለይ ዋነኛ መገለጫው የሆነው እንደ አዲስ አበባ ባለ ሀገረ ስብከት ጎልቶ ይታያል። እንደ ማሳያ በተለያየ ጊዜ የተሾሙ ብፁዓን አባቶችም ሆነ በተለያየ እርከን ያሉ ሓላፊዎች የግላቸው የአሠራር ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ አንዱ የችግሩ ምንጭ እንደ ሲኖዶስ አብረው የሚወስኑ ጥቂት የማይባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ቅጠርልኝ፤ አዛውርልኝ፣ መድብልኝ፣ አታዘዋውርብኝ፣ አትቅጣብኝ የሚሉ ጫናዎች እንደሚያሳድሩባቸው ሁሉም በሚባል ደረጃ የሚገልጹት ለተበላሸ አሠራር ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ይህ የመልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የቅዱስ ሲኖዶስ ቁርጠኛ አቋም ከሆነ አባቶች ለወዳጅ ዘመድ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ማስቆም ያስፈልጋል ።
ረ. ውስን ሊቃነ ጳጳሳት በእርግና ምክንያት በግልፅ አስተዳደራዊ ሥራ ማከናወን እንደማይችሉ እየተስተዋለ ስለ ነፍሳቱ እረኛ ማጣት ደንታ ቢስ በመሆን መፍትሔ ሳይሰጥ ቀርቷል፤ እንዲሁም ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ሊቃነ ጳጳሳት ከምእመናን ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው ሀገረ ስብከቱ ታውኮ፤ ምእመናን አዝነው እና ከበረቱ ተገፍተው ወጥተው ሲቀሩ ሲኖዶስ በዝምታ ተመልክቶታል። ሀገረ ስብከታቸውን በሚገባ በማያስተዳድሩ ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተደነገገው መሠረት አስተዳደራዊ እርምጃ አለመወሰዱ እና የበዛ ዳተኝነቱ ቤተ ክርስቲያንን ክፉኛ ጎድቷታል። በመሆኑም በእርግና ላይ ለሚገኙ ብፁዓን አባቶች ረዳት መሾም ፣ የታወቀ የአስተዳድር ድክመት ያለባቸውን አባቶች ተገቢውን የተጠያቂነት አሠራር በተግባር ላይ ማዋል ይገባል።
ሸ. በመንፈሳዊ አገልገሎት ማለትም በፍትሐት፣ በሥርዓተ ተክሊልና በሥርዓተ ቀብር ላይ ከመንፈሳዊ አሠራር ያፈነገጠ የለየለት ንግድ ምእመናንን አስመርሯል። በቅዳሴ ሰዓትና አገልግሎት፣ ማሕሌት፣ ሰዓታት እና በሌሎች መንፈሳዊ አገልገሎቶች ላይ እየተሰተዋለ ያለው ከመጻሕፍትም ከአባቶችም ያላገኘነው ዐዲስ ባዕድ ልምምድ ተበራክቷ ። በፍቅር እና በረከትን ሽቶ ማገልገል ሞኝነት መስሎ፤ ከመንፈስ ቅዱስ አሠራር ውጪ እንደ መደበኛ ሥራ የማየትና ከፍቅር ይልቅ በሥራ መንፈስ የማገልገል አዝማሚያ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል።
ከ. በከተማ ልማት እና መስፋፋት ምክንያት ምእመናን ከአምልኮ ሥፍራ እንዳይለዩ እና አድባራቱና ገዳማቱ ተገልጋይ እንዳያጡ፣ ዘመኑ በመዋጀት ከአምልኮ ሥፍራና መልሶ ማልማት ጋር የተጣጣማሙ ስልታዊ የተቀናጁ የልማት ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት በአድባራቱ ቦታ እና ከመንግሥት ቦታን በመጠየቅ ምእመናን ተኮር የልማት ሥራ መሥራት ምእመናን ከቀያቸው ሣይርቁ አምልኮተ እግዚአብሔርን መፈጸም ያስችላቸዋል። በመሆኑም ነገን አሻግሮ በመመልከት ዛሬ ላይ ወደ ሥራ መግባት ይገባል።
3. የሥነ ምግባር ግድፈት ክብረ ክህነት፣ ክብረ ምንኩስናን የሚያስነቅፍ የተገለጠ የቀኖና ጥሰት መበራከት:-
የታወቀ፣ የተገለጠ የሥነ ምግባር ግድፈቱ ትውልዱን ከቤተ ክርስቲያን እያራቀው ነው። ትናንት ለቀሳውስት እና ለሊቃነ ጳጳሳት የሚሰጠው ክብር ተሸርሽሮ ጀርባ መሥጠት ተጀምሯል። በከተማ መነኮሳት እና መነኮሳይያት ኢክርስቲያናዊ ምግባር ምእመናንና ወጣቱን የማያንጽ አሰናካይ፤ ከሥርዓተ አበው፣ ከሥርዓት ምንኩስና ያፈነገጠ አሳፋሪ ልምምድ ተበራክቷል።
መንፈሳዊ ሕይወት ተዘንግቶ ፤ ቦታ ተነፍጐት ዓለማዊነትና ሥጋዊ ፍላጎት ነግሧል። ከታወቀ ደሞዝ በላይ ኑሮ ፤ ምንጩ የማይታወቅ፤ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረት ማካበት፣ ከገዳማት እና አድባራት ሠራተኛ እስከ ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ ሕጋዊ እስኪመስል በአደባባይ ተገልጧል። ይኸ አደገኛ በሽታ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፤ ባለቤት የሌለው ይመስል ልቅ የሆነውን ጉዳይ ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ ሁሉም በየተዋረዱ ለሥነ ምግባር ጥሰቱ ተጠያቂነት የሚሰፍንበት ሥርዓት ሊበጅለት ይገባል ።
4. በሀገራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳይ ላይ ተሳትፎን በተመለከተ
ሀ. በሀገር ግንባታ፣ በሰላም እና እርቅ ክዋኔ የካበተ እና ተጠባቂ ልምድ እና አስተዋጽዖ ያላት ቤተ ክርስቲያን ፣ በሊቃውንቷ አዎንታዊ አስተዋጽዎ ማበርከት ሲገባት በግልጽ፤ ከታወቀው አዎንታዊ ሚናዋ ተናጥባለች። በየዕለቱ የሂስና ግለሂስ አስተምህሮን የምትተገበር ቤተ ክርስቲያን ፣ በጸሎትና በውይይት ችግሮች የመሻገር ሰፊ ልምድ ያላት ቤተ ክርስቲያን፤ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ያላትን ግንኙነት በጥበብ በማስኬድ፣ በውይይት ፣ በምልዐት በመመካከር ማስኬድ ይገባታል። በሀገራዊ ጉዳይ ተቋማዊ ተሳትፎና ድርሻን መወጣት ዐቢይ ተግባር መጠናከር ይገባል ።
ለ. በመንግሥት በኩል እየተዘጋጁ ባሉ ልዩ ልዩ ረቂቅ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ተገቢነት ያለው ተቋማዊ ተሳትፎን በማጠናከር፤ ልዩ ልዩ ረቂቅ የሕግ ፣ የደንብ ዝግጅቶች ላይ መሳተፍ፣ ክትትል ማድረግ እነዚህ መመሪያዎች ከመውጣታቸው አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያኒቱና በአማኞቿ ላይ የሚያመጣውን በጎም ይሁን ክፉ ተጽእኖ በባለቤትነት መንፈስ በመመርመር ተገቢነት ያለው ሱታፌ እንዲኖራት የሚያስችል አግባብነት ያለው የውክልና ተሳትፎዎች ማድረግ እንድትችል በባለ ሙያዎች በተደራጀ ቡድን ክትትል እና ተቋማዊ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል።
ሐ . በሀገራችን የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ እና ሀገራዊ ሰላም እንዲረጋገጥ አዎንታዊ የቤተ ክርስቲያን ሚናን በተመለከተ ፦ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሀገራዊ ሰላም ፣ በህዝቦች ስደት፣ ሞት እና አለመረጋጋት ዙሪያ ፤ አስቀድሞ ለዘመናት መገለጫዋ ከሆነው ልምዷ በመነሣት ችግሩ እንዲቀረፍ ፍሬ ያለው ተግባር አልተከናወነም:: ከመግለጫ በዘለለ የተቀናጀ ፣ ውጤት ሊያመጣ የሚችል አዎንታዊ ሚናዋ ደብዝዟል። በመሆኑም ችግሩን ከመቅረፍ እና በወንድማማቾች መሀል የተፈጠረን ልዩነት በማጥበብ ሀገራዊ ሰላም እንዲሰፍን ቤተ ክርስቲያን ተጠባቂ ሚናዋን ከመወጣት አንፃር ሰፊ ሥራ ይጠበቃል ፡፡
መ. ቤተ ክርስቲያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ የሃይማኖት እና ሰብዓዊ ክዋኔዎች ላይ በአግባቡ አለመሳተፍ፤ በአኃት አብያተ ክርስቲያናት መደበኛ እና ልዩ ልዩ ጉባኤያት አለመወከል እንዲሁም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተገቢውን ተሳትፎ እና መብቷን የማስከበር ሥራዎች አለማከናወን ይስተዋላል:: ቅዱስ ፓትርያርኩ ከሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርቲያን ከምትወከልበት መድረክ መሄድ ካቋረጡ ሰነበቱ። በመሆኑም ይኸ ታላቋን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስትያን የማይመጥን ድርጊት ተገቢው ማስተካከያ ሊሰጠው ይገባል።
ከላይ በዝርዝር የተገለጠው በዋነኛነት የብልሹ አስተዳደር ውጤት፤ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቷን እንዳታስፋፋ፣፤የነፍስ ድኅነትን እንዳታውጅ፤ መንግሥተ እግዚአብሔርን እንዳትሰብክ እንቅፋት የሆነ፤ ነፍሳትን ከበረቱ ያስኮበለለ፤ የቀሩትም ለቀቢፀ ተስፋ የዳረገ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ፤ ከአሁኑ የከፋ ጥፋት ሳይከሰት ሥር ነቀል መፍትሔ በመሥጠት እና የምእመናንን የአስፈፃሚነት ሱታፌ በማረጋገጥ የምንረከባትን ቤተ ክርስቲያን እንዲታደግልን እና ሐዋርያዊ አደራውን እንዲወጣ በልጅነት መንፈስ ዝቅ ብለን እንማፀናለን ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!
(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)

