ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይን አስመልክቶ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተሰጠ መግለጫ!
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከተፈጠረ ጦርነት ጋር ተያይዞ በቤተ ክርስቲያን የበላይ መዋቅርና በትግራይ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት መካከል የነበረው አስተዳደራዊ መዋቅር ተቋርጦ መቆየቱ ይታወቃል። የተፈጠረው አለመግባባት በውይይት ተፈቶ መዋቅራዊ አንድነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጠል ሀገራዊ የሰላም እርቁ ከተፈጸመበት ማግስት ጀምሮ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፊርማ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ሲጠየቅ መቆየቱም ይታወሳል፡፡
በትግራይ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት ያሉ አራቱ ሊቃነ ጳጳሳት ግን የሰላም ጥያቄውን በመግፋት መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በመጣስ መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት መሥርተናል በማለት ተገቢነት የሌለው መግለጫ ከመስጠት አልፈው ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ለመፈጸም ለሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዛቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን እየገለጹ ይገኛሉ። የተከሰተውን የቤተ ክህነት አስተዳደር ክፍተት በማስፋት ወደ ቀኖና ጥሰት ለመውሰድ የሚደረገው ሒደት በእግዚአብሔርና በታሪክ ፊት ተጠያቂነትን ያስከትላል። በሊቃነ ጳጳሳቱ በቤተ ክርስቲያን ደረሰብን በሚል የሚጠቀሱ ጉዳዮች አግባብነት የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ በግለሰብ ደረጃ ተነገሩ የተባሉ ንግግሮችንም በመውሰድ ቤተ ክርስቲያንን በምልዓት እንደ ጥፋተኛ መቁጠሩ ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም። ይልቁንም አሁን ያለውን ችግር የበለጠ የሚያወሳስብ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
ተከስቶ ከነበረው ችግር ጋር ተያይዞ ፈጥኖ ለመፍትሔ አለመዘጋጀትና ሰላም እና አንድነት ለማምጣት መዘግየት እንደነበረ ባይካድም በስተመጨረሻ ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሩ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ በይፋ ይቅርታ ከመጠየቅ ጀምሮ በቅዱስ ፓትርያርኩ የተመራ የሰላም ልዑክ በመላክ አንድነቱን ለማምጣት የተሔደበት ርቀት የሚደነቅ ነው። ይሁን እንጂ አራቱ ሊቃነ ጳጳሳት የሰላም ልዑካኑን የአንድነትና የእርቅ ጥያቄ በመግፋት፣ ቤተ መቅደስ እስከ መዝጋት የደረሰ ፈጽሞ የማይገባ አሳዛኝ ድርጊት ፈጽመዋል። እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም፣ ለመክፈል ብሎም ለማጥፋት በሚሠሩ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን እና የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞች ድጋፍና ጫና ኢቀኖናዊ በሆነ መንገድ አዲስ አደረጃጀት ለመፍጠርና ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም ዝግጅት መደረጉን ከሚወጡት መረጃዎች ተረድተናል።
በመሆኑም ይህን ኢቀኖናዊ ሕገ ወጥ አካሄድና አጠቃላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ ከሚመሩት የሰላም ልዑክ ጋር የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ከነበረው ሱታፌና ተጨባጭ ምልከታ አንጻር የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
1ኛ. ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጥር ፲፬ ፳፻፲፭ ዓ.ም በተፈጸመው የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ወቅት በቁርጠኝነት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ለማስከበር በተሔደበት ርቀት ልክ አሁን ላይ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅራዊ አደረጃጀት በመክፈል፣ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ለመፈፀም የተወጠነውን እኩይ ሴራ ለማስቆም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እንደ ከዚህ ቀደሙ በጥብዓት፣ በታላቅ ጥበብና በአንድነት በመቆም ታሪካዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን።
2ኛ. በትግራይ ክልል የምትገኙ ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናት፣ ምእመናን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት እና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ማኅበራት ይህ ፈተና የውጫዊ አካላት ጫና ያለበትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም የታለመ ሴራ መሆኑን በመረዳት፣ የቤተክርስቲያንን አንድነት በማስቀደም እየተፈጸመ ያለውን ኢቀኖናዊ ጥሰት በማስቆም የኦርቶዶክሳውያን አንድነት እንዳይከፈል የበኩላችሁን መንፈሳዊ ኃላፊነት እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
3ኛ. ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በአገልግሎት ላይ ያላችሁ አንዳንድ አገልጋዮች የሰላምና የአንድነቱ አካል ከመሆን ይልቅ ችግሩን በማባባስ በመጠመዳችሁ ከዚህ እኩይ ተግባር በመቆጠብ አንድነት እና ሰላም እንዲሰፍን ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እና የመፍትሔው አካል እንድትሆኑ በአጽንዖት እናሳሰባለን።
4ኛ. በቅዱስ ፓትርያርኩ ዙሪያ ሆናችሁ የዚህ ታሪካዊ ስሕተት ደጋፊ የሆናችሁ እና የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ለማበላሸት የተሰለፋችሁ አካላት ከአፍራሽ አካሔዳችሁ እንድትቆጠቡ እየጠየቅን በስሑት አካሔዳችሁ ምክንያት የሚነሣው እሳት ወላፈኑ መጀመሪያ የሚያገኘው እናንተን መሆኑን በመረዳት ከዚህ ግብራችሁ እንድትታቀቡ በጥብቅ እናሳስባለን።
በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር በሚደረገው ሒደት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በአስፈላጊ ጉዳዮች ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስን በመታዘዝ የልጅነት ድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።
ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
ሐምሌ ፯ ፳፻፲፭