ዕርገተ ክርስቶስ
“እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው” ሐዋ. 1÷9
ዕርገት ማለት ወደላይ ከፍ ከፍ ማለት ሲሆን የመሬትን የስበት ኃይል የሚያሸንፍ ከፍታ ነው፡፡ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ያረገው የመሬት የስበት ኃይልሳይገድበው ነው፡፡ የክርስቶስ ዕርገት ቀድሞ በትንቢት የተነገረ፤ በሚያምኑት ዘንድ በናፍቆት ሲጠበቅ የቆየ እና በራሱ በጌታችን የተሰበከ ነው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለ፴፫ ዓመታት ከሦስት ወራት በምድር ኖሯል፡፡ በ፴ ዓመቱ ተጠመቀ ለ፫ ዓመታት አስተማረ፣ ስለ ኃጢአታችን በመስቀል ላይ ቤዛ ሆነልን፡፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙታንተለይቶ ተነሣ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ተገለጠላቸው፡፡
ዛሬም ጌታችን ኢየሱስ ከዕርገቱ በፊት ከተነሣ በኋላ ስላስተማራቸው ትምህርቶች፣ ደቀመዛሙርቱን ስላዘዛቸው ትዕዛዝ እናያለን፡፡
ጌታችን ከተነሣ በኋላ ባሉት ፵ ቀናት በተለያዩ ጊዜያት ለደቀመዛሙርቱ ተገልጾ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ያስተምራቸው ነበር፡፡ ስለክርስቶስ የተነገረውን የቅዱሳት መጻሕፍት ትንቢት ከዚያ በፊት አላስተዋሉም ነበር፡፡ ጌታችንም ስለ እርሱ የተጻፉትን ተረጎመላቸው፣ አዕምሮቸውንም ከፈተላቸው መጻሕፍትንም አስተዋሉ፤ እምነታቸውን አጸናላቸው፡፡ ስለ ትንሣኤው የነበራቸውን ጥርጣሬም ከልቦናቸው አጸዳላቸው፡፡
የሚከተሉትን ትዕዛዛት እና ኃላፊነቶችም ሰጣቸው፡-
* ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፡፡ ማር ፲፮ ፥ ፲፭
* ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ፡፡ የሐዋ ፩ ፥ ፭
* እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ… አስተምሯቸው፡፡ ማቴ. ፳፰ ፥ ፲፱ – ፳
* እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡ የሐዋ.ሥ ፩ ፥ ፰
በወንጌል ለመስበክ እና በስሙ ለማጥመቅ ወደ ዓለም ሲወጡ፣ እንደሚገረፉ ወደ ነገሥታት የፍርድ አደባባይም እንደሚያወጧቸው ነገሯቸዋል፡፡ እስከመጨረሻም የጸና ግን ይድናል በማለትእስከ ዓለም ፍጻሜ ከእነርሱ ጋር እንደሚሆንና መንፈስ ቅዱስን ሲቀበሉ ኃይልን እንደ ሚያገኙምቃል ገብቶላቸዋል፡፡
ከሙታን በተነሣ በ፵ ኛው ቀን ደቀመዛሙርቱን ወደ ደብረዘይት ወሰዳቸውና ባረካቸው፡፡ ተሰብስበው ትምህርቱን እየሰሙም ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አለ፡፡ ወደ ሰማይም ዐረገ ደመናም ከዓይናቸው ሰወረው፡፡
ደቀመዛሙርቱ ክርስቶስ ወደ ዐረገበት ቀና ብለው እየተመለከቱ ሳለ ሁለት መላዕክት ነጫጭ ልብስ ለብሰው በአጠገባቸው ቆመው “ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለምን ቆማችኋል? ይሄ ከናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል አሏቸው፡፡ ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ በተነሣ በአርባኛው ቀን በድል ዐረገ፡፡ ወደ ሰማይ እያረገ ሲሄድ እንዳዩት ደግሞ በዓለም ላይ ሊፈርድ ይመጣል፡፡ ማረጉን አምነን ዳግም መምጣቱን እንናፍቅ፡፡�
” ደቀመዛሙርቱም ጌታ ካረገበት ከደብረ ዘይት እግዚአብሔርን እያከበሩ ተመለሱ፡፡ እንደታዘዙት መንፈስ ቅዱስን እስኪቀበሉም በኢየሩሳሌም ቆዩ ፡፡
እኛም በኢየሩሳሌም በተመሰለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጸሎትና በአገልግሎት በመትጋት ልንቆይ ይገባል ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር